Wednesday, April 30, 2014

ሦስት ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? እሱ ሲፈቅድ ነው? ወይስ ጌታው ሲፈቀድለት? (ፕ/ር መሰፍን ወ/ማርያም )


በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የፖሊቲካ ድርጅቶች ገዢ የሚባለውንም ጨምሮ ስያሜአቸው እንደሚያመለክተው ከነጻነት ውጭ ናቸው፤ ሌላው ቀርቶ ለነጻነት የተዘጋጁ አይደሉም፤ ራሳቸው በባርነት ውስጥ በጀርባቸው ተንጋልለው ሌሎችን ከባርነት ለማውጣት ማሰባቸው አለማሰባቸውን እንጂ ሌላ አያመለክትም፤ ወያኔ ራሱ ገና ነጻ ያልወጣ የባሪያዎች አለቃ ነው፤ ወያኔ ለባርነት ደረጃ አበጅቶ ጠርናፊና ተጠርናፊ እያለ ከፍሎታል፤ ከወያኔ ጋር በደባልነት አገር ለመግዛት የተመለመሉት ከባርነት ሳይወጡ ካባ ለብሰው በአገልጋይነት የወያኔን ጉድለት ለማሟላት የሚሞከርባቸው መሣሪያዎች ናቸው፤ መሣሪያነታቸው የተሰማቸው ከብዙ ዓመታት ጀምረው በመኮብለል ላይ ቢሆኑም፣ ጭራውን እየቆላ በሞተ-ከዳ እግር ለመግባት የሚተናነቀው ብዙ ነው፤ ወያኔ ለአንድ ትልቅ አገር የሚበቃ ሠራዊት፣ ለአንድ ትልቅ አገር የሚበቃ የፖሊስ ኃይል፣ ለአንድ ትልቅ አገር የሚበቃ የአስተዳደር የሰው ኃይል በቁጥርም በጥራትም የለውም፤ በይድረስ-ይድረስ በብዙ ዶላር አስተማሪዎችን ከውጭ እያስመጡም ሆነ፣ ወይም በፖስታ፣ ወይም ከታወቀው ማምረቻ በሚወጡ የለብ-ለብ ምሩቆች እየተንገዳገደ እዚህ ደረሰ።Prof. Mesfin Woldemariam
እዚህ ደረስን ቢሉና ቢኤ፣ ኤምኤና ፒኤችዲ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ቢያውለበልቡም የሚሠሩት ብቻ ሳይሆን የሚናገሩትም አለመማራቸውን ያሳብቅባቸዋል! ለመሆኑስ በጥይት ለጥይት የተገራ አንጎል እንዴት ብሎ በሀሳብ ይለዝባል? እንዴት ብሎስ ለሕግ ይገዛል? ስለዚህም ወያኔ ስለትምህርት መነሻውንም መድረሻውንም አያውቅም፤ ስለዚህም ለትምህርት ሚኒስትርነት የሰየማቸውን ሰዎች አንድ በአንድ ማስታወሱ ወያኔ ለትምህርት ያለውን ግምት ያሳያል፤ በትምህርታቸውና በሙያቸው እውቀት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በየትም አንቱ የተባሉትን ሰዎች ‹በችሎታ ማነስ› እየተባለ በትእዛዝ በሚነዳ አሻንጉሊት እየተፈረመ ከዩኒቨርሲቲ ማባረሩና ዩኒቨርሲቲውን ወና ማድረጉ ሌላ ማስረጃ ነው፤ ከተባረሩት ውስጥ አንድም በኑሮው የተጎዳ የለም፤ የተጎዳው ዩኒቨርሲቲው ነው፤ የተጎዳችው ኢትዮጵያ ነች፤ የተጠቀሙት ወያኔዎች ናቸው፤ ዩኒቨርሲቲውን ሲያረክሱትና ሲያዋርዱት እነሱ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ለማሳየት መድረኩን የከፈተላቸው መስሏቸው ነበር፤ በአቶ አዲስ ዓለማየሁ ላይ የተረተው ፋሺስት ‹ለካስ ሰው ከሌለበት፣ ቤት ቁንጫ ይፈላበታል!› ያለው እንደተፈጸመባቸው ዛሬም አልገባቸውም፤በዚህም ምክንያት ወያኔ ለተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ለማሰማራት የሚያስችሉት የተማሩና የተመራመሩ ባለሙያዎች የሉትም፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተቋቋሙት እንደኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አንደመብራት ኃይል፣ እንደቴሌ፣ እንደየኢትዮጵያ ዓየር መንገድ፣ … ወዘተ. በአጥንታቸው በመሄድ ላይ ናቸው፤ ማክሸፍ እንዲህ ነው! ለአብራሪዎች ትምህርት ቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ አብራሪዎችን ከኢጣልያና ከሌሎች አገሮች እያስመጣች ነው፤ የሥልጣን ወንበሩን ከያዙት ጀምሮ አከርካሪት ስለመስበር ሲፎክሩ ቆይተው አሁን ኢጣልያዊ አውሮጵላን አብራሪና መሀንዲሶችም ከያለበት እያስመጡልን ነው፤ የማን አከርካሪት ተሰበረ!
ይህ ሁሉ ታዲያ ከነጻነት ጋር ምን አገናኘው የሚል ይኖራል? አለው እንጂ! ወያኔ የሥልጣን ወንበሩን በጠመንጃ ነጻ ካወጣ በኋላ የፈላጭ-ቆራጭነት ነጻነትን ተጎናጸፈና እንዳይመቸው ሆኖ ቁጢጥ አለ፤ በጠመንጃው ከሕግ ነጻነትን አገኘ፤ ከዚህ በኋላ በእውቀትና በልምድ የሚበልጡትን ሁሉ እያደነ እርጭ አደረገ፤ በጠመንጃ ነጻ ባወጣው ወንበር ላይ ተቀምጦ ዋና የጠመንጃ አገልጋይ ባደረገው ሕግ እየተመራ እያፈረሰ መካቡን ተያያዘው፤ መንገድ ሲያፈርስ ሲክብ፣ ባቡር ሲያፈርስ ሲክብ፣ ሐውልት ሲያፈርስ ሲክብ፣ ሕንጻ ሲያፈርስ ሲክብ፣ ማፍረስ ዋና የሚታወቅበት ሥራው ሆነ፤ ይህ አያስደንቅም! ከየትና እንዴት አንደመጣ የታወቀ ነው፤ ነጻነት የሚለመልመው ሕግና ሥርዓት ባለበት ነው፤ ሕግና ሥርዓት በሌለበት አፈና፣ ዝርፊያ፣ ቅሚያ፣ ድብደባ፣ እስር፣ — ይኸ ሁሉ የሰለቸው ደሞ አገር እንደሌለው ሰው በስደት መንከራተትና መዋረድ ነው፤ በገዛ አገሩ የተጠላ ሰው የሌሎች አገሮች ሕዝቦች እንዴት ሊያከብሩት ይችላሉ? በፓሪስ አውሮጵላን ማረፊያ ‹‹ጃፓናውያን ጎብኚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ!›› የሚል ጽሑፍ አይቻለሁ።
እንደኢትዮጵያ ያለች ትልቅ፣ ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነች የጨዋ ሰዎች አገር፣ የሦስት ታላላቅ ሃይማኖቶች ቅርስ ጠባቂ የሆነች አገር፣ እግዚአብሔርንና ሕግን፣ ይሉኝታንና ማናቸውንም የጨዋነት ደንብ በሻሩ ጎረምሶች ጫማ ስር ወደቀች፤ ተጋለጠች፤ ተዋረደች፤ ነጻነት-አልባ ሆነች።
ወያኔ በጣም ጨካኝና የተጠላ ሥርዓትን ገርስሶ ራሱን በአገር ሥልጣን ላይ ሊያወጣ ሲል ከመሸ በኋላ በምዕራባውያን ምክር ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ የሚለውን (ሕወሓት) የተገንጣይ ጎሣ ስም ለወጠና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚል ቀፎ ሠራ፤ በዚያ ቀፎ ውስጥ አንደኛ የተማረኩና ጥላቸውን የሚፈሩ ጭር ያሉ ወታደሮችን፣ ሁለተኛ የተሸነፉና የተበታተኑና መድረሻ ያጡ የኢሕአፓ ቅሪቶችን፣ ሦስተኛ ከያለበት ጭራቸውን እየቆለመሙ የሥልጣን ፍርፋሪ ለማግኘት በጎሣዎች ስም የገበሩለትን ወዶ-ገቦች ሰብስቦ፣ ሌሎችንም ከየመንገዱ ለቃቅሞ ኢትዮጵያን ገነጣጥለው ሊቃረጡ የተሰበሰቡ ሰዎችን የኢትዮጵያ ነጠላ እያለበሰ ቲያትር ሠራበት፤ (አብርሃ ደስታ ወያኔዎች ወያኔነታቸውን ስለሳቱ ወያኔ ሊባሉ አይገባም የሚለውን አስተሳሰብ ብቀበለውም፣ እኔ በበኩሌ የወያኔን ስም ለመለወጥ መብትም ፍላጎትም የለኝም፤ ለራሳቸው የሰጡት ስም ነው፤ በስማቸው መጥራቱን እመርጣለሁ፤ ወያኔነትን እንደመታወቂያ እቀበለዋለሁ፤ ሁለተኛ እኔ ወያኔን ከትግሬ ጋር ማደባለቅ አልፈልግም፤ ወያኔ ያልሆኑትን ትግሬ እላለሁ፤ ወያኔዎቹንም ባወጡት ስማቸው እጠራቸዋለሁ፤ ጀርመን ሁሉ ናዚ እንደማይባል ትግሬ ሁሉ ወያኔ አይባልም።)
የስዊስዘርላንድ ሕገ መንግሥት መግቢያ ውስጥ የሚከተለው ይገኛል፡–
ነጻ የሚባሉት በነጻነታቸው የሚጠቀሙበት ብቻ መሆናቸውን እናውቃለን፤ የአንድ ሕዝብም ጠንካራነት የሚለካው በጣም ደካሞች ለሆኑት አባሎቹ በሚሰጠው የተደላደለ ኑሮ ነው።
ወያኔ ባሪያ ፈንጋይ ነው ቢባል የሚከራከርለት አለ? ባሪያ የመፈንገል ጉልበት አለው፣ ከመኖሪያ የማፈናቀል ጉልበት አለው፣ የመቀማትና የመዝረፍ ጉልበት አለው፤ የማይፈልጋቸውን ሀሳቦች የማፈን፣ በውሸት የመለወስና የማታለል ተግባራትን የሚፈጽሙ መሣሪያዎች አሉት፤ ወያኔ ሻግቶ የሚያሻግት ድርጅት መሆኑን ለማረጋገጥ ከሟቹ መለስ ዜናዊ ሌላ ምስክር መጥራት አያስፈልግም፤ እንዲህ ያለ ድርጅት የነጻነት ጸር ነው፤ የነጻነት ጸር ማለት ባርነት ነው፤ የድርጅቱ አባሎች ነጻነት የላቸውም፤ ነጻነትን የማይፈቅድና ለነጻነት ዋጋ የማይሰጥ ድርጅት መሆኑን ከመለስ ዜናዊ ጀምሮ ሌሎችም ይህንን አረጋገጠዋል፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ይጮሃል! ሕዝበ እስላሙ ይጮሃል፤ ነጋዴው ይጮሃል! ተማሪው ይጮሃል! አስተማሪው ይጮሃል! በግልጽ የማይጮሁት ተናካሾቹ ብቻ ናቸው! ለእግዚብሔር አድሬአለሁ ያለውን ባሪያ አደረገው፤ ለገንዘብና ለመሬት አድሬአለሁ ያለውን ባሪያ አደረገው፤ ለሥልጣን አድሬአለሁ ያለውን ባሪያ አደረገው፤ ለጉልበት አድሬአለሁ ያለውን ዱላ አስጨብጦ ባሪያ አደረገው፤ ገበሬውን በማዳበሪያ ባሪያ አደረገው፤ … ወዘተ.
ሥልጣንን እያሳየ ሥልጣንን እንዲመኙ፣ ጉልበትን እያሳየ ጉልበትን እንዲመኙ፣ የተንበሸበሸ ሀብትን እያሳዩ ሀብትን እንዲመኙ፣ … በማድረግ ሁሉንም ወደባርነት ቀንበር ውስጥ አስገብቶ እየገዛ ነው፤ ሕዝብም የምኞት ባርነቱን ቋጥሮ ነጻነቱን እያስረገጠ ነው፤ አጉል ምኞቶችን ያቀፈባቸውን እጆቹን ነጻ ለማውጣት ሲፈቅድ ያኔ ነጻነቱን ያውጃል!

No comments:

Post a Comment