ሰሎሞን ታምሩ ዓየለ
ውድ ወንድሜ ዳዊት ሆይ! በቀልድ መልክ የጫርካትን መጣጥፍ ሳነብ ጊዜና እኔም ተማርኬና እጅ ሰጥቼ ይኽው መንገድ በብርቱ ጠቃሚና ተፈላጊ ነገር ግን ትኩረት ያልተቸረው የመልዕክት ማስተላለፊያ ቱቦ እንደሆነ ተረዳሁኝ። በተለይ የአገሬ ምሁራን፤ የዕውቀት ልካችው ጥግ የደረሰባቸውና ተሕዝብ ጉያ ወጥተው ወደ ሕዝብ ተመልሰው ገብተው ለማስተማርና የአስተምህሮቱ ዘዴ ጠፍቷቸው ዕውቀታቸውና ችሎታቸው ለሳይንሳዊው ወይም በነሱ አጠራር ለአካዳሚኩ ኅብረተሰብ ክፍል ለሚሉት ብቻ ተገድበው የቀሩቱን፤ ወደ ህዝብ ለመመለስ ዓይነተኛ ዘዴ መሆኑን ለማመላከት ጭምርም ፈልጌ ነውና ተማጽኖዬን ተቀበለኝ ስል የድጋፍ መልዕክቴን እንዲህ ከምኖርበት ተወደ ካሊፎርኒያ በዚሁ ድረ ገጽ በሚሉቱ በትኜዋለሁኝ። ትምህርት፤ ዕውቀት፤ ልምድና ክህሎት ማኅበራዊ ዋጋቸውና ጠቀሜታቸው የሚለካው በማኅበራዊው ኑሯችን ውስጥ በምናገኘው የተስተካከለ ለውጥ፤ በማኅበራዊ አስተሳሰባችንና ምግባራችን እንጂ በግለሰቦች ክብርና የአካዳሚክ ዕውቀት መራቀቅ ብቻ አይደለም። ዕውቀታችንና ችሎታችንም ጭምር ሕዝባዊ ማድረግ ልምድ ማድረግ አለብን። ታለባለዚያ ዕውቀት ሙትና በድን ነው። አይጎተጉትም፤ ለለውጥና ለመሻሻል አያነሳሳም። ዕውቀት ልኳ የሚታወቀው በጆርናል፤ በፔሮዲካልስና በሌሎች ህትመቶች ተጠርዛ ከመደረደሪያ ላይ ተቀምጣ ከማገናዘቢያነት ባሻገር ከፍ ያለ አገልግሎት እንደየደረጃውና እንድ አቅሚቲ መስጠት ስትችል ብቻ ነው። ለሕዝብ መገልገያነቷን እናመቻቻት። ካልሆነ ደግሞ ከጋን መብራትነት የዘለለ አቅም የላትም። ይሄንን ደግሞ አንሻውም። መሆንም የለበትም። ትንሽ የማሰብ ችሎታችንን መጨመር ብቻ ነው። ሁልግዜ የቁጥር ሰንጠረዥና ግራፍ ወዲያም ሲል ትንተና ብቻ ወደ ሕዝብ መቅረቢያና መልዕክት ማድረሻ አይሆንም። መናቄና ማንኳሰሴም አይደል። ወይም ደግሞ አስፈላጊም አይደለም ማለቴም አይደለም። ለሁሉም የሕዝብ ክፍል ግን እኩሌታ አገልግሎት አይሰጥም ማለቴ ጭምር መሆኑ ይታውቅልኝ። መልዕክቱ በቀላሉ በቶሎ ተቀነባብሮ በፍጥነት ለኛ ለመልዕክት ተቀባዮቹ ፈጥኖ ከች አይልም ለማለት ፈልጌ ነው። የቸኮለና ሃሳቤ ያልገባው ለወቀሳ እንዳይቸኩልም ማስገንዘቤ እንጂ።
