ማሳሰቢያ-ይህንን ፅሑፍ በየትኛውም ድረ-ገፅ ላይ ማውጣት ይቻላል።ግን ምንጩን 'ጉዳያችን ጡመራ' መሆኑን መግለፅ ጨዋነት ነው።
በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ ከተካተቱት ንዑስ አርዕስቶች ውስጥ -
• የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣይ እርምጃ ምን መምሰል ይገባዋል?
• የኢትዮጵያ የቅርብ ወቅታዊ ተግዳሮት ምንድን ነው?
• የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ህዝብን የሚንጥ እና ሚልዮኖችን ከጎናቸው የሚያሰልፍ የፖለቲካ ራዕይ ለሕዝቡ ማሳየት ለምን አልቻሉም?
እና ሌሎችም...
መግቢያ
ኢትዮጵያን ውክፕድያ በድህረ ገፁ ላይ እንዲህ ይገልፃታል-''ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በአፍሪካ ነፃነታቸውን ጠብቀው ለመኖር ከቻሉ ሁለት አገሮች አንዷ ነች። በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ስትሆን፣ በቆዳ ስፋት ደግሞ አስረኛ ናት። ርዕሰ ከተማዋ አዲስ አበባ ናት።አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ዕድሜያቸው ከአንድ ምዕተ ዓመት የሚያንስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ ነገሥታት እና ንግሥተ ነግሥታት የተመራች ሀገር ናት። የሰለሞናዊው ሥርወ-መንግሥት የአመጣጡን ዘር እስከ አስረኛው ዓመተ ዓለም ድረስ ይቆጥራል። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የኖረባት ቦታ እንደሆነች ብዙ የሳይንሳዊ መረጃ ተግኝቷል። በበርሊን ጉባኤ በኩል የአውሮፓ ሀያላት ሀገሮች አፍሪካን ሲከፋፍሏት፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃለች። የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል ከነበሩት ሶስት የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ ነበረች። ከአጭር የኢጣልያ ወረራ ጊዜ በኋላም ከየተባበሩት መንግሥታት መሥራቾች አንዷ ናት። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ሲያገኙ፣ ሰንደቅ አላማቸውን በኢትዮጵያ ቀለሞች ማለትም በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ላይ ነው የመሠረቱት። አዲስ አበባ ደግሞ ለየተለያዩ በአፍሪካ ላይ ላተኮሩ አለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ሆነች።'' ይላል
ወግ አጥባቂ የአረብ መንግሥታት እና ፍላጎታቸው
የዛሬ ሰላሳ ሰባት አመት በምዕራቡ አለም የተከፈተው የቀዝቃዛው ጦርነት እጅግ በተፋፋመበት፣ የኢትዮጵያ አብዮት ተጠምዞም ይሁን በጥቂት የወቅቱ 'ልሂቃን' ለደርግ በቀረበ ሃሳብ ወደ ሶሻሊዝም ስርዓት ሀገሪቱን ለማስገባት በሚውተረተርበት፣በደቡብ ምስራቅ የሀገራችን ክፍል በወቅቱ ከሶቭየት ህብረት ባገኘው የመሳርያ ድጋፍ የተመካው የሱማልያ-ዚያድባሬ መንግስት የኢትዮጵያን መሬት በኃይል የወረረበት ወቅት ነበር።በእዚህ ጊዜ ነበር የ’ፋይናንሻል ታይምስ’ ጋዜጣ የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካ ከቀዝቃዛው ጦርነት በዘለለ እይታ የሚያመላክት አንድ ፅሁፍ ይዞ የወጣው። ፅሁፉ እንዲህ የሚል ነበር’’በወግ አጥባቂ የአረብ መንግሥታት በሳውድ አረብያ ቀንደኛነት በግብፅ፣ሱዳን እና ሶርያን ጨምሮ በቀይባሕር እና በአካባቢው ሃገራት የአረብ ወይንም የእስልምና መንግሥታት እንዲመሰርቱ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ።’’
’’the conservative Arab states, marshalled by Saudi Arabia and including Egypt, Sudan and Syria, want to create a band of Arab or Muslim states along the shores of the Red Sea and its approaches.'' (Financial Times May 2 1977)
የ ሶስት ሚልዮን ሕዝብ አናሳነት በፖለቲካ ስሌት አንፃር
ከሱማልያ ጎን ቆማ የቀዝቃዛውን ጦርነት ትዋጋ የነበረችው ሶቭየት ህብረት (የዛሬዋ ሩስያ) ከቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ መውረድ በኃላ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ ለማዞር አፍታም አልቆየችም።ለእዚህ ውሳኔ ካበቃት ጉዳይ አንዱ የኢትዮጵያ ስልታዊ ጠቀሜታ ዘለቄታዊ ጥቅሟን የሚያረጋግጥባቸውን ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነበር።እነኚህም ኢትዮጵያ በአካባቢው ያላት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ መካከል እንደ ድልድይ የምትጠቅም ብቸኛ መሬት መሆኗ እና በሕዝብ ብዛትም ሆነ በተፈጥሮ ሃብቷ ከአካባቢው ሃገራት የምታማልል መሆኗ ነበር።በሕዝብ ብዛት አንፃር ካላት ጠቀሜታ አንፃር ሶቭየት ህብረት ኢትዮጵያን እንደምትመርጥ የገለፀችበትን ሰነድ የሚያመላክተው አሁንም ከዛሬ ሰላሳ ሰባት አመት በፊት እ ኤ አቆጣጠር ግንቦት 14/1977 ዓም በሱማልያ የሶቭየት ህብረት አምባሳደር የተናገሩትን 'ዘ ኢኮኖሚስት' መፅሄት እንዲህ ፅፎት ነበር-''መንግስቱ ኃይለማርያም ጥሩ ልጅ ነው።ሶሻሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሸነፈ 30 ሚልዮን ወዳጆች በተጨማሪም የአሰብ እና ምፅዋ ወደብ ይኖሩናል።እናንተ ሱማሌዎች እኮ 3ሚልዮን ብቻ ናችሁ'' ነበር ያሉት።
‘Mengistu Haile Mariam is a good boy. If socialism wins in Ethiopia we will have 30 million friends there plus the ports of Assab and Massawa. You Somalis are only 3 million.’ (The Economist, May 14 1977)
እዚህ ላይ የ 3 ሚልዮን ሕዝብ አናሳነት በፖለቲካ ስሌት አንፃር ኢትዮጵያን ዛሬም ከአካባቢው ሀገሮች በበለጠ ባላት የህዝብ ብዛት እና የተፈጥሮ ሀብት በተለየ ተመራጭ ሀገር እንደሚያደርጋት አያጠራጥርም።እዚህ ላይ ይህንን ተመራችነቷን ለመጠበቅ እና እንደሀገር እንዳትቀጥል ከገዛ መንግስቷ የሚገዳደሯት ፈተናዎች የመኖራቸውን እውነታ ሳንዘነጋ ማለት ነው።
መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ
ይህ ከሆነ ዛሬ ሰላሳ ሰባት አመታት ተቆጥረዋል።በእነኝህ ሰላሳ ሰባት አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ አንድ ትውልድ አልፎ አዲስ ትውልድ ተተክቷል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ 30 ሚልዮን በሶስት እጥፍ ወደ 90 ሚልዮን ተተኩሷል፣የባሕር በሯ ተዘግቷል፣ወጥ የነበረው የመንግስት ስሪት በጎሳ እና ቋንቋ ላይ በተመሰረተ አስተዳደር ተቀይሯል፣ከተሞች በመጠን ሰፍተዋል።በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ከገጠሩ ጋር ሲነፃፀር ግን በእነኝህ ሁሉ ከ ሶስት አስር አመታት በኃላም ከ 90 በመቶ ወደ 85 (83) በመቶ ነው ዝቅ ያለው።የህዝቡ የኑሮ ደረጃ እ አ አቆጣጠር በ 1970 ዎቹ ነፃነታቸውን ከተቀዳጁት የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች አንፃርም ገቢው ዝቅተኛ የሚባል እና ከእጅ ወደ አፍ ነው።ከላይ የተጠቀሱት 'ፋይናንሻል ታይምስ' እና 'ዘ ኢኮኖሚስት' ፅሁፎች ሲወጡ በአፍሪካ ቀንድ የነበረን አማላይነት በምድር ጦር፣በአየር ኃይል እና በባህር ኃይል የነበረን የበላይነት የተገለፀ ሲሆን ዛሬ በሕዝብ ብዛት እና ዙርያችንን ያሉት የትናንሽ ደካማ ሃገራት መኮልኮል አጉልቶ ካሳየን የበላይነት ባለፈ መድረስ የሚገባንን ደረጃ አለመድረሳችንን ለማረጋገጥ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም።ባለፉት 37 አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የገጠማት ተግዳሮቶችን በሁለት መልክ ማስቀመጥ ይቻላል።እነርሱም የውስጥ ቁርሾ በአምባገነንነት መታገዝ እና የውጭ ግፊቶች ናቸው።የውስጥ ቁርሾው በተቻለ መጠን የሚቀልባቸው መንገዶች እንዳይኖሩ እልህ የተጋባው የአምባገነንነት እርምጃዎች በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ያክል ብዙዎች ሳያስቡት ቁርሾውን ለማባባስ ሰበብ እንዲሆኑ አደረጋቸው።ደርግ የእርስ በርስ ጦርነቶቹ በተቻለ መጠን ለማቅለል ከውስጥ የነበረበትን የህዝብ ድጋፍ ማጣት ስልጣንን ለሕዝብ በማስረከብ ሊያቀለው አልፈለገም።ይልቁንም ጦርነቶቹ የሰራዊቱን በሥራ መጠመድ ማምጣቱ የታያቸው ወገኖች እንደ መልካም እድልም ተመለከቱት።በዘመነ ኢህአዲግ/ወያኔ ደግሞ የውስጥ ቁርሾው በደርግ ዘመን ከነበረው የህዝብን ስልጣን ለሕዝብ ማስረከብ ብቻ ሳይሆን ''መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ላይ አደገኛ ጥላ አጠላ።የጎሳ ግጭቱ ከክልሎች የመሬት ግጭት አልፎ እስከ መንደር የከብቶች መሰማርያ ሜዳ ድረስ ኢትዮጵያውያን ተጋጩ።በእነኝህ የጎሳ ግጭቶች የተነሱ ፀቦችን ለማስቆም ዋናው ችግር ''የመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' መሰረት ያደረገውን የፌድራል ስርዓት በትክክለኛ የመሬት አቀማመጥ እና የህዝቦች ታሪካዊ አሰፋፈር መሰረት ያደረገ የፌድራል ስርዓት መቀየር መሆኑ እየታወቀ ኢህአዲግ/ወያኔ የተጋጩትን የጎሳ አባላት መዳኘትን እንደ ትልቅ ግብ እየቆጠረ በዜና እወጃው ላይ በስኬት ዜናነት ማውራቱን ቀጠለ።
የመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ መዘዝ ለአፍሪካውያን እየተረፋቸው ነው
የመንግስታዊው የጎሳ ፖለቲካ ውጤት ከሀገር ውስጥ አልፎ ለጎረቤት ኬንያ የእራስ ምታት የሆነባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ።ይህም ምን ያህል ኢህአዲግ/ወያኔ ''የፌድራ ስርዓቱ ለአፍሪካ ምሳሌ ሆነ'' እያለ የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ባዶ መሆኑን ያረጋግጣል። መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ ለቅርብ ኬንያ የየዕለት እራስ ምታት መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ዜና ነው።ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓ/ ም ኢሳት ዜና ለእዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው።ዜናው እንዲህ ይነበባል -’’በደቡብ ኢትዮጵያ የተፈጠረው የጎሳ ግጭት ድንበር ተሻግሮ ኬንያ ውስጥ የሚገኙ ጎሳዎችንም እያተራመሰ ነው ተባለ በደቡብ ኢትዮጵያ በቦረናና በገርባ ጎሳዎች መካከል ከግጦሽ መሬትና ከውሀ ጋር በተያያዘ በተነሳው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል።
ግጭቱ ወደ ኬንያም ተስፋፋቶ በአካባቢው የሚገኙ 17 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ታወቋል።
ከአካባቢው ርቀት አንጻር እስካሁን ድረስ የተጠናከረ መረጃ ባይቀርብም፣ በሞያሌ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደሚሉት በግጭቱ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ ብዙዎችም አካባቢውን እየለቀቁ ተሰደዋል።በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ ደግሞ በሶማሊ እና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል በቅርቡ የተፈጠረው ግጭት ፣ ዳግም ያገረሻል የሚል ፍርሀት መኖሩን የአካባቢው ነወራዎች ገልጠዋል።ሞያሌን የሶማሊ እና የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ከሁለት ከፍለው የሚያስተዳድሩዋት ሲሆን፣ በሁለቱ ብሄሮች ግጭት የከተማው ሰላም በተደጋጋሚ ሲደፈርስ ቆይቷል።
በቅርቡ ከትምህርት ቤት ንብረት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የፌደራል ፖሊሶች አሁንም አካባቢውን እንደተቆጣጠሩት ነው።’’ የዜናው መጨረሻ
በሌላ በኩል ከውጭ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ገብተው ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የመዘወር ግፊት የሚሰሩት ኃይላት ፍላጎት ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋብ ማለት በስተቀር ሌሎቹ ምክንያቶች ማለትም የአካባቢው እስልምና ተከታይ ሃገራት(ሳውዲ አረብያን ጨምሮ) በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸው ግብም ሆነ ተግባራት ምንም ለውጥ አላመጡም። ከእዚህ በተለየ የአለም ሃያላን መንግሥታት በሽብርተኝነት ጉዳይ፣በምጣኔ ሀብታቸው መዛባት እና ቻይና አዲስ አማራጭ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ በታዳጊ ሃገራት ላይ ያላቸው የበላይነት የመርገብ አዝማምያ አሳይቷል።ይህ መርገብ ግን ምናልባትም ከያዝነው አመት ጀምሮ ባለበት ላይቆይ ይችላል።የአራቱ የዓለም ኃይላት ማለትም የአሜሪካ፣የቻይና፣የአውሮፓ እና የሩስያ በግልፅ በወጣ የመገፋፋት ሂደት አለመኖር እና በተሸፈነ ዲፕሎማሲ ነገሮችን ማቀዝቀዛቸው ደካማ ሃገራት በጥቅማቸው ጉዳይ ላይ ከአንዱ ጋር የመቦደን ግዴታ ውስጥ እንዳይገቡ እረድቷቸዋል።ይህ ሁኔታ ግን እሰከመቼ ድረስ እንደሚዘልቅ የምናየው ይሆናል።በተለይ ከባድ የምጣኔ ሀብት ቀውስ መምጣት እና እጅግ በተሳሰረው የአለም ምጣኔ ሃብት አንፃር ከአራቱ ሃያላን አንዱ ወይንም ሁለቱ አልያም ሶስቱ ተነጥለው የመሄድ አዝማምያ ከመጣ የአለም የኃይል ቁርሾ ወደ 1970ዎቹ የማይወርድበት ምክንያት አይኖርም።ምናልባት ‘ሲ ኤን ኤን’ ''ቀዝቃዛው ጦርነት'' የሚለውን የቀድሞ ፕሮግራሙን ሰሞኑን እንደ አዲስ ልከልስልን የተነሳው በመጪው ላይ ያለው ስጋት አይሎበት ይሆን?
የኢትዮጵያ የቅርብ ወቅታዊ ተግዳሮት ምንድን ነው?
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ከ ሁለተኛው አለም ጦርነት አንስቶ እስከ 1980ዎቹ እ አ አቆጣጠር ተጋግሎ የቆየው የቀዝቃዛው ጦርነት ኢትዮጵያ ወደራሷ የችግር ፈቺነት አቅም ሳያሸጋግር ''ለመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' አስረክቧት ቀዘቀዘ።ቀድሞ በምዕራባውያን ትምህርት የተዋከበው የእድገት ስልት ቀጥሎ በመጣው በደርግ ሶሽያልስታዊ አስተሳሰብ ተተራምሶ ከዛሬ 22 አመት ገደማ ደግሞ በ''መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' ቅርፁም ሆነ ይዘቱ ትውልድ አሻጋሪ እንዳይሆን ሆነ።ዛሬ የምዕራባውያን ''ሌክቸር'' መሰል አመራርም ሆነ የሶሻልስቱ አለም የማያላውስ ቀጭን ትዛዝ የኢትዮጵያ እራስ ምታቶች አይደሉም።የአካባቢ የአረብ መንግሥታት ግፊት ግን የቅርብ እና ከባድ የኢትዮጵያ ተግዳሮት ነው።ከኢህአዲግ/ወያኔ በፊት የነበሩት መንግሥታት በማዕከላዊነት ይዘውት የነበረውን የሀገር ጉዳይ በጎሳ ስለሸነሸነው ለአካባቢ ''ኢትዮጵያን አረብ ማድረግ አለብን'' እንቅስቃሴዎች እጅግ አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።ኢትዮጵያን አረባዊ የማድረጉ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁር ህዝቦች ላይም የተሞከረ እና የታቀደ ይልቁንም እስልምናን ከሃይማኖት ይልቅ ፖለቲካዊ ጥቅሙን ብቻ ነቅሶ የመንቀሳቀስ አላማ የያዘ ነው።
ኢትዮጵያን አረባዊ (እስላማዊ ሀገር ) በማድረግ ሂደት ላይ በጉልህ የተሳተፉ ውስጣዊ ኃይላት አሉ።እነርሱም-
1/ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስ እና ‘ፅፈኛ አጋር’ ተብዬ የጎሳ ድርጅቶቹ
2/ ኢህአዲግ/ወያኔን እንቃወማለን የሚሉ ግን የመገንጠል አላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለምሳሌ የ ዑጋዴን ነፃነት ግንበር የመሳሰሰሉ ናቸው።
እነኝህ ኃይላት የተለያዩ ይምሰሉ እንጂ ያጣላቸው የበላይ ለመሆን የሚደረግ ግፍያ ካልሆነ በቀር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው።ለምሳሌ ትግራይን የመገንጠል አላማ ይዞ በፕሮግራሙም አካቶ ይንቀሳቀስ የነበረው ህወሓት ዛሬም መንግስት ከሆነ በኃላም የቀድሞ የጎሳ ስሙን ካለመቀየሩም በላይ ለስልጣን ያበቃቸው አጋር ድርጅቶቹ ባብዛኛው በአንድም ሆነ በሌላ ኢትዮጵያን አረባዊ (እስላማዊ) ለማድረግ ከሚሹ ኃይላት በተገኘ የስልጠና፣የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረቱ ናቸው።ይህ ድጋፍ ዛሬም ድረስ እያገኙ ነው።
እነኝህ ኃይላት አላማቸውን ለማስፈፀም የሚሞክሩት እና የሚተገብሩት በአፈሙዝ ነው።ይህ ማለት በሌላ አገላለፅ መጭውም የፖለቲካ መድረክ የሚስተናገደው በአፈሙዝ ስልጣን ላይ የሚወጣ የሚደመጥበት ነው ማለት ነው።አሁንም ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አልታደልንም ማለት ነው።በእዚህ ሁሉ ውጥንቅት ውስጥ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነበረው አካሂድ ምን መምሰል ይገባዋል?
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣይ እርምጃ ምን መምሰል ይገባዋል?
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግርም ሆነ ወደ ነፃነት እና ዲሞክራሲ የሚደረገው ጉዞ በሁለት ጉዳዮች የተወጠረ ነው።እነኝህ ሁለት ጉዳዮች ላይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ግልፅ እና ጥርት ያለ መስመር ማሳየት አለባቸው።ይህ መስመር ዛሬ ያለውን ጥቂቱን ወይም ብዙውን ያስከፋል ወይንም ያስደስታል ከሚል አንፃር ሳይሆን መሰመር ያለበት መጪውን ዘመን ያገናዘበ ብሎም አዋጪ እና አማራጭ መስመር ከመሆን አንፃር ብቻ መታየት ይገባዋል።እነኝህ ሁለት ጉዳዮች-1/ ባለፈ ታሪክነት ማንነት ላይ የጠራ አቋም ማሳየት
2/ ከባለፈ ታሪክ፣ባህል፣ማንነት፣ከአሁኑ እና ከመጪው ትውልድ ማንነት አንፃር ወደፊት ሊኖር ስለሚገባው የመንግስት ቅርፅ በግልፅ ማሳወቅ
1/ ባለፈ ታሪክነት ማንነት ላይ የጠራ አቋም ማሳየት
የኢትዮጵያን ያለፈ ታሪክ በአንድ ገላጭ አረፍተ ነገር ሊጠቃለል ወይንም ይህንን ከማለት ውጭ ይህንን ማለት አይቻልም የሚል አስተሳሰብ የሚራመድበት ወቅት ላይ አይደለንም።በሌላ በኩል ደግሞ በድፍኑ የጋራ የሚያደርገንን ታሪክን እንደምናምን ቆጥሮ በዝምታ እና በብዥታ መቀጠልም ህዝብን ከሚመራ የፖለቲካ ኃይል የሚጠበቅ አይደለም።ይህ ያለንበት ወቅት የአንድን የፖለቲካ ድርጅት ባለፈ ታሪክ ላይ ያለው አመለካከት በራሱ የፖለቲካ ፓርቲውን የወደፊት ራዕይ የሚያመላክት ያክል እንደማሳያ እየሆነ ለመምጣቱ ብዙ ማሳይዎችን መጥቀስ ይቻላል።እዚህ ላይ ትልቁ ጉዳይ ዛሬ ያለው ትውልድ ስለአለፈው በጎም ሆነ በጎ ያልሆነ ታሪክ ቅንጣት ታክል ተጠያቂ ሊሆን አይችልም።እርሱ የሚጠየቀው ዛሬ በሚሰራው እና ነገ ሊሰራ ስለሚያስበው ታሪክ ነው።በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እና ታሪክን ተመርኩዘው ነገን በሚማትሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ሁለት አይነት ስሜቶች ይንፀባረቃሉ።
አስተሳሰብ አንድ - የባለፈው ታሪክን በዛሬ መነፀር የሚመለከት
የመጀመርያው ክፍል ባለፉት ዘመናት የተደረጉትን ታሪካዊ ሁኔታዎች ዛሬ 21ኛው ክ/ዘመን ላይ ሆኖ ለመገምገም የምፈልገው ነው።የዛሬ 600 አመት አፄ ዘርያቆብ ለምን እንዲህ አላሰቡም? እንዴት እንዲህ ይላሉ? እያለ በወቅቱ የነበረውን ስነ-ልቦና የማኅበረሰቡን ባህል፣እምነት እና ወግ ሳያጠና እንዲሁ ለዛሬ የኢትዮጵያ እሷነት መነሻ ሰበብ ሲፈልግ ከድሮ ታሪክ ጋር እያዛመደ መማሰን ሙያ ተብሎ ተይዟል።ይህ ክፍል ትልቁ ግቡ ስልጣን ነው።ስልጣን ለመያዝ ደግሞ ዛሬም ሆነ ነገ እንቅፋት ይሆኑኛል የሚላቸው ሁለት ''ደንቃራዎች'' ከፊቱ ይታዩታል። እነርሱም- በረጅም ዘመናት የተገነባው ያለፈው እና አሁን በሕዝቡ ልብ ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊነት ነው።ይህ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ባለፈ ማንነት፣ታሪክ፣ባህል እና እምነት ላይ የተመሰረተ ነው።ስለዚህ ዛሬ ሰበብ አስባብ ፈልጎ ያለፈ ማንነትን የሚንዱ ናቸው ያላቸውን የህዝብ ግጭቶችን፣በነበሩበት ጊዜ ጀግና ያስብሉ የነበሩ በ 21ኛው ክ/ዘመን ግን ክፉ ተግባራትን እና ፈፅመው የሌሉ ታሪኮችን በመፍጠር የኢትዮጵያዊነት መሰረቶች እንዲናዱ ይሞክራል።
ለምሳሌ የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ እና ፌድራሊዝም አስተዳደሮች በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ባልተፈጠሩበት ዘመን ለምን አልታወጁም ነበር? በሚል ውኃ ቀጠነ ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ይሳደባል።ይልቁን ፌድራልዝም በአለም ሳይታወቅ እነ አባ ጅፋር የራሳቸውን ግዛት በራሳቸው ያስተዳድሩ እንደነበር ግን በጋራ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በሚያገናኛቸው ጉዳይ ላይ አብረው ይሰሩ እንደነበር አያስተውልም።በዚህ ክፍል ውስጥ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስትን ጨምሮ በፅንፈኛ የእስልምና እምነት የፖለቲካ አላማቸውን ለማሳካት እስከሚፈልጉት ኃይሎች ድረስ የባለፈውን ታርክ በዛሬ መነፀር እያዩ ህዝብን ማደናገር እና የዛሬውን ትውልድ በማያውቀው ጉዳይ አበሳውን ሲያሳዩት መመልከት የተለመደ ነው።አሁን ባለንበት ዘመን በእዚህ አስተሳሰብ ሺዎች ተገለዋል፣ሌሎች አያሌ ሺዎች ከመኖርያቸው ተፈናቅለዋል።ከእዚህ ሲዘል ደግሞ ማስረጃ ለሌለው ተረት ሁሉ ሃውልት ይሰራ ባይ ነው። የእዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ዋና ግባቸው ''እኛ ስልጣን ላይ ከሌለን እና የምንፈልገውን ካልፈፅምን ጭር አይልም ባዮች ናቸው።ለእዚህ እኩይ ተግባር የምተባበራቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል ጋር ለመተባበር ዝግጁ ናቸው።ኢትዮጵያዊነት፣አንድነት እና ህብረት ሲጠነክር ይደነግጣሉ።ምክንያት የእነርሱ አስተሳሰብ በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ፊት ሞገስ እንደሌለው እና እነርሱንም ወደ ስልጣን ኮርቻ ላይ እንደማያፈናጥጣቸው ይረዳሉና።
አስተሳሰብ ሁለት - የባለፈው በጎውን ይዘን ክፉውን ወቅሰን ያሁኑን ትውልድ ተጠያቂ ሳናደርግ ለወደፊቱ እናስብ
ሁለተኛው አስተሳሰብ የብዙ ኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ነው።ኢትዮጵያ በአንድ ምሽት በቤተ-ሙከራ ውስጥ የተሰራች ሀገር አይደለችም።የብዙ ዘመናት የህዝቦቿ አብሮ የመኖር፣የመተሳሰብ፣የመሰደድ፣የጦርነት፣የሰላም ሁሉ ውጤት ነች።ባለፈው ታሪካችን ብዙ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች አሉ።ብዙ የዛሬ ማንነታችን ላይ አሻራ ያላቸው ማንም በቀላሉ እንዲነቅላቸው የማይፈቀዱለት የጋራ ታሪክ አለን።በአንፃሩ ደግሞ የሚያሳዝኑ ታሪኮች ባለቤትም ነን።ዛሬ የሚያስፈልገን ያለፈው አንድ የሚያደርጉንን አጉልተን ባለፈው ለተሰሩት ስህተቶች ምንም ተጠያቂ ባንሆን ወደፊት እንዳይሰሩ አርመን መኖር ብቸኛ አማራጫችን ነው።ከእዚህ በዘለለ ባለፈ አሳዛኝ ታሪክ ሊሽር የሚችለው በዛሬው ትልውድ በጎ የታሪክ ተግባር ነው ብለው ያምናሉ።
አሁን በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የሚታዩት አስተሳሰቦች ከላይ ከተጠቀሱት ከሁለቱ አንዱ እንደሆኑ ይታወቃል።የኢትዮጵያ ሕዝብም የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያላቸውን ግልፅ አስተያየት እና ይህ እይታቸው የነገውን የሀገራችንን መፃኢ ዕድል ማሳያ እንደሆነ አመላካች ነው።ኢትዮጵያ ነገ እንዴት እንድትሆን እንደሚፈልጉ ሁሉ የባለፈው ዕይታቸውም በግልፅ መቀመጥ ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ከባለፈ ታሪክ፣ባህል፣ማንነት፣ከአሁኑ እና ከመጪው ትውልድ ማንነት አንፃር ወደፊት ሊኖር ስለሚገባው የመንግስት ቅርፅ በግልፅ ማሳወቅ
አሁን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ፣በሰላማዊ ትግልም ሆነ በትጥቅ ትግል ላይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ የጋር ነጥብ እና አሰልቺ ቋንቋ አለ። ይሄውም ''ዲሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት'' ይመሰረታል የሚል ነው።ደርግም ሆነ ኢህአዲግ/ወያኔ ''ዲሞክራሲያዊ'' ያሉትን መንግስት ኢትዮጵያ እንዳጣጠመች ነግረውናል።ነገም ይህንኑ ተረኛው ስደግምልን መስማት ምንኛ ዘግናኝ ታሪክ መሆኑን ለአፍታም ማሰብ ይከብዳል።የብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰረታዊ ችግር እና ሚልዮኖችን በአጭር ጊዜ ማሰለፍ ያልቻሉት ነገ የሚመሰርቱት መንግስትን በደፈናው ''ዲሞክራሳዊ'' ከማለት ባለለፈ መልክ አሁን ያለውንም ሆነ መጪውን ትውልድ የሚያማልል የኢትዮጵያን ታሪካዊ ዳራ ያገናዘበ ብሎም ነገ ተመንጥቃ የምታድግበትን አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ አልቻለም።ኢህአዲግ/ወያኔ በትጥቅ ትግል ላይ ሳለም ይህንን ማድረግ አልቻለም ነበር።ግን ያስቀመጠው አንድ ሕዝቡን ያማለለ ጉዳይ ነበር ይሄውም ደርግ ይገረሰሳል የሚል ራዕይ ነበር።
ራዕይ ያሸፍታል፣ራዕይ ካላገኙት በቀር እረፍት ይነሳል፣ ራዕይ አያስበላም፣አያስጠጣም፣ዛሬን በጨለማ ያሳያል ነገን ግን በብሩህ ብርሃን አንቆጥቁጦ ያሳያል።የፖለቲካ ራዕዩን በትክክል የገለፀ እና ያ ራዕይ ደግሞ የሕዝብ ስስ ብልትን የነካ ሲሆን ሚልዮኖችን ያነቃንቃል፣ይፈነቅላል፣ሺ መትረጌስ ቢደገን ተራምዶት ይሄዳል።በትክክል የተቀመረ የፖለቲካ ራዕይ እንዲሁ ነው።ከእዚህ በተለየ ''ዲሞክራሲያዊ'' መንግስት ይመጣል በሚል ንግግር የትም አይደረሰም።በ 1997 ምርጫ ቅንጅት የሰራው ተአምር ይህ ነው።የራሱ ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር ሳይኖረው የህዝቡን ሥሥ ብልት የሚነካ ጉድለቱን የሚሞላ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ራዕይ ብልጭ አደረገ በአንድ ቀን ሚያዝያ 30/1997 ዓም ሰልፍ ብቻ በአዲስ አበባ ከ አንድ ሚልዮን ሕዝብ በላይ ደግፎት ተሰለፈ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ህዝብን የሚንጥ እና ሚልዮኖችን ከጎናቸው የሚያሰልፍ የፖለቲካ ራዕይ ለሕዝቡ ማሳየት ለምን አልቻሉም?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ላይ ይስተዋላል። አንደኛው የአመሰራረታቸው ሂደት ችግር ሲሆን ሁለተኛው የሕዝቡን ባህል፣እምነት እና ታሪክ ያገናዘበ ፕሮግራም ለማስተዋወቅ ድፍረት ማጣት ናቸው።
ሀ/ የአመሰራረታቸው ሂደት ችግር
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን በሰላማውም ሆነ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉት መካከል ነገ ሊያመጡልን ይችላሉ በምንላቸው በጎ ነገሮች ላይ አንዳቸውን ካንዳቸው የምንለይበት ነጥብ ካጣን ቆይተናል።ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመሰረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና እና ብቸኛ ችግር የዲሞክራሲ እጦት ችግር ብቻ ነው በሚል ትምህርት ቤት በተማሩት የምዕራቡ ፍልስፍና መግባብያነት ብቻ ይመሰረታሉ ወደ ትግል ይገባሉ።ኢትዮጵያን የሚያህል ከሶስት ሺህ አመታት በላይ የመንግስት ስሪት ያላት ሀገር ግን ችግሯ የዲሞክራሲ ብቻ ሊሆን አይችልም።የማንነት መከበር፣በራስ ላይ ተመስርቶ የመፍጠር ክህሎት ማሳየት፣የራሷ የሆኑ የፖለቲካ ፍልስፍና እና ምጣኔ ሃብታዊ ተምኔቶች ማሳየት እነኝህ ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንገዱን በተጠና እና ሊደረስበት በሚችል ራዕይ ለሕዝቡ እንዲያሳዩ ተደርገው አልተመሰረቱም።ለእያንዳንዱ ወቅታውም ሆነ የቆየ የሀገራችን ችግር ''የዲሞክራሲ እጦት'' ነው ችግሩ እያሉ ህዝብን ማዘናጋት ለማንም አይበጅም።
ለ/ የሕዝቡን ባህል፣እምነት እና ታሪክ ያገናዘበ ፕሮግራም ለማስተዋወቅ ድፍረት ማጣት
ይህ ችግር ከመጀመርያው ከአመሰራረት እና ችግርን ከዲሞክራሲ ጋር ብቻ በማያይዝ ላይ በተመሰረተ የፖለቲካ ፓርቲ አንፃር የሚከሰት ይልቁንም ፕሮግራሙ እራሱ ይህኛውን ቡድን እዳያስከፋ፣ያኛው እንዲደግፍ ወዘተ በሚል ፍርሃት የተሸበበ ማዕከላዊ መንገድ የያዘ ፕሮግራም ለመፈለግ የሚታታር አካህያድ ውጤት ነው።የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝቡን ባህል፣እምነት እና ታሪክ ያገናዘብ የፖለቲካ ፕሮግራም ማንንም ከፋው ወይንም ደስ አለው ሳይሉ በእውነታው ላይ ተመስርተው እንዳይቀርፁ የሚፈሯቸው ያለፉት 40 አመታት የሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ክስተትን ነው።ኢትዮጵያ በመንግሥትነት የኖረችው አሁንም ልድገመው ላለፉት 40 አመታት አይደለም ለ ሶስት ሺህ አመታት ከዛም በላይ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራሞች ሲቀረፁ ካለምንም ማጋነን መሰረት ያደረጉት ያለፉት 40 አመታት የአለማችንን እና የሀገራችንን የፖለቲካ የተደጋገመ እና አሰልቺ ቋንቋ ነው።የኢትዮጵያ ስነ-መንግስት ታሪክ ግን ሰፊ፣ትልቅ እና ለቀሪው አለም ብዙ ቁም ነገሮችን ያበረከተ ነው።ለሙሴ አስተዳደርን ያስተማረ ኢትዮጵያዊው ዮቶርን የሚያስበው የለም።መገናኛ በሌለበት ዘመን የኢትዮጵያ የስነ-መንግስት ጥበብ መዋቅሩ ምን እንደነበር ሊመለከት የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ የለም።አውሮፓ እና አሜሪካ የተፃፉ መፃህፍትን ግን ለመጥቀስ የምያክለን የለም። ለአለም ልዩ ልዩ መንግሥታት ሕጎች የኢትዮጵያ 'ፍትሃ ነገስት' በምን መልክ ለግብአትነት አውሮፓውያን እንድተጠቀሙበት ሊመረምር የሚፈልግ የለም።ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባው መንግስት ሕዝብ ሊታገልለት እና ሊሞትለት የሚችለው ልዩ ጥበብ እኛው ጋር እንደተደበቀ ለሕዝቡ ገልፆ ካለፍርሃት ሊነገረው፣ሊመራው እና ለእድገት ሊያበቃው የሚችል ጥበብ እንደሚያስፈልገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ካላሰቡ ዛሬ የአስተሳሰብ ለውጥ የማመንጫ ሰዓት ላይ ይመስሉኛል። ከእዚህ በኃላ ኢትዮጵያውያን የምሸከሙት የመከራ ጫንቃም ሆነ የአስተሳሰብ ድግግሞሽ ጆሮ ያላቸው አይመስለኝም።
ባጠቃላይ
የኢትዮጵያ የመንግስት ስሪት ቅጥ ባጣ አምባገነኖች እጅ ከወደቀ አስርተ አመታት አስቆጠረ።ይብሱን ዛሬ ሀገራችን ሕልውናዋን በሚፈታተን ''መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' ውስጥ ተነክራ ህዝቧ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ውስጥ ይገኛል።ታሪካዊ ጠላቶቿ የዛሬ 40 አመት የደገሱትን ድግስ ዛሬም አልቀየሩም።ኢትዮጵያን አረባዊ ለማድረግም ሆነ የፅንፈኛ እስልምና አላማ ያነገቡ ኃይሎችአንዴ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ሌላ ጊዜ ባለፈ ታሪክ ስም እያሉ የሚፈልጉትን ግብ ለማድረስ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ነው።የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስትም እንደ ማስፈራርያ ወጥ በብዙ መልኩ ድጋፉን ሲሰጣቸው እና ''ከእኔ ጋር ከልሆናችሁ አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል'' እያለ ሲያስፈራራን ዘመናት አልፏል።አቦይ ስብሐት ይህንን ጉዳይ ደጋግመው ለተለያዩ የዜና አውታሮች ገልፀውታል።
የህወሓት ፈጣሪው አቦይ ስብሐት አንድ ወቅት ለኢሳት በሰጡት ዘገባ ላይ '' ማንም በኃይል ስልጣን ሊይዝ አይችልም።ከሆነ ሌላው ክልል የራሱ ምክርቤት፣በጀት ወዘተ አለው የራሱን አማራጭ ይወስዳል።ስልጣን የሚይዝ ኃይል አዲስ አበባን ብቻ ይዞ ይቀመጣል እንዴ?'' በማለት ከኢህአዲግ በኃላ ኢትዮጵያ እንደምትበታተን ሁሉም የእራሱን መንግስት እንደሚያውጅ በተዘዋዋሪ ነግረውናል።አቦይ 22 አመት ቆይተው ሕዝቡን አለማወቃቸው አይደንቅም።
ቁም ነገሩ ግን ይህ አይደለም የአቦይ ንግግር የሚያመለክተው ኢህአዲግ/ወያኔ ኢትዮጵያን እየስራት ያለው ከእርሱ ውጭ እንዳትኖር ''እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል'' መርህ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ነው።እዚህ ላይ ነው የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች የህዝቡን ያለፈ ታሪክ፣እምነት፣ባህል እና ጥበብ ያገናዘበ አዲስ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብታዊ ራዕይ የሚያሳይ ፕሮግራም (''ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ'' ከሚል መዝሙር ባለፈ) ማሳየት ያለባቸው።
በመሆኑም የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች እና ፓርቲዎች አዲስ እና ባለ ራዕይ ፕሮግራማቸውን በተናጥል ወይንም ግንባር በመፍጠር አዲስ መንፈስ በመፍጠር ማሳየት ይገባቸዋል።ይህ አዲሱ ሀሳባቸው ኢትዮጵያን በጎሳ እና በፅንፈኛ የእስልምና አስተሳሰብ ለመምራት የሚፈልጉትን ለማቀፍ አይድከም።እነኝህን ኃይሎች በሚቃረን መልኩ የህዝቡን የልብ ትርታ ባዳመጠ እና የማይረገጥ የመሰላቸውን በመርገጥ ለድል ይበቃሉ።ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በአንድነት ኃይሎች እና በበታኝ ኃይሎች ጎራ ተከፍሏል።ከአንድነት ኃይሎች ጎራ የዲሞክራሲ ጉዳይ ብቻ ሲለፈፍ ከበታኝ ኃይሎች በኩል ደግሞ የጎሰኝነት እና የፅንፈኛ እስልምና አስተሳሰቦች ይንፀባረቃሉ።አሁን ጥያቄው የአንድነት ኃይሎች ኢትዮጵያዊ ታሪክ፣እምነት እና ፍልስፍና የያዘ ጥበብ የተላበሰ ራዕይ ይዘው መውጣት እና ሕዝቡን ከአዙሪት 'ዲሞክራሲ' ከሚል ዲስኩር ማላቀቅ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ዲሞክራሲ አያስፈልገውም እያልኩ አይደለም።የህልውናው ጥያቄ ሲመጣ ግን ኢትዮጵያን በሁለት እግር የሚያቆም እና የሚያራምድ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፍልስፍና በእጅጉ ተርቧል።ያን ጊዜ በኩራት እና በድፍረትይነሳል።በእዚህም አያቆምም የበታኝ አስተሳሰብ የተጠናወታቸውን በምክርም በግሳፄም ያስተካክላል።የሩቅ ጠላቶቹን ያሳፍራል።የሚፈለገው ልማት እና እድገትም በራሱ ጊዜ መስመር ውስጥ ይስገባዋል።ከእዝያ በኃላ ማን ያቆመናል?
አበቃሁ
ጉዳያችን ጡመራ
ጌታቸው በቀለ
ጥር 5/2006 ዓም
ኦስሎ፣ኖርዌይ
ይህንን ፅሑፍ በየትኛውም ድረ-ገፅ ላይ ማውጣት ይቻላል።ግን ምንጩን ጉዳያችን ጡመራ መሆኑን መግለፅ ጨዋነት ነው።
No comments:
Post a Comment