Sunday, March 16, 2014

“እኛና አብዮቱ” የሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግ ደረስ ጸጸት አልባ ትዝታዎች


ከኤፍሬም የማነብርሐን
ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግ ደረስ በጣም አስደናቂም አስገራሚም የሆነ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። የደርግ አባልና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለአምባ ገነኑ ኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እንደቀኝ እጅ ባገለገሉበት ዘመን የሆነውን ሁሉ እሳችው ካመኑበት አቋም በመንደርደር ተርከውታል።  በጣም ብዛት ያላቸው የውስጥ ሰው ብቻ ሊያውቃቸው የሚችላቸው መረጃዎችን (ፋክትስ) መጽሐፉ አካቷል።  ብዙ ሰው ወደ ጀርባ ገፍቶት የነበረውን የዚያን የደም ዘመን ትዝታዎች እንደ አዲስ ይቀሰቅሳል።  ደራሲው መረጃዎችን በመሰብሰብና በተቀናጀ መልክ ታሪኩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማቅረባቸው ሊደነቁ ይገባል። ታሪክም ላቀረቡት ጽሑፍ እንደባለውለታ ያያቸዋል የሚል ግምት አለኝ።  የዚያ አስከፊና በኢትዮጵያ ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ያለፈው የደርግ ቡድን አባል በመሆን ከድርጅቱ የተቆራኙ ቢሆኑም፣ ጽሑፉን በማዘጋጀታቸው ለአገር፣ ለወገን በአመዛኙ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ለማቅረባቸው መጽሐፉ ቋሚ ምስክራቸው ይሆናል።Former Ethiopian official Fikreselasie Wegderes new book
መጽሐፉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግስትና የገዢውን የፊውዳል ሥርዓት ለማንበርከክና ደርግ በሥልጣን ተፈናጦ ለመቀመጥ እንዲያስችለው እርምጃዎች በወሰደ ቁጥር ያጋጠሙትን ተቃውሞዎች፣ የብሔራዊ ዘመቻንና የሶማሌን ወራሪ ጦር ለመመከትና ወደመጣበት ለመመለስ የተደረገውን ርብርቦሽና በተለይ አኩሪ የሆነውን የታጠቅ ጦር ሠፈር ግንባታና አስተዋጽኦ፣ የገጠርና የከተማ ቤት አዋጆችን ለማውጣትና ለማሰፈጸም የተደረጉ ጥረቶችንና ቅዋሜዎችን፤ የፖለቲካ ቅራኔዎችን ለመግታት፣ ለመገደብ፣ ለማምከንና ብሎም የኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን አምባ ገነንነት ለማረጋገጥ የተደረጉ ፍልሚያዎችን በሰፊው ተንትኗል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከተፈጸሙት ብዙ ግዙፍ ስሕተቶች አንጻር ሲታይ የደራሲውን ጸጸት አልባነት፣ ይባስም ብሎ ለነዚህ ስሕተቶች መከላከያ ለማቅረብና ኃላፊነትን ለሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ለማስተላለፍ መሞከሩ የመጽሐፉ ጉልህ ደካማ ጎን ነው። መጽሐፉን ካነበብኩ በኋላ “ደርግ ሰው ገደለ እንጂ፣ ኢትዮጵያዊነትን ግን አልገደለም” እየተባለ እንደ ቀላል ወርወር የሚደረገውን አባባል ወደ ትልቅ ሥሕተት እንደሚወስድ ድምዳሜ ላይ አድርሶኛል።  ኢትዮጵያዊነት አሁን ለደረሰበት አስጊ ደረጃና አገሪቱ ያለዲሞክራሲ የጉልበተኞችና የዘረኞች መፈንጫና የአንድነት ኃይሎች መደበቂያና ማፈሪያ እንድትሆን ምክንያቱ ወያኔ ብቻ እንዳልሆነና፣ ደርግም ግዙፍ ሚና በእጅ አዙር እንደተጫወተ መጽሐፉ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።  በርግጥም ኢትዮጵያን በቀጥታ ፈቃደኝነትም ባይሆን፣ በእጅ አዙር ለወያኔ ገጸ በረከት ያቀረቡትና ፣ ለኢትዮጵያዊነት ስሜት የዝግታ የመጥፋት ጉዞ መነሻውና፣ ምናልባትም በእኩይ ወሳኙን ሥራ የሰሩት አሰከፊው የደርግ መንግስትና፤ በተለይም የግል ሥልጣንን ለማካበት ቆርጠው ማንኛውንም ጥፋት ከማድረስ ወደኋላ ያልተመለሱት ኮለኔል መንግስቱ ለመሆናቸው መጽሐፉ ደራሲው ባላሰቡት መንገድ በቂ ግንዛቤ ይሰጣል።
መጽሐፉ በአገሪቱ ላይ በቅርብ ዘመን በማይታወስ መጠንና ስፋት የጭካኔ መረቡን ዘርግቶ በሺዎች ለሚቆጠሩ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ጥፋት ዋና ምክንያት የሆነው ደርግን የውስጥ አሰራር አቅርቦልናል።  ምንም እንኳን ደራሲው መንግስቱን “ቆራጥና “ከፍተኛ “የሃገር ፍቅር” እንደነበራቸውና፣ ይወስዷቸውም የነበሩት ጨካኝ ድርጊቶች አገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሳ ለማየት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ እንደሆነ ለማሳየት ቢሞክሩም፣ በኮለኔሉ ቀጥታ ትእዛዝና አመራር ሰጭነት አብዛኛዎች ኢትዮጵያውያን የተጨፈጨፉት በእጅ ወድቀው እስር ቤት ከተወረወሩ በኋላና ምንም አደጋ በደርግ መንግስት ላይ ሊያደርሱ በማይችሉበት ሁኔታ ስለነበረ፤ የሻምበሉ የኮለኔሉን በከፊልም ቢሆን መልካም ገጽታ ለማቅረብ ያደረጉት ሙከራ ብዙም አልተሳካላቸውም።
ሊቀ መንበሩ ለምን ይሆን እንዲህ ቃታን በቶሎ የመሳብ ፈንጭ (ትሪገር ሃፒ) የሆኑት? ከድንቁርናና ጅልነት ይሁን? ምናልባት ከመናቅ ሳቢያ በተፈጠረባቸው ድብቅ የበታችነት ስሜትና የበቀል ጥማት ይሆን? ለምን ይሆን እንዲህ ለፍትሕና ለርሕራሔ ዕውር ያደረጋቸው? መጽሐፉን ማንበብ ስጀምር ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ በትንሹም ቢሆን አገኛለሁ የሚል ግምት ነበረኝ። ከመጽሐፉ ያገኘሁት ግን አምባ ገነኑን መንግስቱን ማድነቅን፣ ታላላቅ ወንጀሎችን አድበስብሶ ማለፍን፣ የፈረደበትን “የፊውዳል” ሥርዓትን ማውገዝን፤ ላስከፊ ግድያዎች ራሳቸው የሾሟቸውን ዕድለ ቢስ ጄነራሎችን፣ ከመንግስቱ ለየት ያለ አቋም የወሰዱትን የደርግ አባላትን፣ የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የወዝ ሊግ፣ ወዘተ መሪዎችንና ጀሌዎችን ተጠያቂ ማድረግን፤ መንግስት እንደአባት ዜጎችን በርሕራሔና በፍትሕ መዳኘት ይገባው የነበረ መሆኑን ተዘናግተው ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ሟቾችንና ተበዳዮችን ተጠያቂ አድርጎ ማቅረብን፤ ወዘተ ብቻ ነው።  ቢያንስ ጸጸት አልፎም ይቅርታ መጠየቅን አላየሁበትም።  በመሆኑም መጽሐፉ በጣም ረብሾኛል። ጸሐፊውም እኔን በበኩሌ ቅር አሰኝተውኛል።
መኖር ደጉ ደራሲው እንኳን ይህንን ለመጻፍ በቁ
ሌላው በጣም አስገራሚው የመጽሐፉ ይዘት ደራሲው እርሳቸው ከሞት ተርፈው ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ ቢበቁም፣ ይህንን ዕድል በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ያላገኙት ባብዛኛው በሳቸውና በግብረ አበሮቻቸው የጭካኔ ሥራና ውጤት መሆኑን ለጥቂት እንኳን ቆም ብለው ያላሰቡ መሆኑ ነው። እሺ ኢሕአፓና ሌሎችም ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩት የደርግ ተለጣፊዎች ደርግ ባደረሰው ደረጃም ባይገመት፣ በወሰዷቸው የተሳሳቱ የፖሊሲ አቋሞች ሳቢያ ለብዙ ንጹኃን ኢትዮጽያውያን መጥፋት ምክንያት ሆነዋል። ይህ ማናችንም ልንክደው የማንችለው ሀቅ ነው። ወንጀለኛን በፍርድ ቤት የማቅረብ ሥራ በኢትዮጵያ ባሕልና ወግ አንዲሁም በፍትሐ ነገስትም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ለረጅም ሲሰራበት የነበረ መሆኑን ደራሲው የተገነዘቡ አይመስለም። ለእስር የተዳረጉት ሁሉ ለምሳሌ እንደ ልጅ ካሳ ወልደማርያም፣ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ብርሐነ መስቀል ረዳ፣ ኃይሌ ፊዳ፣ ኅልቆ መሳፍርት የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የወዝ ሊግ ወዘተ አባላት ያለ ፍርድ እየተወሰዱ መረሸንን በሚመለከት ስለተደረጉ ሥሕተቶች ደራሲው ትንፍሽ እንኳን እንዴት አይሉም? የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ በባሕሉ ከፍ ያለ የፍትሕ መለኪያ ያለው ነው።
እንዲህ እንደወንጀለኛ ደርግ የሚኮንናቸው ንጉሥ ኃይለሥላሴ እንኳን በትረ መንግሥታቸውን ከጅለው ለነበሩትና ብዙ ባለሥልጣናትን ያለፍርድ ወዲያው ለረሸኑት ለጄነራል መንግስቱ ንዋይ እኮ ትልቅ ችሎታ ያላቸውን ተከላካይ ጠበቆች እንዲቆሙላቸው የፈቀዱ ሰው ነበሩ። እንዴት ደርግ ወደተራ ሽፍትነት ወርዶ ያለሕግ አፋጣኝ የግድያ ውሳኔዎችን (ሰመሪ ኤክሴኪውሽን) ማስተላለፉንና በመሆኑም የብዙ ሺሕ ንጹኃን ዜጎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ሃያ ዓመታት እስር ቤት ከርሞ መልካሙን ከመጥፎ ለመለየት ጊዜና ቦታ ያጋጠመው ሰው የፍትሕን መስፈርት አለመሟላት መመልከት ያዳግተዋል?  የሳቸውስ መንግስት በያዘው የሥልጣን መጠንና ስፋት ሳቢያ የኃይል እርምጃ አወሳሰድን ተመጣጣኝነት መንገዘብ ይገባው እንደነበርና፣ ያንንም አለማድረጉ ከመንግስትነት ይልቅ ወደተራ ወንበዴነት እንዳወረደው የጊዜና ቦታ እድል ያገኙት ደራሲ እንዴት መመልከት ተሳናቸው? ታንክና መትረየስ፣ ተዋጊ አይሮፕላንና፣ በመቶ ሺ የሚቆጠር ወታደራዊ የሰው ኃይል የነበረው የደርግ መንግስት የሚያስተዳድረውን ሕዝብ መጨፍጨፍ እንደማይገባው እንዴት ሊረዱ አልቻሉም? ምርኮኛ የውጭ ጠላት እንኳን ተገቢ እንክብካቤና ፍትሕ ሊደረግለት ይገባዋል እንኳን የራስ ወገን። ደራሲው ግን “በወቅቱ ለተሰዘረብን የጸረ አብዮተኞች እርምጃ ተገቢውን አጸፋ ነው የወሰድነው” ብለው ሊያስረዱ ይሞክራሉ።
በርግጥ ደርግን ተከትሎ የመጣው የወያኔ መንግስት በአገሪቱ ላይ ቀላል የማይባል የታሪክ ጥፋት አድርሷል፤ በማድረስም ላይ ይገኛል።  በዚህ እውነታ ሳቢያ ግን ደርግ ያደረሰውን ጥፋት ወደጎን አድርገን መተው የለብንም። ደራሲውም ከዚያ ጥፋት የተማርኩት ይህንን ነው፤ መጪው ትውልድ ይህንን ስሕተት መድገም የለበትም፤ ብለው መምከር ይገባቸው ነበር። ነገር ግን እኝህ ሰው በሕይወት የመኖር እድለኛ ሆነው በተለይ ደግሞ በእስር ቤት ውስጥ ብዙ ነገር ከዕለታዊ ግርግር ወጣ ባለ ሁኔታ የቀድሞ ሥራዎቻቸውን፣ አቋማቸውንና፣ ስሕተቶቻቸውን ለመመርመርና ለማውጣት ለማውረድ ዕድል ያገኙ ቢሆንም፤ ከጸጸት አይደለም መጽሐፉን የጻፉት። ያውም እንዲህ ግልጽ ለሆነ የደርግ ጥፋት። አገሪቱን ከፍተኛ ውድቀት ላይ ጥለዋትና ለዘረኞች አጋልጠዋት ያልሄዱ ይመስል መልካም ተሰርቶ እንደነበር በጽሑፋቸው ለማቅረብ መሞከራቸው የመጽሐፉ ታላቅ ድክመት ነው። እሺ በወቅቱ የዕውቀትና የልምድ ማነስና ውዝንብር የተጠናወታቸው እነርሱ ብቻ አልነበሩም። ስንቱ የተማረውም የሃገሪቱን ሥልጣኔ፣ ባሕል፤ ታሪክ ያላገናዘቡ፣ ለአገሪቱ የማይስማሙ መጤ ርዕዮተ ዓለሞችን ለኢትዮጵያ ይስማማሉ ብሎ አንዲያውም ደርግን በሚያስንቅ አኳኃን የሚያስተምርበት ጊዜ ስለነበረ፣ አገር የዕብደት ፈረስ ጭኖ በሚጋልብበት ዘመን ከደርግ አባላት የተለየ መጠበቅ ተገቢ አይሆንም።  ከሃያ ዓመታት በኋላ ግን ይህን ላልተገነዘቡ ተመሳሳይ ይቅርታ ለማድረግ ያስቸግራል።
Next Pages: 1 2 3

No comments:

Post a Comment