ቀልድ፤ ጨዋታ፤ ትዝታ፤ አሽሙር፤ ፌዝ፤ ሙሻዙር፤ ትረካ፤ ተረት ተረት፤ ነገር በምሳሌ አባባል፤ ብሂልና ሌሎችም የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ችግራቸውን፤ ብሶታቸውን፤ እሮሮዋቸውን፤ ስጋታቸውን፤ ፍርሃታቸውን፤ ጭንቀታቸውን፤ ተስፋ ማጣታቸውን፤ ሃዘናቸውን፤ ደስታቸውን፤ ፍላጎታቸውን፤ ምኞታቸውን፤ ጥጋባቸውን፤ ቆራጥነታቸውን፤ አይበገሬነታቸውን፤ ጀግነነታቸውንና ጥንካሬያቸውን ሌላም ባህሪያቸውንና ጠባያቸውን ጭምር መግለጫም እንደነበር እናስታውሳለን። በአንዳንዶቻችንም ውስጥ ዛሬም እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሁኔታዎች ይንጠባረቃሉ፤ ይታያሉ፤ ይገለጣሉ።
ቀልድና ጨዋታ በአግባቡ ከተያዙና ከተገለገልንባቸው የሕይወታችን ቅመም ናቸው። ኑሮንም ትርጉም ይሰጡታል። ሳይበዙ በመጠኑ ደግሞ እንደ ብትን ጨው፤ ስኳርና ማርም ናቸው። በተለይ በተለይ ድግሞ በቁም ነገር ከታጀቡና እንደ ጭብጦ በቅቤ ከታሹ ጉልበት አላቸው። አስተማሪዎች፤ አዝናኖኞች፤ ለፍትህና ርትዕ አነሳሶች፤ አደራጆችና አነቃቂም ናቸው። ሰውነታችን በድብርትና ጭንቀት ብዛት የሚያመነጨውን ማንትስ የሚባል “ጎጂ ኤንዛይም “ እያዝናና ድራሹን ያጠፋል በምትኩም ሌላ ሰውነት የማይጎዳውን ቅመም ያመነጫል። በሽታ የመፈወስም ባህርይ ሊኖራቸውም ይችላል። የደነደነን ልብ ይከፍታሉ፤ አእምሮንም በማነቃቃት መልዕክትን በፍጥነት በመልካም ፍቃደኝነት መቀበሉን ያረጋግጣሉ፤ መንፈስንም ያረካሉ፤ ነፍስንም ደስ ያሰኛሉ፤ በስተመጨረሻም እንደ ጂምናስቲክ እንቅስቃሴ የተወጠረ አካልን ያበረታታሉ፤ያዝናናሉ።
ቀልድ፤ ጨዋታ፤ ትረካ፤ ትዝታና ሌሎችም ትክክለኛ ፍቺያቸው ምን እንደሚመስሉ፤ አንዱ ከአንዱ የሚለይበትም ሆነ አንዱ በአንዱ ውስጥ የመገኘትና አንዱ አንዱን አጉልቶ የማሳየት ሚስጥሩ፤ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው ምን መልክ እንዳለው የተረጋጋጠ ማስረጃ ማቅረብ ግን አልችልም። እንደው በደምሳሳው ሳስበው ግን ቀልድም ሆነ ጨዋታ የጥበብ ዕውቀት ዘርፍ መሆናቸው ግን ፍንትው ብለው ይታዩኛል። በቀልድና ጨዋታ የጠለቀ ዕውቀትም ትምህርትም የለኝ። ለመማር ግን ዝግጁ ነኝ ። ብርቱና ፈጥኖ የሚያደርስ አስተማሪ ካገኘሁኝና ጊዜው ያላለፈብኝ ተማሪ ካልሆንኩኝ በስተቀር። ግን እንደ አንድ የህብረተሰቡ ክፍልፋይ አካል፤ ጤናማና ሰላም ወዳድ ዜጋ ደግሞ አጔጉል ቀልዶችም ሆኑ ጨዋታዎች አደግኝነታቸውንም ያሳስበኛል። ጎጂና አፍራሽ ቀልድም ጨዋታም ፍቅር ያበላሻል። ከነሱ ድግሞ መራቅና ጆሮ አለመስጠት ነው። አበውና እማዎች ሲተርቱ “ቀልድና ቤት ያበላሻል “ መባሉንም አንዘንጋ። ገንቢ ቀልዶች ደስታን ይፈጥራሉ፤ ወዳጅም ደንበኛም ያበዛሉ።
