Tuesday, January 21, 2014

የኢዜአ ማደናገሪያ ዜና – አንድ ተጨባጭ ምሳሌ


ታደሰ ብሩ
በቅድሚያ የሚከተለውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) ዜና አጣጥሙልኝ።
ጎባ ጥር 10/2006
በባሌ ዞን   ከእርሻ ስራ በተጓዳኝ በንብ ማነብ ፓኬጅ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ከ53 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘታቸውን የዞኑ የእንስሳት ሀብት ልማትና ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በጽህፈት ቤቱ የእቅድና ግምገማ በለሙያ አቶ ታዬ ኣጋ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የማር ምርቱን ለአካባቢው ገበያ ያቀረቡት ከ89ሺ 200 የሚበልጡ አርሶ አደሮች ናቸው ።
የማር ምርቱን ለአካባቢያቸውና ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል ከ21 ሺህ 699 የሚበልጡት ሴቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል ።
በዞኑ ዘጠኝ ደጋማ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች የማር ምርቱን የሰበሰቡት ከ100ሺ ከሚበልጡ ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በመጠቀም እንደሆነ አብራርተዋል ።
በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለገበያ የቀረበው የማር ምርት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1ሺህ ኪሎ ግራም ብልጫ ያለው እንደሆነም አስታውቀዋል ።
ጽህፈት ቤቱም የዞኑን አርሶ አደሮች የማር ምርትና ምርታማነት በሁለት እጥፍ ለማሳደግ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሮቹ በማሰራጨት ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል ።
ይህንን ዜና  እዚህ ያገኙታል።
ዜናውን በጥንቃቄ ያላነበበ ሰው የተለመደ ልማታዊ ዜና በመሆኑ ምንም የሚያስደንቅ ነገር አያገኝበትም። ሆኖም ትንሽ ስሌት ብጤ እንጨምርበት።
ሀ.  ከሽያጭ የተገኘው ገንዘብ 53.7 ሚሊዮን:   ብር 53, 700, 000
ለ.  የአምራቾቹ ብዛት:                          89, 200 ገበሬዎች
ሐ.  የፈጀባቸው ጊዜ:                           6 ወር
ከዚህ በመነሳት የሚከተለውን ማስላት ይቻላል።
የአንድ አምራች አማካይ የሽያጭ ገቢ:           53, 700, 000  ÷ 89, 200 = ብር 602.02
የአንድ አምራች አማካይ ወርሃዊ የሽያጭ ገቢ:    602.02/ 6 = ብር 100.34
በዚህ “ድንቅ ስኬታማ ፓኬጅ” አንድ ገበሬ በወር በአማካይ የሚያገኘው የሽያጭ ገቢ ብር 100.34 ነው። በአማካይ ማለት ደግሞ ከዚህም በታች የሚያገኙ ብዙ አሉ ማለት ነው። በተለይ አንድ ብርቱ “ልማታዊ” ገበሬ ካለ የሌሎቹ ሰብስቦ ነው የሚወስደው። ለማንኛውም ግን የገበሬዎች ምርታነት እኩል ነው ብለን እናስብና ስሌታችንን በአማካይ እንቀጥል።
አንባቢ እንደሚያውቀው የሽያጭ ገቢ የተጣራ ገቢ (ወይም ትርፍ) አይደለም። ገበሬዎች ከዚህ ፓኬጅ ምን ያህል እንደተጠቀሙ ለማስላት ወጪያቸው መሰላትአለበት። ከዜናው በመነሳት በአዕምሮዓችን የሚመጡ ወጪዎች የሚከተሉት ናቸው።
  1. እያንዳንዱ ገበሬ በአማካይ በወር ምን ያህል ሰዓታት በዚህ ሥራ ላይ አዋለ?
  2. “ከ100ሺ ከሚበልጡ ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች” በሥራ ላይ ውለዋል። የእነዚህ ቀፎዎች የእልቀት ዋጋ (depreciation) በወር  ምን ያህል ነው?
(በነገራችን ላይ ይኼ ራሱ ሌላ ዜና የሚወጣው ነገር ነው። በአገሪቱ ትልቁ የዜና አገልግሎት በትላልቅ ፎንት ዜና የሠራለት “ፓኬጅ” ለአንድ ገበሬ በአማካይ ሁለት ቀፎ እንኳን ሳያቀርብ ነው።  ለ 89,200 ሰው 100, 000 ማለትም በአማካይ ለአንድ ገበሬ 1.12 ቀፎ ነው!)
  1. ማሩ በምን ታሸገ? (ስልቻም ከሆነ የስልቻው ዋጋ)
  2. ማሩ በምን ተጓጉዞ ገበያ ደረሰ?
የገበሬን ድካም ለሚያውቅ ወጪዎቹ እነዚህ ብቻ እንደማይሆኑ ይረዳል፤ ግን ይብቃኝ።
ይህንን ሁሉ ስናስብ ነው ዜናው እጅግ አስገራሚ የሚሆነው።  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜና አቀራረብ ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን አንባቢን ያሳፍራል። ይህንን ዜና ሳነብ የተሰማን ስሜት እፍረት ነው። ይህ ነው የኢዜአ ልማታዊ ጋዜጠኝነት!!!
የኢዜአ ስኬትን የማጋነን ፍላጎት፤ ማለትም የተገኘው ገንዘብ እና በፓኬጁ የተሳተፉ ገበሬዎችን ብዙ አድርጎ የማቅረብ ፍላጎት፣ ብዙ ሲካፈል ብዙ ትንሽ የሚሆን መሆኑ ያስረሳው ይመስለኛል።
ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም
ፀሐፊውን ለማግኘት tkersmo@gmail.com

No comments:

Post a Comment