Wednesday, February 12, 2014

ትግራዊ ማንነት ካለ ኢትዮጵያዊ ማንነትም አለ! (አብርሃ ደስታ)


“ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነት አለኝ” ብዬ ስል የራሴ (የግሌ) ማንነት የለኝም ማለት አይደለም። የአከባቢ ማንነት የለኝም ማለት አይደለም። የክልል (የብሄር) ማንነት የለኝም ማለት አይደለም። ወይም እነዚህ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ማንነቶቼ መጥፋት አለባቸው ማለት አይደለም። እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል የራሴን ማንነት አልቀበልም ማለት አይደለም። የራሴ ማንነት ስላለኝ ነው ኢትዮጵያዊ ማንነት ሊኖረኝ የቻለው። እኔ የግል ማንነት ባይኖረኝ ኑሮ ኢትዮጵያዊ አልሆንም ነበር። ምክንያቱም የግል ማንነት ከሌለኝ የሀገር ማንነት ሊኖረኝ አይችልም። እያንዳንዱ ሰው የግሉ የሆነ ማንነት አለው። የግሉ ማንነት ስላለው ነው ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለው። ኢትዮጵያዊ ማንነት ራሱ የቻለ የሁላችን የጋራ ማንነት ነው።
Abraha Desta the facebook
አብረሃ ደስታ
የትግራይ ማንነት ካለን የኢትዮጵያ ማንነት ለምን አይኖረንም? “ትግራዮች አንድ ነን” ካልን “ኢትዮጵያውያን አንድ ነን” ብንል ችግሩ ምንድነው? ኢትዮጵያዊነትኮ ከብሄር (ከክልል) ሰፋ ያለ ሀገራዊ ማንነት ነው። ሀገራዊ ማንነታችንን ብንቀበል ችግሩ ምንድነው?
ኢትዮጵያውያን አንድ አይደለንም አትበሉኝ። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን አንድ ካልሆንን ትግራዮችም አንድ አይደለንም፤ አማራዎችም አንድ አይደለንም፣ ኦሮሞዎችም አንድ አይደለንም። አንድ የሆነ አይኖርም።
“ኢትዮጵያውያን አንድ አይደለንም ምክንያቱም የተለያየ ታሪክና ባህል አለን” አትበሉኝ። ምክንያቱም እያንዳንዱ ግለሰብ፣ አውራጃ፣ ክልል (ብሄር) ወዘተ…ም የተለያየ ታሪክና ባህል ሊኖረው ይችላል። ኢትዮጵያውያን የተለያየ ባህልና ታሪክ ስላለን አንድ አይደለንም ካላችሁኝ ኦሮሞዎችም አንድ አይደሉም እላቸዋለሁ፤ ምክንያቱም የወለጋ ኦሮሞዎች፣ የሸዋ ኦሮሞዎችና የአርሲ ኦሮሞዎች የተለያየ ታሪክና ባህል አላቸው።
ኢትዮጵያውያን የተለያየ ባህልና ታሪክ ስላለን አንድ አይደለንም ካላችሁኝ አማራዎችም አንድ አይደሉም እላቸዋለሁ፤ ምክንያቱም ወለየዎች፣ ጎጃሞችና ጎንደሬዎችም የተለያየ ታሪክና ባህል አላቸው።
ኢትዮጵያውያን የተለያየ ባህልና ታሪክ ስላለን አንድ አይደለንም ካላችሁኝ ትግራዮችም አንድ አይደሉም እላቸዋለሁኝ፤ ምክንያቱም ተምቤኖች፣ ዓድዋዎች፣ ዓጋሜዎች፣ ራያዎች፣ ወልቃይቶች የተለያየ ታሪክና ባህል አላቸው።
“የተለያየነው በቋንቋ ነው” ካላችሁኝ። የተለያየ ቋንቋ የማንነት መለያ መስፈርት ከሆነና እኛ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ቋንቋ ስለምንናገር የተለያየን ከሆንን ትግራዮችም አንድ አይደለንም። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገር ህዝብ አይደለም፤ አንድ ዓይነት ባህል ያለው ህዝብ አይደለም። ምሳሌ ኢሮብ (ቋንቋ ሳሆ) የራሳቸው ቋንቋና ማንነት አላቸው። ግን በትግራይ ክልል ዉስጥ ናቸው። በትግራይ ኩናማዎች አሉ (ወልቃይቶች ጨምሮ)። የራሳቸው ባህል አላቸው። ራያዎች የራሳቸው የሚኮሩበት ባህል አላቸው። ስለዚህ በትግራይ ክልል የተለያዩ ባህሎችና ቋንቋዎች አሉ። ግን ትግራዮች (ተጋሩ) አንድ ነን። ተጋሩ አንድ ነን ስንል አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል ብቻ አለን ማለታችን አይደለም፤ ተጋሩ አንድ ነን ስልን ሌላ ቋንቋ፣ ማንነት፣ ባህል ወዘተ ያላቸው ህዝቦች እውቅና አንሰጥም ማለት አይደለም። ማንነታቸው እንዲቀይሩ እናስገድዳቸዋለን ማለትም አይደለም። ተጋሩ አንድ ነን ስንል የግላችን ማንነት ጠብቀን የጋራ በሆነ የትግራይ ማንነት በአንድነትና በእኩልነት እንኖራለን ማለት ብቻ ነው።
ተጋሩ አንድ ነን። ኢትዮጵያውያንም አንድ ነን። የተለያየ ቋንቋ መናገራችን የተለያየን ስለመሆናችን ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም። ስለ ኢትዮጵያዊ ማንነት ስናወራ ስለ ሌሎች ማንነቶች እውቅና እየሰጠን ነው። ምክንያቱም የያንዳንዳችን ማንነት ከሌለ የጋራ ማንነታችን አይኖርም። የያንዳንዱ ግለሰብ ማንነት ካከበርን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ማንነት እናከብራለን። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ማንነት ማለትኮ የኛ ማንነት ማለት ነው። “እኛ” ማን ነን? እኛ ሁላችን ነን።
ኢትዮጵያዊ ማንነት ከሌለ የክልል (ብሄር) ማንነትም አይኖርም። ኢትዮጵያዊ ማንነት አለ፤ ምክንያቱም የያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን የየግላችን ማንነት አለን።
ኢትዮጵያዊ ማንነትን ስናስቀድም ሁሉም ኢትዮጵያውያንን እናስቀድማለን። የዓድዋ ወይ የራያ ወይ የኢሮብ ማንነት ብናስቀድም እያስቀደምነው ያለነው ህዝብ የአንድ ወረዳ ወይ አከባቢ ብቻ ነው የሚሆነው። የትግራይ ማንነት ብናስቀድምም የምናስቀድመው የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው የሚሆነው። ትንሽ ጠበብ ያለ ነው። ሌሎችስ ለምን እንተዋቸዋለን? ሌሎች (አማራዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ሶማሌዎች፣ ደቡቦች፣ ዓፋሮች፣ ጋምቤላዎች፣ ቤኑሻንጉሎች፣ ጋምቤላዎች፣ ሃረሪዎች ወዘተ) ለምን በእኩል ዓይን አናስቀድማቸውም?
የትግራይን ማንነት የሚያስቀድም ሁሉ የኢትዮጵያ ማንነትም ማስቀደም አለበት። ምክንያቱም የትግራይን ማንነት ስታስቀድም የሌሎች ወገኖች ማንነት ትተወዋለህ። የኢትዮጵያ ማንነት ስታስቀድም ግን የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች (የትግራይ ጨምሮ) ማንነት ነው የምታስቀድመው።
በኢትዮጵያዊ ማንነት የማምነው ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማስቀደምና ማክበር ስላለብኝ ነው። በኢትዮጵያ ዉስጥ እየኖረ የራሱን ብሄር የሚያስቀድም ሰው በሁሉም ብሄሮች (ኢትዮጵያውያን) እኩልነት አያምንም ማለት ነው። በብሄሮች እኩልነት የማያምን ደግሞ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ አይችልም። ምክንያቱም እኩልነት ከሌለ አንድነት የለም። አንድነት ከሌለ ሀገር የለም። ሀገር ከሌለ ሉአላዊነት የለም። ሉአላዊነት ከሌለ የህዝብ ደህንነት አይጠበቅም። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነት የማያስቀድም ለህዝብ አይበጅም።
አንድ የወረደ ሐሳብ ላንሳ።
የቡድን (የብሄር) መብትን የሚያስቀድመው የኢህአዴግ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት እንዳረጋገጠ ይተርክልናል። ግን በትክክል የኢህአዴግ መንግስት ሁሉንም ብሄሮች በእኩል ዓይን ያያል? ትንሽ እንውረድና …!
በፓርላመንታዊ ስርዓት (ኢህአዴግ የሚከተለው ዓይነት) የሀገር ከፍተኛው የፖለቲካ ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስተርነት ነው። ሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦች እኩል ናቸው ካልን ለዚህ ከፍተኛ የሀገር ፖለቲካዊ ስልጣን እኩል ዕድል አግኝተው መወዳድር አለባቸው።
ታድያ በኢህአዴግ ዘመነ ስልጣን አንድ የዓፋር ወይ የሶማሌ ወይ የቤኑሻንጉል ጉሙዝ ወይ የሃረሪ ወዘተ ተወላጅ የጠቅላይ ሚኒስተርነቱን ስልጣን ለመያዝ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በእኩልነት የመወዳደር ዕድል አለው? በኢህአዴግ ዘመን ዓፋር ወይ ሶማል ወይ ጋምቤላ ጠቅላይ ሚኒስተር ሊኖረን ይችላል? አይችልም። ለምን?
የሀገር ጠቅላይ ሚኒስተር ሁኖ መመረጥ የሚችለው የገዢው ፓርቲ አባል የሆነ ብቻ ነው። አባል መሆን ብቻ በቂ አይደለም። የፓርቲው ሊቀመንበር መሆን አለበት። የፓርቲ ሊቀመንበር የሚመረጠው ከፓርቲው አባል ፓርቲዎች ነው። የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች የደቡብ፣ ትግራይ፣ አማራና ኦሮምያ ብሄር ተወላጆች ብቻ ናቸው። ድርጅቶቹ ብሄር መሰረት ያደረጉ ናቸው። ስለዚህ በኢህአዴግኛ አሰራር አንድ የዓፋር ወይ የሶማል ወይ የቤኑሻንጉል ወይ የጋምቤላ ተወላጅ ጠቅላይ ሚኒስተር የመሆን ዕድል ወይ መብት የለውም። ይሄ ነው እኩልነት!?
በግለሰባዊ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለማንኛውም ስልጣን ወይ ሐላፊነት እኩል የመወዳደር ዕድል ይኖረዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ የሚመዘነው እንደ ሰው (እንደ ዜጋ) እንጂ በመጣበት ብሄር ወይ አከባቢ ወይ በሚናገረው ቋንቋ መሰረት አይደለም። ስልጣን ለመያዝ ወይ ስራ ለማግኘት ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆኑ ብቻ በቂ ነው። ከሌላው ጋር በትምህርት ደረጃው፣ በብቃቱ ወዘተ ይወዳደራል። ምክንያቱም ሁላችን እኩል ነን። ለሁሉም ነገር እኩል ዕድል ይኖረናል።
ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነት ማስቀደም የምንፈልገው ሁሉም ዜጋ በእኩል ዓይን ማየት ስለምንፈልግና ጠንካራ ሀገር መመስረት ስላለብን ነው።
ትግራዊ ማንነት ካለ ኢትዮጵያዊ ማንነትም አለ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።
It is so!!!

No comments:

Post a Comment