ቀልድና ጨዋታ የትም አለች። ትኖራለችም። በጊዜና በቦታም ልትወሰን ብትችልም ቅሉ፤ ምንአልባትም አንድ ቀን ከህዋው ወይም ከጠፈሩ ዓለምም እንሰማት ይሆናል። ይኽው ከመንግስተ ሰማያት ከሚኖሩ ሰዎችና ወደ ፊትም አምባገነኖችና አንዳንድ የመንግስት ሰዎች ገነ ለገና አያ ሞት ሲመጣባቸውና ስልጣናቸውን ነጥቆ ጉዞ ወደ መቃብር ሲሉ ስለሚጠየቁትና ሰለሚሰጡት መልስ ከወዲሁ እየተቀለደ አይደለም እንዴ? እስቲ ማነው የማይቀልድ ? ማንስ ነው የማይጫወት? መልሱ ምንም የሚል ነው። በፓርላማ ታዋቂ ፖለቲከኞቻችንና ሚኒስትሮቻችን፤ ከዜና ማሰራጫዎቻችን ኢቲቪና የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጥሩ ቀልደኞችና ፌዘኞች አይደሉምን? በተለይ ደግሞ “የዜና ምርቶቻቸው” በሽ አይደለም እንዴ! በቁጥር፤ በብር፤ በዕድገትና ልማት፤ በድራማና በትዕይንት ዝግጅታቸው የታወቁ ቀልደኞች አይደሉም የሚለኝ ካለ ለፍልሚያው በየትም ዝግጁ ነኝ። ወይ ጉድ! ነፍሳችንን ጮቤ እያስረገጧት አይደለም። ድሮ እንደተባለው ልድገመውና “ኢቲቪና ሬዲዮ ኢትዮጵያ” ትክክለኛውን የሚናገር ሰዓቱን ብቻ ነው ከተባለ ቆየ። መንግስትም ይቀልዳል፤ ያፌዛል፤ እኛም በአጸፋው እንቀልዳለን።
ቀልድና ጨዋታ መንግስትም ቤት በፓርላማም አለች። ጠ/ሚንስትር መለስ ጥሩ ቀልደኛና የሚያፌዙ ሰው ነበሩ። አብረዋቸው በም/ ቤቱ ደፋ ቀና በሚሉት አገልጋዮችም ሲያፌዙ አይተናል። ከበረከት ጋር በመሪ ተዋንያንነት “አኬል ዳማንና” ትንሽ ዘግየት ብሎ ከሳቸው መጥፋት በኋላ “ጂሃዳዊ ሃረካትን “ተመልክተናል። በቅርቡም እነሱ” አክራሪ አርቶዶክስ “ ብለው በሚጠሯቸውም ላይ የተለመደ ትዕይንታቸውን እያቀነባባሩ እንደሚገኙ ያነበብኩኝ መሰለኝ። አይጣል ነው! ይህ መንግስት የሚባል ተቋም ይሄንን ስራዬ ብሎ ከሚሰራ ለምን ኑሮ እንዲሻሻልል ማድረግ የሚችለውን አያደርግም? ዕድገትና ልማት ድራማና ትዕይንት ማምረት ነው እንዴ? እውነትም ይሄ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ጭንቅላት ሳይሆን ድንጋይ ብቻ እንደሚያመርት ማራጋጫ እራሱ እየሰጠ መሰለኝ። በ1985 የአ አ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ቡጥሮስ ጋሊ ከቤታቸው መጥቶ ሳለ ተቃውሞ ለማድረግ ግቢዋን በር ወጣ እንዳሉ በጥይት የሚችሉትን ከገደሉ በኋላ ለምን ጥይት አስተኮሱ ?ሲባሉ የሚያስለቅስ ጢስና ግፊት ያለው ውሃ የሚረጭ መኪና የለኝም ብለው አስገርመውን ነበር። የታምራት ላይኔ ስኳር ቀመሳን ቅሌት እንዴት አድረገው በፓርላማቸው እንዳብራሩታ አይጣል ያሰኛል። በተጨማሪም በሳቸው አገዛዝ ዘመን የአገሬ ገበሬ ሻይና ቡና በስኳር መጠጣት መጀመሩንና ስኳር ከገበያ ጠፍቶ መወደዱን መግለጻቸውንም እናስታውስ። አባ ዱላም አንዱ ቀልደኛና ፌዘኛ ነበር። በሙስና የሰራውን ቤት ለድርጅቱ ኦሕዴድ ገቢ አደረገ። ወ/ ሮ አዜብም በቀልድ ጨዋታና ፌዝ ከቀዳሚ እመቤቶቻችን ዋና ናቸው። ባለቤታቸው መለስ ሚስኪን ሰው እንደነበሩ፤ የቀበሌና የመንጃ ፍቃድ ጊዜ ኖሯቸው ሳያወጡ እንደሞቱና በፔሮል ላይ ብር 4ትሺ ብቻ የሚያስፈርም ደመወዝ እንደነበራቸው አሳዝነው አስለቅሰውናል። የሙስናው ቀልድም ጨዋታም እጅግ ያሳዝናልም፤ ያበሳጫልም። የፍርድ ቤቶቻችን አሰራርም፤ ብያኔ አሰጣጣቸውም እንዲሁ በፌዝ የተሞላ ነው። በቅርቡም ጠ/ሚንስትር ኃይሌም ስለ ድርጅታቸው ዲሲፒሊን አክባሪነት ሲናገሩ ድርጅቴ ” ሊስትሮ ሆነህ ስራ ቢለኝ እሰራለሁ “ ማለታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ፕሮፌሰር መራራም ቀላል ቀልደኛና ፌዜኛ አልነበሩም። “ተባበሩ፤ አለባለዚያ ተሰባበሩ “ ብሎናል። “ኢሕአድግ አፍ እንጂ ጆሮ የላትም “ “ ምርጫ፤ ቅርጫ” ብሎም ፈገግ አስደርጎናል። አንድ ውቅት በተለይ በ1984ቱ አካባቢ “በሙዳይ “ መጽሄትም ላይ ከፋብሪካው የሚፈጭ ስንዴ ጠፍቶ ስብሰባ የሰለቸው ላብ አደር “ዴሞክራሲ እየፈጩ” እንደሆነ ቀልዶ አልፏል። አንድ በግል የምትታተም ጋዜጣም በ1993ቱ መሰለኝ የጠ/ሚንስትር መለስ እናትን ከዚህ ዓለም በሞት መለየትና የቀብራቸውም አፈጻጸም በአድዋ መደረጉንና የመንግስት ሄሊኮፕተሮች አስክሬን ይዘው ከስፍራው በቶሎ መገኘታቸውን መረጃ የደረሰው ጋዜጠኛ በሁኔታው በመገረም መሰለኝ (ቀብሩ የግል ጉዳይ መሆኑን ለመግለጽ መሰለኝ) “ጠ/ሚንስትሩ መዘዙ ወይስ አዘዙ” ብሎ በመጻፉ በጠዋቱ ፈገግ አስደርጎናል። ቀልድና ጨዋታ ጦር ሜዳ ድረስ ዘልቃ ከሻዕብያ ጋር ፍልሚያ ላይ የነበረውን የሃገር መከላከያ ሠራዊትም ለአፍታ አዝናንቶታል። አንባቢያን ሰለ ጦር ሜዳዋ ቀልድ ማውቅ ከፈለጉ በሻለቃ ማሞ የተጸፈውን “የወገን ጦር ትዝታዬን “ እንዲያነቡ ይመከራሉ። እኔ ግን ከዚያም ባሻገር በቀነ ቅዳሜ የሬዲዮ ፋና እንግዳ ሆኖ ቃለ መጠይቅ ለሻለቃ ወጋየሁ ደግነቱ (ወጋየሁ ራሱ ኢጆሌ ካራ ሚሌ ስለሆነ ጨዋታና ቀልዱ አይጣል ነው። ነፍስ ይማር_ሃርኬ ሁማ።) ሲደረግለት በጆሮዬ ትረካውን በራሱ አንዳበት ስለሰማሁኝ ሳቅ በሳቅ ሆንኩኝ የጀኔራል ረጋሳ ጅማ አመራር ሃይለኛ ነበር። ቆርጦ ቆርጦ መጣል ነበር የምትል ዘፈኑ ነች ለዛ ያበቃችው። አንዳንድ የወያኔ ኢሕአድግ ፖለቲካ ደጋፊዎች ደግሞ በቅርቡ የጤፍ ሰብል እንዲህ አነጋጋሪ በሆነችበት ዘመን ንብረትነቷ ኢትዮጵያዊ መሆኗ ቀርቶ በዕውቀት ማነስ ነው መሰለኝ ” መለስ ጤፍን ዲስከቨር “ አደረገ ብሎ የሚከራከርም አንብቤአለሁ። በስራ ዘመኔም አንድ የወሎ ገበሬ ያለኝን ላጫውታችሁ። ከዚያ ከአስከፊው ድርቅ በኋላ በምግብ ለስራ ፕሮግራም ተሳትፎ የሚያገኛትን ተጨማሪ ምግብ በዘመነ ወያኔ ያጣ እንዲህ ነበር ግጥሚቱን በፊቴ ያነበነባት። ” ከልማቱ እንጂ ምን አለኝ ከፊቱ፤ እንደገና ይምጣ ኮሎኔል መንግስቱ።” ቀልድ በሕዝብ ፊት ንግግር በሚያደርጉ ታላላቅ ሰዎችም ትዘወተራለች። ታዋቂ መምህራንም የዕለቱን ትምህርት ከመጀመራቸው አስቀድሞም ቀልድና ጨዋታ የተለመደ ተግባራቸው አድረገዋታል። የመድረክ አስተዋዋቂ ሰዎችማ መደበኛ ስራቸው ነው። ቀልድና ጨዋታም “ቢዝነስ” ነች። የገቢ ምንጭም መሰብሰቢያም ሆና ገበያ ላይ ወይ በክር አሊያም በሲዲ ላይ ተቀርጻም እኛው ገዝተናት አብረን ነፍስ አስደስትነንባታል። በቅርቡ ደግሞ አንድ ራሱን ” አባ መላ “ እያለ የሚጠራ ቀባጣሪና አንድ ጎበዝ እህቴ ደግሞ ” አባ በላ” (በላን ጠበቅ ተደርጎ ይነበብ) ብላ የጠራችውና ውርደት እንደ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቀለቡ የሆነ ሰውዬም ተፈጥሯል። ደረጃውና ምደባው ግን ከተራ ቅሌት ሰፈር ነው። እንደ አቶ ስብሃት ነጋ ዓይነቱ ደግሞ ቀልድ የሚባል የማይገባውም እንዳለ ማወቅ ደግ ነው። ስብሃት የአማራና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን አከረካሪ በመስበር ብቻ ነው መታወቅ የሚፈልግ። ሲሰራም፤ ሲበላም፤ መለኪያም ሆነ ብጭርቅ ሲጨብጥና ከተቃራኒ ጾታም ሲዳራ የሚታየው አማራን ሰባብሮ ገደል መጣል ነው። አከርካሪውን ብሎ ሺባ ማድረግ ነው ምኞቱ ሁሉ። የ፲ አለቃ( የምን ጄኔራል ነው!) ሳሞራ የኑስም እንደዛው ጸረ አማራ ነው። ነገር አልጥምና ቶሎ አልገባ ሲለው” ኧረ የሰው ባህሪ” እያለ የሚደጋግም ወድ ጓደኛ ነበረኝ። እኔም ይቺኑ እንደ ሞኝ ይዤ “ኧረ የስብሃትና ሳሞራ ባህሪ” ብልስ?
ስለ ቀልድና ጨዋታ ስናወሳ ቀልደኞችንም ዝም ማለት አይቻለንምና ማነው ቀልደኛ መሆን የሚችለው ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው። ጥሩ ስብእናና መልዕክት የማስተላለፍ፤ ሃሳቡን በቀላል ቋንቋ መግለጽ የሚችል፤ አመቺ ቦታና ጊዜን መምረጥ የሚችል መሆን አለበት። ልማታዊ የሆነ ቀልደኛ ደግሞ ለአምባገነኖች ጥሩ ፈረስ ነው። ቀልደኞችና ጨዋታ አዋቂዎች ቀልዶቻቸው ወጥነት (ወሪጅናሌ) ቢይዙ ይመረጣል ። ግልባጭ ከሆኑ ብዙም አያስፈግጉንም፤ አያዝናኑንም። ለምሳሌ፦ ገበሬ ስኳር ገዝቶ ቡናና ሻይ ጠጣን፤ ገበሬው ጤፍ ገዝቶ መብላት ማብሰሩን እንደ ኑሮ ውድነት ምክንያት አድሮጎ ማቅረብ ደስ አይልም። ግልባጭ መሆን ነው። ራስን አቅል ማጣት እንጂ የነገር አዋቂነትን አያሳይም። ድግግሞሽ ነው። አንዳንድ ሕዝብ ደግሞ አብዛኛው ነዋሪው ጥሩ የመቀለድና የተጫዋችነት ባህርይ ይይዛል። ለምሳሌ በቡልጋሪያ አገር ጋብሮቭስኪ ክልል የሚኖሩቱ ጥሩ ቀልደኞች ናቸው። አንድ ደራሲም በአማርኛ ቋንቋ ” የጋብሮቮ ቀልዶች” በሚል ዐርዕስት ተጽፋ ለገበያ ከቀረበች እነሆ ከ25 ዓመት በላይ ሊሆናት ነው። በኛም አገር ቢሆን የሐረርጌ ልጆች ጥሩ ቀልድ ይሰራሉ። ምንአልባትም ያቺን አረንጓዴ ጓደኛቸው(ጅማ) ዛፍ ላይ ለመውጣትና ለመቃም (ለመብላት ሳቅ!) ሰብሰብ ስለሚሉም ይሆን? እንግዲህ ይህንን በምርምር፤ በጥናትና ክትትል ማረጋገጥ የማኅበራዊ ሳይንስ ወይም ጥበብ ሰዎች ተግባርም አይደል?
እንግዲህ ልጠቅለለውሳ። ቀልድ፤ ጨዋታ፤ ፌዝ፤ አሽሙር፤ መሸወድ፤ ማታለል፤ ማጭበርበር፤ ቁጭ ይበሉ ሌላም ሌላም ትክክለኛ ፍቺዋንና ትርጉማንና አመዳደቧን እስከምናውቃት ድረስ ዝም ብለን እንደዛ እንደ ” ዴሞክራሲ ወፍጮ መፍጨት” ነው። ይሄ የዴሞክራሲ ወፍጮ ደግሞ አንዳንዴ ይከካል፤ ይሸረክታል፤ ክኩን ከጥሬው መለየት ያዳግተዋል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ አድቅቆና አልሞ ይፈጫል። የወፍጮውን ጥርሶች እሽክርክሪት የሚያስተካክል ጥሩ መሃንዲስና ሜካኒክ ያሻናል። ብቻ ዕውቀትና ምንትስ እያደር ይጠራል ብልስ ስህተት የሰራሁ አይመስለኝም። ለጊዜው ሁሉ ነገር ዝብርቅርቅና ድብልቅ ነው። ገና እንደ ፖለቲካችን አልጠራም። ሚናውንም አልለየም። ቀልዱ ከፌዙ፤ ጨዋታው ከሃሜቱ፤ አሽሙሩ ከሹፈቱ፤ ሽወዳው ከማታለሉ፤ ሙስናው ከስርቆቱ፤ ቢዝነሱ ከዝርፊያው ሌላም ሌላም። መንግስት ያሾፋል፤ ፖለቲከኞች ይዋሻሉ፤ ይቀልዳሉ፤ ሕዝቡም በራሱም ኑሮ ይጫወታል ፤ ይቀልዳል አንዳንዴም ግጥም እያወረደ ያቀነቅናል። ለመሆኑ በኢትዮጵያችን የመጀመሪያው ቀልደኛና ጨዋታ አዋቂ አለቃ ገብረሃና ናቸው የሚባለው እውነት ነውን? እህሳ ምን ይሰማሃል? አበቃሁ! እናመስግናለን!!!!!
ሠሎሞን ታምሩ ዓየለ
No comments:
Post a Comment