የነገሮች ሁሉ መድረሻ እስር ቤቶች እየሆኑ መጥተዋል፡፡
‹‹ይህንን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች መወያየት ክልክል ነው፡፡›› በማለት በተንጎላጀጀ ድምፅ ጠባቂው ተናገረ፡፡ ቀጠል አደረገናም ‹‹መነጋገር የምትችሉት ስለቤተሰብ ጉዳዮች ብቻ ነው›› በማለት ተናገረ፡፡ ይህን ከላይ ያለውን ሐሳብ የሚመለከት ማንኛውም አንባቢ፣ ጉዳይ የተፈፀመው እዚህችው እማማ ኢትዮጵያ ሰማይ ስር ባሉ አጃኢበኛ እስር ቤቶች፣ ቤተሰብ መጠየቂያው እንደሆነ መጣራቱ አይቀርም፡፡
ይሁንና በመግቢያው ላይ ያለው ጽሑፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ ‹እናት› ከተሰኘውና እ.ኤ.አ. በ1906 ከታተመው የስመ ጥሩው ሩስያዊ ደራሲ ማክሲም ጎርኪይ ታሪካዊ ልቦለድ ገፅ 102 ላይ ነው፡፡ የዛሬ 108 ዓመት አካባቢ ማለት ነው፡፡ አቤት ርቀቱ!… ይህ ርቀት ግን ለእኛ ምንም ማለት ያልሆነ ይመስላል፤ ለምን? ቢሉ ዛሬም ይህንንና ይህን የመሳሰለውን አስፍተን እየሠራን እንገኛለን፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች እየተጓዝን ያለነው የቁልቁለት ሩጫ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኖ ይገኛል፡፡
የነገሮች ሁሉ መድረሻ እስር ቤቶች እየሆኑ መጥተዋል፡፡
‹ጠበቅ ያለ እርምጃ፣ የማያዳግም እርምጃ፣ የማስወገድ እርምጃ፣…› ወዘተ የሞሉ ከሕግ መርሕዎች ሳይሆን ከጥላቻ ፖለቲካ የሚመነጩ ፀያፍ አነጋገሮችን በሕዝብ የመገናኛ ዘዴዎች ሲተላለፉ እየሰማን እየታዘብን ነው፡፡ ቃል በቃል ‹ቀይ ሽብር ይፋፋም› ብሎ ማወጅ የቀራቸው የሕግም የግብረገብም ሚዛን ያልወጣላቸው ቀረርቶች በተለይ በእስር ቤት የምንገኝ ኢትዮጵያውያንን እየሰበሰቡን ይገኛሉ፡፡
ዝዋይ የአገራችን ‹ሳይቤሪያ ግዞት›
በኢ.ቴ.ቪ. የአብዮታዊ እርምጃ ፕሮግራሞች በቀረቡ ማግስት አሁን በዝርዝር ብለው የብዙ ቤተሰቦችን ስሜት ሊያሸማቅቁ የሚችሉ ሰቆቃና እንግልቶች በአስደማሚ ስልት ተቀናብረው ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ እስኪ የተወሰኑትን እንይ፡፡ ማንኛውም ታሳሪ ቤተሰብ በቅርብ ሊጎበኘው በሚችለው እስር ቤት ይታሰር የሚለው ሕግ የተሻረው በእኛ ላይ ነው፡፡ ዝዋይ የአገራችን ‹ሳይቤሪያ ግዞት› ማለት ናት፡፡ ቤተሰብ ያን ያህል የበርሃ ጉዞ አቋርጦ የእኛዋ ሳይቤሪያ ሲደርስ በአድካሚና ግብረ-ገብ በጎደለው ፍተሻ መከራውን ማየቱ አንሶ ጆሮ ግንዱ ላይ በቆሙ የቤተሰብ አገናኞች ቤተሰባዊ ገመናውን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ሕፃናት ልጆች ወላጆቻቸው አንድ ላይ ሆነው ናፍቆታቸውን መወጣት አይችሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶቹ ሲዘናጉልን ልጆቻችንን አቅፈን እንስማለን፡፡ ይህ ከሆነ ቁጣና ዘለፋው ምንም አይደለም፡፡ ግን በሁኔታው ሕፃናቱ ክፉኛ ይበረግጋሉ፣ የእኛ ስጋት ይጋባባቸዋል፤ በዚህም መንፈሳቸው እርብሽብሽ ብሎ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡
ሁኔታው በዚህ አያበቃም፡፡ ምንም እንኳን የመጠየቂያ ሰዓቱ በግልፅ የተቀመጠ ቢሆን ከቤተሰቦቻችን ጋር ገና መነጋገር ስንጀምር ‹‹በቃ… ቶሎ ጨርሱ›› የሚባልባቸው ጊዜዎች ብዙ ናቸው፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው የእስር ቤት ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማለትም ለሳሙና፣ ለምግብ ማጣፈጫ፣ ለሻይ ለቡና፣ ለውስጥ አልባሳት፣ ለውኃ ማከሚያ/ውኃ አጋር/ ወዘተ፤ ገንዘብ የሚያስፈልገን ቢሆንም እና እንደሚያስፈልጉ ቢታወቅም ጉዳዩ ለይቶለት የማሰቃየት፣ ማንገላታት፣ መበቀል ሆኗልና ለአንድ ወር ከአንድ መቶ ብር በላይ መጠቀም እንዳንችል የተከለከልን የመሆኑ አሳፋሪ ሐቅ ነው፡፡ ይህ እየተፈፀመ ያለው ደግሞ ዝዋይ እስር ቤት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ለመግለጽ በሚከብድ ሁኔታ ሰብኣዊ ክብራችንን የማዋረድ ሙከራዎች እየተፈፀሙ ነው፡፡ በአገራችን ላይ እኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የጨረስኩት ዝዋይ በመሆኑ ብዙ ወዳጅ ዘመዶቼ በእዚህ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ለአካባቢው ነዋሪዎች በሳምንት እንዲጠይቁን የተፈቀደላቸው አንድ ቀን /ረቡዕ/ ብቻ ሲሆን ‹‹የት ነው የምታውቁት? እንዴት አወቃችሁት? ምንድን ነው የሚያመላልሳችሁ?›› በሚሉትና በሌሎችም ጥያቄዎች ተደናግጠው መምጣቱን እርግፍ አድርገው ትተውታል፡፡
ሀገሩ ሞቃታማ ነውና በዚያ ላይ በእያንዳንዱ ቤት እስከ 150 ሰው ይታሰርበታል፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ እስረኛው የቱንም ያህል ፅዳቱን ለመጠበቅ ቢሞክርም የተባዩ መርመስመስ የእነ ትኋን እንዲህ መራባት፤ ለማሰብ እንኳን ይዘገንናል፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ገላን ሲቆፍሩ ማደር ነው፡፡ ሊናገሩት ይከብዳል፣ አንባቢንም ቅር ያሰኛል፤ ግን ይህ የፊልም ትረካ ሳይሆን በእማማ ኢትዮጵያ ልጆች ላይ ሆን ተብሎ እየተፈፀመ ያለ ደባ ነው፡፡ […] ግን የባሰ አታምጣ ማለት ነው!
የዝዋይን ልጅ ውሃ ጠማው
ግን የባሰ ነገር አለ፡፡ አፈር ቅጠል የማይል ምግብ ይቀርብናል፡፡ ‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ› ከፍተኛ የውኃ እጥረት /ዝዋይ ሀይቅ አናት ላይ ተቀምጠን/ አለ፡፡ የእስር እስር እንዲሉ ጄኔራል መኮንኖቹን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አባሪዎቻቸውና ሌሎች ሌሎች የተወሰንን እስረኞች የምንገኘው በልዩ ቅጣት ጭለማ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ እንደምንም ለመቋቋም ጥረት ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡ አዲሱ ስልት ግን መዘዙ በጣም አደገኛ በመሆኑ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ እያንዳንዱ ሃይማኖት ያለው፣ ፈርሐ እግዚአብሔር ያለው፣ እያንዳንዱ የመሠረታዊ ሰብኣዊ መብቶችና ነጻነቶች መከበር የሚያሳስበው እያንዳንዱ ሰው የሆነ ሰው ሁሉ ሊያውቀው ይገባል ስንል ድምፃችንን እናሰማለን፤ በሕክምና ንፍገት ወደሞት እየተገፋን ነው፡፡
ሕመም ካልታከመ መጨረሻው ሞት ነው፡፡ የሞቱም ሰዎች አሉ!
ከወር በፊት ገደማ ወጣቱ የአንድነት ፓርቲ አባል ናትናኤል መኮንን ለሕክምና በሪፈር ወደ ቃሊቲ ተልኮ የነበረ ቢሆንም፣ የዛኑ ዕለት ሕክምናውን ተነፍጎ ከሌሊቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ እስካሁን በሕመሙ እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ የኢብአፓ ሊቀመንበር የነበረው ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር እንደዚሁ ለተጨማሪ ሕክምና ሪፈር ተብሎ ሲጠባበቅ ከቆየ በኋላ ዘዴው ተፈፃሚ ሆነበት እጁን አጣጥፎ ተቀምጧል፡፡ ከሕመሙ ጋር በተያያዘ በአካሉ ላይ አሳሳቢ ሁኔታ እየታየበት ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ገልጬው የነበረው የእኔ የኩላሊት ሕመም አሁን ለመቀመጥም፣ ለመንቀሳቀስ እያወከኝ የሚገኝ ሲሆን፣ እኔን ከቃሊቲ ዝዋይ ለማምጣት የተደረገው የተቀናጀ መረብ ሩብ ያህሉን ለሰብኣዊነት አውለውት ቢሆን ኖሮ እኔም ፋታ፣ እነሱም እርካታ ባገኙ ነበር፡፡ ሕመም ካልታከመ መጨረሻው ሞት ነው፡፡ የሞቱም ሰዎች አሉ!
የጄኔራል መኮንኖቹ አባሪዎች የነበሩት ኮረኔል ተስፋዬ ኃይሉ እና ኢንጂነር ክፍሌ ስንሻው፣ በዶክተር መረራ በሚመራው ኦሕኮ ፓርቲ አባል የነበሩት አሕመድ ነጃሺ፣ በጭለማ ቤት የከረመው ተስፋሀን ጨመዳ፣ የቤንሻንጉሉ አዛውንት ወዘተ ተገቢውን ሕክምና በማጣት ሕይወታቸውን ያጡ የእማማ ኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ እንዴት ሕክምና ይከለከላል!? ግፍና ጭቆና ተቃውመው ደማቸውን ያፈሰሱና አጥንታቸውን የከሰከሱ ታጋዮችን በሥልጣን ማግስት ከፍርድ በመለስ በየእስር ቤቱ ያሉ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸው በሕክምና እጦት ሲረግፉ በእርካታ ማርመምን ከየት ተማሩት!? የኢትዮጵያ ሕዝብስ ምን ይላል!? ሰው የሆኑ ሰዎች ሁሉ ከቶ ምን ይላሉ!?
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ምንጭ ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment