Thursday, November 14, 2013
በቅድስቲቱ ኢትዮጵያ ልጆች ደም ሳዑዲዎች የነቢያቸውን ምድር አረከሷት (ሰይፉ ኣዳነች ብሻው)
NOV 14,2013 እና … ቁጣዬን ለመግለፅ ተነስቻለሁ!
“እንደ ሴት ቁጭ ብዬ እሸናለሁ፤ ወንድ አይደለሁም፣ እውነት ሱሪ አልታጠቅሁም” የሚሉ ወንዶች በጣሙን ይገርሙኝ ነበር ድሮ። ንግሥት ሳባን የመሰለች ንግሥት፤ ጣይቱን የመሰሉ እተጌ፤ ሸዋረገድ ገድሌ የመሰሉ ጀግና ዐርበኛ ኢትዮጵያዊያት እንደነበሩን እየታወቀ ወንዱ ከሴቷ እበልጣለሁ ብሎ ሲፎክር ይከፋኝ ነበር። አገራችን ኢትዮጵያ ተከብራ እንድትኖር ጀግኖችን ማፍራት ብቻ ሳይሆን በጀግንነት ለአገራቸው የተዋደቁና ሉዓላዊነቷን ያስከበሩ እንስቶቻችን ዛሬ የዐረብ መጫወቻ ሲሆኑ ቁጭ ብሎ የሚያይ፤ በዶላር አሽከርነታቸውን ለማሳየት መንግሥት የሌላት ሶማሊያ ውስጥ ሠራዊት የሚያሰማሩ የጦር ጄኔራል ግብስብሶች፤ የአገር ሉዓላዊነትና ፍትሕን ለመታደግ ሕግ አርቃቂው የፓርላማው ጥርቅሞች ዜጎቻችን እንደ ውሻ ተቆጥረው በየዐረቡ አደባባይ ሲገደሉ እያዩ ሱሪያቸውን አውልቀው ተቀምጠዋል። ሴት ለክብሯ ቁጭ ብላ ትሸናለች እነሱ ግን በቁማቸው ለቀውት ያታያሉ። በየትኛውም አገር የአገሩን ክብርና የራሱን ነፃነት ለማስጠበቅ የማይቆም መንግሥት የለም። በሳዑዲ በደል በሚፈፀምበት ዜጋችንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ምንም ልዩነት የለም። ኹለቱም ኢትዮጵያውያን ናቸውና። ሳዑዲ ያለው ኢትዮጵያዊ/ት ሲደፈር/ስትደፈር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደፋሯል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ተደፍሯልና። “ጌታውን ካልናቁ ውሻውን አይመቱ ወይን አጥር አይነቀንቁ” ይባል የለ። ሳዑዲ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብታከብር ኖሮ ኢትዮጵያዊውን ለመግደልና ሰንደቅ ዓለማውን ለማዋረድ ባልሞከረች ነበር። ሳዑዲ እንደሆነ ፈረንሣይን የምታክል መሬት ከአገራችን ወስዳ በፔትሮ ዶላር ቀኝ ገዢነት ይሰማታል። የቅኝ አስተሳሰብ ያለው አገር ደግሞ ሌላውን ዜጋ ለርሱ ባርያው አድርጎ ነው የሚያየው። ዶላር ስላላቸው እንጂ እርቧቸው አይደለም? ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው ለም መሬት የሚገዙት። ነዳጅ ባይኖራቸው የት ነበር መድረሻቸው?
ሳዑዲ ውስጥ ሰይጣን (ሸይጣን) ገብቷል። የነቢዩ መሐመድን ትምሕርት አርክሰዋል። ቅድስቲቱ ምድራቸውን የግፍ ምድር አድርገዋታል። ነቢዩ መሐመድ አትንኳት ያሏትን ዜጋ ሕይወት እየጨፈጠፉ ናቸው። እስልምና በዓለም ላይ እንዲንሰራፋ ከለላ የሆነችውን አገር ለቁጣ ጋብዛለች። እንዴት መካሪ አጣች?
