Wednesday, March 19, 2014

11% እድገታችን’ ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር:-


Sebhat Amare( Norway)
Imageእንደሚታወቀው በአንድ ሃገር የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ክንውኖች የቀን ተቀን ለውጥ ውስጥ የህብረተሰብ ተሳትፎ(አስተዋጽኦ) ጉልህ ሚና አለው፡፡ እንዲሁም በሂደቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ጉዳዮችም ይሁኑ ወይም በተቃራኒው የሚከሰት ተፈጥሯዊም ሆነ በመልካም አስተዳድር ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች ዞሮ ዞሮ ከህብረተሰብ ጫንቃ ላይ አይወርድም፡፡ ይህ ስለሚታወቅ ሃላፊነት የሚሰማቸው፣ ለሃገርና ለሕዝብ ታማኝ የሆኑ፣ በሕዝብ ይሁንታ ስልጣን የያዙ መንግስታት ያላቸው ሃገሮች በየትኛውም ሃገራዊ እንቅስቃሴ ላይ ሕዝባቸውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በማድረግ በብሔራዊ ስሜት የታነፀና በሃገሩ ጉዳይ ላይ ቅንጣት ታህል የማያመነታ ብርቱ ህብረተሰብን ይገነባሉ፡፡ የእንደኛ አይነቶቹ የሃገርና የሕዝብ ፍቅር የሌላቸው አምባገነን የወያኔ መሪዎች ግን እንኳን ‘የሃገርህ ጉዳይ ያገባሀል’ ብለው ሊያሳትፉት ቀርቶ የአንድን ሕዝብ የዴሞክራሲ መሰረት የሆነውን የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ተፈጥሮዊ የሆነውን መብቱን እንኳ ገፍፈው ሃገሪቱን የቁም እስር ቤት አድርገዋታል፡፡
የወያኔ ጁንታ ’11% እድገት አሳይተናል’ እያለ በሌለ ተስፋ ላይ ተቀምጦ በሚኮፈስበት እና ሳተላይት ልናመጥቅ ነው፤ አውሮፕላን ፈበረክን፤ ልማታዊ መንግስት ……. እያለ ትምክህቱን በሚያሳይበት በአሁን ወቅን በሃገራችን መኖር ያልቻልን ኢትዮጵያውያን ድንበር አቋርጠን በተፈጥሮ የበለጸገች ሀገራችንን ጥለን ወደ ተለያዩ ሀገራት በስደት ተበትነን እንገኛለን፡፡ በአንጻራዊ የተሻለ የመኖርያ ቦታ ፍለጋ ለስደት የወጣው ወገናችን ያሰበበት ቦታ ሳይደርስ በበረሃ አሸዋ የተበላውና በባህር ሰጥሞ የቀረውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እንደ ሰው አንድ የያደርገን ባሕርይ፤ እንደ ኢትዮጵያዊነትም ሁላችንንም የሚመለከተንና የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት ያልታየበት በደል ባለፈው ሰሞን በሳዑዲ ዐረብያ ግዛት እንደተፈጸመን መጥቀስ በቂ ነው። የጥቃት ዒላማዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የጥቃቱ ልክ የለሽነትና አሰቃቂነት ደግሞ ይበልጥ የጎላው በሴት እህቶቻችን ላይ ነው። የዱር አውሬ እንኳን ከዚህ የተሻለ ክብር አለው። እነዚህ እጅግ ኋላ ቀር የሆኑ አረመኔዎች ከእንስሳ እንኳን አንሰው አንዲት በፍርሃት ነብሷን የሳተችን ሴት የሚደፍሩትን እያየን የተደፈሩት ‘ህጋዊ’ ናቸው ‘ህገወጥ’ የሚል የሕግ አንቀጽ መረጣ ውስጥ ልንገባስ እንዴት ይቻለናል? ህዝባችን እረኛ እንደሌለው መንጋ ተበትኖ፤ ተዋርዶና ክብሩን ጥሎ መኖር ከጀመረ እነሆ 23 አመታትን አስቆጠሯል፡፡ ዜጎቻችን በቄያቸዉ በሰላም ሰርተዉ እንዳይኖሩ በወያኔ አረመኔያዊ አገዛዝ መሬታቸውን ተቀምተውና ተማርረው በስደት የበረሀና የባህር ሲሳይ እየሆኑ ከዛም የተረፉት ይኸዉ አሁን እንደምናየዉ በጨካኝ መንግስታት ፖሊሶች ለእንግልት እና ለአሰቃቂ ሞት ተዳርገዋል፡፡ በሰለጠነ ዘመን ወደኋላ እንደ ጋርዮሽ የጨለማ ዘመን በወገኖቻችን ላይ በአረብ ሀገራት መንግስታት የሚደርሰዉን እንግልት የአለም አይን እና ጆሮ እንዲያይ እና እንዲሰማዉ በየቦታው ባሉ የሳዑዲ ኤምባሲዎች የተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች በመጠኑም ቢሆን የአለም ህዝብ ችግሩን እንዲረዳ ለማድረግ አስችሏል፡፡
”ነፃነት፣ አንድነት፣ ፍትህ እና እኩልነት በወሬና በዲስኩር አይመጣም” እንደተባለው የመስዋዕቱ አይነት ይለያይ እንጂ አነሰም በዛም ለነፃነት የሚደረግ ትግል ወይ ሃብትን ወይም የህይወት መስዋዕትነትን ይፈልጋል፡፡ ይህንን ሁሉ በህዝብና በሃገር ላይ የሚደርሰውን ለከት ያጣ ጭቆና የምናይ እና የምንሰማ በተለይ በሰለጠነው አለም የምንኖር ወገኖች እኛ በሰው ሃገር የምናገኘውን እንዲህ ያለውን የመፃፍ፣ የመናገር፣ የመሰብሰብና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ወገናችን በገዛ ሃገሩ ሲያጣ፣ ይህ ነው የማይባል ችግር ሲወርድበት በተግባር መልካም ውጤት የሚያመጣ ስራ ለመስራት ቆርጠን ልንነሳ ይገባል፡፡ በአንድነትና በቁጭት ለሃገራችን ህዝብ ነጻነት ካልተነሳን በስተቀር የወያኔን ተንኮል ችላ ማለት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የወገኖቻችንንና የውዲቱ ሃገራችንን የመከራ ጊዜ ማራዘም ማለት ነው፡፡ ዘረኛው ወያኔ በነፃ አውጪ ስም ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እንዲሁም ከዛም በፊት የሚከተለው የተሳሳተ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት የማፍረስና የመበተን የመገነጣጠሉንና ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ ለባዕዳን የመስጠቱን እኩይ ተግባር መመልከት የተለመደና የቀን ከሌት ክንውናቸው መሆኑ በሃይል ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬዋ ዕለት የሚታይ እውነታ ነው፤ ለዚህም ለማስረጃ ያህል ሰሞኑን በስፋት እንደሚወራው የ’ድንበር ማካለል’ ስም ተሰጥቶት የምዕራቡን የሃገራችንን ክፍል ለሱዳን አሳልፈው መስጠታቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያችን መልካም አስተዳደር ጠፍቷል፤ ሙስና እንደ ሸረሪት ድር በየቦታው አድርቷል፤ ‘የሕግ የበላይነት አለ’ በሚባልበት አገር ፍትህ ርቋል፤ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ከመቼውም በላይ ተንሰራፍቷል፤ በሕገ መንግሥት የተረጋገጡ መብቶች ተጨፍልቀዋል፡፡ 
በነፃነት በመኖር የምንቀድማቸው ሃገራት ሰልጥነው በዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም አሰተዳደር የህዝቦቻቸውን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ ደፋ ቀና በሚሉበት በዚህ ዘመን የኋሊት የሚጓዘው ከዘመኑ ጋር መዘመን ያቃተው ወያኔ ከብዙ ዘመናት በፊት በነበረው ኢትዮጵያዊነትን የማፍረስ አስተሳሰብና የሃይል አምባገነናዊ አገዛዝ ተሸብቦ ያላስነባው ህዝብ፤ ያልጣሰው ህግና ስርዓት፤ ያላፈረሰው አንድነት፤ ያላዋረደው የህዝብ ስብዕና፤ ያልገባበት የእምነት ተቋም፤ ያልበተነው የሞያ ማህበራት፤ ያልገደለው፣ ያላሰረውና ያላስለቀሰው የህብረተሰብ ክፍል የለም:: 
ባለፉት አመታት በወያኔ አገዛዝ በግልጽ እንዳየነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እኩልነቱን፤ መብቱንና ነጻነቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ትግል ለማኮላሸት እርስ በርሱ የሚቃረኑ ህጎችና መመርያዎችን አርቅቆ አያጸደቀ ሠላማዊ ዜጎችን አስሯል፤ አንገላቷል፤ ገድሏል፤ ከአገር በግፍ እንዲሰደዱም አድርጓል። ይሄንኑ የወያኔን ግፍ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተፈፀሙ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርት ሰሞኑን አውጥቷል፡፡ በሪፖርቱ የተካተቱት የመብት ጥሰቶች በህዝባችን ላይ በተደጋጋሚ እና በከፍተኛ ሁኔታ ወያኔ እያደረሰ ያለውን ግፍ በእማኝነት ያሳየ ሪፖርት ነው፡፡ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሪፖርቱ ያካተታቸው እንደተጠበቁ ሆኖ፤ በወያኔ የተፈጸሙ እና እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከዚያም የላቁ እንደሆኑና ሃገራችንና ህዝቧ ምን ያህል ውጥንቅጥ ውስጥ እንዳለን ያሳየ ሪፖርት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ሃገራችን ሀሳብን በነፃነት ያለፍርሀት መግለፅ የማይቻልባት፤ የዜጎች የኑሮ ደረጃ ከዕለት ዕለት እየተባባስ የሚሄድባት፤ ዘመናዊ የመረጃ መገናኛዎች ሆን ተብለው የታገዱባት፤ የህዝቦቿን ጥንታዊና ብርቅዬ የሆነውን መከባበርና አንድነት በዘር ጥላቻና በሀይማኖት ለመከፋፈል አገዛዙ የሚጥርበት፤ ዜጎች አለአግባብ የሚታሰሩባት፣ የሚገደሉባት፤ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰደዱባት፤ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያልተካሄድባት፤ ዜጎች ከመኖሪያቸውና ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉባት፤ ለሕግ ተገዢ ያልሆነ መንግሥት ያለባት፤ ዜጎች የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑ በስተቀር በነፃነት ሠርተው መኖር የማይችሉባት፤ ነፃ ሚዲያ የሌለባት፤ ዜጎች ለሀብት ንብረታቸው ዋስትና የማያገኙባት፤ ህዝባዊ መንግሥት የሚናፍቅ ህዝብ ያለባት፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ መጠቀሚያ የሆኑባት፤ ቤቶች በቁመታቸው ማደጋቸው እንደዕድገት የሚቆጠርባት ሀገር ሆናለች። ስለሆነም ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለመታደግ በየትኛውም የትግል መስክ ተሳትፎ በማድረግ ለነፃነት፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት በሚደረገው ትግል ውስጥ የየራሳችንን አሻራ ለማሳረፍ ለተግባራዊ ትግል እንትጋ፡፡ 
ለዚህ ሁሉ በሃገርና በህዝብ ላይ ለሚደርሰው እንግልትና መዋከብ ምንም እንኳን የመንግስትን እርካብ የተቆናጠጡት ’ገዢዎቻችን’ ከተፈጥሮ ባህሪያቸውና የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ከማፍረስ አንፃር የፈለጉትንና ያሻቸውን ቢያደርጉም በየግዜው በህዝብና በሃገር ላይ የሚያደረሱትን ሰቆቃ የየሰሞኑ መነጋገሪያ ከማደረግ በዘለለ በአንድነት በማበር በደል በቃኝ፣ ግፍ በቃኝ፣ መሰደድ በቃኝ፣ መታሰርና መገረፍ በቃኝ፣ ከሃብትና ከቀዬ መፈናቀል በቃኝ ብለን ለለውጥ እንድንነሳ በህብረት በመስራት ውዲቱ ሃገራችንን ከውድቀትና ከጥፋት ለማዳን የኢትዮጵያዊነት ሃላፊነታችንንና ድርሻችንን እንወጣ፡፡ 
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

source:- http://ethiopianewsforum.com/viewtopic.php?f=2&t=74165

No comments:

Post a Comment