Friday, March 21, 2014

ጥፋተኛ ጥፋቱን በይቅርታ እንጂ በዉሸትና በዕብሪት መሸፈን አይችልም


በቅርቡ አንድም የወያኔ ጌቶቹን ለማስደሰት ደግሞም ከህወሃት ካድሬዎች ስድብና ግልምጫ የማያድን ጎደሎ ስልጣን ለማግኘት ሲል ተወልዶ ያደገበትንና እመራዋለሁ የሚለዉን የአማራን ህዝብ ክብርና ታሪክ ያጎደፈዉና ያዋረደዉ የአለምነዉ መኮንን አስጸያፊ ንግግር በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያንን ያስቆጣና ያነሳሳ ጉዳይ ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል። ይህ የአማራን ህዝብ ማንነትና ይህ ጀግና ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ ያለዉን አኩሪ ቦታ ያላገናዘበና ባልተሞረደ አንደበት የተነገረ አስጸያፊ ንግግር ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተዉን የአማራን ህዝብ ብቻ ሳይሆን አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚኖሩትን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን አስቆጥቷል። አይናቸዉ ከገንዘብና ከሥልጣን ዉጭ ሌላ ምንም ነገር የማይመለከት ለሆዳቸዉ ብቻ ያደሩ ሰዎች የተከፈተ ሆዳቸዉንና ማለቂያ የሌለዉ የሥልጣን ጥማታቸዉን ለማርካት ሲሉ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ ወያኔ በሥልጣን ላይ የቆየባቸዉ ያለፉት ሃያ ሦስት አመታት በግልጽ አሳይተዉናል። ሆኖም ግን አይናቸዉ የታወረና ጭንቅላታቸዉ ባዶ የሆነ ሰዎች በነገሱበት በወያኔ ስርዐት ዉስጥም ቢሆን የሚጠሉትን፤ የሚንቁትንና የገዛ ወገኖቹን የገቡበት ቦታ ሁሉ እየተከተሉ ወደ አገራችሁ ግቡ እያሉ የሚያፈናቅሉ ዘረኞችን ለማስደስት ሲል ስቃይ የበዛበትን የራሱን ህዝብ ያዋረደ ከሀዲና ሂሊና ቢስ ሰዉ ያየነዉ አንድ አለምነዉ መኮንንን ብቻ ነዉ። አለምነዉ የተናገራቸዉን አጥንት የሚሰብሩ የንቀት ቃላት ይሀንን ከንቱ ሰዉ ባወገዝን ቁጥር እየደጋገምን ብንጠቅስ በአንድ በኩል የወያኔን ዘረኞች አላማ ያራምዳል ብለን ስለምናምን በሌላ በኩል ደግሞ እንደዚህ አይነቱን ጸያፍ ንግግር መደጋገም ሂሊናችን ስለማይፈቅድንና የጠፈፈ ቁስል መቆስቆስ ይሆናል ብለን ስለምንሰጋም ንግግሩን አንደግመዉም።
አሜሪካንን በመሳሰሉና በዕድገት ወደፊት በገፉ አገሮች ዉስጥ ዉሻ የሚታወቀዉ የሰዉ ልጅ ታማኝ ወዳጅ በመባል ነዉ። ዉሻ ባለቤቱን ለማስደስት ጭራዉን ከመቁላት ባሻገር የባለቤቱን እግር ይልሳል፤ ይንበረከካል፤ እግር ስር ይተኛል፤ ደግሞም አምጣ ብለዉ የወረወሩለትን ነገር እየሮጠ ሄዶ ያመጣል። የሚገርመዉ እንስሳዉ ዉሻ እንኳን እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሚያደርገዉ ለባለቤቱና ለለመደዉ ወዳጁ እንጂ ለሌላ ለማንም ሰዉ አያደርግም። ዉሻ ባለቤቱንና ወዳጁን በተለይ ደግሞ የሱንና የባለቤቱን ጠላቶች ለይቶ ያዉቃል፤ ስለዚህም ዉሻን ባለቤትህን ንከስ ብለን ያንን የሚወደዉን ስጋ ያሻንን ያክል ብናሸክመዉ እኛዉ ላይ መልሶ ይጮህብን እንደሆነ ነዉ እንጁ ዉሻ ባለቤቱን በፍጹም አይነክሰም።
ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ እነ አለምነዉን የመሳሰሉ ለወያኔ ያደሩ ሂሊና ቢሶች፤ ሹምባሾች፤ ምስለኔዎችና ሆዳሞች አንድ የጎደላቸዉ ትልቅ ነገር ቢኖር የዉሻን ያክል ታማኝ መሆን ነዉ። እነ አለምነዉ እናስተዳድረዋልን ለሚሉት ህዝብ ታማኝነት ቢኖራቸዉ ኖሮ ዛሬ እነሱ እራሳቸዉ፤ የሚመሩት የአማራ ህዝብም ሆነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአገሩ ተስድዶ እንደ አዙሪት በየአገሩ ከሚዞር በገዛ አገሩ ተከብሮ በወግና በማዕረግ ይኖር ነበር።ችግሩ “ባለቤቱ ያቀለለዉን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለዉም” ነዉና የኢትዮጵያ ህዝብ በእነ አለምነዉና መሰሎቹ የተነሳ ኢትዮጵያ ዉስጥም ከኢትዮጵያ ዉጭም መብቱንና ነጻነቱን ተገፍፎ የሚኖር ባተሌ ህዝብ ሆኗል። የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ነኝ ባዩ አለምነዉ መኮንን እንደማናችንም እግዚአብሄር በአምሳያዉ የፈጠረዉ ሰዉ ነዉ፤ ታድያ ለምንድነዉ ሂሊና የሌላቸዉና ነገሮችን አመዛዝነዉ የመመልከት ባህሪይ የልታደላቸዉ እንስሳት እንኳን የማያደርጉትን አስጸያፊ ነገር እሱ በገዘ ወገኖቹ ላይ ያደረገዉ? በእርግጥ ይህንን ጥያቄ አለምነዉ በጥቅም የተገዛ ወይም ለሆዱ ያደረ ሰዉ ነዉ ብለን በቀላሉ መልሰን ማለፍ እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ከብዙ አፍሪካዉያን በተለየ መልኩ ነጻነቱንና አንድነቱን ጠብቆ መኖር የቻለበትን ምክንያት ለምንረዳ ሰዎች ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠዉ መልስ የችግሩን ያክል የተወሳሰበ መሆኑን እንረዳለን። ይህንን ስለምንረዳም ነዉ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከወያኔ መዳፍ ዉስጥ ፈልቅቆ ለማዉጣት መከፈል ያለበት መስዋዕትነት የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ቤት ያንኳኳል የምንለዉ።
ወያኔ ወይም ህወሀት በሚባለዉ የዘረኞች ድርጅት ዉስጥ የታቀፉ ሰዎች ስልታዊ አላማ አንድና አንድ ብቻ ነዉ- እሱም ኢትዮጵያ የምትባል ገንዘብና ንብረት የምትታለብ ላም ወተቷ እስኪነጥፍ ድረስ ብቻችንን እንለባት የሚል የስስት አላማ ነዉ። ይህንን የስስት አላማ ተግባራዊ ለማድረግ የነደፉት እስትራቴጂ ደግሞ የአላማችን ዋነኛ ጠላት ነዉ ብለዉ የሚያምኑትን የአማራዉን ህዝብ መግደል፤ ማሰር፤ ማሳደድ፤ ማፋናቀል፤ መደብደብና ማዋረድ ነዉ። ይህንን ከጠላቶቻችን ከነሙሶሊኒና ግራዚያኒ የተማሩትን አማራዉን የማሳነስና የማጥፋት ስልት ደግሞ እግራቸዉ አዲስ አበባን ከረገጠበት ቀን ጀምሮ የአማራዉን ግዛት ቆርሰዉ የራሳቸዉ በማድረግና አማራዉን በመግደል፤ በማሳደድና በማሰር በተግበር አሳይተዉናል ዛሬም እያሳዩን ነዉ።
የወያኔ ዘረኞች የቂም በቀል እርምጃዎች ሁሉ ያነጣጠሩት በአለምነዉ መኮንንና በወገኑ የአማራ ህዝብ ላይ ነዉ፤ ወያኔ ወልቃይት ጠገዴን ቆርሶ የወሰደዉ ከአለምነዉ መኮንንና ከወገኑ ከአማራ ህዝብ ላይ ነዉ፤ ከጉራ ፈርዳና ከቤንሻንጉል አካባቢዎች ሂድ ከዚህ ተብሎ የተፈናቀለዉ ህዝብ አለምነዉ መኮንን እመራዋለሁ የሚለዉ የአማራዉ ህዝብ ነዉ። ታድያ አለምነዉ መኮንን እሱንና የገዛ ወገኖቹን ለዘህ ሁሉ ዉርደትና መከራ የዳረጉትን የወያኔ ዘረኞች ለማስደስት ሲል የተወለደበትን ማህበረሰብ መሳደቡ ምን ይባላል? ወያኔ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተማረዉ መጥፎ ነገር ቢኖር ዘረኝነት ነዉ፤ አለምነዉ መኮንን በዚህ መጥፎ የወያኔ ትምህርት ተለከፈ ብለን ብናምን እንኳን ዘረኝነት የራስን ዘር ከሁሉም በላይ እንድናይና ሌሎችን እንድንጠላና እንድንንቅ ያደርገናል እንጂ የራሳችንን ዘር እንድንሰድብና እንድናዋርድ አያደርገንም። ታድያ አለምነዉ መኮንንን የተጠናወተዉ የወያኔ ዘረኝነት ነዉ ወይስ የሚያድኑትን እያስጠላ የሚገድሉትን የሚያስወደድ የታምራት ላይኔ በሽታ ነዉ?
ሌላዉ የአለምነዉ መኮንንና የብአዴን ችግር አለምነዉ ያንን አሳፋሪ ንግግር ካደረገና ንግግሩ የህዝብ ጆሮ ዉስጥ ገብቶ አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ብዙ ሰዎችን ካስቆጣ በኋላ ጥፋታቸዉን ተረድተዉ ህዝብን ይቅርታ አለመጠያቃቸዉና ሌላ ቢቀር አስተዳድረዋለሁ የሚለዉን ህዝብ ሙልጭ አድርጎ የሰደበዉን ሰዉ ህዝብን ከመምራት ሀላፊነት ቦታ ላይ እንዲነሳ አለማድረጋቸዉ ነዉ። አለምነዉ መኮንን የአማራን ህዝብ ከተሳደበ በኋላ ወያኔም ሆነ ብአዴን ከመጋረጃ ጀርባ የተባባሉትን ነገር ባናዉቅም ስድቡን አስመልክቶ በግልጽ ህዝብ እንዲያዉቀዉ የወሰዱት ምንም እርምጃ እንደሌለ ግን በሚገባ እናዉቃለን። ይህ የሚያሳየን ወያኔና ብአዴን ለህዝብና ለአገር ምንም ደንታ እንደሌላቸዉ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሁለት ጸረ ህዝብ ድርጅቶች ህዝብን እንዳሻን ረግጥን መግዛት እንችላለን የሚሉ ዕብሪተኞች እንደሆኑ ነዉ። የወያኔ ሹሞችና በየቦታዉ የበተኗቸዉ ሆዳም አፈቀላጤዎቻቸዉ የአለምነዉ መኮንንን መረን የለቀቀ ንግግር ለማስተባበልና እንዲያዉም ተባለ የተባለዉ ንግግር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሆን ብለዉ ያቀነባበሩት የፈጠራ ስራ ነዉ እያሉ ህዝብን ለማሳመን ብዙ ደክመዉ ነበር፤ ነገርግን ብዙም ሳይቆይ ግለሰቡ በባዕዴን ስብሰባ ላይ የደረገዉ ንግግር በመጀመሪያ በኢሳት ሬድዮና ቴሌቪዥን ከዚያም በማህበራዊ ሜድያዎችና በተለያዩ ድረገጾች ላይ በብዛት መሰራጨት ሲጀምር ወያኔና ቡችሎቹ ማስተባበሉን ትተዉ ሳይወዱ በግድ ዝምታን መርጠዋል።
ወያኔና ብአዴን ህዝብን ሰድበዉና አዋርደዉ ዝምታን ቢመርጡም የተሰደበዉ የኢትዮጵያ ህዝብና መሪ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ግን የአማራን ህዝብ አስጸያፊ ስድብ የሰደበዉ አለምነዉ መኮንን ከጥፋቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ እስካልተወሰደበት ድረስ ዝም እንደማይሉ ለሚመሩት ህዝብም ለወያኔም ይፋ አደረጉ። በተለይ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲና መላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ አለምነዉ መኮንን የሰደበዉ የአማራ ህዝብ በክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ዉስጥ በነቂስ ወጥቶ ተቃዉሞዉን እንዲያሰማ የሰላማዊ ሠልፍ ጥሪ አደረጉ። ይህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሠላማዊ ሠልፍ ጥሪ ለህዝብ ከተላለፈና ህዝቡ ቁጣዉን ከመግለጽ ወደኋላ እንደማይል ከተረዱ በኋላ ነበር እነ አለምነዉ መኮንን ሰድብዉት እንዳሻህ ብለዉ የዘጉትን ህዘብ በፕሬስ መግለጫ ስም እንደገና ማደናገር የጀመሩት። እዚህ ላይ አንድ እጅግ በጣም የሚያናድድና አንጀት የሚያሳርር ነገር ቢኖር ባለፈዉ ሐሙስ አለምነዉ መኮንን በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በጉጉት ይጠበቅ የነበረዉ ይህ ግለሰብ የሰደበዉን ህዝብ ይቅርታ ይጠይቃል ተብሎ ነበር። ሆኖም አለምነዉ መኮንን፤ብአዴንና ህወሀት ከዕባብ እንቁላል አርግብ እንደማይጠበቅ በግልጽ አሳይተዉናል።
ባለፈዉ ኃሙስ ዬካቲት 13 ቀን 2006 ዓም አለምነዉ መኮንን የአገር ዉስጥ ጋዜጠኞች ያንን መረን የለቀቀ ስድቡን አስመልክተዉ የጠየቁትን ጥያቄ ሲመልስ እዉነትም “ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል” የሚያሰኝ የቂል መልስ ስጥቷል። ነፃ ሜድያ በሌለባት ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዳሰኘዉ መለፍለፍ የለመደዉ አለምነዉ መኮንን “ተቃዋሚዎች አለ ያሉትን ነገር እኔ በፍጹም አላልኩም . . . እኔ ለህዝብ ክብር ያለኝ ሰዉ ነኝ በማለት ነገሩ እየቆየ ሲሄድ እሱ እራሱ የተናገረዉ ንግግር ገርሞት “እኔ እንዴት እንደዚህ ልል እችላለሁ”ሲል ጋዜጠኞች የጠየቁትን ጥያቄ መልሶ እራሱን ጠይቋል። ይህ እፍረተ ቢስ ሰዉ ህዝብን የተሳደበዉ አልበቃ ብሎት ጭራሽ ጥፋቱን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ለማላከክ ሲሞክር ተድምጧል። ማንም ሰዉ ተናገር ብሎ ሳያስገድደዉና ቁጭ ብለዉ የሚያዳምጡት ሰዎች እየሳቁ በራሱ አንደበት የተናገረዉን ፀያፍ ንግግር ተቃዋሚዎች መሪዎችን ከህዝብ ለመነጠል ሆን ብለዉ የሰሩትና በቆርጦ ቀጥል የኮምፒተር ዘዴ ያቀነባበሩት ነገር ነዉ እንጂ ዬኔ ንግግር አይደለም ሲል የራሱን ድምፅ ዬኔ አይደለም ሲል ሽምጥጥ አድርጎ ክዷል።
ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር ተምራ የምትመጣዉን ነገር እናዉቃለንና ከወያኔ ዘረኞች ጋር ለአመታት የከረመዉ አለምነዉ መኮንን በመዋሸቱ ብዙም ላንፈርድበት እንችላለን፤ ደግሞም ወያኔና ዉሸት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸዉና ወያኔን ባየን ቁጥር ትዝ የሚለን እንደ ሰዉ ቆሞ የሚሄደዉ ዉሸቱ ነዉና የአለምነዉ ዉሸት በፍጹም አይገርመንም። ይልቅ እኛን የገረመን አለምነዉ መኮንን የራሱን ድምጽ ዬኔ አይደለም ማለቱ ነዉ። መቼም አንድ ሰዉ ለይቶለት አማኑኤል ካልገባ በቀር እኔ “እኔ” አይደለሁም ብሎ የመናገር ደረጃ ላይ የሚደርስ አይመስለንም። ደግሞስ አለምነዉ መኮንን የማንሰማዉ መስሎት ባልተገራ አንደበቱ ህዝብን ሲሳደብ በድንገት ሰምተነዉ ነዉ እንጂ እስኪ እግዚአብሄር ያሳያችሁ አለምነዉ መኮንንን ማን ከቁም ነገር ቆጥሮት ነዉ የሱን ተራ ንግግር አየቆረጠ የሚቀጥለዉ? ማንስ ስራ የፈታ ሰዉ ነዉ የራሱንና የኮምፒተሩን ግዜ የአለምነዉ መኮንንን ቆሻሻ ንግግር ቆርጦ በመቀጠል የሚያጠፋ?
ሌላዉ የአለምነዉ መኮንን ጉድ ይህ ሴራ ተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችን ከህዝብ ለመነጠል የሚያደርጉት ሴራ ነዉ ብሎ መናገሩ ነዉ። ወይ ጉድ . . . “ ወግ ነዉ ሲዳሩ ማልቀስ” ይላል የአገራችን ሰዉ። ለመሆኑ ጭንቅላተ ባዶዎቹ የወያኔና የብአዴን መሪዎች ቀድሞዉኑ ከህዝብ ጋር መች ገጥመዉ ያዉቃሉና ነዉ ተቃዋሚ ድርጅቶች እነሱንና ህዝብን ለመነጣጠል እያሴሩ ነዉ ተብሎ የሚነገረዉ? ወንድምዬ የምትሰማኝ ከሆነ እናንተና ህዝብ ዉኃና ዘይት ናችሁ፤ ተገናኝታችሁም አንድ ላይ ሆናችሁም አታዉቁም። በዚህ ስድባችሁ፤ ክህደታችሁና ዕብሪታችሁ ደግሞ ለወደፊትም ቢሆን ከህዝብ ጋር አትገጥሙም። ከህዝብ የነጠላችሁ ክፉ ስራችሁና መጥፎ ጠባያችሁ ነዉ እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም።
አለምነዉ መኮንን እሱ እራሱ የአማራ ተወላጅ ነዉ፤ ያንን የመሰለ አስጸያፊ ንግግር የተናገረዉም በአማራ ህዝብ ላይ ነዉ፤ሆኖም በዘለፋዉና በዉርደቱ አንጀቱ ያረረዉ ወይም ዘለፋዉ ያነጣጠረዉ በአማራ ህዝብ ላይ ብቻ ነዉ ብለን የምናስብ ሰዎች ካለን እኛም ዘለፋዉን እንደሰነዘረዉ ሰዉ እራሳችንን ስተናል፤ ወይም ዋነኛዉ የወያኔ ወጥመድ ዉስጥ ገብተናል አለዚያም አርቆ የመመልከት ችሎታችን ከከዳን ቆይቷል ማለት ነዉ። ዘለፋዉና ንቀቱ የተሰነዘረዉ በሁላችን ላይ፤ ነዉ፤ የተዋረድነዉም ሁላችንም ነን፤ ስለሆነም አለምነዉንና አቅፈዉት ከለላ የሰጡትን ሁሉ ለፍርድ ለማቅረብ የሚደረገዉ ትግል የሁላችንም ትግል መሆን አለበት። ባህር ዳር ዉስጥ የታየዉ ህዝባዊ ቁጣ በመላዉ ኢትዮጵያ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሎ ወያኔ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐት ለብልቦ ከምድረ ኢትዮጵያ እስኪያጠፋ ድረስ ትግላችን መቀጠል አለበት። በዚህ ትግል ዉስጥ “እኔ” ወይም “አንተ” የሚባል ቃል በፍጹም ሊኖር አይገባም። የትግላችን ብቸኛ መነሻና መድረሻ “እኛ “ ብቻ መሆን አለበት። ወያኔን አጥፍተን እንደ ህዝብና እንደ አገር በሠላም፤ በነፃነትና በብልጽግና መኖር የምንችለዉ ኢትዮጵያዊነታችን “እኛ” በሚለዉ አስተሳሰብ ላይ ሲገነባ ብቻ ነዉ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment