Tuesday, April 8, 2014

እኛና አብዮቱ፤ በፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ ፀሐይ አሣታሚና አከፋፈይ፣ታህሣሥ 2006 ዓ ም፤ ግምገማ በታደለ መኩሪያ


በታደለ መኩሪያ
ደራሲው መጽሐፉን ለምን ለመጻፍ እንደተነሳሱ በመግቢያው ላይ ገልጸዋል፤ በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ተካፋይ የሆኑበት የደርግ መንግሥት የሚገባውን የታሪክ ሥፍራ አልተሰጠውም፤ ስለደርግም የጻፉ ቢኖሩም ፣ ለመጪው ትውልድ ትክክለኛውን የታሪክ ሐቅ አላስጨበጡትም  ባይ ናቸው።Former Ethiopian official Fikreselasie Wegderes new book
መጽሐፉን አንብቤዋለሁ፤ 440 ገጾች አሉት፤ኩነቶች ባይደጋግሙ በ200 ገጽ ሊያጥር ይችላል፤ ደራሴው በተለያዩ የሥልጣን እረከኖች ሠርተዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በቅተዋል፤ ከግል ማኅደራቸው ተነስተው  ይህቺን ጥንታዊ ሀገርና ሕዝቧን   ለአሥራ አምስት ዓመት ‘እኛ’ ከሚሏቸው ጓዶቻቸው ጋራ እንዴት  እንደመሯት ከዚያም ያገኙትን ተመክሮ ለትውልድ የሚያስተላልፉበት አጋጣሚ አግኝተዋል፤ የኔ ጥያቄ አጋጣሚውን ‘እኛና አብዮቱ’ በሚለው መጽሐፋቸው ተጠቅመውበታል ወይ ነው? ይህን በጋራ የምናየው ይሆናል። ለአንድ ወታደር ስለጦር ሜዳ ውሎ  ቢጽፍ ይብልጥ  ውጤታዊ ይሆናል፤ በተግባር ተካፍሏልና። ደራሴው በነፃ አስተሳሰብ ተኮትኩተው ባላደጉበት፣ ሕብረተሰቡም በነፃነት ሐሣቡን በማይገልጽበት፤ በሕዝብ ስም ሀገር የሚመሩትም ለዜጎች ግልጽ ባልሆኑበት፣ትክክለኛ ታሪክ ጽፎ ለትውልድ ማስተላለፍ ይቻላል ወይ? የሚለውን ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ግን ትክክለኛ ነው ያሉትን ታሪክ  በተረጋገጠ እውነት ላይ መሥርተው ካለቀረቡት የታሪክነት ደረጃውን አጥቶ ተረት ተረት ይሆናል።  ከሁሉ በላይ ደግሞ የጸሐፊው እውነትን በተረጋገጠ እውነት ለማቅረብ  ያለው የስዕብና ጥንካሬ  ወሳኝ ነው።
ስለ ስዕብናን ካነሣሁ ዘንዳ ‘የሕይወቴ ታሪክ’ የፊታውራሪ ተክለሃውሪያት ተክለማሪያም የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ነው፤ ከዚህ መጽሐፍ ያገኙሁት ቁምነገር ጀባ ብያችሁ ወደ ግምገማዬ አመራለሁ፤ ፊታውራሪ ተክለሃውሪያት በልጅነታቸው ራስ መኮንንን ተከትለው አደዋ ዘምተዋል፤ አጎታቸውን በጦርነቱ ላይ አተዋል፤ ከጦርነቱ በኋላ ራስ መኮንንን አስፈቅደው ወደማያውቁት አገር ሶቪየት ሕብረት ሄደው በታወቀ የጦር ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገር ተመልሰዋል። የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር በመሆን ሲሰሩ በዙ የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ግብር በላዎች ሊያሰሯቸው አልቻሉም። አልጋ ወራሹም እንደሌሎቹ ሎሌያቸው እንዲሆኑ ጠየቋቸው። የሀገራቸውን ነፃነት ተክብሮ እንዲኖር ለመታደግ ስለጦርነትና የጦር መሣሪያ ያጠኑት ፊታውራሪ ተክለሃዋሪያት ተክለማሪያም ሎሌነትን ተጠየፉት፤ የእርሶ ሎሌ አልሆንም አሏቸው፤ በአልጋ ወራሹ ሥር የሚያሽቃብጡ ግብር በላዎች የሆነ ያልሆነውን እያስወሩባቸው፣በእግር ብረት ታሰሩ፣ከቤተሰባቸው ተነጠሉ፣ በቤተመንግሥት እንደለማኝ ፍርፋሪ ተጣለላቸው፤ ግን ቅንጣት ታክል ስዕብናቸውን ዝቅ አላደረጉትም፤ የኢትዮጵያዊነት ስዕብና! የእኛነታችን አሸራ! የታላቅ ሙሑር ተመስሌት፣ የመጪው ትውልድ አብነት እንበላቸው።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም  ከመፈቅሉ መንግሥቱ  አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ሐረር ሒርና ድረስ ሄደው ጎብኝተዋቸዋል።እንደሀገራቸው ገበሬ በማሳቸው ላይ በቀለሷት ጎጆ ውስጥ አብረው አድረዋል፤በአንድ ወቅት በሥልጣን ምክንያት ባላጋራ የነበሩት የአንድ ሀገር ልጆች የእግዝአብሔር ፍቃዱ ሆኖ በመጨረሻው ቀን በመካከላቸው ዕርቅ ፈጥረዋል፤ ሁለቱም በሕይወት የሉም፤ ሌላው ቢቀር በመጨረሻው ዘመናቸው ለፈጠሩት ሰላም እንዘክራቸዋለን። ለእኛም ለቀሪዎቹ ሰላም ይውረድ!
ይህን ሰንቄ ወደ ፍቅረሥላሴ መጽሐፍ ‘እኛና አብዮቱ’ ልመልሳችሁ፤የገብሱን ፍሬ ከገለባው ለመለየት በበሮች ኮቴ የበረየውን ገለባ በመንሽ ለንፋስ እንደሚሰጠው እኔም በብዕሬ ላይ ላዩን ለንፋስ ልስጠው፤ በላይዳ ልሂድበት ካልኩኝ ደግሞ ሌላ መጽሐፍ ሊያጽፈኝ ነው። አጠር ባለ ሁኔታ በተከታታይ ለማቅረብ እሞክራለሁ፤ ሰለቸን ካላችሁ አቆማለሁ።
ደራሲው በመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች የፊዳላዊ ሥረዓቱ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያደረሰውን አሉታዊ ሀኔታዎች አቅርበዋል፤ በ1967 ዓ ም በመንግሥታቸው ባጀት ተፈቅዶለት ከተቋቋመው የሕዝብ ድርጅት ጽፈት ቤት ለፖለቲካ ቅስቀሳና ፍጆታ ‘በሰፊው ሕዝብ ድምፅ’ ከሚወጣው መጸሔት ላይ ትክክለኛ ቅጂ ነው። የኢትዮጵያ ጉልታዊ ሥረዓት ከአሮጌው የሌላው ዓለም የፊዷል ሥረዓት ጋር የሚለያይበት ወይም የሚመሳሰልበት ጥናት አላቀረቡም፤ በጅምላው ፊዳሊዝምን ማስወገድ የሚቻለው በአንድ መንገድ ብቻ ነው፤ በማለት የማሰብን አድማስ አጥቦ  ሥር ነቀል በሚለው አብዮቱ እንዲካሄድ ሆኗል።
ምዕራፍ 3 እና 4 በየጦሩ ሠፈር ለተፈጠረው የምግብ እጥረትና የደመወዝ ጭማሪ የተቀሳቀሰው ሠራዊት ሲወድቅ ሲነሣ ሰኔ 28 1966 ድረስ ወታደራዊ አስተባበሪ ኮሚቴ ነበር፤ ከዚያ በኋላ የጦር ኃይሎች የፖሊስ ሠራዊትና የቤሔራዊ ጦር ደርግ ተባለ፤ ‘ደርግ’ የሚለውን ቃል የሰጠው የብስራት ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ነበር። ደራሴው ይህ ስብስብ ለራሱ እንደፈጠረው አድርገው አቅርበውታል። ይህን ሰብስብ’ እንደ ፓሪስ ኮሚዩ ከታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል የተነሣ የአብዮታዊ አንቅስቃሴ ጅምር ይመስላል’  ይሉታል፤ገጽ 66፤ ደራሴው የፓሪሱ ኮሚዩን ስብስብ መሣሪያ የታጠቀ ሥረዓተ አልባነት የሚያጠቃው መሆኑን ታሪክ አጣቅሰው የነገሩን ነገር የለም።
ገጽ 87 ላይ ይሄው ስብስብ እንዳልካቸው መኮንንን ከሥልጣን አውርዶ ወደ እስር ቤት በመጣሉ ደስታውን ሲገልጽ፤ ‘እንደኢንግሊዝ ፓርላማ ሰብሰባ፣ በንግግር መሐል ማቋረጥ መንጫጫትና አላስፈላጊ ድምፅ ማሰማትም የተለመደ አሰራር ሆኖ ነበር’ ይላሉ። ስለፊዳሊዝም ቀደም ብለው ተንትነው ስለነበር ምናልባት እየነገሩን ያሉት በመጀመሪያ በኢንግሊዝ ታሪክ ውስጥ የሕዝብ ተመራጭች ከነገሥታቱ በላይ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ሰነድ ’ Magna Charta’ ማጋናአ ካርታ  ከመፈረሙ እ ኤ አ 1215 ዓ ም በፊት የነበረውን የኢግሊዝ ፓርላማ ወይስ ከዚያ በኋላ ያለውን ግልጽ አላደረጉም።  ገጽ 177 ላይ የመሬትን አዋጅ ሲያስተላልፉ በሦስት መከፈላቸውን  በሮማዊያን ዘመን የነበረውን የፓርላማ ቅርጽ እንዳለው ሊያሳዩን ሞክረዋል። ከፋሽሽቱ የመሶሎኒ ፓርላማ የንፁሃን ኢትዮጵያዊያን  ደም  እንዲፈሰ ካደረገው  የተለየ ነው ማለታቸው ይሆን?  ገጽ 247 ላይ ደግሞ ‘የሩሲያውያንና የእኛ አብዮት አንድ ነው’ ይላሉ። በሩሲያውያ አብዮት ከአስር ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያለቀበት እንደሆነ ይገለፃል፣ መንግሥታቸው ያንን ያህል ኢትዮጵያውያን መግደሉን እስከ ዛሬ የገለጸ ጸሐፊ የለም።
ገጽ 140 ላይ፣ ጅንራል አማን ሚካኤል አምዶም በተገኙበት ስብሰባ ላይ አንዱ ወታደር ተነሰቶ‘የተማርን ነን የሚሉ ሰዎችና ዳኞች የለውጡ እንቅፋት ናቸው’ ሲል ጅንራሉ ‘እባካችሁ የዚህን ዓይነት የተዛባ ሐሣብ አታቅርቡ’  በማለት መክረው ነበር። በመጽሐፉ ውስጥ በዙ የተዛቡ ነገሮች  እናገኛለንና ታገሱኝ።
ከገጽ 68 እስከ 74 የ 108 የደርግ አባላት የስም ዝርዝር፣ የመጡበት የጦር ክፍልና የዘር ሐረጋቸውን ጠቅሰዋል፤ በነካ ብዕራቸው ከሞት የተረፉትን በየጊዜው ወደስብሰባቸው የሚጠሯቸውን ጅንራሎችና የወያኔን ጅንራሎች የዘር ሐረግ ቢነግሩን መልካም ነበር፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዘር እንደተመረጠ አድርገው ካቀረቡት ዘንዳ ማለቴ ነው።  የሚገርመው ሻለቃ አጥናፉ አባተን ነጠለው በብሔረተኝነታቸው መፈረጃቸው ነው፤ ለማስተባበል በሕይወት የሉም፤  ገጽ 265 ይመልከቱት፣ የሶሻሊስትን ዓለም አቀፋዊነትን አይቀበሉም ለማለት ይሆን ወይስ ጎጃሜ ነኝ ይላሉ ነው? ካሉም ስህተት የለውም፤ኢትዮጵያዊነታቸው ጥያቄ ውስጥ ሰለማይገባ፣መግቢያቸው ላይ፣  ደራሴው እስር ቤት ያገኙት ወጣት የመረኸቤቴን አካባቢ ወክለህ ነው ወይ? ወደ ሥልጣን (ደራሴው መንግሥት ነው ያሉት ) የመጣኸው ሲላቸው አካባቢውን መጥቀሱ ነው፣ የዘረኞችን ፈለግ ተከትሎ ‘የአማራ’ ቢል ይሻል ነበር?
ከምዕራፍ አራት መጨረሻ ላይ ገጽ 77 ላይ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማሪያም የስብስቡ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን ያሳያል፤ ቀደም ሲል ሰብሰቢው ሊቀመበር ሻለቃ አጥናፉ አባተ፣ ሲሆኑ ምክትላቸው  አሥር አለቃ አበራ አጋ ነበሩ፤ ሻለቃ አጥናፉ አባተ ምክትል ሆነው ሲቀጥሉ አሥር አለቃ አበራ አጋ ተራ አባል ሆኑ። አርቀው ያስተዋሉት ሻለቃ አሥራት ደስታና ሻለቃ ሕሩይ ኃይለሥላሴ አመራሩ እንደነበር እንዲቆይ አጥበቀው ተከራከሩ፣እኝኽ ሁለት ሻለቃዎች ከጅንራል ተፈሪ በንቲ ጋር በ ኢ ሕ አ ፓ አባልነት ተረሽነዋል።  ደራሴው ሻለቃ መንግሥቱን ሲገልጿቸው ከልጅነታቸው ጀምሩ በወታደር ሰፈር ያደጉ ሠራዊቱን መምራት ይችላሉ ይላሉ፣ በእርግጥ በጦሩ ሠፈር  ሠራዊቱ በሻለቃ ፣ በብርጌድ እየተቧደነ በልዩ ልዩ እስፓርቶች ይወዳደራል፤ ችሎታ  ቢቻውን ለድል አያበቃም ነበር፣ ቲፎዞ ወሳኝ ነው፤ሻለቃ መንግሥቱ የተጠቀሙት ያንን ነው። ሥልጣንን በቲፎዞ ተቆጣጠሯት፤ የቀረው ታሪክ ነው፤ ነጮች’ ONE MAN SHOW’  ይሉታል፤ከራስ ጋር ሮጦ ማሸነፍ፣ የአንድ ሰው ትዕይንት! ሌላው አድማቂ ወይም ሎሌ፤ ከምዕራፍ አምስት ጀምሮ ካለው እቀጥላለሁ፣ ሰላም እንክረም።
ታደለ መኩሪያ
tadele@shaw.ca

No comments:

Post a Comment