Thursday, March 27, 2014

“ለውጡ እንደቀረበ ጥርጥር የለኝም” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር


ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ከሁለት ወር በፊት ወደ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ለስራ ጉብኝት ሄደው ነበር፡፡ አሁንም ወደ አሜሪካ ጉዞ ሊያደርጉ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የአሁኑ ጉዞ አላማ ምንድን ነው?
Eng. Yilkal Getnet Semayawi party chairman with Negere Ethiopia newspaper
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር
ኢንጅነር ይልቃል፡- መጀመሪያ ያደረኩት ጉዞ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የፓርቲውን አላማና ፕሮግራም፣ የሰራናቸውን እንዲሁም ወደፊት ልንሰራቸው ያሰብናቸውን ስራዎች፤ ሰማያዊ እንደ አዲስ ኃይል ሲመጣ የቆመላቸው ሀሳቦችና እምነቶች ምን እንደሆኑ ለማስተዋወቅ ታስቦ የተደረገ ነበር፡፡ የአሁኑ ግን ከበፊቱ የተለየና ለሰማያዊ ሊቀመንበር በሚል በቀጥታ በአሜሪካ መንግስት ስቴት ዲፓርትመንት የተደረገ ግብዣ ነው፡ ፡ የአሁኑ ወጣት የአፍሪካ መሪና ወደፊትም ለአገራቸው መሪ ሊሆኑ የሚችሉ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ጥሩ ስራ የሰሩ፣ በውድድር ከተመረጡ በኋላ በአሜሪካ መንግስት ስቴት ዲፓርትመንት በሚደረግ ምርጫ መመዘኛዎቹን ለሚያሟሉ ሰዎች የሚሰጥ እድል ነው፡፡ በመመዘኛዎቹ መሰረት በማሸነፌ የአሜሪካ መንግስት ሙሉውን ወጭ ሸፍኖ ለሶስት ሳምንት በአሜሪካ የመንግስት አወቃቀርና ዴሞክራሲን ጨምሮ በተግባር የሚሰጡ ስልጠናዎችን የማግኘትና፣ የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናትም ባሉበት ከተለያዩ ተቋማት ጋርም ለመገናኘት እድል ይኖረኛል፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የፖለቲካ መሪዎች ጋር ተወዳድረው ነው ያሸነፉት ማለት ነው?
ኢንጅነር ይልቃል፡- አዎ! ግን ሌሎች ያሸነፉ ተጨማሪ ሰዎች ይኑሩ አይኑሩ አላውቅም፡፡ ይህ የፕሬዝዳንቱም ‹ኢኒሸቲቭ› ይመስለኛል፡፡ ለእኔ ግን የተሰጠኝ አዲስ ትውልድ አመራሮች፣ ወደፊትም በአገራቸው መሪ መሆን የሚችሉ፣ ስትራቴጅካሊ የሚያስቡ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይም ሆነው መልካም ስራ ለሰሩ ሰዎች የሚሰጥ ልዩ የጉብኝት እድል ነው፡፡ በአጠቃላይ ውድድርም ተደርጎ የሚወሰድ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- የአሜሪካ መንግስት ይህንን እድል ሲሰጥ እርስዎ እንደ መሪም ሆነ ሰማያዊ እንደ ፓርቲ ያሸነፋችሁበትን ዋና ዋና መመዘኛዎች ነግረዋችኋል?
ኢንጅነር ይልቃል፡- ሲመርጡኝ ዝርዝር መረጃዎችን ወስደዋል፡ ፡ መሰረታዊ የሚባሉትን ለምሳሌ ያህል የፖለቲካ ቆይታዬ፣ የትምህርት ዝግጅቴን፣ በፖለቲካው ውስጥ የነበረኝን ተሳትፎ የመሳሰሉትን መረጃዎች ለእጩነት በቀረብኩበት ወቅት ከእኔ ወስደዋል፡፡ ከዛ በኋላ ያስመረጠኝን ዝርዝር መስፈርት አላውቅም፡፡ ነገር ግን ወጣት (እስከ 45 አመት ባለው ውስጥ)፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ መልካም ስራ የሰራ፣ ወደፊትም የአገሩ መሪ ሊሆን የሚችል የሚሉት ዋና ዋና መመዘኛዎች እንደሆኑ አውቃለሁ፡ ፡ ይህም በተለይ ከሰማያዊ አንጻር ከሁለት ነገሮች አኳያ እንድናየው ያደርጋል፡፡ አንደኛው በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ፖለቲካና እስካሁን ጠቅልሎ የያዘው ኢህአዴግ ነበር፡፡ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አድርጎ ነበር የሚያየው፡፡ ሆኖም እንደዚህ አይነት እድል እንደ አሜሪካ ባለ ትልቅ መንግስት የተቃዋሚ መሪ የተለየ ስራ ሰርቷል ተብሎ ሲጋበዝ ሰማያዊ ፓርቲ አዲሱንና ወደ ፖለቲካ ያልመጣውን ትውልድ ወደ ፖለቲካው ለማምጣት በሚያደርገው ጥረት እንደ አንድ ማበረታቻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ በሌሎች መስኮች ከምናደርጋቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች በተጨማሪ ለሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ይህኛው ግብዣ ሲደረግለት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ከአሁን በፊት ለሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ የ35 አገራት ኤምባሲዎች የ‹ኢትዮጵያ ፓርትነርስ ግሩፕ› የሚባለው ሲደረግ በአመታዊ ስብሰባቸው ላይ ዋና ተናጋሪ ሆኜ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካና ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ዋና የትግል እንቅስቃሴና የወደፊት አላማችን እንዳስረዳ የተለየ እድል ተሰጥቶኛል፡፡ ይህም ለፓርቲው ሌት ተቀን ለሚሰሩ ወጣቶች፣ እንዲሁም ሁል ጊዜም ቢሆን ወጣቱ ተከታይና ጀሌ እግረኛ ከመሆን አልፎ ራሱ ኃላፊነት የሚወስድ፣ መምራትና የራሱን መሪዎች ማውጣት የሚችል ትውልድ መምጣቱን የሚያሳይ መልካም ጅምር ነው፡፡

ነገረ-ኢትዮጵያ፡- የአሜሪካ መንግስት ከ9/11 እንዲሁም ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ሶማሊያ ውስጥ ባለው ጥቅም ኢህአዴግ ላይ እስከመጨረሻ ግፊት ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡ አሁን ለእርስዎና ለፓርቲዎ ይህን እድል ሲሰጥ ለኢህአዴግ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው? የተቃውሞ ጎራውም ቢሆን እስካሁን የሚመራው በ1960ዎቹ ፖለቲከኞች ነው፡፡ አሁን የአሜሪካ መንግስት ይህን እድል ለእርስዎ እንደ መሪና ለሰማያዊ እንደ ወጣት ፓርቲ ሲሰጥ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚኖረው አንድምታ ምንድን ነው?
ኢንጅነር ይልቃል፡- እንግዲህ ይህን ጉዳይ ህዝቡም ሆነ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ማህበረሰቡ እየተረዳው የመጣ ይመስለኛል፡፡ ባለፈው አርባ አመት በገዥውም ሆነ በተቃዋሚው ያለው በአንድ አይነት እድሜና የግራ ርዕዮት የሚሽከረከር ነበር፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ፖለቲካም ሆነ ኢትዮጵያን በሁሉም መመዘኛዎች ወደ ፊት ሊያራምድ አልቻለም፡፡ እንዲያውም ጥላቻ፣ ቂምና ቆርሾ፣ የእስር በእርስ መጠላፍና የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሆኖ ቆይቷል፡ ፡ ያ ትውልድ ያላመጣውን ውጤትም ወጣቱ ያመጣዋል የሚል ነው፡ ፡ ኢትዮጵያ የወጣት አገር ነች፡፡ 70 ከመቶ የሚሆነው ከ35 አመት በታች ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል በውክልና ደረጃም ሆነ አዲስ አስተሳሰብና ከበድ ያለ ነገር ይፈልጋል፣ ከዓለም ከተለያየ አቅጣጫ መረጃ ያገኛል፣ በአስተዳደጉም አንጻራዊ ነጻነት አለው፣ በአመለካከትም ቢሆን ይህ የህብረተሰብ ክፍል ወደ ፊት እየመጣ ነው፡፡ ከዚህም አንጻር በታክቲክም ሆነ በአመለካከት ይህን የህብረተሰብ ክፍል መደገፍ የሚያዋጣና አይቀሬነቱን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ዋናው የኢህአዴግ የፖሊሲ መሰረት ማታለል ነው፡፡ ‹‹እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትበታተናለች፡፡›› በሚል የምስራቅ አፍሪካንም ሆነ የሶማሊያን የሽብር ሁኔታ እንደ ማታለያ እየተጠቀመ፤ እነሱ የስጋት ፖለቲካ ውስጥ መግባታቸውን ስለሚያውቅ እሳት የማጥፋት ስራ ነበር የሚሰራው፡ ፡ ይህ ግን መሰረታዊ መፍትሄ የሚያመጣ ሳይሆን ነገሮችን እያዳፈነ፣ ችግሩን እያባባሰ በመሆኑ እንዲሁም የጠቅላይነት ፖለቲካን ለቀጠናውም ሆነ ለኢትዮጵያ እየጠቀመ አለመሆኑ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ኃይሎች ተረድተውታል፡፡ አማራጭ የፖለቲካ ኃይልና መሰረታዊ የሆኑ የዴሞክራሲ መመዘኛዎችን ማምጣት፣ መሰረታዊ የሆኑ የዜጎች ልማትና ዴሞክራሲ ማፋጠን፣ በአቻነት የተመሰረተ ግንኙነትን ካልሆነ በስተቀር በጉልበትና በጠብመንጃ የሚደረገው አገዛዝ እንደማያዋጣ የተረዱበት ጊዜ ነው፡፡ አሜሪካኖች አባቶቻቸው የሞቱበት ነገር (the ideals of ower founding fa­thers) የሚሉት የሰውን ልጅ መብትና የሰብአዊ መብት ማክበር ለሁሉም አገራት መድሃኒት መሆኑን ራሳቸው አፍጋኒስታንና ኢራቅ ውስጥ በነበሩበት ወቅት አይተውታል፡፡ በየመን፣ በምስራቅ አፍሪካዋ ሶማሊያም ቢሆን ተመሳሳይ የእሳት ማጥፋት ፖለቲካ ለውጥ እንዳላመጣ ተገንዝበውታል፡፡ በየ ደረጃው በህዝብ ተሳትፎ የሚያድግ ዴሞክራሲና በዜጎችም ይሁን በአገራት መካከል በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መምጣት ካልቻለ አፋኝነት እንዳልጠቀመ የተረዱበት ጊዜም ይመስለኛል፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- እስካሁን ድረስ ዲያስፖራውም ሆነ አገር ውስጥ ያው የተቃውሞ ኃይል ድምጹን ለማሰማት ሲሞክርም የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ትኩረት አናሳ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እናንተ ይህንን አጋጣሚ ስታገኙ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በስርዓቱ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ በአጽንኦት የምታስረዱት ምንድን ነው?
ኢንጅነር ይልቃል፡- አንደኛ ከመንግስት ጋር መስራት በሚሉት መርህ ላይ ኢህአዴግ ስልጣን ስላለው ብቻ በአጭር ጊዜ የጮሌነት ግንኙነት፣ ከዛም በኋላ ለአሸነፈውና የኃይል ሚዛኑ ካደላው ጋር ግንኙነት የማድረግ ዋናው የዘመኑ መገለጫ፣ ስግብግብነትን መሰረት ያደረገ የካፒታሊዝም መርህ ስለሆነ በየትኛውም መንገድ ተሂዶ የአገርን ጥቅም ማስጠበቅ የሚባለው እንደማይጠቅም ማስረዳት እንፈልጋለን፡፡ መንግስት ቢያልፍም በህዝብ ላይ የሚደርሰው በደልና ግፍን እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ለዘላቂ የአገራቸው ጥቅም እንደማይበጅ፣ ሁል ጊዜም ቢሆን ግንኙነት መመስረት ካለበት ከአገሪቱና ከአገሪቱ ህዝብ ጋር እንደሆነ፣ ግንኙነቱ ታሪካዊና የህዝብን መሰረታዊ መብቶች ጠብቆ የሚደረግ እንጅ ከአንድ ቡድን ጋር የሚደረግ ግንኙነት ኢትዮጵያን ለመሰለ ታሪክና ክብሩን ለሚወድ ህዝብ ውሎ አድሮ የማይጠቅም መሆኑን፣ በአጠቃላይም የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ፣ መሰረታዊ መብቶችና ሀሳቦች በሚከበርባቸው መልኩ የሚያራምድ አይነት አስተሳሰብን መሰረት ያደረገ ግንኙነት እንዲያደርጉ ነው በዋነኛነት ማሳሰብ የምንፈልገው፡ ፡ ከአንድ ቡድን ጋር የሚደረግ የአጭር ጊዜ ግንኙነት ራሳቸውንም እንደሚጎዳቸው፣ በቀጠናው ይገኛል የሚባለውን መረጋጋትና ሰላምም ሊያመጣ እንደማይችል እንዲረዱት እንፈልጋለን፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከዲያስፖራው ጋር በመገናኘት የምትሰሩት ሌላ ድርጅታዊ ስራስ ይኖር ይሆን?
ኢንጅነር ይልቃል፡- አሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባደረገልኝ ግብዣ ላይ ለሶስት ሳምንት እቆያለሁ፡፡ የትኬትና ተመሳሳይ ጉዳዮችን ከሚሰሩት የአሜሪካ ሰዎች ጋር ስንነጋገር ከዚህ ውጭ አንድ ወር ያህል አሜሪካን አገር እንደምቆይ ገልጨላቸዋለሁ፡፡ በዚህም አጋጣሚ ባለፈው በአየር ንብረትና በድካም ምክንያት ያላዳረስኳቸው ቦታዎች ላይ ስብሰባ የማካሄድ ሀሳብ አለኝ፡፡ ምን አልባትም ወደ ለንደንና ካናዳ ልሄድ የምችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ይህ እንግዲህ ከዚህ ካለው ስራ፣ ከጉዞ ሰነዶችና ከጊዜም ጋር ተደማምሮ በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ በድርጅታዊ ጉዳይ ላይ ለመስራት እቅዱም ሀሳቡም አለን፡፡ እዚያው ያሉት ደጋፊዎቻችንም በጉዳዩ ላይ እየሰሩበት ይገኛሉ፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ወደ ሌላ ርዕሰ-ጉዳይ ልውሰድዎትና፣ ባለፈው እሁድ ሴቶች በተሳተፉበት የታላቁ የጎዳና ላይ ሩጫ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስታችኋል በሚል ከተያዙ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ‹‹መረጃን ለማሰባሰብ›› በሚል ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን እንዴት ያዩታል?
ኢንጅነር ይልቃል፡- በዚህ ጉዳይ ከማዘንና ከማፈር ውጭ የምለው ነገር አይኖርም፡፡ ኢህአዴግ በዴሞክራሲ እየማለ፤ ለዜጎች እኩልነት፣ ለጎሳና ሀይማኖት እኩልነት፣ ለሴቶች እኩልነት ጠብመንጃ አንስተን በመዋጋት የልጅነት እድሜያችንን በበርሃ አጥፍተናል እያሉ፤ 23 አመት ቆይተው ግን ሴቶች ለነጻነት በተሰለፉበት ቀን ስለ አገራቸው አንድነትና ስለ መሰረታዊ መብቶች የጠየቁ ሰዎችን እስር ቤት ሲያጉሩ ምን ያህል የማይማርና ወደ ኋላ እየተንደረደረ የሚገኝ፣ የራሱን ሞት እየጠበቀ ያለ መንግስት እንደሆነ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም አዲስ ነገር ባላይበትም ትግሉ ውስጥ መግባታችን ምን ያህል ትክክል እንደሆነ ግን አረጋግጦልኛል፡፡ እሱ የማይፈልገው ሀሳብ ከሆነ ለምንም ነገር የማይመለስና ሴት፣ ህጻን፣ ህጋዊም ሆነ አልሆነ ለእሱ ምኑ እንዳልሆነ፣ በስልጣኑ ላይ ለመጣ ወደኋላ የማይመለስ መንግስት መሆኑን ተረድተንበታል፡፡ ይህም ዘላለም ለመጨቆን የተዘጋጀ መንግስት በመሆኑ ወደ ትግል መግባታችን ትክክል መሆኑ እንድንረዳ አድርጎናል፡፡ ይህም ለትግሌ መሰረት ስንቅ ከመሆኑ በተጨማሪ በኢህአዴግ ላይ አዝኛለሁ፣ አፍሬያለሁ፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ባለፉት ሁለት አመታት አረቦቹ አብዮት አካሂደዋል፡፡ ዩክሬን ውስጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለውጥ ነበር፡፡ ለባለፈው አንድ አመት ተኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥም የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ በአንጻራዊነት እየተጠናከረ ነው፡፡ አመጽ እየተለመደ ከመምጣቱ፣ የኑሮ ውድነትና ጭቆናው ከመባባሱ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በቀጣይነት የሚመጣውን ለውጥ እንዴት ነው የሚያዩት?
ኢንጅነር ይልቃል፡- መቼም እኔ የምናገረው ምኞቴንና የምሰራበትን ነገርም ነው፡፡ ከዛ ውጭ ያለውን ነገር ብንወደውም ባንወደውም ራሱ መምጣቱ ስለማይቀር፣ ስለ እሱ መናገር ለእኛ አወንታዊ አስተሳሰብ ስለማይበጅም ሆነ እርግማት ተናጋሪ ስለሚያሰኝ ማድረግ የሚቻለውን በጎ ነገር እያደረግን ብንሄድ የተሻለ ነው የሚሆነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አይነት በዓለም የመጨረሻ ድሃ ለሆነ፣ ብዙ የጎሳና የእምነት መቃቃር በተፈጠረበት አገር፣ በሩቅም በቅርብም የኢትዮጵያን መረጋጋት የማይወዱ አካላት ባሉት ቀጠና ላይ ሆነን፣ እርስ በራሳችንም በተለያዩ የታሪክ ግጭቶች ውስጥ እያለን እንዲህ አይነቱ ለውጥ ባይኖር ደስ ይለናል፡ ፡ ነገር ግን አልፈለግነውም ማለት አይከሰትም ማለት አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህ አይነት ጉዳይ እንዳይከሰት የተጠና፣ አስቀድሞ በድርጅቱ የተመራ፣ ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ የሚካሄድ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ሌት ተቀን ይሰራል፡ ፡ ሆኖም ገዥው ፓርቲ በጠቅላይነትና ባታላይነት እቀጥላለሁ ካለ ህዝቡ ውስጥ መሰላቸት በግልጽ ይስተዋላል፣ ችግሮች ከዕለት ዕለት እየተደራረቡ ነው፣ ህዝብ አገሩ ውስጥም ሆነ በአካባቢው የለውጥ ምሳሌዎችን እያየ ነው፣ ችግሩ መሸከም ከሚችለው በላይ ሆኖበታል፡፡
በመሆኑም እነዚህ ለለውጥ መሰረት የሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎች እየመጡ ስለመሆኑ የፖለቲካ ተንታኝ መሆን አያስፈልግም፡፡ በዚህ ሁኔታ አገዛዙ ውስጥ ያሉት ሰዎች የሚፈተኑት ከመግዛትና ከመጨቆን አስተሳሰባቸው ወጥተው ወደ እውነታው ቀርበው ለለውጥ ይዘጋጃሉ ወይንስ በተለመደው ግትርነት ይቀጥላሉ? በሚለው ነው፡፡ በሌላ በኩል እኛም ደግሞ አማራጭ ሆነን፣ እነሱን ሳናስደነብር፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲፈጠር መቻቻልና ይቅር ባይነቱ ኖሮን አገራችንን ማዳን የምንችልበት ሆደ ሰፊነትና አስተዋይነት ፖለቲካ በሁለታችንም በኩል ይጠበቃል፡፡ ግን ይህን ታሪካዊ ጉዳይ ከሁለታችን አንዳችን ከሳትነው ሂደት በተፈጥሮ የሚያመጣው ጉዳይ አለ፡፡ ሁሌም ታሪክም፣ ስልጣኔም፣ የሰው ልጅም ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይለወጣል፡፡ ልቡን የደፈነ ሰው ካልሆነ በስተቀር ለውጥ አይቀሬ ስለመሆኑ የሚጠራጠር ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ምን ያህል ንብረት ይወድማል፣ ምን ያህል የሰው ነፍስ ይጠፋል፣ በሂደቱ ምን ያህል የተጠና እና ለአገራችን የሚጠቅም ለውጥስ ይመጣል የሚለው ነው እንጂ የሚያስጨንቀኝ ለውጡ እንደቀረበ ጥርጥር የለኝም፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ይህ ለውጥ ቢከሰት ለውጡን በሚገባው መልኩ ለማስተናገድና ለመምራት ትክሻ ያለው አካልስ አለ ብለው ያስባሉ?
ኢንጅነር ይልቃል፡- እኛ ሰማያዊ ይህን ለውጥ መሸከም የሚችል ትክሻ አለው ብለን ነው የምናምነው፡፡ በእኛ አገር ይህንን አይነት ነገር ደፍረን ስንናገር በሁሉም ወገኖች ዘንድ አይወደድልንም፡ ፡ ለምን እንደማይወደድም ይገባናል፡፡ ባይወዱትም መናገር አለብን፡፡ ከማይወደድበት ምክንያት የመጀመሪያው በጭቆና መንፈሳችን መላሸቁ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ይቻላል!›› ማለት እንደ ቅዠትና እብደት ይቆጠራል፡፡ ይህም ‹‹ይቻላል›› የሚለውን ከመጥላት፣ ከጭቆናው መብዛት፣ በተደጋጋሚ ከመክሸፍ የመጣ የአቅመ ቢስነት ችግር እንጅ የእኛ ችግር አይደለም፡፡ እነዚህ በጭቆና አስተሳሰብ ስር የወደቁት የእኛን አመለካከት እንዲይዙ ጥረት በማድረግ በተደጋጋሚ ስለ ጉዳዩ እንናገራለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅት ሆነን ስንቋቋም እኛ የተሻለ አማራጭ አለን፣ አገርና ህዝብን ወደተሻለ ደረጃ እናደርሳለን ብለን ነው፡፡ ስለሆነም ስለ ራሳችን ስለ ድርጅታችን በሙሉ ልብ ‹‹እንችላለን!›› ስንል፣ ሌሎች ድርጅቶች ቅር ይላቸዋል፡፡ ይህ ከፖለቲካ እውቀት ማነስ የመጣ ነው፡፡ እኛ እንደ ድርጅት ተቋቁመን ‹‹እንችላለን!›› ካላልንና ህዝብና አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደምናደርስ መናገር ካልቻልን ህዝቡ እንዴት ሊከተለን ይችላል? ለምንስ ጊዜያችንን እናጠፋለን?
ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው አንድ አመት ተኩል የፖለቲካ ነገር በቀላሉ የማይመዘን ሆኖ እንጅ መብት መጠየቅን፣ መነቃቃትን፣ ከአይቻልም ባይነት ይቻላል ባይነትን፣ አዲሱ ትውልድ የራሱን እጣ ፈንታ ለመወሰን በድርጅት የመታቀፍንና የመታገልን በአዲስ መልክ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ይህም ለረዥም ጊዜ በወደቀና በከሸፈ የፖለቲካ አመለካከት ውስጥ በጣም ረዥም ጊዜን የሚጠይቅ ስራ ነው፡ ፡ ይህም በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን በርካታ የሰማያዊ ወጣቶች የራሳቸውን የህይወት አማራጭ ትተው በዚህ ጉዳይ ላይ ጥርሳቸውን ነክሰው፣ በግልጽ የፖለቲካ አመለካከት ሌት ተቀን ከአገዛዙ ጋር እየተጋፈጡ፣ እየታሰሩ፣ ዋጋ እየከፈሉ የመጣ ነገር ነው፡፡ በዚህ ሂደታችን ውስጥ ወጣቶች ወደ ፖለቲካው እንዲመጡ ማነቃቃት ችለናል፡ ፡ ከትልልቅ የአደባባይ ምሁራን፣ ከዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች፣ ከውጭም ከአገር ውስጥም ክብርና ይሁንታን አግኝተናል፡፡
ከክርስትናም ሆነ እስልምና ሀይማኖት መሪዎችና አማኞች አካባቢም መከበር ችለናል፡፡ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ቢሆን እንደሚታየው ወጣትና ወደፊት አገራቸውን መምራት የሚችሉ ተብለን መወደስና መሸለም ችለናል፡፡ የዓለም አቀፉም ሆነ የአገር ውስጥ ሚዲያው እንደ አንድ የፖለቲካ ኃይል አይቶናል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለስልጣን መሰረት የሆኑት ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ወጣቶች፣ የአደባባይ ምሁራን፣ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡና ሚዲያው ሰማያዊን እንደ አንድ የፖለቲካ ኃይል ማየት ችሏል፡፡ በእነዚህ ኃይሎች ተቀባይነት ካገኘ አገሪቱን ለመምራት የሚያቅተው ምንም ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ የራሱ አላማ፣ የራሱ ፕሮግራም አለው፡፡ ይህን ለማስፈጸም የሚችል ቆራጥ አመራር አለው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ብትሆንም ሰማያዊ ለውጥን በአግባቡ ለመረከብና ለመምራት የሚያስችል አቅም እንዳለው መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ዲያስፖራው የገንዘብም፣ የመረጃና የእውቀትም አቅም እንዳለው ቢታመንም ከ1997 በኋላ ግን ለአገሪቱ ፖለቲካ አሉታዊ ጎን እንደነበረው በስፋት እየተጠቀሰ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት እናንተ ከዲያስፖራው ተቀባይነት እያገኛችሁ ነውና መልካም ጎኑንና ፖለቲካውን ላይ አለው የሚባለውን አሉታዊ ተጽዕኖ እንዴት ነው የምታስታርቁት?
ኢንጅነር ይልቃል፡- ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ አንድን አካል በቅራኔ መድቦ መታገል የተለመደ ባህል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰማያዊ ፓርቲ ወጣቱ ላይ ያተኩራል ሲባል፤ በየትኛውም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ግን የሽማግሌዎችን፣ የአደባባይ ምሁራንንና የትልልቅ ሰዎችን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የሰማያዊ አመራር አገር ውስጥ ቢሆንም የራሳቸው የፖለቲካ ፋይዳ፣ ካፒታል፣ አንጻራዊ ነጻነት ያላቸው፣ የአገራቸውን ነጻነት በቀናነት የሚመኙ፣ በመረጃው በኩል ቅርብ በመሆናቸው በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ እገዛ ከሚያደርጉት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተቀባይነት አለው፡፡ ይህን ጉዳይ ሚዛናዊ በመሆነ መልኩ የመምራት ችግር ካልሆነ በስተቀር በውጭ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን አገር ውስጥ ከሚገኙት የተለዩ አይደሉም፡፡ አገር ውስጥ እንዳለው ሁሉ ውጭ ያለውም የአገሩ ሁኔታ ያሳስበዋል፡፡ የአገር ውስጡ የራሱ ሚና ይኖረዋል፡ ፡ በውጭ የሚኖረው ደግሞ የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል፡፡
እነዚህን ሁለት ጉዳዮች አገር ውስጥ ያለው በተገቢው መንገድ ማስተባበር ይኖርበታል፡፡ አገር ውስጥም ውጭም ያለውን አጣጥሞ የማስኬድ ስራ ነው የምንሰራው፡፡ መሪነት ሲባል እኮ የሰዎችን አቅም ለግብ መጠቀም ነው፡፡ የትኛውም የማህበረሰብ ክፍል፤ አርሶ አደር፣ ነጋዴ፣ ውጭ ያለ፣ አገር ውስጥ የሚገኝ፣ የተማረም ይሁን ያልተማረ፣ ሁሉ ጥቅምና ፍላጎት አጣጥሞ ወደፊት መምራት ነው ዋናው ስራችን፡፡ ዲያስፖራውንም እንደ አፈንጋጭ፣ እንደ አጥፊና ለኢትዮጵያ ችግር ተጠያቂ አድርጎ ማየት በሰማያዊ ፓርቲ የተለመደ አይደለም፡፡
ባለፈው ጉብኝት ባደረኩበት ወቅት የዲያስፖራውን ድክመትና ስህተቶች ያልኳቸውን በአደባባይ ተናግሬያለሁ፡፡ እነሱም ከጊዜ ብዛትና ከመውደቅ መነሳት ብዙ የተማሩት ነገር አንዳለ ተረድቻለሁ፡፡ ይህን ጉዳይ አጣጥሞ የሚመራ አስተዋይ፣ ብልህና ሆደ ሰፊ መሪ ያስፈልጋል፡፡ ይህ እኛ እንደ ድርጅት አዲስ ብንሆንም በፖለቲካው መውደቅ መነሳት ከ1997 ዓ.ም ጀምረን የነበርን ሰዎች በመሆናችን የተፈጠሩትን ነገሮች በቅርበት እናውቃቸዋለን፡፡ ባገኘነው በቂ ልምድም ጉዳዩን በጥበብ መያዝ ችለናል፡፡ ወደፊትም በጥሩ ሁኔታ እንሄዳለን የሚል እምነት አለኝ፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- የዲያስፖራውን ጉዳይ ካነሳን አይቀር፤ ከ1997 በኋላ በነበረው ፖለቲካ ተስፋ ከመቁረጡም ባሻገር በቅንጅት አባል ፓርቲዎች መካከል ተከፋፍሎ እንደነበር ይነገራል፡፡ ባለፈው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ዲያስፖራውን እንዴት አገኙት? አሁንስ ምን አዲስ ነገር ይጠብቃሉ?
ኢንጅነር ይልቃል፡- እኔ ስሄድ የምጠብቀው አነስ ያለ ነገር ነው፡፡ ትግል ውስጥ ስትገባ ያለውን አስቸጋሪ ነገር ቀይሬ ከዚህኛው ወደዚህኛው አሻሽለዋለሁ ነው እንጂ፣ ይህኛው አለኝ ብለህ አትኩራራም፡፡ የዓለም የመጨረሻ ድሃ አገር ነን፡፡ የፖለቲካ ባህላችን አስቸጋሪ ነው፡፡ የእምነት አገር ነው፡፡ የ1966 አብዮት የፈጠረው ችግር አለ፣ 1997 የፈጠረው ችግር አለ፡፡ እንደ ፖለቲከኛ ይህን ችግር እለውጣለሁ የሚል እምነት ይዤ ነው የተነሳሁት፡ ፡ ከላይ የተጠቃቀሱት ችግሮች በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት መኖራቸውን ብገነዘብም አንድ መልካም ነገር መኖሩ ሌሎቹን ችግሮች ያቃልላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የኢሳት መኖር በአገሩ ጉዳይ ተስፋ ቆርጦ የነበረውን የዲያስፖራ ማህበረሰብ መረጃ እንዲኖረውና ተነቃቅቶ እንዲጠብቅ በማድረግ መልካም ስራ አከናውኗል፡፡ በተለይ የሰማያዊ ወጣቶች ‹‹አይቻልም!›› በተባለበት አገር ትንሽም ነገር ሲሰሩ ሲታይና ይህም የማህበረሰባዊ ድህረ- ገጾችን ጨምሮ ለበርካታ ሰዎች መድረሱ አድናቆት አስገኝቶልናል፡፡
እንዲያውም እኛን ከልክ በላይ የማወደስና ነጻ አውጭ አድርጎ የማየት እንጂ በእኛ ላይ ቅሬታ ያለው ሰው የለም፡፡ ለዚህም እድሜያችን እንደመልካም አጋጣሚ ሊታይ የሚችል ነው፡ ፡ እድሜያችን፣ በኢህአፓ፣ በደርግ፣ በመኢሶን የተቋሰለው ትውልድ አለመሆናችን ለፍረጃ ክፍተት አልሰጠም፣ ሰውም እንዲጠላን ምክንያት አልሆነም፡፡ ይህ በእኛ ስራ ሳይሆን በትውልድ ያገኘነው መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ እንዲያውም በሰማያዊ በኩል እንደ ችግር ይቆጠራል ከተባለ ሁሉም ኃይል የራሱ ለማድረግ ስለሚሞክር ሚዛን የማስጠበቅና ማዕከል ላይ ሆኖ የማሰባሰብን ሚና ነው እየተወጣ የሚገኘው፡፡
ከዚህ ውጭ ከርቀት ሆነው ወጣትነታችን ሲያዩ የቆዩና ትውልዱ ጫታም፣ ስደተኛና ይህ ነው የሚባል ቁም ነገር የማይሰራ የሚመስላቸው የነበሩ ሰዎች ስንቀራረብ ትልቅ አድናቆት ችረውናል፡፡ መጀመሪያ ላይ በሆይ ሆይታና በጮኸት የተሰባሰብን ቢመስላቸውም ስለ እኛ ካወቁ በኋላ ‹‹እንዲህ አይነት ወጣትም አለ?›› በሚል ተገርመውብናል፡፡ በመልካም ሁኔታም ነው የተቀበሉን፡፡ እስካሁን ያለው ተስፋ ሰጭ ቢሆንም አሁንም ትልቅ ስራ ይጠይቃል፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ያለፉት የፖለቲካ ውድቀቶች በመፍራት ወጣቱም ሆነ ዲያስፖራው ፓርቲዎችን ለመቅረብ ይፈራል፡፡ ‹‹ምንድን ነው ማረጋገጫችን?›› የሚል ጥያቄም በስፋት ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ጥያቄ እናንተስ መልሳችሁ ምንድን ነው?
ኢንጅነር ይልቃል፡- እኛ የምንሰራው ለአገራችን ብለን እንጂ ማንም እንዲያወድሰንና እንዲያምነን ብለን አይደለም፡፡ የሰራነው ነገር ሲያሳምነው ይከተለናል፤ ያምነናልም፡፡ ባለፈው 10 አመት ውስጥ ፖለቲካው ውስጥ ስለነበርን በመውደቅ በመነሳቱ ላይም አልፈናል፡፡ የራሳችንን ታሪክ ያለን እንጂ ከምንም ዱብ ያልን ፖለቲከኞች አይደለንም፡፡ የሚያከብሩን ሰዎች አሉ፣ በቅርብ የተማርንባቸው ሰዎችም አሉ፣ በተግባር ውጣ ውረድ ውስጥም አልፈናል፡፡ ይህ ለመታመን በቂ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሰማያዊን የመሰረትን ሰዎች ስብሰባ ላይ በአጋጣሚ የተገናኘን ሳይሆን ከእነ ድክመትና ጥንካሬያችን ለረዥም ጊዜ የምንተዋወቅ ሰዎች ነን፡፡ በጎሳ፣ በወንዝ ልጅነት ሳይሆን ነጻ በሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተገናኝተን በደንብ የተዋወቅን ሰዎች በመሆናችን በቀላሉ እንዳንፈርስ መልካም እድል ይሰጠናል፡፡
በተጨማሪም ይህ አስተሳሰብ ከመውደቅ የመጣ እንጂ ከእኛ ጥፋት የመጣ አይደለም፡፡ ስጋቱ ቢኖርም እኛ በመታመን እንሰራለን እንጂ አያስጨንቀንም፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ከእኔ አሊያም ከአንዱ ጓደኛዬ ድክመት የመነጨ ስላልሆነ ነው፡፡ አገራችን ውስጥ አለመተማመን በመኖሩ፣ ሰዎች ደጋግመው በመውደቃቸው፣ አጠቃላይ ክሽፈት በመብዛቱ የተፈጠረ የወል ስነ ልቦና ነው፡፡ ይህ እንደ አገር የጋራ ችግራችን በመሆኑ ይህን ባህል ለመቀየር እንሰራለን እንጂ አንድ ሰው ለምን አላመነኝም ብዬ አልጨነቅም፡፡ ይህን የወል ስነ ልቦና በድፍረት፣ ከራስ ወዳድነትና ከዝርክርክነት ወጥተን፣ አርዕያና ታማኝ በመሆን፣ የውሳኔ አሰጣጥም ሆነ የገንዘብ አወጣጥን ተጠያቂነት በተሞላበት መንገድ በመፈጸም፣ ከአባላት ጋር የቅርብ ግንኙነት በመመስረት፣ የስልጣን ልዩነትን በማጥፋት ሰው ከአሉባልታ ይልቅ በሳይንስና በምክንያታዊ ነገር እንዲመዘን ማድረግ ይቻላል፡፡
እኛ ልናደርግ የምንችለው ሰውን ተስፋ ያስቆረጡትንና ለመለያየት ምክንያት የነበሩትን ነገሮች መቀነስ ነው፡፡ አለመተማመኑ ግን ደጋግሞ የመክሸፉ ችግር እንጂ የሰማያዊ ልጆች ችግር አይደለም፡፡ የሰማያዊ ልጆች ከአሁን በኋላ ምንም ይምጣ እስካሁን ባደረጉት ነገር ብቻ ሊደነቁ ይገባቸዋል፡፡ ባለፈው አስር አመት ውስጥ የግል ህይወታቸውን መኖር እየቻሉ ለአገርና ለወገን ሲሉ ብዙ ስቃይን የሚቀበሉ ልጆችን ማፍራት ችለናል፡፡ ለነጻነታቸው የሚዘምሩ ወጣት ሴቶችን ማፍራት ችለናል፡፡ የወደቀውንና አይቻልም የሚለውን መንፈስ ማነቃቃት ተችሏል፡፡ የወደፊቱ እንዳለ ሆኖ በእስካሁንም ቢሆን ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡ ፡ አለመተማመኑ በውድቀት የመጣ እንደመሆኑ እሱን መቀየር የሚቻለው በስራ ነው፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ::
ኢንጅነር ይልቃል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment