Saturday, February 1, 2014

ይድረስ ለዶክተር ታደሰ ብሩ – ባሉበት! (ነፃነት ዘለቀ፣ ከአዲስ አበባ)


ነፃነት ዘለቀ (ከአዲስ አበባ)
ከምቸገርባቸው ነገሮች አንዱ ለምጽፋቸው መጣጥፎች ርዕስ ማውጣት ነው፡፡ አንዳንዴ ርዕሴና በጽሑፌ ውስጥ የማነሳው ጉዳይ አልገናኝ ይሉብኛል – ልክ እንደአሁኑ፡፡ ዛሬና አሁን ለዶክተር ታደሰ ብሩ የምለው አንድም ነገር የለኝም፡፡ ነገር ግን እሱ አሁን በትምህርት ብልጭታ የኢሳት ቆንጅዬ ፕሮግራሙ ላይ ባነሳው የእስታስቲክስ ጉዳይ  እኔም አንድ ቀን እተነፍስበታለሁ ብዬ እዝት ስለነበር ያን ስላስታወሰኝ ርዕሴን ለሱ መታሰቢያ አደረግኋት፡፡ ደርባባው ታዱ የሥራ-ፈት ኤፍኤሞቻችንን ቋንቋ ልጠቀምና “እወድሃለሁ፤አከብርሃለሁ” – ባለህበት ይመችህ፡፡(ኤፍ ኤሞችን የማልወዳቸው አዘናጊ ስለሆኑ ነው፤ በተለይ ወጣቱን በእግር ኳስ ጨዋታ ሱስ እያሰከሩ፣ በአይሬ የጫት ዙርባ እያመረቀኑ፣ በፆታዊ ወሬ ምድረ ሴሰኛን እያነሆለሉ፣ በትርኪ ምርኪ ወሬ ማኅበረሰቡን እያጃጃሉ ወያኔያዊ ተልእኮኣቸውን በመወጣት ላይ ስለሚገኙ ነው፡፡ በተለይ ያቺ ሙግድ አፍማ … ቆይ ብቻ፣ ይንጋማ! ልክ ልኳን ያልነገርኳት እንደሁ ቁጭ ብዬ ተኝቻለሁ፡፡)Dr. Tadesse Birru ESAT journalist
በዚያ ላይ የወያኔ  የስለላ መረብ ጋማ ኢንተርናሽናል ከተባለ የእንግሊዝ የስለላ ቴክኖሎጂ አፍላቂ ባለዬ ድርጅት በገዛው አንድ የቴክኖሎጂ ውጤት የታዴ ኮምፒውተር በስለላ ቫይረስ መጠቃቱን በዚያው ኢሳት የዜና ዕወጃ ስለሰማሁ በእግረ መንገድ እግዜር ያጽናህ ለማለትም ነው፡፡ እነዚህ ወያኔዎች ግን በርግጥም ይሠሩትን አጥተዋል ማለት ነው – ሶልዲ አሰከራቸውና እሚሆኑትን አሳጣቸው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? እኛ እዚህ ኑሮ እንትኗን አፈንድዳብን እምንቀምሰውንና እምንልሰውን አጥተናል፤ እነሱ ከድሃው ሕዝብ በሚዘርፉት ገንዘብ ወንበራቸውን ለማስጠበቅ በውድ ዋጋ የስለላ ሶፍትዌሮችን ይገዛሉ – ዓለመኞች ናቸው፤ ግፈኞችም ጭምር! ይህን ዕኩይ ተግባራቸውን ያጋለጠው ፕራይቬሲ ምንትስ የተባለው ድርጅት እንደታዘበው እነዚህ ሰዎች ከድሃ ሕዝብ ጉሮሮ እየነጠቁ ይህን ውድ ዕቃ መግዛታቸው በርግጥም የገቡበት ክፉ አጣብቂኝ ቢኖር ነው ብሎ መጠርጠር ይቻላል፡፡ አባታቸው ሰይጣን ይሁናቸው ከማለት ውጪ ምን ይባላል?
