Monday, January 13, 2014

ሲአይኤ ፤ መለስ ዜናዊ እና ኢትዮጵያ (ክፍሌ - 1)

በሉሉ ከበደ

 
ዘመኑ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1990 ላይ ነበር ። ለደርግ የአስተዳደርና የፖለቲካ ድህነት ምስጋን ይግባውና ሐገራችን ከገንጣይና አስገንጣይ ሀይሎች ጋር ታደርግ የነበረው ትንንቅ በኛ ሽንፈት ወደማክተሙ ሲቃረብ ፤ ዋናው ምክንያት የወያኔና የሻእቢያ ጦር ከኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ጀግናና ሐያል ሆኖ ሳይሆን ፤ የኢትዮጵያ ጦርሰራዊት በገጠመው የአመራርና የአስተዳደር ቀውስ የውጊያ ሞራሉ ሊጠገን በማይችል መልኩ ስለተጎዳና ውግያውን ስለተወው ፤ በሩ ሁሉ ለጠላት ክፍት ሆኖ በመገኘቱ ነበር ።
ሻዕቢያ አስመራን ሲቆጣጠር ፤ ወያኔም ከክፍለ ሐገር ክፍለ ሐገር በግሩም በመኪናም እየሮጠ ሐገሪቱን በሙሉ አዳርሶ ሊቆጣጠር በተቃረበበት ወቅት ፤ የጉዳያችን ባለቤቶች ሆነው ብቅ ያሉት አሜሪካኖች ፡ ከደርግ በሗላ ያለችውን ኢትዮጵያ እንዴት አድርገው ለራሳቸው እንደሚያበጃጇት ፤ ጥሩ ጉዳይ ፈጻሚ አስፈጻሚ ለሚሆናቸው ለማን እንደሚሰጧት መምከር ነበረባቸው።

 
       የሲአይኤው መኮንን ፖል ሄንዝ ፤ በተለያዩ  የዓለም ክፍሎች እየተዘዋወሩ ፤ የሽምቅ ውጊያዎችንና መሪዎቻቸውን በመከታተልና በማጥናት ፡ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ የአሜሪካ ግብና ጥቅም አስፈጻሚ መሳሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን በስልት በመመልመል ፤ በመርዳት የምክርና ሌላም ድጋፎችን በመለገስ ፤ ለስልጣን እንዲበቁ በማድረግ ለሐገራቸው ጠቃሚ ስራ የሚሰሩ የስለላ መኮንን ነበሩ ።
 
         መለስ ዜናዊ በጦርነቱ በለስ እንደቀናው ሁሉ ሲአይኤም መለስን የመሰለ ጸረ ኢትዮጵያ  የሽምቅ ውጊያ መሪ በማግኘቱ ረገድ ቀንቶት ኖሮ ፤ መለስ ባላሰበው አጋጣሚ እጁ ላይ የወደቀችለትን ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ ፡ እንዴት እንደሚያደርጋት ፤ እንደሚበልታት ፡ እንደሚበላትና እንደሚያስበላት ምክር ሊሻ ይሁን ወይም ደግሞ ሲአይኤ በመጋረጃ ጀርባ ብልሀቱ ምን እንደሚያደርጋት መመሪያና ምክር ሊሰጠው አስጠርቶት ፡ ብቻ ሁለቱ መናፍስት ደርግ ሊሞት በጣዕር ላይ እንዳለ ፖል ሄንዝና መለስ ዋሺንግተን ዲሲ ላይ ተገናኝተው ሁለት ቀን ብዙ ብዙ መክረው ነበር ።
 
        በወቅቱ ከመለስ ጋር ያደረጉትን አምስት ሰዓት የፈጀ ምክክርና ውይይት ፖል ሔንዝ “ ማስታወሻ “ ብለው በጥያቄና መልስ መልክ አቀናብረው ፤ የተባባሉትን በሙሉ ስለ ሰውየውም ሰብዕና ያላቸውን አስተያየት አክለው በጽሁፍ ሰነድ አኑረውታል ። ይህንኑ ሰነድ ደቂ አራዊት ጁን 6/2011 ኢትጵያን ሪቪው ድረ ገጽ ላይ ያቀረቡት ሲሆን ሰነዱ ከጥሩ የታሪክ መረጃነቱ ባሻገር ወያኔ ወደስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ እየወሰዳቸው ካሉት እርምጃዎች በስተጀርባ ማን እንዳለና ፡ መለስ ዜናዊ በማን ጭንቅላት እንደሚንቀሳቀስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስውር ነገር ባይሆንም ሰነዱ የበለጠ ማረጋገጫ የሚሆን ይመስላል ። ይህም በመሆኑ የፖል ሄንዝ ጽሁፍ ወደ አማርኛ ቢተረጎም ለአንባቢያን ግንዛቤን ያዳብራል በሚል እምነት ሳዘጋጀው  ላስታውስ የምሻው ነገር ፖል ሔንዝ እንደመግቢያ ካቀረቧቸው አናቅጽ ቀጥሎ የውይይታቸውን አንኳር አንኳር ነጥቦች ሰብሰብና አጠር እድርገው ያቀረቡበትን ከፍል ዝር ዝር ሀሳቡ በጥያቄና መልሱ ውስጥ ስላለ ለአንባቢያን ጊዜ ቁጠባ ስል አልፌዋለሁ ። በተጨማሪም አንዳንድ ቦታዎች ላይ አጠር ለማድረግ ሞክሬአለሁ ።
 
ፖል ሔንዝ በመግቢያቸው እንደጻፉት ፦
       
ይህ ጽሁፍ የሚያጠቃልለው በግምት አምስት ሰዓት የፈጀ ኤፕሪል 3 እና 5 1990 ዓም ዋሺንግተን ዲሲ ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ጽህፈት ቤት ውስጥ በኔ በራሴና በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መሪ መለስ ዜናዊ መካከል ለሁለት ቀን የተደረገ ንግግር ነው ። የመጀመሪያው ንግግር ጠዋት ነበር የተካሄደው ። የሁለተኛው የእራት ጊዜውን ጨምሮ መሽቱን በሙሉ የወሰደ ነበር ። አብረው የነበሩ ነገር ግን በንግግራችን ወቅት አልፎ አልፎ ይሳተፉ የነበሩ የወያኔ አመራር አባላት ፤ ብርሀነ ገብረ ክርስቶስ ፤ የህውሀት የአውሮፓ ተወካይ ተቀማጭነቱ ለንደን የሆነ ። ስዩም ሙሴ ፤ የህውሀት የውጭ ጉዳይ ሀላፊ እና አሰፋ ማሞ በዋሽንግተን ተወካይ ፡ ሶስቱም  ዋሺንግተን የገቡት ማርች 31 እና ኤፕሪለ 1 ከሮም የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለደርግና ለነሱ ባዘጋጀው ንግግር ላይ ተሳትፈው ነበር ።
 
      ንግግራችንን እስከተቻለ ድረስ በጥያቄና መልስ መልክ ለማቀናበር ሞክሬአለሁ ። አንዳንዴም ቅደም ተከተላቸውን ሳልጠብቅ በርካታ ጥያቄና መልሶችን አንድ ላይ ቀላቅያቸዋለሁ ።
 
      አጭር ከረር ያለና በሰላሳዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ሰው መለስ ዜናዊ ጥሩ እንግሊዝኛ ይናገራል ። ባለመጠራጠር መልኩ በሚገባም ፈጥኖ ይረዳል ። ምንም እንኳ ሲጋራ ካፉ ባይነጠልም የተረጋጋና ራሱን የገዛ ራሱን የሚቆጣጠር መሆኑን የሚያሳይ እንድምታ ያለው ነው ። አለባበሱ እንደነገሩ ነበር ። በምሽቱ ንግግራችን ወቅት ባዶ እግሩን ፎቴ ላይ ተቀምጦ ሳለ ፡አልፎ አልፎ ከመቀመጫው እመር እያለ እየተነሳ ፤ ነገሮችን በአጽንዖት ለመግለጽ እጆቹን ያወራጭ ነበር ። የ ኢትዮጵያውያን የሆነ የንግግር አዋቂነት ተሰጥኦ ያለው ይመስላል ። አንዳንዴም በንግግሩ የመቀለድ ተክህኖ አለው ። ለማነጋገር የሚቀል ሰው ኮስተር ያለና ከልቡ የውነቱን የሚናገር ሆኖ አግኝቸዋለሁ ።ፖል  ቢ.  ሄንዝ
 
ማጠቃለያና አስተያየት  ...... ( ታልፏል)
 
ንግግር ፦
 
መለስ፤  በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የጻፍካቸውን አብዛኛዎቹን ጽሁፎችህን አንብቤአቸዋለሁ ፤ በሁሉም ማለት   ይቻላል ባልካቸው ነገሮች እስማማለሁ ። ለዚህም ነው በዚህ የአሜሪካ ጉብኝታችን ወቅት ካንተ ጋር ለመነጋገር የፈለኩት ። አንድ ችግር ብቻ አለ ። ለምንድነው እኛን ማርክሲስቶች እያልክ ማለትህን የቀጠልከው ?
 
ፖል ሄንዝ፤ ምክንያቱም ማርክሲስቶች እያላችሁ እራሳችሁን ስለምትጠሩ ነው ። አንተ እራስህ ከተናገርከው የሚጠቀስ ነገር አለ ። ለወደፊቷ ኢትዮጵያ የአልባኒያን አይነት ስርዓት በሞዴልነት  እንደምትቀበል ተናግረሀል ። እስታሊንን እንደምታደንቅም ብዙ ሪፖርቶች አሉ ። ማርክሲስት ካልሆንክ ከዚያ የጸዳህ መሆንህን ለማረጋገጥ ብዙ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብሀል ።  
 
መለስ፡  እኛ የማርክሲስት ሌኒኒስት ንቅናቄ አይደለንም ። ማርክሳዊ ሌኒናዊ ፍልስፍናን ትግራይ ውስጥ አንተገብርም ። የድርጅታችን ስም እራሱ ማርክሳዊ ሌኒናዊነትን ያጠቃለለ አይደለም ። በንቅናቄአችን ውስጥ ማርክሲስቶች አሉን ። ይህን እቀበላለሁ ። እኔ እራሴ በ1970 ዎቹ መባቻ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆኘ ያመነ ኮሚኒስት ነበርኩ ። ንቅናቄያችንም ተነሳሽነትን ያገኘው በማርክሲዝም ነው ። ግና ቀኖናዊ ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን  መስክ ላይ ልትተገብረው እንደማትችል ተምረናል ። ማናቸውም አይነት የውጭ አሰራር በሐገሪቱ ላይ ሊጫን ይችላል ብለን አናምንም ። ሕዝብ ነጻ የሚወጣበት ብቸኛው መንገድ የራሱን ሁኔታና ልምድ ባሕሉን ተከትሎ ብቻ ነው ። ለገጠመን ችግር የራሱን የመፍትሄ አቅጣጫ ማጎልበት እንዳለብን እናምናለን ። በዓለም ላይ ምን እየሆነ እንዳለ እናውቃለን ።
 
ፖል፡ ምንድነው ታዲያ ስለ አልባኒያ አድናቆትህ የሚዘገበው ? የአልባኒያ አይነት ኮሚዩኒዝም ትግራይ ውስጥ መተግበር ትሞክራለህ ? 
 
መለስ፤ የአልባኒያን አይነት ሲስተም ስራ ላይ ለማዋል አንሞክርም ። የሶቬትን ሲስተም ወይም የቻይናን ሲሰተም አንተገብርም ። አልባኒያውያን እራሳቸው አንዳንድ አሰራሮቻቸውን እንደቀየሩ እናውቃለን ።
 
ፖል፡  አልባኒያ ውስጥ ኖረህ ታውቃለህ ? ከአልባኒያውያን ጋር አንዳችም አይነት ግንኙነት አለህ ?  
 
መለስ ፡ መቸም አልባኒያ ውስጥ አልነበርኩም ። ከአልባኒያውያን ጋርም ግንኙነት የለንም ። አልባኒያውያን በሀገራቸው ውስጥ ያደረጉትን ነገር እኛም ትግራይ ውስጥ እንደምናደርግ አድርገው ሰዎች ለምን ያስባሉ ?

 ፖል ፡  የኢትዮጵያን ጉዳይ በሚከታተሉ ወገኖች  ዘንድ በጣም የተስፋፋ አመለካከት አለ ። እናንተ ተነጣይ ማርክሲስቶች ናችሁ ። በርግጠኝንት አንተም ታውቀዋለህ ። በቀላሉ ሊረዷችሁ የሚቻል ሰዎች አልሆናችሁም ። የማርክሲዝም ፍልስፍና ስኬት አልባ ሆኖ በጎደፈበት ሰዓት የናንተ እዚያ ላይ መጣበቅ ። ከአምስት ዓመት በፊት ጽፌአለሁ ። ፍጹም ባህላዊ የሆነውን የትግራይ ህዝብ ኮሚዩኒዝም እንዴት ሊማርከው ይችላል ። አውራጃችሁን ከአብዮቱ በፊት አውቃታለሁ ። አብዛኛውን ክፍል ተጉዤበታለሁ ።
 
መለስ ፤  የጻፍከው ፍጹም ትክክል ነው ። ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን ንቅናቄአችን ትግራይነት ነው ። እናውቃለን የህዝብ ግንኙነት ችግር አለብን ። ለዚህም በከፊል ጥፋተኛ ልንሆን እንችላለን ። አሁን እዚህ የመጣንበትም ምክንያቱ  ያ ነው ። ከትግራይ ውጭ አንዳችም እርዳታ የለንም ። ለየትኛውም አካል ጥገኛ አይደለንም ። ነገር ግን በትግራይ ውስጥ ባለን ድጋፍ እንተማመናለን ። እናም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ድጋፍ እንተማመናለን ።
 
ፖል ፤ ከትግራይ ውጭ ምን ያህል ትግሬዎች ይኖራሉ ብለህ ትገምታለህ ?
 
መለስ ፤ ከአጠቃላይ ትግሬ አንድ ሶስተኛው በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል እንደሚኖር ነው ። ትግሬዎች ሁል ጊዜ ወደ ሌላው ይሄዳሉ ። አንዳንዶቹ ለመቆየት ፤ አንዳንዶቹ የጉልበት ስራ ፍለጋ ወደ ሌላው የሀገሪቱ ክፍል ይሄዳሉ ። ያም ነው እነሱን ከደርግ የነጠላቸው ። የጉልበት ስራ ሰርተው እንዳይኖሩ መደረግን ያህል የመሬት ስሪት ለውጥ ብታመጣባቸው ትግሬዎች አይናደዱም ። የትግራይ ሰዎች ወደ ሌላው የሀገሪቱ ክፍል ሄደው አንዳንዴም ከስድስት ወር በላይ ይቆያሉ ። ያገኙትን ይዘው ወደ ቤተሰባቸው ይመለሳሉ ። ቤተሰባቸውን ይረዱበታል ፤ ለእርሻ ስራም ያውሉታል ። እንደዚያ ሁኖ የሚገኝ  ገንዘብ በጣም አስፈላጊው የሆነ የህብረተሰብ ከፍል በኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም ። ደርግ እስቱፒድ ነው ። ያንን ከለከለ ። ስለዚህ ህዝባችንን ድህነት ውስጥ አስገብቶ ተስፋቢስ አደረገው ። ያም ነው ከመሰረቱ ድጋፍ ያስገኘልን ።
 
      እዚህ መተናል  ( አሜሪካ ማለቱ ነው) ምክንያቱም ውጭ ያለ ሕዝብ ምን ለማድረግ እየሞከርን እንዳለ  እንዲረዳን እንፈልጋለን ። ሰዎች ወደ ትግራይ መተው ምን አይነት ሕብረተሰብ እየገነባን እንዳለ እንዲያዩ እንፈልጋለን ፡፡ ሁሉም ሰው ያውቃል ደርግ ቀኖናዊ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም በሀገር ላይ ጭኖ ምን እንዳመጣ ። እኛም ያንን ለማድረግ ከሞከርን ሞኞች ነን ። የእያንዳንዱ ክልል ህዝብ ምን አይነት ስርዓት እንደሚፈልግ ራሱ እንዲወስን እንፈልጋለን ። ለዚህም ነው ደርግን ለመውጋት በምናደርገው ትግል ብዙ ህዝብ እየደገፈን ያለው ፡፡
 
ፖል ፤ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ እንዴት ትመለከተዋለህ ?
 
መለስ ፤ ደርግ የመሰረተው ስርዓት መውደም አለበት ። አለበለዚያ ሀገሪቱን ያወድማታል ። የተቃውሞ ንቅናቄዎች ሁሉ አንድ ላይ መምጣትና የሀገሪቱ የወደፊት እጣፈንታ ምን መሆን እንዳለበት መወሰን አለባቸው ። ከሁሉም ተዋጊ አንጃዎችና  ፓርቲዎች ፤ ንቅናቄዎች ፤ የተውጣጣ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም አቅደናል ። ግራ ዘመም ፡ ቀኝ ዘመም ፡ አንዳቸውም አይቀሩም ።  የሽግግር መንግስቱ ሕገ መንግስት የሚያረቅ የህገመንስት ጉባዔ ለማዋቀር እቅድ ይነድፋል ። ሀገሪቱ ፌዴራላዊ ነው መሆን ያለባት ። ሕዝቦች የራስ ገዝ መብት እውቅና ሊኖራቸው ይገባል ። ከንግዲህ በሗላ የአማራ የበላይነት ሊኖር አይችልም ። አይኖረንም ።
 
ፖል ፤ የአማራ የበላይነት ስትል ምን ማለትህ ነው ? የምታስተላልፈው መልእክት ይህ ከሆነ አሁን እየተቆጣጠራችሗቸው ያላችሁት አካባቢዎች ፤ ላስታ ፤ ጋይንት ፤ ሳይንት ፤ መንዝ መራቤቴ ባብዛኛው አማራ ነው የሚኖርባቸው ። ንቅናቄአችሁን እንዴት ነው የሚመለከቱት ?
 
መለስ ፤ እነዚህ አማሮችማ  የተጨቆኑ ናቸው ። ስለ አማራ የበላይነት ስናወራ የሸዋ አማራ ማለታችን ነው ። እናም ባለፉት አንድ መቶ አመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ላይ የሰፈነው የሸዋዎች የበላይነት ። ይህ ስርዓት መለወጥ አለበት ። አዲስ አበባ ላይ እኛ የበላይ የመሆን መብት አለን ብለው የሚያስቡ ካሉ አስተሳሰባቸውን መለወጥ አለባቸው ። ይህ ደርግ ከጅምሩ ይዞት የተነሳው አስተሳሰብ ነው ። ማንም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዱ ካንዱ የበላይ የመሆን መብት የለውም ።
 
ፖል ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ምንድ ነው ? የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ምንድ ነው ? እነማን ድርጅቶች ናቸው የፈጠሩት ?
 
መለስ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርንና የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባርን አዋሕደን ነው ። አብረን ሰርተናል ። ወደ ደቡቡ ክፍል ዘልቀው እንዲይዙ ወታደራዊ ድጋፍ አድርገንላቸዋል ። ጎን ለጎን ነው የምንዋጋው ። ....  አዲስ  አበባ ለመግባት ጥቂት ነው የቀረን ። ሀይላችን ወደ ደቡብ እየገፋ ይገኛል ። .... የደርግ ወታደር በደንብ  አይዋጋም ። ባካባቢው ያለው ሕዝብ ወደኛ መቷል ። ብዙ አማሮች ንቅናቄአችንን ተቀላቅለዋል ።.....
 
ፖል ፤ “ ባለፈው ጥቅምት ወር የወጣ ፤ የኢሕአደግን የፖለቲካ መርህ በቅርቡ አነበብኩ ። ቆመንለታል ከምትለው ነገር በጣም የተለየ ነው ። የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አይነት ነው ።ለኢትዮጵያ ያለው እቅድ ፡ በመንግስት የሚመራ የተማከለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት ነው    እንደዚህ አይነቱ ነገር እስካሁን ማርክሲስቶች መሆናችሁንና የአልባኒያን ሞዴል የምትከተሉ መሆኑን ነው የሚያረጋግጠው ። ”
 
መለስ ፤ “ በዚያ ጽሁፍ ፍርድ አትስጥ ። በተቆጣጠርነው አካባቢዎች በምናደርገው ነገር ዳኘን ። ትግራይ ውስጥ በምናደርገው ነገር ዳኘን ። ለራስህ ባካል ትግራይ ውስጥ ናና ተመልከት ። እና የኢሕአደግን ሰላማዊ የስልጣን ሸግግር በኢትዮጵያ ፕሮግራሙን አንብብ ።
 
ፖል፤ በተቆጣጠራችሗቸው አካባቢዎች የሰፈራውን ሁኔታ  እንዴት ነው የመታደርጉት? ስለ ንግድና ገበያስ እንዴት ነው ? አራሹ መሬትን ስለመቆጣጠሩ ሁኔታስ ? የህብረት እርሻም ሆነ የመንግስት  እርሻ ቢኖር ምንድነው የምታደርጉት ?
 
መለስ ፤ ህዝቡ ምን ማድረግ እንደሚፈልግ እንዲወስን እንፈቅድለታለን ። ይህን ተከተል ብለን አንድም አይነት ፖሊሲ ልንነግረው አንፈልግም ። የሰፈሩበትን አካበቢ ለቀው ወደመጡበት ተመልሰው መሄድ የሚችሉ መሆኑን እንነገራቸዋለን ። ብዙዎቹ አድርገውታል ። አንዳንዶቹ የገበሬ ማህበር ሊቀመናብርቱን አባረዋቸዋል ። አንዳንዶቹ ምን እንደሚሻላቸው አያውቁም ። እስካሁን ውሳኔ ላይ ናቸው ። የህብረት እርሻዎችን ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ እንዲወስኑ እንነግራቸዋለን ። ደርግ የሾማቸው ተመራጮች ይሸሻሉ ። ስለዚህ ገበሬውን የሚያዘው ማንም ሰው አይኖርም ። ብዙ አርሶ አደሮች የማህበር እርሻዎችን እንደራሳቸው ሀብት አይመለከቷቸውም ። በመንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው ። አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን ወስደው በእንዴት ያለ ስርዓት ቢተዳደሩ እንደሚፈልጉ እንዲወስኑ እንነገራቸዋለን ። በትግራይ መሬትን ብሄራዊ (የመንግስት?) ነው የምናደርገው፤ ግን ደርግ እንዳደረገው ብሔራዊ አይነት አይደለም ። መሬት የመንግስት ነው ። ግን ባርሶ አደሩ እጅ ነው የሚሆነው ። አርሶ አደሮቹ ሊሸጡትም ይችላሉ ። ለወራሾቻቸው ሊያስተላልፉም ይችላሉ ። በየሰባት ዓመቱ መሬትን መልሶ የማከፋፈል ተግባር ይኖራል ። የድሮዎቹ የሰፋፊ መሬት ባለቤቶች ተመልሰው መተው በሰፋፊ መሬቶች ላይ ቁጥጥር እንዲኖራቸው አንፈልግም ። እያንዳንዱ ሰው  መሬት የሚያስፈልገው ሁሉ እንዲኖረው እንፈልጋለን ። ምክንያቱም በትግራይ ውስጥ አርሶ አደሮች እንዲኖሩና ቤተሰባቸውን እንዲመግቡ የሚደረግበት አንዳችም መንገድ የለም ። ኢንዱስትሪና ሌላ የስራ መስክ የለም ። ስለዚህ መሬቱ ሁሉ ግልጋሎት ላይ መዋል አለበት ። በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል እነዚህን ጥያቄዎች ህዝቡ እራሱ ውሳኔ እንዲሰጣቸው አንፈልጋለን ። እነዚህ ጉዳዮች የሽግግር መንግስት ሲኖረን ውይይት ሊደረግባቸውና አዲስ ፖሊሲ ሊቀረጽላቸው የሚገባ ነው ። ደርግን የሚቃወሙ ንቅናቄዎች ሁሉ በዚህ ውሳኔ ላይ መሳተፍ አለባቸው ።
 
ፖል ፤ “ የሰማሁት ነገር አለ ። የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ነጻ የሆነና የራሱ ባሕሪ ያለው ድርጅት አይደለም ። ወያኔ የፈጠረው ነው ይላሉ ። እውነት ነው ? “
 
መለስ ፤ ኢሕዴን እንደ ህውሀት በደንብ የተደራጀ ንቅናቄ አይደለም ። ነገር ግን እንደው በቀላሉ ህውሀት የፈጠረው አይደለም ። ከትግራይ በስተደቡብ ክልል  ያሉ አማሮችን የሚወክል ነው ። ዋና ጽፈት ቤቱም ሰቆጣ ነው ።
 
ፖል ፤ ድርጅታችሁን ግንባር ትሉታላችሁ ። በመሰረቱ ግንባር ከብዙ ድርጅቶች የሚመሰረት ነው ። በትግራይ ነጻነት ግንባር ውስጥ ያሉ ሌላ ድርጅቶች እነማን ናቸው ?
 
መለስ ፤ ‘’ሌላ የተለየ ድርጅት የለንም ። በትግርኛ የኛ ስም ትርጉሙ  ‘ ንቅናቄ ’ ማለት ነው ። ሀርነት ወያኔ የሚለውን አባባል ነው የምንጠቀመው ። ምክንያቱም ስሙ በትግራይ ውስጥ ታሪካዊ ትርጉም አለው ። በውጭ ወራሪዎች ጭቆና ላይ የተነሳ ሕዝባዊ አመጽ ማለት ነው ። ያም የወያኔ አመጽ በ 1943 ላይ የነበረ ነው ።  የሸዋን የበላይነትና የትግራይን ብዝበዛ በመቃወም የተካሄደ ትግል ነበር ። ደርግም ወያኔ ይለናል ። ያን እንወደዋለን ። በውስጣችን የተለያየ ሀሳብ ያለን ሀይል ነን ። በንቅናቄአችን ውስጥ የውይይት ነጻነት አለን ።
 
ፖል ፤ ኢህዴን አንድ ድርጅት ነው ወይስ በውስጡ በርካታ ድርጅቶችን አቅፏል ? ....
 
                                         ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment