Tuesday, December 10, 2013

በብሔር ፖለቲካ ሥር “የተቀበረው ፈንጂ”! – (ዳዊት ሰለሞን)


article 39
 
የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ ምላሽ እንዳገኘ የሚያስተጋባው ኢህአዴግ “የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በዓልን ማክበር ከጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአንፃሩ “ተመልሷል” የተባለው ጥያቄ እንደተቀበረ ፈንጂ በየጊዜው በየቦታው እየፈነዳ በህይወት፣ በንብረትና በኢትዮጵያዊነት ላይ አደጋ ማድረሱን ዳዊት ሰለሞን ሁነቶችን በመጥቀስ ይሞግታል፡፡
ከአስርት አመታት በፊት
የኢትዮጵያ ተማሪዎች በለውጥ አብዮት ናፍቆት እየተናጡ ነው፡፡ እዚህም እዚያም በተፈጠሩ ቡድኖች የማርክሲስት-ሌኒንስት ፍልስፍናን የሚሰብኩ የርዕዮተ ዓለም ጽሁፎች ይነበባሉ፡፡ ተማሪው ይከራከራል፣ የሌኒኒዝም ፍልስፍና ቀለም ቀለም መሽተት ለጀመረው የ1960ዎቹ ትውልድ ልብ የቀረበ ሆኗል፡፡ ፍልስፍናውን በአገራቸው የፖለቲካ ግለት ለመተርጐም የቋመጡት ወጣቶች በሁለት ጠርዝ ተሰልፈው በኢትዮጵያ ያለው “የመደብ ወይስ የብሔር ጭቆና ነው” በሚል በጠረጴዛ ዙሪያ ይፋለማሉ፡፡
የብሔር ጭቆና በአገሪቱ መስፈኑን ለማሳመን ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል የብዙዎችን ቀልብ ለመስረቅ የበቃው ዋለልኝ መኮንን በተማሪዎች መጽሔት “On the Question of Nationalities in Ethiopia” የሚል ጽሑፉን ማስነበብ ጀመረ፡፡ ዋለልኝ በጽሑፉ ኢትዮጵያ አንድ አገር ሳትሆን ብዛት ያላቸው ብሔሮች በአማራ የበላይነት ተጨፍልቀው የሚኖሩበት መሆኗን ሞገተ፡፡ የዋለልኝን መከራከሪያ የተቀበሉ ተማሪዎች የብሔር ጥያቄን ዋነኛ መፈክራቸው አድርገው አረፉት፡፡ በአገሪቱ የሰፈነው ጭቆና የመደብ መሆኑን በመግለጽ “አንዱን ብሔር ጨቋኝና ሌላውን ተጨቋኝ” በማድረግ የተነሱትን እነ ዋለልኝን የተቃወሙ ተማሪዎች የብሔር ጭቆናን በሚያስተጋቡ ተማሪዎች “የነፍጠኛ ልጆች” የሚል ተቀጥላ ተበጀላቸው፡፡
ዋለልኝ ከማርክሲስት – ሌኒኒስት ፍልስፍና በቀጥታ የገለበጠባቸውን ቃላቶች በመጠቀም ኢትዮጵያን “የብሔሮች እስር ቤት” በማለት ሰየማት፡፡ በዋለልኝ እንደተዋወቀ የተነገረለትን የተጨቆነ ብሔርን ነፃ የማውጣት ፍልስፍና የትግራይ ተማሪዎች መሬት ላይ ለማዋል በማቀድ የነጻ አውጪነት ቡራኬን ተቀብለው ደደቢት በረሃ ገቡ፡፡ ወጣቶቹ ትግላቸውን በማስመልከት በእጅ ጽሑፍ ባሰፈሩት የመጀመሪያ ማኒፌስቷቸው ትግራዋይ በአማራ ጨቋኝ ብሔር ሲጨቆን መቆየቱን በመግለጽ ጨቋኙን (አማራን) ብሄር በጠብ መንጃ ትግል በመፋለም ትግራይን ነፃ ለማውጣት መነሣታቸውን አወጁ፡፡ በለስ የቀናቸው የትግራይ ነፃ አውጪዎች መላዋን ኢትዮጵያን በመዳፋቸው ስር ካስገቡ በኋላ በ1987 በጸደቀው ህገ መንግሥት የጆሴፍ ስታሊንን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አተረጓጐም ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እንዲሰፍር በማድረግ የስታሊን ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን በተግባር አሳዩ፡፡
የአገሪቱ የመንግሥት አወቃቀርም ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም እንዲሆን ተፈረደበት፡፡ ከብዙ አስርት አመታት በኋላ በዋለልኝ መኮንን “የብሄሮች እስር ቤት” ተብላ ከተጠራችው ኢትዮጰያ የተጨቆኑ ብሄሮችን ነፃ ለማውጣት ብሶት አርግዞት እንደወለደው የነገረን ገዥው ፓርቲ ራሱን በነጻ አውጪዎች ሰረገላ ካስቀመጠ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የነገው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓልም በገዥው ፓርቲ እምነት ጥያቄው ምላሽ ለማግኘቱ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ለፓለቲካ ፍጆታ እየዋለ ከሚገኘው ህዳር 29 በስተጀርባ መሬት የረገጡ እውነታዎችን ለመፈተሽ የተነሱ ሰዎች ከ73 የሚልቁ ብሄር ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶችን ያገኛሉ፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ዋነኛ የትግል ማዕቀፍ “ጥያቄው” አለመመለሱን የሚያሳይ ነው፡፡ በአገሪቱ ከመቼውም ግዜ በላይ መንግስትን በትጥቅ ትግል ለማንበርከክ ዱር ቤቴ ያሉ “ብሔር ተኮር” ድርጅቶች ስለመኖራቸውም እየተደመጠ ነው፡፡
በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጭምር ዘውጌ ተኮር ግጭቶች በስፋትና በብዛት እየተደመጡ ነው፡፡ “በኢትዮጵያዊነት” ጥላ ተሰባስበው የትውልድ መንደራቸውን በመልቀቅ በሌሎች ክልሎች ሀብትና ንብረት ያፈሩ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው እንደ ባይተዋር ተቆጥረው “እየተገደሉ ነው፡፡ በአሩሲ፣ በአርባጉጉ፣ በበደኖ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በወለጋ፣ በአሰበ ተፈሪ፣ በጋምቤላ፣ ኦጋዴን፣ ጉራፈርዳና በቦረና “ከክልላችን ውጡ” የተባሉ የሌላ ክልል ተወላጆች ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፣ ከእነ ህይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተወርውረው ሴቶቻቸው ተደፍረዋል፡፡
በዘመነ ደርግና ከዚያ ቀደም በነበሩ አስተዳደሮች ግጭቶች የሚነሱባቸውና የሰው ህይወት ለከፋ ጉዳት የሚጋለጥባቸው አጋጣሚዎች የነበሩ መሆናቸውን መካድ ባይቻልም እነዚህ ግጭቶች ግን ይነሱ የነበሩት በግጦሽ መሬት ፍለጋ እንደነበር መዘንጋት አይገባም፡፡ በአገሪቱ የጐሳ ፖለቲካ አየሩን ከተቆጣጠረበት ከ22 ዓመታት ወዲህ ግን የግጭቶች ይዘትና መንስኤ ወደ አንድ ጫፍ በማዘንበል ላይ ይገኛል፡፡ “ክልላችንን ለቅቃችሁ ውጡ” የሚለው ድምፅ በሁሉ ልብ ማስተጋባት ሲጀምር “በህዝብ መካከል አለመተማመንን በመዝራት በመጨረሻ የሚያሳጭደው ውጤት አገርን ለመበታተን ይዳርጋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የሚከበረውም “እኛና እነርሱ” በሚል መንፈስ መሆኑም የተቀበረው ፈንጂ ሰዓቱን እየሞላ እንዲሄድ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር ስለመኖሩ ብዙዎች ይጠራጠራሉ፡፡
ሁሉም የራሱን መንደር እየፈለገ ወደቀረበው እንዲሄድ የሚያደርግ መድረክ መፈጠሩን የሚተቹት ዶክተር ዘውዱ ውብእንግዳ “የፌደራሊዝም ታሪካዊ አመጣጥ” በሚለው መጽሐፋቸው ትዝብታቸውን እንዲህ ያሰፍራሉ፡፡ “በደርግ ዘመን ቀበሌዎች ስብሰባ ህዝቡን ሲጠሩ በ … ቀበሌ የምትገኙ … አዳራሽ ስብሰባ ስላለ እንዳትቀሩ ይሉ ነበር፡፡ አሁን ግን … ብሔር ተወላጅ የሆናችሁ … አዳራሽ እንድትገኙ ማለት ተጀምሯል፡፡ በፊት በአንድ ቀበሌ መኖር የአብሮነት መለኪያ ተርጐ ይወሰድ ነበር፡፡ አሁን ግን በአንድ ቀበሌ መኖር ብቻ በቂ ሳይሆን የብሔር ማንነት እንደመታወቂያ እየተወሰደ ነው” ይላሉ፡፡ ልዩነቶቻችን ጐልተው እንዲታዩ የሚደረጉባቸው መድረኮች በመንግሥት አታሞ እየተጐሰመላቸው አጀንዳ ሲሆኑ ከማየት የበለጠ ህመም የሚፈጥር ነገር የለም፡፡
በዓሉ የሚከበርባቸው ሥነ ሥርዓቶች ለኢህአዴግ ቱባ ባለስልጣናት አትሮንስ በመሆን ከማገልገል በዘለለ የብሔር ፖለቲካው፣ ፌዴራሊዝሙና የክልል መንግሥታት ነጻነት ለውይይት የሚቀርብባቸው መድረኮች አለመዘጋጀታቸውና እስካሁን ብሔርን/ዘውጌን ተገን በማድረግ በተፈጠሩ ቀውሶች ዙሪያ ውይይት የሚደረጉባቸው መንገዶች አለመፈጠሩ በእኔ እምነት በዓሉን “ከፈንጠዝያ” የዘለለ አያደርገውም፡፡ የአማራው ባህል ለትግሬው፣ የጉራጌው ለኦሮሞው፣ የከምባታው ልጅ ለስልጤው እየተሰጠች ያደግንባት አገር፣ አፋሩ ለሃድያው ዘብ የሚቆምባት ምድር ያፈራችን ሰዎች ለአክሱም ሀውልት ጋምቤላው የሚጨነቅባት የቅኖች ምድር ኢትዮጵያ በብሔር ፖለቲካ በናወዙ ጥቂት ቡድኖች ትልቁን ምስል ጠብቃ እንድትኖር እነዚህ መድረኮች “የእኛና የእነርሱ” የሚሉ ስሜቶች ስር ሳይሰዱ የሚቀርቡባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ያን ጊዜም “የተቀበረው ፈንጂ” ይመክናል፡፡
የብሔር ፖለቲካ መዘዝ
በአገሪቱ ከ84 የሚልቁ ብሔረሰቦች እንዳሉ ከመነገሩ ባሻገር የትኛው የማኀበረሰብ ክፍል ብሔር፣ የትኛው ብሔረሰብ ወይም ሕዝቦች የሚሰኙት የትኞቹ እንደሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በአንዳንድ አደባባዮች የጆሴፍ ስታሊንንና የዋለልኝ መኮንን ንግግሮች እንደወረደ በመደስኮር “አንደበተ ርትዕ” ተብለው የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንኳን እነዚህን የማኀበረሰብ ክፍሎች ሳይተነትኑ አልፈዋል፡፡ ከስምንት ዓመት ወዲህ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በተለየዩ ሥነ ሥርቶች እንዲከበር እያደረገ ነው፡፡
በዚህ ቀን ከተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎች የመጡ ሰዎች በመሰባሰብ እለቱን ይዘክራሉ፡፡ በዚህ ቀን እንኳን የትኛው ብሔር፣ የትኛውብሔረሰብ፣ የትኞቹ ደግሞ ህዝቦች መሆናቸው አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ፍቺ ባልተገኘበት ሁኔታ በዓሉ ይከበራል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር በህገ መንግሥቱ “ሕዝቦች” ተብለው የተጠቀሱ ክፍሎች ምንም አይነት መገለጫ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ለምሣሌ ህገ መንግሥቱ ስለመሬት የሚለውን እንውሰድ፡፡ መሬት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መነሻነትም ክልሎች በቋንቋ መነሻነት የየራሣቸውን ወሰን እንዲካለሉ ተደርገዋል፡፡ ህዝቦችስ? ነገሩን ትንሽ ለጠጥ በማድረግ እንውሰደው፡፡
በጉራፈርዳ ሰፍረው የነበሩ አማሮች “እንደ ህገወጥ ሰፋሪ ታይተው በክልሉ መንግሥት ውሣኔ ለአመታት ይዘውት የቆዩትን መሬት ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ መሬቱን እንዲለቅቁ የተደረጉት “የክልሉ ተወላጅ” ባለመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የክልሉ ተወላጅ ባይሆኑም ሕዝብ በመሆናቸው እንደ ህገ መንግሥቱ የመሬት ባለይዞታነት መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባ ነበር፡፡ የፌዴራሊዝሙ ተሳክሮት ዶክተር ዘውዱ በመጽሐፋቸው ለፌዴራል መንግሥት ምስረታ መንስኤ የሚሆን መሠረታዊ ነጥብ “ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መንግስታት ወይም የየራሣቸውን መንግሥታዊ አስተዳደር ያካበቱ ሕዝቦች በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚያቋቁሙት ሦስተኛ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም ፌዴራላዊ መንግሥት ከትንሹ ቁጥር ሳንነሳ የሦስት መንግሥት ጥምር ነው” ይላሉ፡፡ በዘውዱ ገለፃ ፌዴራሊዝምን በማስተዋወቅ የመጀመሪያዋ ተጠቃሽ አገር ለመሆን የበቃችው ለ100 ዓመታት ያህል በእንግሊዝ ቅኝ ተገዝታ የነበረችው አሜሪካ ናት፡፡
ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ሀገሪቱን በ13 የቅኝ ግዛት አስተዳደሮች በመከፋፈል ስታስተዳድር ቆይታለች፡፡ አሜሪካኖች ራሣቸውን ነፃ ካወጡ በኋላ ተከፋፍለው የነበሩት ክልሎች በፌዴራሊዝም አማካኝነት መልሰው አንድነታቸውን አግኝተዋል፡፡ ሌሎች በቅኝ ግዛት ስር የነበሩና የተለያዩ አስተዳደሮችም የአሜሪካውን ፌዴራሊዝም በአርአያነት በመከተል የተበታተኑት አንድ መሆን ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ግን የጐሳ በመሆኑ በአለም ከሚታወቀው የፌዴራሊዝም አመሰራረት ጽንሰ ሀሣብ ያፈነገጠ ነው፡፡
በህገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት የክልል መንግሥት ለማቋቋም መመዘኛ ሆኖ የቀረበው ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች በሚል መነሻነት ነው፡፡ አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአገሪቱ ውስጥ ከ84 የሚልቁ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ክልል እንዲመሰረቱ እውቅና የተሰጣቸው ዘጠኙ ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹስ? ለምን ክልል የመመስረት መብትን ተነፈጉ?
በህገ መንግሥቱ በዘጠነኛ ክልልነት የተቀመጠው “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል” ተብሎ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ የፌዴራሉመንግሥት ክልሎች የተመሠረቱት ቋንቋን ማዕከል ባደረገ መልኩ ቢሆንም ይህ ወደ ደቡብ ሲያመራ “ጂኦግራፊያዊ” እንደሆነየተፈለገበት መንገድ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ በደቡብ ክልል ከ46 የሚልቁ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ብሔረሰቦች በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ብሔረሰቦች የራሣቸውን ክልልና መንግሥት የሚመሰርቱበትን መብት ሲጐናጸፉ በደቡብ ያሉት ግን ይህንን መብት ተነፍገዋል፡፡
የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር በቋንቋ በአንድ ቦታ ሲሰራ በሌላ ቦታ በጂኦግራፊ መሆኑም የአወቃቀሩን ተሳክሮት ወለል አድርጐ ያሳያል፡፡ በጎሳ ላይ የተንጠለጠለ የመንግሥት አወቃቀር በሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኮሶቮና ሩሲያን በመሳሰሉ አገራት የፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ የተመለከቱ ሰዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት የአወቃቀር ተሳክሮት በአገሪቱ ላይ በጊዜ የማይተነብይ ምስቅልል ሊፈጥር እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

No comments:

Post a Comment