(በነገራችን ላይ ለዕድገታችን ቀን ከሌሊት የሚለፉልን የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ሣምንት አዲስ አበባ ላይ ለስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ መንገድ እየተዘጋጋ መንቀሳቀስ አቅቶናል፡፡ እነሱ ባይኖሩ ኖሮ – ባይሰበሰቡልንም ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? ስብሰባውን እየተው ሸቀጥ የሚያጋብሱም ገጥመውኛል፤ ለሴትና ለሸቀጥ እንዲሁም በመብል በመጠጥ ከርሳቸውን እየሞሉ በጭቁኖች ገንዘብ እንደልባቸው ለመዝናናት የሚመጡት ይበልጣሉ – ሌላ ምን ቁም ነገር ሊሠሩ ዱሮውንስ፡፡ ፍሬፈርስኪ ለሆነ ስብሰባ ከአፍሪካ ድሆች በግድ የሚዘረፈው ገንዘብ አለመላው ሲከሰከስ ለሚታዘብ ጤናማ ወገን ያሳዝናል፡፡ አንድ የሰማሁት አስገራሚ ነገር አለ፤ እነዚህ የአፍሪካ አለኝታዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የአፍሪካ ኅብረት የተባለው ሥራ-ፈት ድርጅት ከግለሰቦችና ከድርጅቶች ለእንግዶቹ ማጓጓዣ መኪና ይከራያል፡፡ ያስገረመኝ ነገር ታዲያ ወያኔ የሠረገበት ይህ ድርጅት መኪና የሚከራየው ከወያኔዎች እንጂ ከሌላ አለመሆኑ ነው፡፡ ሾፌር የሚቀጠረውም ከወያኔው ዘውግ ብቻ እንደሆነ ውስጥ ዐዋቂ ሰሞኑን አረዳኝ፤ ለዚህች ለሣምንት ሥራም አድልዖ ይፈጸምባታል፡፡ ገቢው ከፍተኛ ስለሆነ ለማንም ከወያኔዎች ውጪ ለሆነ ግለሰብና ድርጅት አይሰጥም፡፡ እነሱው በነሰው ያለውን ሁሉ ይቀራመቱታል፡፡ አሁንስ የበይ ተመልካችነታችን ጠርዝ ለቀቀ፡፡ አይ፣ በጣም ተናደድኩ፡፡
እንደአንዳንዶች ሃሜት በርግጥም ይሉኝታ ከሰሜን ተጠራርጎ ወጥቷል ማለት ነው? ሰሜን ተወልጃለሁ፤ ሰሜን አድጌያለሁ፤ ሰሜን ኖሬያለሁ፤ ያኔ እንዲህ ያለ ይሉኝታቢስነት አላየሁም፡፡ አሁን ምን እንደመጣብን አላውቅም፤ ይህ ዘረኝነት ከምን እንደመነጨ መመርመር አለበት፡፡ ዐይን ያወጣ ዘረኝነት ነው እየታዬ ያለው፡፡ መሌ ገሞራው ስለህዳሴው ግድብ አንድ ወቅት እንዲህ አለ፡- “መሃንዲሶቹም እኛው፤ የገንዘብ ምንጮቹም እኛው፤ ምናምንቴዎቹም እኛው …”፡፡ እኔ ደግሞ እላለሁ፡-  ከሳሾቹ እነሱ፣ ዳኞቹ እነሱ፣ ፍርድ አስፈጻሚዎቹ እነሱ፤ ሻጮቹ እነሱ፣ ገዢዎቹ እነሱ፤ ባለሥልጣኖቹ እነሱ፣ በፍጥነትና በጥራት ተስተናጋጆቹ እነሱ፤ ጨረታ አውጪዎቹ እነሱ፣ ጨረታ ተወዳዳሪዎቹ እነሱ፣ ጨረታ አሸናፊዎቹ እነሱ፤ ኮንታራት ሰጪዎቹ እነሱ፣ ኮንትራት ተቀባዮቹ እነሱ፣ ኮንትራት አዳሾቹ እነሱ፤ ሕንጻ ተቋራጮቹ እነሱ፣ ሕንፃና የገበያ ማዕከላት ባለቤቶቹ እነሱ፣ ፋብሪካና ኢንዱስትሪ ገምቢዎቹ እነሱ፣ አየር ኃይሎቹ እነሱ፣ አየር ወለዶቹ እነሱ፣ አየር አብራሪዎቹ እነሱ፤ ሹዋሚዎች እነሱ፣ ተሸዋሚዎች እነሱ፣ ሰላዮቹ እነሱ፣ ተሰላዮቹ እኛ፤ ባለገንዘቦቹ እነሱ፣ ከግብርና ከቀረጥ ነፃ ሆነው የሚነግዱ እነሱ፣ ግምባርና ኪስ ቦታዎችን እያደኑ የሚይዙና የሚሸጡ የሚለውጡ እነሱ፣ ከሕግ በላይ ሆነው ማንም ላይ እሚያሽቃንጡ እነሱ፣ ገና ጡት ሳይጥሉ ቱጃር ሆነው በመቶ ሺዎች የሚገመት ብር በአንድ አዳር በየዳንኪራ ቤቱ ሲከሰክሱና በገንዘባችን ሲሸራሞጡ የሚያድሩ እነሱ፣ ጠግበው የሚዘፍኑና እንደኬንያ ማታቱ አደንቋሪ ሙዚቃ ሌሊት ከየቤታቸውና ከየመኪኖቻቸው  ሙዚቃ  እስከጣራ እየከፈቱ እንቅልፍ የሚነሱን እነሱ፣ … በችጋርና በችግር የምናንቋርር እኛ፣ የነሱን ዕዳ የምንከፍል እኛ፣ የምንታሠር የምንሰደድ እኛ፣ ከትምህርትና ከዕውቀት ዓለም ወጥተን ወደምድራዊ ሲዖል የተጣልን እኛ፣ የምናቀምሳቸውን ምናምኒት አጥተን ልጆቻችንን በርሀብ አለንጋ የምናስገርፍ እኛ፣ የትውልድ መርገምት የተሸከምን እኛ፣ … አፄ ቴዎድሮስ ያናደዱትን ካህናት ሰብስቦ “አንድሽ አንባቢ አንድሽ ተርጓሚ ሆነሽ መንግሥቴን ታውኪያለሽ…” ያለው ለካንስ ወዶ አልነበረም፡፡ ወያኔም የተለያዬ ካባ እየለበሰች አባት ዳኛ ልጅ ቀማኛም እየሆነች በኢትዮጵያ ላይ ታሪካዊ ሚናዋን መጫወቷን ቀጥላለች፡፡ ማን ተይ ብሏት? ማንንስ ፈርታ? (አንዱ አንዱን “ሚስትህ ወንድ ወለደች?” ብሎ ቢጠይቀው “ማንን ወንድ ብላ!” አለው አሉ፡፡) ወያኔ እያጠራቀመችው ያለችው ታሪካዊ ዕድፍ የሚያመጣባትን ዕዳ ግን ከፍላ የምትጨርሰው አይመስለኝም፡፡ የፈጣሪ የጽዳት ቀን ሲመጣ ምን ይውጣት ይሆን? ክበበው ገዳ፡- “ወዮልሽ አንቺ ኮሜዲ ሆይ…” ያለው በተወራራሽ ለወያኔም ይሠራል፡፡
(Literally, almost all privileges and benefits that Ethiopia has in her meager store, within or without her ever-shrinking border, willy-nilly belongs to TPLFites; Oh, shame on them! What a curse has descended upon these crooked creatures, and by extension, upon us, the oppressed majority? I wish I had a chance to examine the essence of the gray mud they are supposed to carry in their skull; I hope its content must be the same as that of the hyenas’ and pigs’ brain. They have fallen in love with MONEY and have gone crazy with this blind love. There is no JOKE; they do everything and anything to get MONEY. They have already evicted most of OTHERS from any ETHIOPIAN income generating means. They have convinced themselves that they are the sole owners or possessors of this ill-fated nation. Wonderful!  They have controlled virtually everything. There is a rumor that some of them have gone as far as owning their own minting machine which is why the circulation of Birr has become uncontrollably rampant especially in the hands of TPLFites; am not lying; what I am talking is the stark truth. Most of them are joining the camp of billionaires, while on the other hand, we the majority of OTHERS are obliged to join the camp of absolute poverty where there is nearly nothing for survival. The gap between the rich (in this specific case the TPLFites) and the poor is beyond explanation; there is no word (of any language on earth) to explain the discrepancy between THEM and US. Life in Ethiopia is skyrocketing in an alarming manner. The life style of THEIRS and OURS, i.e., the difference between THEM and US, is terribly shocking. Since the time this dichotomy, the ‘THEM’ and ‘US’ duality, has come onto the surface of this country, the ‘THEM’ group has boldly been committing all sorts of crimes and mischievous acts under the sun to impoverish the ‘US’ bloc.)
ታደሰ ብሩ በግሩም ሁኔታ እያቀረበው የነበረው አንዱ ሀገራዊ ችግር በእስታትስቲክስ ረገድ ሀገራችን ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮ የምታሳየውን “ዕድገት” ነው፡፡ እናንተዬ በርሀብና በጦርነት እንዲሁም አረመኔና አውሬ መንግሥታትን በማፍራትና በመሸከም ብቻ ሳይሆን በውሸትም አንደኛ ሳንሆን እንቀራለን? ምን ዓይነት ጉድ ነው? ይሄ ቤተ መንግሥት አንድ መቶና ሁለት መቶ ሰባቶችን ካልተጠበለ ከገባበት አባዜ በቀላሉ የሚፈወስ አይመስለኝም፡፡ አንድ የበቃ ባህታዊ ተፈልጎ ድርሣነ ሚካኤልን ይድገምበትማ እባካችሁ፡፡ አድምጥ ልንገርህ፡-
ደግሞ ለውሸት አለው ድካ፤
አምሳ ሰው ገዳይ ባንድ አማሪካ፡፡
ይህ ሥነ ቃል የቋንቋ መምህራን ስለ ግነት ሲያስተምሩ በረጂም ዘመን ትውፊት  ከደለበው ቃላዊ ሥነ ጽሑፋችን የሚመዙት አንዱ የንግግር ማጉሊያ ፈርጥ ወይም የጨዋታ ማድመቂያ ሰበዝ ነው፡፡ እውነት ነው – ውሸት ድካ ወይም ድንበር የለውም፡፡ ድንበሩ የተናጋሪው ኅሊና ብቻ ነው፡፡ ኅሊናውን መጠቀም የማይፈልግ ወገን፣ ኀሊናውን ለገንዘብ ወይም ለጥቅምና ለተለዬ ዓላማ የሸጠ ሰው እውነትን ሽምጥጥ አድርጎ ሲክድ ቅር አይለውም – የበሽታ ከሆነ እንዲያውም አንዳንዴ ምናልባትም ሁልጊዜ፣ መዋሸቱን ላያውቀው ይችላል – መረገም ነው፡፡ መዋሸትም ይባል ማጋነን በግለሰብ ደረጃ የጥፋት አድማሱና ክብደቱ ቀለል ስለሚል ምንም አይደለም ሊባል ይችላል፤ በሀገር ደረጃ ሲሆን ግን የሀገርን ኅልውና እስከመፈታተን የሚደርስ አደጋና ችግር ሊፈጥር ይችላል፤ በኛ ሀገር በተለይ በመንግሥት ደረጃ መረጃን ማንሻፈፍና በቤተ ሙከራ የተፈበረኩ ቁጥሮችን በሚዲያ መዝራት እንደሱስ ሳይጣባን አልቀረም፡፡ “እውነትን ተናግሮ እመሸበት ማደር” የ‹ፋራው ዘመን› ብሂልና የ‹ፋራዎች› ተረት ሆኗል፡፡
ውሸት ዓይነቱ ሊለያይ ቢችልም ሁሉም ውሸት እውነትን ለማፈን እስከዋለ ድረስ ማንም ይዋሸው ማን ያው ውሸት ነው፤ ጉዳቱም ከፍተኛ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ እኔም አንተም እንዋሻለን – ቀላልም ከባድም ውሸት፡፡ “እኔ አልዋሽም” ብሎ የሚመፃደቅ ሰው ካለ እርሱ የመጨረሻው ውሸታም ነው – ግን ስንዋሽ መልክ ውሸታችን መልክ ያለው እንዲሆን መጣር የሚኖርብን ይመስለኛል – እንደወያኔና ሚዲያው የለዬለት ቀዳዳና ቱሪናፋ መሆን አይኖርብንም፡፡ በልማድ ለደግ ነገር – ለምሳሌ የተጣሉ ሰዎችን ለማስታረቅ – መዋሸት መልካም እንደሆነ ሲያንስ ለክፋት እንደማይሰጥ ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
እዚህ ላይ በኩሸት፣ በውሸትና በእውነት መካከል ያለውን ልዩነት ልብ ማለት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ኩሸት ትንሽ እውነት ይዞ ምናልባትም ከባዶም ተነስቶ አንድን ሰው ማጋነን ወይም ማሽበልበል ነው – ለምሳሌ ባልዋለበት ጦር ሜዳ እንዳሸነፈ፣ ባልታጠቀው መሣሪያ ልክ እንደሶምሶን(ሳምሶን) መቶዎችን እንዳረገፈ፣ ወዘተ. በመኳሸት ፈሪን እንደጀግና፣ ንፉግን እንደቸር፣ ጨካኝን እንደሩህሩህ የሚያደርጉበት ሥነ ምግባራዊ ብልሽት ኩሸት እንደሚባል መምህራን ይናገራሉ፡፡ በመሠረቱ ውሸትም ኩሸትም በብዙ ነገር ይመሳሰላሉ፡፡ ጊዜ ለመቆጠብ ወደ ሀገራችን ይሉኝታቢስ እስታትስቲክስ እንለፍ፡፡
በመንጌ ጊዜ ነው፡፡ መንጌ ገሞራው በኢትዮጵያ ያለው እራሽ መሬት (arable land) ምን ያህል እንደሆነ ተጠንቶ ይቅረብልኝ ይልና ለግብርና ሚኒስቴር ትዕዛዝ ያስተላልፋል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በተዋረድ ይህን ትዕዛዝ ለአሥራ አራቱም ጠቅላይ ግዛቶች ይልክና በቶሎ ተጠንቶ እንዲቀርብለት ያዛል፡፡ ከየክፍለ ሀገሩ “መረጃው” ቀረበ፡፡ ማዕከላዊ ፕላን ይባል በነበረው የስብሰባ ቦታ የሚኒስትሮች ጉባኤ ይዘጋጃል – ጥቁሩ ነብር አራስ ሲሆን እፊቱ የሚገኝን አሽትሬይና እስክርቢቶ በደመ ነፍስ እያነሣ ወዳናደደው ባለሥልጣን ይወረውር በነበረበት ዘመን መሆኑ ነው፡፡ የግብርና ሚኒስትሩ ተራው ይደርስና ሪፖርቱን በንባብ ማሰማት ይጀምራል፡፡ … ሰውዬው በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ለእርሻ ተስማሚ የሆነ የመሬት የቆዳ ስፋት ሲናገር ከሞላ ጎደል ሁሉም ተሰብሳቢ በሣቅ ይፈነዳል፡፡ ለካንስ በቀረበው እስታትስቲካዊ መረጃ መሠረት ከየጠቅላይ ግዛቱ የመጣውና አንድ ላይ የተደማመረው ሊታረስ የሚችለው የመሬት ስፋት ከጠቅላላው የሀገሪቱ የቆዳ ስፋት በልጦ ኖሯል! የኛ አስታስትስቲክስ እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡ “የኛ ስታይል እንዲህ ነው!” የሚል የቀልድ ዘፈን አለ፡፡ ያስ ዱሮ ነው፡፡ አሁን ብሶ ቀጠለም አይደል? ይሄ ቆርጠህ ቀጥል የምንለው የውሸት ሀድራ ከመንግሥታችን እንዲወገድ በርትተን እንጸልይ ግዴላችሁም፡፡ ግን ግን እኮ ያልዘሩት አይበቅልምና እኛም እንደነሱው ቆርጠህ ቀጥል እንሆን እንዴ?
በቁሙ የሞተ የእስታቲስቲክስ መሥሪያ ቤት ያላት ኢትዮጵያ ብቻ ለመሆኗ ሌላ ባያውቅ እኞች እናውቃለን፡፡
በግንቦት 97 ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ በብዛት ወጥቶ መሪዎቹን የመረጠበት ወቅት ነበር – የምርጫውን ውጤት ያልተቀበለው ወያኔ ሥልጣኑን በኃይል እንደያዘ ቀጠለ እንጂ፡፡ ያኔ በወያኔ መንግሥት የቀረበው የመራጭ ብዛት 26 ሺህ አካባቢ ነው፡፡ ውሸት ነበር፡፡ ውሸት መሆኑን የምንረዳው የቀጣዩን የ2002ዓ.ም ምርጫ ተመዝጋቢ ቁጥር ስናይ ነው፡፡ በ2002 መረጃን መፈብረክ ተፈጥሮው የሆነው ወያኔ  ለምርጫ የተመዘገበውን የሕዝብ ቁጥር 32 ሺህ አደረሰውና አሣቀን – እኔ ጥርሴን ተወቅሬ ነበር በሣቅ የፈነዳሁት፡፡ ይታያችሁ – ሕዝብ በነቂስ በወጣበት ምርጫ የተመዝጋቢው ቁጥር አነሰ፡፡ ሕዝብ ተስፋ ቆርጦ እቤቱ በተሰበሰበበትና ከወያኔው ጋር በጥቅምና በዓላማ የተቆራኙ አንዳንድ ዜጎች ውር ውር ባሉበት የምዝገባ ወቅት ቁጥሩ ተነረተና 32 ሺህ ደረሰ፡፡ ምን ትሉታላችሁ? የእስታትስቲካዊ መረጃው ሲነፋ(ሲያብጥ) ወያኔን የሚጠቅም ከሆነ ነፊዎቹ አንድም የይሉኝታ አጥር ሳይገድባቸው ሰማይ ያደርሱታል፤ ትዝብት ግዛዕምዛ አያውቁም፡፡ ዋናው ዓላማቸው የላይኞቹን ማስደሰት ብቻ ነው፡፡ የእስታትስቲክሱ መረጃ መጫጫት መንግሥታቸውን የሚያስደስት ከሆነ ደግሞ ለምሳሌ “ከመቀሌ አዲስ አበባ ያለው ርቀት መቶ ሜትር ነው” ብለው በዓይነቱ ልዩ የሆነ መረጃ እስከመስጠት በሚደርስ ድፍረት አዲስ እስታትስቲክስ ከመፍጠር አይመለሱም – “ዋሽ ቢሉኝ እዋሻለሁ፤ ንፋስ በወጥመድ እይዛለሁ” ያለው ባላገር እንዴት ብልህ ነበር፡፡ አንዱ ወያኔን በውሸት ፈጠራ የሚስተካከል ልጅ ደግሞ አባቱን “አባዬ፣ እስኪ ውሸት አስተምረኝ” ብሎ ይጠይቀዋል አሉ፡፡ አባትም በእሺታ ይቀበለውና ማስተማሩን ሊጀምር “ልጄ፣ እዚያ ሰማይ ላይ በነጫጭ በሬዎች ሰዎች እህል ሲያበራዩ ይታዩሃል?” ይለዋል ወደሰማዩ አንጋጥጦና ሌባ ጣቱን ወደተባሉት ሰማይ ላይ እህል ወደሚወቁት ሰዎች ቀስሮ፡፡ ልጅም ቀበል ያደርግና “ውይ ውይ አባዬ …” ብሎ ይጮሃል – ዐይኖቹን በእጆቹ ከድኖ፡፡ አባት ይደነግጥና “ምን ሆንክ ልጄ ምን ነካህ” ይለዋል፡፡ የውሸት ሥልጠና ኮርስ ከመመዝገቡ ትምህርቱን የጀመረው ታዳጊ ወያኔ “ውይ አባዬ፣ የጭዱ ብናኝ ዐይኔ ውስጥ ገባ!” ይላል፡፡ አባትም “አሃ፣ አንተንማ ውሸት ማስተማር አልችልም፤ ከኔስ በልጠህ የለም እንዴ” ይለውና ኮርሱን ‹ድሮፕ› አድርጎ የኤግዘምሽን ቅጽ እንዲሞላ ይመክረዋል – እንዲህ እየተቀላለዱ ነው የወያኔን ዘመን ሸውዶ ማለፍ ወንድምዬ ፡፡ እባክህን በነካ እጄ አንድ የወያኔን ባሕርይ የሚያሳይ ሌላ ረቀቅ ቀልድ ልንገርህና ትንሽ ዘና በል፡፡ …
አንድ ጉልበተኛ ጨቡዴና አንድ የኔ ቢጤ ኮሣሣና ፈሪ የሆኑ ሁለት ጓደኛሞች ወደ አንድ ቦታ በመጓዝ ላይ እንዳሉ መንገዳቸው ላይ አንድ ጥቁር ነገር ቁጭ ብሎ ከሩቅ ያያሉ፡፡  ይሄኔ ጨቡዴው “አየኸው ያንን በግ?” ይለዋል – ለአቅመ ደካማ ጓደኛው፡፡ ፈሪ ጓደኛም  “የቱን በግ?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ “እዛ ጋ ቁጭ ያለው ጥቁር በግ” ይለዋል እሱ ከሩቅ አይቶ ከነምንነቱ የለዬውን ጥቁር በግ ጓደኛው ከነአካቴው ምንም ነገር አለማየቱን ተገንዝቦ በመደነቅ፡፡ “እንዴ፣ አሞራውን ነው እምትለኝ?” ይለዋል፡፡ “የምን አሞራ አመጣኽብኝ! በግ ነው እንጂ” በማለት ጡንቻውን ጭምር እያሳዬ በኃይል ሊያሳምነው ይሞክራል፡፡ በዚህ መሀል ወዳጨቃጫቂው ነገር እየቀረቡ ሲሄዱ ያ በጉልበተኛው ጓደኛ ጥቁር በግ የተባለው ነገር ይበራል፡፡ ይሄኔ ደካማ ጓደኛ “ይሄው፣ በግ አይደለም – አሞራ ነው አላልኩህም? በረረልህ፡፡ ” ቢለው “በረረም አልበረረም በግ ነው ብዬሃለሁ በግ ነው!” ይልና ዐይኖቹን እያጉረጠረጠ ያስፈራራዋል፡፡ ደካማ ጓደኛ ምን ምርጫ አለው? “እሺ ይሁንልህ በግ ነው” አለውና ከጡጫው ተረፈ፡፡ እኛስ ምን ምርጫ አለን? ምርጫችን “ወያኔ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ዘላለማዊ ክብር ለሕዝብ ለተሳዋው ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ የኢሕአዴግ ዕድሜ ዘላለማዊ ይሁንልን፤ ወያኔ ከጠፋ ኢትዮጵያ ትበታተናለች፤ ወያኔ ከወረደ ልማታችን ይደናቀፋል፤ ወያኔ ከጠፋ ዘረኝነት ተመልሶ ኢትዮጵያን ድምጥማጧን ያጠፋዋል፤ ከኢሕአዴግ ጋር መጪው ዘመን ጨለማ ማለትም ብሩህ ነው፤ ቀኝ መንገደኛው መኢሶንና ማለቴ ሽብርተኛው ግንቦት ሰባትና ሰማያዊ ፓርቲ ለተፋጠነው ልማታችን ፀርና አሸባሪዎች ናቸው …” እያሉ መፈክር ማሰማት ነው፡፡
እነመንግሥቱ እነመለስ  እነሂትለር እነሙሶሎኒ እነኢዲያሚን እነሳዳም እነአላሳድ እነሁሉም እነዚህን በእናታቸው ማኅጸን ቢጨነግፉ የሚሻላቸው ሰብኣዊ ፍጡራንን የመሰሉ ሰዎች ሁሉ ባሕርያዊ ተፈጥሯቸው አንድ ነው፤ አንድኛቸው የሌላኛቸው ቅጂ ናቸው፡፡ አባ ጉልቤዎች በመሆናቸው የሚያስቡት በአንጎል ሳይን በጡንቻ ነው – ሁሉም አምባገነኖች ከፍ ሲል በተቀመጠው ምሳሌ እንዳየነው ጨቡዴ ናቸው፡፡
ወደእስታትስቲክሳችን እንመለስ፡፡ በ1997 ሚያዝያ 29 ቀን ለወያኔ ድጋፍ የወጣው ሰው ብዛት በወያኔ ሚዲያ ሲገለጽ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነበር፡፡ በማግሥቱ ሚያዝያ 30 ለቅንጅት የወጣው ሠልፈኛ ግን በአሥር ሺዎች የሚገመት ነበር – አሁንም በወያኔ ሚዲያ፡፡ ይህን ምን እንለዋለን ? የሰዎች ተፈጥሮ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ የወያኔ በቁጥርና በመረጃ የመጫወት ልምድ እጅግ የሚያሣፍር የሚያስቅም ነው፡፡
የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር ማነስ ለወያኔ የሚጠቅም ሆኖ ከተገኘ 500 ሊሆን ይችላል፡፡ የገጠሩ ሕዝብ ብዛት ለወያኔ የሚጠቅም ሆኖ ከተገኘ ከሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር በእጅጉ በልጦ እስታትስቲካዊ መረጃው ሊለጠጥ ይችላል፡፡ ወያኔ አዲስ አበቤዎችን ስለማይወዳቸው ቁጥራቸውን ሁልጊዜ እንደቀነሰው ይኖራል፡፡ አሁን ድረስ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን እምብዝም አይበልጥም – በወያኔ ግምት ወይም ቆጠራ፤ ወያኔ ሲዋሽ ትንሽም አፈር አይልም – ይገርመኛል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ማለት እኮ የመርካቶ ሕዝብ ብቻውን ሊሆን ይችላል፡፡ አዲስ አበባ በኔ አነስተኛ ግምት ከስምንት ሚሊዮን ያነሰ ሕዝብ አይኖርባትም ባይ ነኝ፤ እምዬ አዲስ አበባ  በጣም ብዙ ሕዝብ ይኖርባታል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባን ሕዝብ ምርጫ ዋጋ ለማሳጣትና ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር አንጻር አቅልሎ ለማሳየት ሲፈልጉ ለከት የሌለው እስታትስቲካዊ ውሸት ይዋሻሉ፡፡ እስታትስቲክስ ማለት ባጭሩ የመንግሥት የውሸት ፋብሪካ ማለት ነው ቢባል ትክክል ነው፤ ሠራተኞቹ ደሞዝ የሚከፈላቸው መንግሥትን የሚያስደስት ውሸት ለመጠፍጠፍ ነው፤ የሕዝብ አንጡራ ሀብት በብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከንቱ እየባከነ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ የአፍሪካ መንግሥታት በተለይም የኛዎቹ ካልዋሹ ሥልጣናቸው የሚረጋላቸው አይመስላቸውም፡፡ የወያኔን ሚዲያ ስትከፍቱ ውሸቱ በቲቪው መስኮት አልፎ ወደዬስሜት ሕዋሳታችሁ ይገባና ያጥወለውላኋል፤ ሊያስታውካችሁም ይደርሳል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰዓትም ይዋሻሉ፡፡ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሆኖ እያለ እነሱ ሁለት ከአምስት ሊሉ ይችላሉ፡፡ ኢትሬድ ማለት እውነት እሚያቅረው ነጋ ጠባ እንደጣቃ የሚቀደድና የውሸት ቱሪናፋ የሚያሰራጭ የወያኔ ብስናት ነው፡፡ የወያኔ መሥሪያ ቤት ሁሉ በውሸት መረጃ የተጥለቀለቀ የተሳሳተና የተጋነነ እስታትስቲክሳዊ አሃዝ በመስጠት ታችኛው ላይኛውን ለማስደሰት አደግድጎ ያለበት ሁኔታ ነው የሚታየው – በነሱው አገላለጽ፡፡ ሰዎች በውሸት መረጃ እንዴት እንደሚደሰቱ አይገባኝም – “አለባብሰው ቢያርስ ባረም ይመለሱ” እየተባለ በሚተረትበት ሀገር ውስጥ ይህን ያህል በውሸት መለከፍ የሚያሳዝንም የሚቆጭም ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ እውነቱን ልቦናቸው እያወቀው በመዋሸት የመደሰት ተፈጥሮ እንደምን እንደተጠናወታቸው ሲያስቡት ይጨንቃል – የመፍትሔው መራቅ ደግሞ ይበልጥ ያበሳጫል፡፡ ከዚህ ከውሸት ዓለም የምንወጣበት ጊዜ ናፈቀኝ፡፡ እዚህም ውሸት፣ እዚያም ውሸት፡፡ ትልቁም ውሸት ትንሹም ውሸት፡፡ የግሉም ውሸት የመንግሥቱም ውሸት፡፡ በተናጠል ውሸት – በቡድንም ውሸት፡፡ በንግዱ ውሸት በፖለቲካውም ውሸት፡፡ በሃይማኖቱም ውሸት በኢኮኖሚውም ውሸት፡፡ ውሸት – ግነት – ውሸት፤ ዕብለት – ቅጥፈት – ጉራ – ዕብሪት ፤ አቤት ያንት ያለህ!!

No comments:

Post a Comment