መቼም ኢትዮጵያ ተምዘግዛጊ መሣሪያ ኖሯት በሳዑዲ ላይ ጦርነት ለመክፈት ገንዘቡም (ለግድብ፣ ለልማት እያለች ከስደተኛ ዜጎቿ ገንዘብ የምትጠይቅና በምዕራባውያን ምፅዋት ያለች በመሆኗ) አሜሪካም ከጎኗ የሏትም። ለፔትሮሏ ስትል አሜሪካ ሳዑዲን መክዳት አትፈልግምና። እኛ ግን ከምድራችን ላይ ንቅል አድርገን በ24 ሰዓት ማባረር እንችላለን። ደርግ እንኳን አሜሪካን መንጥሮ ነበር ያስወጣት። አንድ አገር ሉዓላዊነቱንና የዜጋውን መብት ለማስጠበቅ የትኛውም ኀያል መንግሥት ሊያቆመው አይችልም። ምኒልክን ማስታወስ ነው፤ የአውሮጳን ኀያል ወራሪ ድባቅ የመታውን። ፋሽስትንም ተዋግተው የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ ጥቂት ዐርበኞቻችንን መጎብኘት የጦር መሣሪያ ኀይል የማይበግረው የአገር ወዳድነት ወኔ መሆኑን ከነሱ ለማወቅ ይቻላል። ወኔ የሌላቸው ገዢዎቻችን ግን ሱሪያቸውን አውልቀው ሲያዋርዱን እናያለን። የእነሱ መደፈርና መናቅ ነው ዜጎቻችን ለጥቃት የተጋለጡት። ኢትዮጵያዊነት እንዲረክስ ያደረጉት።
ውሻ እየተባለ ዜጋው ሲረገጥ እያየ በለሆሣሣ የበታችነትን በሚያንፀባርቅ ዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ ተቃውሟችንን አሰምተናልን የሚለውን የወያኔ ፕሮፖጋንዳ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚቀበለው አይደለም። ኢትዮጵያውያን አገራችንን መልሰን መረከብ አለብን። መሬታችንን ያስረከቡትንና የተረከቡትን ጠራርጎ ማስወጣት ያስፈልጋል። ሰላማዊ ሠልፍ በውጪ የምንገኘው ቁጣችንን ለዓለም ለማሳየት እንጂ በአገር ውስጥ ከዚህ የጠነከረ መልስ መስጠት አስፈላጊ ነው። ያዋረዱንን ገዚዎቻችን የዐይን ቀለማቸው ጠርቶ ይታወቃል። መሹለኪያ መንገድ እንዳይኖር ዘግቶ ለፍርድ ማቅረብ ያስፈልጋል። በስደት ቢሄድም እንኳን በዘረፈው ገንዘብ ተንደላቅቆ የሚኖርበት ምድር እንዳይኖር ማድረግ ፍትሓዊ ነው።
ገዢዎቻችንና አጋሮቻቸው ኹሉ ለስደት፣ ለሞት፣ ለርሃብ፣ ለጥማት፣ ለውርደትና ከሰብዓዊነት በወጣ መልኩ በአገርም ኾነ በባዕድ አገር የተዋረድክና ነፃነትህን ብቻ ሳይሆን አገርን ያጣህ አድርጎሃል። ቤተሰቤን ልርዳ ብላ ለግርድና ልጅህ ስትሸጥ መልካም ብለህ ተቀመጥክ። ሲደፍሯት መንግሥት እንደማይደርስ እያወቅህ ጥያቄ አላነሳ አልክ። የልጅህ መርዶ ሲመጣ የምትጮኸውን ጩኸት ያኽል አልጮህ አልክ። የትግሉ ሜዳ ሚናው የለየ ነው። ታጋዮችንህ ይገድሉብሃል። ለአገርና ለወገን ደራሽ ለመሆን የሚችል እንደ ሙሉቀን መስፍን ለአንተ አጋር የሆኑትን ታጋዮች እንዲገድል ኤርትራ ከሚልክ ይልቅ ዜጋን ከጥቃት ጠባቂ አድርጎ ሳዑዲ ቢልከው እንዴት ባኮራ ነበር። መንግሥት የሌላትን ሱማሊያ ከመውረርና ያልታጠቀ ሰላማዊ ኢትዮጵያውንን ከመጨፍጨፍ በቀር ወኔ የሌለው ጠላትን ተቀብለህ ትኖራለህ። ቅኝ ለማድረግ የሚመጣን ትኩስ ጠላት አይደለም የምንዋጋው፤ 22 ዓመታት በጭቆና እየገዛ ያለውን ዐምባገነን በመጣል ነፃነትን ለመጎናፀፍ ነው ፍልሚያው። መከራ የመከረህ ወገኔ ምክር አያስፈልግህም፤ የሚያስፈልግህ አንድነት ብቻ ነው። ያለብህ ቆርጠህ መነሳት ነው። ኀይሉ ካንተ ጋር ይሁን! አሜን!!!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment