Friday, March 21, 2014

ለአልሙዲ “ማፅናኛ”(ከጋዜጠኛ ተስፋዬ ተሰማ)



በቅርቡ ባህርዳር ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያ ስፖርት በአል ሼኽ አልሙዲ በክብር እንግድነት ተጋብዘው ነበር። የበአሉን መክፈቻ በቲቪ ስከታተል አንድ ጥያቄ ወደ በአእምሮዬ መጣ። አልሙዲንን የክብር እንግዳ አድርጐ መጋበዙ ለምን አስፈለገ?..ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። “የገዢው ፓርቲና የባለስልጣናቱ ታማኝ ወዳጅ ስለሆኑ፣ በባህርዳሩ ስታዲየም ግንባታ ድርጅታቸው ስለተሳተፈ ወይም ሼኹ ለስፖርት ያላቸውን ፍቅር በማየት..” የሚሉ ነገሮችን መደርደር ይቻላል።

በእኔ ግምት አልሙዲ በባህርዳሩ በአል በእንግድነት የተጋበዙት በሰሜን አሜሪካ ስፖርት በአል ላይ ስለተዋረዱ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት የፈጠርዋት ማፅናኛ ትመስለኛለች። ባለፈው አመት እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በአንድ ሳምንት ሁለት የኢትዮጵያ ስፖርት በአል ተከበሮዋል። አንድኛው በሼኽ አልሙዲና የዳይስፖራውን ማንነትና ፍላጐት ባልተገነዘቡ ወዳጆቻቸው የተዘጋጀ ነበር። በነዚህ ወገኖች ግምት “ዳያስፖራው በተወሰኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ካድሬዎች የሚሽከረከር የዋህ ህዝብ” አድርገው ይወስዱታል።

 አሜሪካ ሀገር ከኅይለስላሴ ጀምሮ በደርግ ጊዜ ከዛም በኋላ የመጣው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ (በምንም መንገድ አሜሪካ ይምጣ) ለዘሩ፣ ለጐሳው ሳይሆን ለኢትዮጵያዊነቱ ጥልቅ የሆነ ፍቅርና ክብር አለው። በዚህ ምክንያት የኢህአዴግን የዘር ፖለቲካ አይደግፍም። ከደጋፊዎቹም ጋር የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ የገባው በዚህ አገር ወዳድ አቋሙ ነው። ይህ እውነት ያለገባቸው አልሙዲና ተከታዮቻቸው በስፖርቱ አስታከው ዳያስፖራውን እንቆጣጠራለን በማለት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ቢከሰክሱም አልተሳካላቸውም። ባዶ ስታዲየም ታቅፈው ነው የቀሩት። ሁለተኛው ኢ.ኤስ.ኤፍ.ኤን የሚባለው ኢትዮጵያዊ ፌዴሬሽን የነሱን ያክል ገንዘብ ሳይኖረው በርካታ ህዝብ ከጎኖ ማሰለፍ ችሎዋል። እንዲያውም ስታዲየሙ ሞልቶ ሰው እስኪመለስ ድረስ። በዚህ በአል ከፍተኛ የሆነ የአንድነትና የአገር ፍቅር ስሜት የታየበት፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ በብዛት የተውለበለበበትና ያሸበረቀበት፣ ሰዎች ከብሄራቸው ይልቅ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያገነኑበት ትልቅ በአል ነበር።

ባዶ ስታድየም የታቀፉትና አፍረው በውርደት ለተመለሱት አልሙዲ የባህርዳሩ እድል በማፅናኛነት ተሰጣቸው። ኢትዮጵያዊያን በነፃነት በሚኖሩበት አሜሪካ ግን አልሙዲ በገንዘባቸው የህዝብን ድጋፍ መግዛት አይችሉም። በገንዘብ ምንም ማድረግ እንደማይችሉም ሊያውቁት ይገባል።

No comments:

Post a Comment