Sunday, January 12, 2014

ሻምበል ጉታ ዲንቃ፤ ጊዜውን ጠብቆ ይነጋል (ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም)


ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
በአሁኑ ጊዜ ወያኔ ሰውን እያፈረሰ፣ ማህበረሰብን እያፈረሰ ሰማይ-ጠቀስ ሕንጻዎችን በሚሠራበት ጊዜ፣ ከትናንት ወዲያ የሰዎችን ቤቶች አፍርሶ ትናንት የመኪና መንገድ ከሠራ በኋላ ዛሬ መንገዱን አፍርሶ የባቡር መንገድ እየተሠራ አዲስ አበባ በትራፊክ መጨናነቅ መኪና መንዳት አደገኛ በሆነበት ጊዜ፣ ዛሬ ባለሥልጣኖች የሚሠሩት ጠፍቶአቸው የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የሚባለውን በአማካሪዎች ከሞሉት በኋላ ለሚኒስትሮችም አማካሪ መሾም በተጀመረበት ጊዜ፣ ዛሬ በሳኡዲ አረብያ ኢትዮጵያውያን እንደአደገኛ አውሬ እየታደኑ በሚደበደቡበት፣ በሚታሰሩበት፣ በሚደፈሩበትና በሚገደሉበት ጊዜ፣ ዛሬ በኬንያና በዩጋንዳ እንዲሁም በእሥራኤል ኢትዮጵያውያንን የማንገላታት ዝንባሌዎች በሚታዩበት ጊዜ፣ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከስዊድን እስከአውስትራልያ እየተሰበሰቡ በመጮህ ለማይሰሟቸው ሁሉ አቤቱታቸውን በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ዛሬ በተለያዩ አገሮች በኢትዮጵያውያን ላይ በሚፈጸመው ጥቃትና በደል፣ አለሁላችሁ የሚል መንግሥት በሌለበት ጊዜ —- ዛሬ ታሪካዊትዋ ኢትዮጵያ፣ ራሳቸውን የሚያከብሩና ኩራት ራታችን የሚሉት ኢትዮጵያውያን አልቀው ለሆድ በየሰው አገር መሰደድ ባህል በሆነበት ጊዜ፣ ዛሬ ዶር. በድሉ ዋቅጅራ ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያውያን ውርደት ደጋግሞ የነፍሱን ኡኡታ ባሰማበት ጊዜ በድንገት አንገታችንን ቀና አድርጎ ኩራታችንን ሊያስጎነጨን የሞከረ ሰው ተገኘ! ኢትዮጵያ ሁሌም የተአምር አገር ነች።Capitain Guta Dinka an Ethiopian soldier, responsible for Madiba's safety during his stay
በታላቁ ሰው በኔልሰን ማንዴላ እረፍት ምክንያት አንድ ተደብቆ የኖረ ክቡር ኢትዮጵያዊ ብቅ አለ፤ ማንዴላ ለሥልጠና በኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜ ምናልባትም እንግሊዞች ማንዴላን ሊያስገድሉ ከጠባቂዎቹ አንዱ የነበረውን ወታደር በገንዘብ ገዝተው ዓላማቸውን ለመፈጸም አቅደው ነበር፤ ወታደሩ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ሀሳቡን ለውጦ ገንዘቡን ለአለቃው ሰጠ፤ ማንዴላ ከሞት ተረፈ፤ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ራሱንና አገሩን የሚያስከብር ሥራ ሲሠራ የሚኮሰኩሳቸው ባለሥልጣኖች ለእነሱ የማይተላለፍ ክብር በመሆኑ ተዳፍኖ እንዲኖር አደረጉት፤ እነሱ ሞተው ወይም ተሰድደው ሲያልቁ የተዳፈነው ምሥጢር ብቅ አለ፤ ባለሥልጣኖቹ ሸልመውት ይሆናል፤ ግን አላከበሩትም፤ ሻምበል ጉታን ያከበረው የማንዴላ ሞት ነው፤ የሚያሳዝነው ማንዴላ ይህንን የሱን ሕይወት ለማትረፍ ሁለት ሺህ ፓውንድ ያጣውን ኢትዮጵያዊ ወታደር ሳያውቀው መሞቱ ነው።
የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪካቸው ተቀብሮ የቀረው እንዲህ እየሆነ ነው፤ ታዴዎስ ታንቱ ሥራዬ ብሎ የተረሱ አርበኞችን ከመቃብር እያወጣ ያስተዋውቀናል፤ በሌሎች አገሮች እንደዚህ ለአገር ትልቅ ፋይዳ ያለው ሥራ በአንድ ሰው በበጎ ፈቃድ የሚሠራ ሳይሆን ዋና የመንግሥት ተግባር ነው።
ሻምበል ጉታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባይሆንም ራሱን ችሎ ለኔልሰን ማንዴላ መቃብር ደርሶአል፤ በአገር ደረጃ በሥልጣን ወንበሮቹ ላይ ለአገር የሚያስቡ ሰዎች አለመኖራቸውን ለማወቅ ግሩም ማስረጃ ነው፤ ለቀብር የሄደው ባለሥልጣን ሻምበል ጉታን ይዞ ቢሄድ ኖሮ ለራሱም ሆነ ለአገሩ ክብርና ጌጥ ይሆንለት ነበር፤ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝብም ሆነ ለዓለም በመላ አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር አልሸጥም-አልለወጥም ብሎ የኔልሰን ማንዴላን ሕይወት ማትረፉን በማስታወቅ አገሪቱን ያስከብር ነበር፤ የታፈነው ታሪክ አፈትልኮ ሲወጣ ከስደተኞች ጋር ተያይዞ መሆኑ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የአደባባይ መክሸፍ የሚያሳይ ነው፤ ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ ተቀበለው፤ መንግሥት ያፈነውን ክብር ስደተኞች አጌጡበት!
ለእኔ አሁን አንድ ጥያቄ ይቀራል፤ ሻምበል ጉታ የአገሩን ክብር ከራሱ ጥቅም በላይ በማድረጉ፣ የተቀበለውን አደራ በመጠበቁ ቢያንስ ሁለት ሺህ ፓውንድ አጥቷል፤ እንዳጣ ሊቀር ነው? ቢያንስ የከፈለውን ሁለት ሺህ ፓውንድ ወይስ ያንን አሥር እጥፍ አድርገን እንከፍለዋለን? ሻምበል ጉታን የምናመሰግነው በርጥቡ ነው በደረቁ? እኛ ያለጥርጥር ኮርተንበታል፤ ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታችን የሱን ክብር በመጋራት ራሳችንን አክብረናል፤ ሻምበል ጉታም በእኛ እንዲኮራና በእኛ እንዲከበር ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፤ ስለዚህ ምን እናድርግ? ለራሱ ክብር፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ክብር ሲል የከፈለውን እስቲ ከወሬ ያለፈ ነገር እናስብና ለዚህ ጀግና የምንችለውን አድርገንለት እግዚአብሔር ዕድሜ ይስጥህ እንበለው።

No comments:

Post a Comment