Wednesday, November 27, 2013

ከኢትዮጵያ እሳት ወደ ሳውዲ አረቢያ እረመጥ፣ ከድጡ ወደ ማጡ


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሀገሬ

What “foreign minister” Adhanom said and did not even know he said it
Tedros Adhanom, the malaria researcher-turned-instant-foreign-minster
ባለፉት አስርት ዓመታት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች በአገራቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር በተለየ መልኩ ተንሰራፍቶ እየተፈጸመ ካለው ጭካኔና ርህራሄ የጎደለው አምባገነናዊ ስርዓት ለማምለጥ ሲሉ እግራቸው ወዳመራቸው አገር በመሰደድ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ “ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር” እንደዘገበው ከሆነ እ.ኤ.አ በ2012 በግምት 200,000 ኢትዮጵያውያት ሴቶች በውጭ አገር በአብዛኛውም በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የውጭ የስራ ዕድል ለመፈለግ ተገደዋል፡፡ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያት ሰራተኞች አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ከሚገኘው አምባገነናዊ የእሳት ነበልባል አመለጥኩ የሚል እምነት ነበራቸው፣ ሆኖም ግን ወደ ሳውዲ አረቢያው የእሳት እረመጥ ተወርውረው እራሳቸውን አገኙት፡፡
በኢትዮጵያውያን ስደተኛ ሰራተኞችና በሌሎች በሳውዲ አረቢያ ጥገኝነት በጠየቁ ዜጎች ላይ ገደብ የለሽ አደን እየተካሄደ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ወር በየዕለቱ በሚባል መልኩ የሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች፣ የደህንነት ኃላፊዎች፣ ወሮበሎች እና ህገወጦች ኢትዮጵያውያንን/ትን ሁሉ በየመንገዱ እያደኑ ይደበድባሉ፣ ያሰቃያሉ፣ አንዳንድ ጊዜም ይገድላሉ፡፡ የሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን ሲደበድቡ የሚያሳየውን የዩቱቤ የቪዲዮ ምስል መመልከት ለህሊና የሚሰቀጥጥ ነገር ነው፡፡ የሳውዲ አረቢያ ወሮበሎችና ህገወጦች ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን በየመንገዶች ሲያሳድዱ፣ ሲያጠቁና ሲገድሉ የሚያሳየው የቪዲዮ ምስል ለኩነቶቹ እውንነት ምንም ዓይነት ማብራሪያ አላስፈለገውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሳውዲ አረቢያ ወሮበሎችና ጋጠወጦች በኢዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ እየፈጸሙት ያለው በቪዲዮ ማስረጃነት ተደግፎ የቀረበው የሰብአዊነት መብት ረገጣ ወንጀል በጣም የሚዘገንንና በሰለጠነ የሰው ልጅ ህሊና ሊታሰብ የማይችል ነገር ነው፡፡
ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ፡ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች፣
ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ የሳውዲ አረቢያና የኢትዮጵያ ገዥዎች ከአንድ ጥለት የተቆረጡ ናቸው፡፡ የሳውዲ አረቢያ መንግስት በሰብአዊ መብት አያያዝ መዝገቡ በመጥፎ ተምሳሌነቱ ይታወቃል:: በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ መንግስት በሰብአዊ መብት አያያዝ እንደ ሳውዲ አረቢያ ሁሉ ያስጠይፋል፡፡ የሳውዲ አረቢያው ገዥ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን በጣም ሰብአዊነት በጎደለው መንገድ ከግዛቱ በኃይል እንዲጋዙ/እንዲባረሩ የሚያደርግ መርህን ተከትሏል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ መደብም በተመሳሳይ መልኩ በሀገሩ ግዛት ውስጥ ኢትዮጵያውያንን/ትን ከሚኖሩበት ቀያቸው በግዳጅ ወደሌላ አካባቢ በማጋዝ አስደንጋጭ የሆነ የሀገር ውስጥ የማጋዝ (ሰፈራ) መርህን ተከትሏል፡፡ የሳውዲ ገዥ አናሳ የእምነት ተከታዮችን አሰቃይቷል፣ የኢትዮጵያ ገዥ መደብም እንደዚሁ አድርጓል፡፡ በሳውዲ ያለው ገዥ መደብ ዜጎችን በስፋት በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ያውላል፣ በእስር ቤት ያጉራል፣ ያሰቃያል፣ እንዲሁም በህግ ከለላ ጥላ ስር በሚገኙት ዜጎች ላይ ህገወጥ የእስር ቤት አያያዝን ያራምዳል፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ መደብም በተመሳሳይ መልኩ የሳውዲ ገዥ የሚፈጽማቸውን የአፈና ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል፡፡ የሳውዲ ገዥ የባሪያ ንግድን እ.ኤ.አ በ1962 በአዋጅ ካስቆመ በኋላ “ከፋላ” “kafala” (ተያዥ ያላቸው ስደተኛ ሰራተኞች፣ ሆኖም ግን በባሪያ ንግድ የአሰራር ሁኔታ የሚሰሩ) የሚል ቅጥያ በመስጠት ብዝበዛውን ቀጥሎበታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 የባህሬን የሰራተኛ ሚኒስትር ማጅድ አል አላዊ ሲናገር ከፋላ የሚለውን የማደናገሪያ ቅጥያ ከባሪያ ንግድ ጋር አመሳስሎታል፡፡ እ.ኤ.አ የ2013 ዓለም አቀፍ የባርነት አመላካች አሀዝ/Index እንዳመለከተው 651,000 የሚሆኑ በባርነት ተይዘው ህይወትን በመግፋት ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች ሲኖሩ ከእነዚህም የዓለምን ሶስት አራተኛ ከሚይዙት ከመጀመሪያዎቹ አስር አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች/Human Rights Watch እ.ኤ.አ በ2013 ባቀረበው ዓለም አቀፋዊ ዘገባው የኢትዮጵያንና የሳውዲ አረቢያን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሬከርድ በሚመሳሰል መልኩ እንደሚከተለው አቅርቦታል፤
በ2012… የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ሀሳብን በነጻ የመግለጽ፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ መሰረታዊ መብቶችን መገደብን በስፋት ቀጥለውበታል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባውን በመቀጠል በአዲስ አበባ ማዕከላዊ እየተባለ በሚጠራው የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ማዕከል ፣ እንዲሁም በሶማሊ፣ በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎች እስር ቤቶችና በወታደራዊ ማዕከሎች የሚፈጸሙትን የማሰቃየት ድርጊቶች ዝርዝር ዘገባ አቅርቧል፡፡
የሙስሊሙን ህብረተሰብ አመጽ ተከትሎ በኦሮሚያና የአገሪቱ መናገሻ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ አመጹን ለመግታት በሚል ሰበብ የደህንነት ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር በማዋል፣ እስራትና ድብደባዎችን ፈጽመዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ድብደባን ጨምሮ በአገሪቱ ከፍተኛ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ላይ መንግስት ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም የሚጠይቀውን የሙስሊሙን ህብረተሰብ ሰላማዊ ተቃውሞ ለመግታት ሲል መንግስት ከልክ ያለፈ ኃይልን ተጠቅሟል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ በሚል ሰበብ የመንደር ማሰባሰብ ተግባሩን እውን ለማድረግ በአምስት የአገሪቱ ክልሎች 1.5 ሚሊዮን የገጠር ሰፋሪዎችን የማሰባሰብ ስራ ቀጥሏል፡፡ በጋምቤላ ክልል ብዙ ሰፋሪዎች ከሚኖሩበት ቀዬ በኃይል ተፈናቅለው ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል… በመንግስት ጥረት የሚከናወን የሸንኮራ አገዳ ልማትን ለማፋጠን ሲባል በኢትዮጵያ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የሚኖሩትን ኗሪ የፓስቶራል ህዝቦች መንግስት በኃይል አፈናቅሏል:: በደቡብ ኦሞ ዞን ወደ 200 ሺ የሚሆኑ የአካባቢው ኗሪ ህዝቦች መሬታቸውን ለሸንኮራ አገዳ ልማት ይፈለጋል በሚል ሰበብ መንግስት መሬታቸውን በመንጠቅ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡
ሳውዲ አረቢያን በሚመለከት ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚከተለውን ዘገባ አቅርቧል፣
እ.ኤ.አ በ2012 ከህግ አግባብ ውጭ የሚከናወኑትን እስራቶችና ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን የማዋከቡ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው ምክንያት የሳውዲ አረቢያ መንግስት የኃይል እርምጃን ተጠቅሟል… እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ፍትሀዊ ያልሆነ ፍርድን ተቀብለዋል፣ ወይም ደግሞ ከህግ አግባብ ውጭ ለእስራት ተዳርገዋል… እስረኞች ህጻናትን ጨምሮ ስልታዊ የህግ የበላይነት ጥሰት እና ፍትሃዊ ህግ የማግኘት መብት የመነፈግ፣ ከህግ አግባብ ውጭ እስራትና ማሰቃየት እንዲሁም ህገወጥ የእስር ቤት አያያዝ ደባ ይፈጸምባቸዋል… ባለስልጣኖች የ9 ሚሊዮን የውጭ ሰራተኞችንና የ9 ሚሊዮን የሳውዲ ሴቶችና ልጃገረዶች መብት ማስከበር አልቻሉም ወይም ጭቆናውን ቀጥለውበታል…
ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የአገር ውስጥ ስደተኛ ሰራተኞች ከ2005 የሰራተኞች ህግ ውጭ ተደርገዋል… ባለፉት ዓመታት የኤሲያ ኤምባሲዎች ዘገባ እንደሚያመለክተው ከሀገር ውስጥ ሰራተኞች ቅሬታ እንደሚያሳየው በቀን ከ15 እስከ 20 ሰዓታት፣ በሳምንት ደግሞ 7 ቀናት እንዲሰሩ ከመገደዳቸውም በላይ ደመወዛቸውን ያለመክፈል ሁኔታም ተንጸባርቋል፡፡ የሀገር ውስጥ ሰራተኞች በአብዛኛውም ሴቶች በተደጋጋሚ ጊዜ ተገደው እንዲወልዱ ይደረጋል፣ ምግብ የማግኘት መብታቸውን ያጣሉ፣ እንዲሁም የጾታ ትንኮሳ፣ የአካልና የስነልቦና ጫናዎች ይደረጉባቸዋል፡፡
ሳውዲ አረቢያ ከእስልምና አስተህምሮ ውጭ የሌሎችን እምነቶች አስተምህሮዎችን ለመቀበል ትዕግስቱ የላትም፡፡ ባለፈው መጋቢት ወር ልዩ ልብስ ለባሹ ሸክ በአረቢያ ፔንሱላ የሚገኙ ማናቸውም ቤተክርስቲያኖች በሙሉ እንዲወድሙ ጥሪ አስተላልፎ ነበር…
“የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር” ቴዎድሮስ አድሃኖም ምን እንዳሉና ያሉትንም እንዳላወቁ፣
በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ በአሁኑ ጊዜ እየደረሰ ያለውን አስፈሪ ሁኔታ በማስመልከት የሚሰጠው ምላሽ ጭንቅላትን ይበጠብጣል፡፡ የወባ ትንኝ ተመራማሪውና ከመቅጽበት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተቀየሩት ቴዎድሮስ አድሃኖም እንዲሁም እ.ኤ.አ ከ2015 ሀገራዊ ምርጫ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁት ባለስልጣን ስለሳውዲ አረቢያው የኢትዮጵያውያን/ት ሁኔታ አስመልክቶ በኖቬምበር አጋማሽ በአዲስ አበባ ላይ በተካሄደው በ3ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ምጣኔ ጉባኤ ላይ ሲናገሩ ግራ ተጋብተዋል፣ እዚህና እዚያ የሚዋዥቅ ንግግርም አሰምተዋል፡፡ ቅንነት የጎደለው እርግጠኝነትና በባዶ ተስፋ የተሞሉ ቃልኪዳኖችን አነብንበዋል፡፡ ወገኖቻችን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመጡ በደስታ ለመቀበልና ዓለም ቀፋዊ ተብብርን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ በየኋህነት/ሞኝነት አገላለጽ አስቀምጠውታል፡፡
እንደምታውቁት፣ ከሳውዲ አረቢያ እንደምታውቁት ኢትዮጵያውያንን ብቻ ቢያግዙም/ቢያባርሩም ቅሉ ሌሎችን ዜጎችም እንዳባረሩ እንረዳለን… ባለፉት አስርት ቀናት እንዳየሁትም፣ ምክንያቱም በቤተሰብ ምጣኔ ዕቅድ እንደምንለው ለልጃገረዶችና ለሴቶች ክብካቤ እናደርጋለን፣ ከጣቢያዎች እርዳታ በመፈለግ ከሚጮሁ ሴቶች በቀጥታ ጥሪዎች ደርሰውኛል… በመቶዎቸ የሚቆጠሩትን በእርግጠኝነት ተቀብለናል፣ በሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን እንቀበላለን ብለን እንጠብቃለን፣ በእርግጠኝነት ለመናገር የምፈልገው ዜጎቻችንን ወደ አገራቸው እንዲመጡ ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነን፡፡
በጣም አዝኛለሁ፣ ስሜቴም ተጎድቷል፡፡ ለዚህም ነው ይህ ሁኔታ ከተጀመረ ወዲህ ባለው የጊዜ መደበላለቅ ምክንያት ወደዚህ ላለመምጣት ዶ/ር ተከስተን ጠይቄ የነበረው፡፡ ሆኖም ግን በዓለምአቀፋዊነት ትብብር መሰረት ህገወጦችን ማባረር/ከአገር ማስወጣት የምንችል ቢሆንም ይህንን ጉዳይ በሰከነና በሰለጠነ መልክ እናደርገዋለን፣ ምክንያቱም ይህ ድርጊት የጦርነት ሁኔታ አይደለምና፡፡ እንደዚህ ያለው ሁኔታ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው አገሮች በጦርነት  ላይ ሲሆኑ ብቻ ነው፣ ህዝብም በፈጠነ መልኩ ነገሩን ሊረዳው ይችላል፣ ነገር ግን በሰላማዊ ሁኔታ ሊሆን አይችልም፡፡
…በመሆኑም በዚህ መልክ በመጀመሬ አዝናለሁ፣ ይህ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ እየቆጠቆጠኝ የቆየ ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡
በእርግጥ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የአጭርና የረዥም ጊዜ መፍትሄ በማስቀመጥ ችግሮቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፣ ምክንያቱም ችግሮቹ ስር የሰደዱና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ ያለባቸው በመሆናቸው ነው፡፡ እንደምታውቁት ኢትዮጵያ እያደገችና ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት ምጣኔ እያስመዘገበች ነው፣ በዚህም አካሄድ ከጨለማው ዋሻ የውስጥ ጉዞ በኋላ ከጫፍ ላይ ብርሀን ይታየኛል፣ እና ይህንን ያለጥርጥር ተግባራዊ እናደርገዋለን፣ በዚህም ጥረታችን ድህነትን ተረት እናደርጋለን፡፡ በትክክለኛው መንገድ ላይ ነን፣ ሆኖም ግን ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እምነቴ የጸና ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ይሳካል ብለን አንጠብቅም፡፡
ነገሩን ለማታውቁት አንድ ነገር ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ነብዩ መሀመድ ታላቁን የእስልምና እምነት አስተምህሮቱን ሀ ብሎ ሲጀምር በደረሰበት መሳደድ ምክንያት ደቀመዝሙሮቹን/ተከታዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ነበር የላከው… ስለዚህ አዝናለሁ፣ ንግግሬንም እዚህ ላይ አቆማለሁ…ሆኖም ግን የሚሰማኝን ስሜት ሁሉ በዝርዝር በመግለጼ፣ ያለፉት 10 ቀናት በህይወቴ ካየኋቸው ነገሮች ሁሉ እንዴት መራር እንደነበሩና ይከሰታሉ ብለን የማንጠብቃቸው አስገራሚ ነገሮች እየሆኑ በማየቴ እዚህ በመካከላችሁ በመገኘት ለእናንተ ሀሳቤን በማካፈሌ ደስታ ይሰማኛል…::
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ በሳውዲ አረቢያ መንግስት አየተፈጸመ ያለውን አስደንጋጭ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል በማስመልከት የኢትዮጵያ “ቁንጮ የዲፕሎማት ሰው” እንደዚህ ያለ ተያያዥነት የሌለው፣ የተበታተነ፣ ዝብርቅርቅ ያለ እና እጅ እግር የሌለው ትንታኔ እና ገለጻ ሲያቀርቡ ስሰማ እጅጉን ነው ያዘንኩት፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከወባ ትንኝ ተመራማሪነትና ከመቅጽበት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በተቀየሩ ግለሰብ የአፍ ካራቴ ዥዋዥዌ ልምምድ መቀለጃ ሆነ! ማንም ሊያደርገው እንደሚችለው የአድሃኖምን ቅጥ አምባሩ የጠፋ ንግግር መሰረት በማድረግ የሚከተሉትን ጭብጦች መመርመር ተገቢ ይሆናል፡፡
1. አድሃኖም እንዲህ አሉ “…በቃላት ሊገለጽ በማይችል መልኩ በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ያደረሰውን ሰቆቃ ሲያስታውሱ “እስከ አሁን ድረስ ነገሩ እየቆጠቆጣቸው“ እና አሁንም ድረስ “እንዳዘኑ“ እና የሳውዲ አረቢያ መንግስት በኢትዮጵያውያት ሴቶች ላይ በሚፈጽመው ደባ ምክንያት ሰብአዊ መብታቸው እየተረገጠ ያሉ ሴቶች እገዛ ለማግኘት በሚያሰሙት ጩኸት “ስሜታቸው እንደተጎዳ“ ተናግረዋል፡፡ ይኸ “ታላቁ የዘመኑ ውሸት!“ ሊባል ይችላል፡፡
ምናልባትም አድሃኖም በእንግሊዝኛ ቃላት መካከል ያለውን ጥቃቅን ልዩነት ማስተዋል ባለመቻላቸው በተለይም ቀጥተኛ ያልሆነውን የአነጋገር ዘየ/colloquialism ተከትለው ይሆናል በማለት አስተያየት መስጠት ይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን እንደ ቁንጮ የዲፕሎማት ሰውነታቸው ለአላዋቂነት የቃላት አጠቃቀሞቻቸው ይቅርታ ሊደረግላቸው አይገባም (በእርግጥ የቃላት እና የሀረጎች አመራረጣቸው አመለካከታቸውንና ስሜታቸውን የሚገልጹ ቢሆንም)፡፡ በኢትዮጵያውያን/ት ላይ በሳውዲ አረቢያ መንግስት እየተደረገ ያለው ግፍ “እስከ አሁን ድረስ ነገሩ እየቆጠቆጣቸው“ እንደሆነ የሚገልጸው አባባል ተጎጂ ኢትዮጵያውያን/ት በሳውዲ አረቢያ ያሉበት ሁኔታ የንዴት ምንጭ እንደሆናቸውና ጥቂት እንዳሳሰባቸውም ጠቋሚ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ጉዳይ አይደለም እንደማለት አነጋገር ነው ፡፡ በዓለም ላይ የየትኛውም አገር የዲፕሎማሲ ቁንጮ የሆነ ሰው በዜጎቹ ላይ ኢሰብአዊና ኃላፊነት የጎደለው አያያዝ መደረጉን አስመልከቶ “እስከ አሁን ድረስ ነገሩ እየቆጠቆጠው” መሆኑን ለሌላ አገር ሰው ሲናገር አልተሰማም፣ አልታየምም፡፡
አድሃኖም በውል ያላጤኑት ቢሆንም ቃላት በዓለም አቀፍ የዲፖሎማሲው ቋንቋ ትልቅ ትርጉም አላቸው፣ ቃላት የዲፕሎማቶች ዓላማ ማስፈጸሚያ መሰረታዊ ሀብቶች ናቸው፡፡ የዲፕሎማቲክ ሰዎች እነርሱ በመረጧቸው ቃላትና የቃላት አጠቃቀም ዓለም እንዲቆምና እንዲሄድ የማድረግ ወይም አንዳንድ ጊዜም ሆን ብለው ለትርጉም ልቅ የሆኑ ወይም ደግሞ ውሱን የሆኑ ቃላትን በመጠቀም ዓላማቸውን ለማሳካት የሚሄዱበት ዘዴ ነው፡፡ የዲፕሎማቶች ቃላት ግልጽና ድብቅ ትርጉም ባላቸው መልዕክቶች የተሽሞነሞኑ እና ድብቅ ዓላማን ለማሳካት የተዘየዱ ማስፈጸሚያ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ በሰዋስዋዊው የቃላት አመሰራረትና በሚሰጡት ትርጉም ጥንቁቅነት በዲፕሎማሲው ቋንቋ ቃላት ሰላምን ያሰፍናሉ፣ ጦርነትን ያውጃሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዲፕሎማቶች ቃላት የዲፕሎማቶችን ግላዊ የሀዘን ስሜትና የስሜታቸውን መጎዳት ብቻ የሚገልጹ ሳይሆን ከዚህ በተጨማሪ የዲፕሎማቶቹን የሞራል ስብእና፣ የስቅይቱን ጥልቀትና የሀገራቸውን ህዝቦች ስሜት ሊያንጸባርቅ ይገባል፡፡
አድሃኖም በሳውዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ሁኔታ “እስከ አሁን ድረስ ነገሩ እየቆጠቆጣቸው“ እንደሆነ ሲገልጹ ለሳውዲ አረቢያ መንግስት አደገኛ የሆነ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ እንዲህም ብለው እየነገሯቸው ነው፣ አዲሱ የይስሙላው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማውገዝ በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው የተናገሩትን በመዋስ “የዘር አደን“ በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኛ ዜጎች ላይ በሳውዲ አረቢያ ፖሊሶችና ጋጠወጦች በየመንገዱ እየተደረገ ያለውን ሁከትና ትርምስ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ተገቢ የዲፕሎማሲ ንግግር ከተደረገ ይህንን አደገኛ ሁኔታ  እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሳውዲ አረቢያ እየተካሄደ ያለው ኢትዮጵያውያንን/ትን የማዋረድና ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት የመፈጸም ሁኔታ ትልቅና በጣም ትልቅ የሆነ አገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በግሌ ለምሳሌ በዋና የስራ ሰዓት ጊዜ የሚይዝ የትራፊክ መኪና መጨናነቅ የንዴት ደረጃየን ከፍ ያደርገዋል፣ የተሰጣቸውን የቤት ስራ ሳይሰሩ በሚመጡ ተማሪዎቼ ላይ የሚኖረኝ ንዴት ከልኩ ያለፈ ነው:: ሳውዲዎች በኢትዮጵያውያን/ት ላይ እየፈጸሙት ያለው ግፍ ግን እንድናደድ ብቻ አላደረገኝም፣ ደሜ እንዲፈላ ጭምር አደረገኝ እንጅ፡፡ የሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች በኢትዮጵየውያን/ት ላይ ሲፈጽሙት የነበረውን አረመኒያዊና ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት ስመለከት እሳት ነበልባል ሆኛለሁ፡፡ የሳውዲ አረቢያ ወሮበሎችና ጋጠወጦች በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ ሲፈጽሙት የነበረውን አረመኒያዊና ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብት ረገጣ ስመለከት በንዴት ድብን ብዬ አራሴን አስከ መሳት ደርሼ ነበር፡፡ በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኞች ላይ በሳውዲ አረቢያ ወሮብሎችና ጋጠወጦች እየተደረገ ያለውን ኢሰብአዊና ከህግ አግባብ ውጭ እየተደረገ ያለውን ጀብደኝነት የሳውዲ ገዥው አካል እያየ ጆሮዳባ ማለቱ የበለጠ እንድበሳጭና እራሴን እንድስት አድርጎኛል፡፡ የሳውዲ መንግስት ዓለም አቀፍ ሕግን በጠበቀ መልኩ በኢትዮጵያውያን ስደተኛ ሰራተኛ ዜጎች መብት አያያዝ ላይ ምንም ነገር ባለማድረጉ በጣም ተበሳጭቻለሁ፣ አማርሪያለሁም፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት በሳውዲ አረቢያ እየተፈጸመባቸው ያለው ግፍና መከራ አድሃኖምን ብዙም ያሳሰባቸውና ያስጨነቃቸው አይመስልም፡፡
በዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ቋንቋ መርህ መሰረት ጠንካራና ፊትለፊት በመግጠም የሚደረግ እና አስታራቂና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ ለስለስ ባለ ቋንቋ ለመጠቀም የራሱ ጊዜ አለው፡፡ በእውነቱ ይህ ታላቅ ሀገራዊ ውድቀት ነው፣ አድሃኖም በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት በውል የተገነዘቡት አይመስለኝም፡፡
2. ሳውዲ አረቢያዎች በኢትዮጵያውያን/ት ላይ እንዲህ በፈጣን መልኩ እየፈጸሙ ያሉት ከአገር የማባረርና የማስወጣት ሁኔታ “አንድ አገር በጦርነት በወደቀችበት ጊዜ የተደረገ ቢሆን ኖር ተቀባይነት ሊኖረው ህዝብም ሊረዳው ይችል ነበር” ብለዋል አድሃኖም፡፡ ከዚህ አንጻር አድሃኖም ያልተገነዘቧቸው በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ በጣም መሰረታዊ የሆኑ መርሆዎችና ህጎች መኖራቸውን ያሳያል፡፡ ከጦርነት ጋር በተያያዘ መልኩ ዜጎችን ከሀገር የማባረሩ ሁኔታን አስመልክቶ ያሉትን ህጎችና ልምዶች አንዳንድ ጊዜም የዘር ማጽዳት ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ አድሃኖም የተገነዘቡ አለመሆኑን ይህ ሁኔታ በግልጽ ያመላክታል፡፡ እ.ኤ.አ 1990ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ገደማ በሄርዞጎቪና እና ቦሲኒያ መካከል በተደረገው ጦርነት በርካታ የቦሲኒያ እስልምና እምነት ተከታዮች፣ ክሮሽያዎች፣ ሰርቦችና ቦሲኒያዎች ከትውልድ ቦታቸው የተቀነባበረ የማባረር/የማስወጣት ስልት በመጠቀም ተግባራዊ ተደርጎባቸዋል፡፡ ያ የጦር ወንጀለኝነት ነው፡፡ ይኸ እንዲሁ “ህዝብ በቀላሉ ሊረዳው የሚችል” ጉዳይ አይደለም አድሃኖም አንዳሉት፡፡ በጦርነት ጊዜ በኃይልና በማስገድደ ከአገር የማስወጣት አስፈላጊነት ለህዝቡ ደህንነት ሲባል በሚጠበቁ ሰዎች ወይም በጦር መሪዎች ላይ የሚፈጸም መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1949 የጸደቀው ስምምነት (IV) በጦርነት ጊዜ የሲቪል ሰዎችን ለመከላከል የተዘጋጀው ሰነድ በግልጽ ያሳያል፡፡ የስደተኞችን ጉዳይ አስመልክቶ በ1951 ስምምነት መሰረት በ1967 የስደተኞችን ሁኔታ አስመልክቶ የተዘጋጀው ፕሮቶከል እንዲሁም በአንቀጽ 3 በ1984 ማሰቃየትን በተመለከተ የተዘጋጀውን ስምምነት መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኞች ከማንኛውም ህገወጥ ማባረር/ማስወጣት ድርጊት መጠበቅ እንዳለባቸው በግልጽ ያሳያሉ፡፡ በጣም መሰረታዊ በሚባሉ የዓለም አቀፍ ህጎች፣ ደንቦችና መርሆዎች አንጻር አድሃኖም ያላቸው ግንዛቤ ሲመዘን በጣም አናሳ ሆኖ መገኘቱን ስናጤን እንደ ሀገር አሳሳቢ ሀገራዊ ኪሳራ መሆኑን ያሳያል፡፡
3. በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ ለሚፈጸመው ሰቆቃና አንገብጋቢ ችግር መፍትሄው ዜጎቹ ከዚያ ሀገር የሚወጡበትን ስራ ማፋጠን እንደሆነ አድሃኖም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን የኃይል እርምጃ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግድያና ማሰቃየት ማስቆም ጊዜ የማይሰጠው አጣዳፊ፣ ወሳኝ፣ አንገብጋቢ እና ክብደት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ አድሃኖም ይህንን ጉዳይ በሚመለከት እንደሚከተለው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ “በእርግጥ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት የረዥምና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን በመንደፍ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፣ ምክንያቱም እነዚህ ችግሮች ለብዙ ጊዜ የቆዩና ስር የሰደዱ በመሆናቸው ነው“ በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡ እርግጥ ነው የረዥምና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎች ሊቆዩ ወይም ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች፣ ወሮበሎች እና ህገወጦች በየዕለቱ እየተፈጸሙ ያሉ የውርደት ሰራዎች፣ ህገወጥ አያያዞች፣ ፍትህአልባነት እና ወንጀሎች በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሊቆዩ በፍፁም አይችሉም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ እየተፈጸመ ያለው መጠነሰፊ ኪሳራ ነው፡፡ ስቅይቱን በፍጥነት ለማስቆም አድሃኖም ምንም ዓይነት ሀሳብ የሌላቸው እና መፍትሄዎችን ያላመላከቱ በመሆኑ ይህ አንገብጋቢ አገራዊ ኪሳራ ነው፡፡
አድሃኖም እንዲህ ይላሉ፣ በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ትዮጵያውያን/ት ስደተኞች ላይ “እንዲህ ያለ ድርጊት ይፈጸማል ብለን በምንም ታምር አልጠበቅንም“፣ እንዲህም ይላሉ ለእራሳቸው፣ “ሁሉም ነገር የሚያስደንቅ ነው“፣ በመቀጠልም እንዲህ ይላሉ፣ “የረዥምና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ለማምጣት ለብዙ ጊዜ ጥረት አድርገናል“፡፡ ይህ የተምታታ እና የተዘበራረቀ አባባል እርስ በእራሱ የሚጣረስ ብቻ አይደለም፣  ሊታመን በማይችል መልኩ አሳሳች መግለጫ እና የአድሃኖምን የዋህነትና የዲፕሎማሲ  እውቀት እጥረትና ችሎታ ማጣት የሚያሳይ መገለጫ እንጅ፣ በሳውዲ አረቢያ የኢትዮያውያንን/ትን ሁኔታ በሚመለከት “ሁሉም ነገር የሚያስደንቅ ነው“ የሚለው የአድሃኖም አባባል ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም እ.ኤ.አ በኤፕሪል 2013 አድሃኖምና የእርሳቸው ገዥው አካል  የሳውዲ አረቢያ ገዥ በሀገሩ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ገብተው ምንም ዓይነት ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው በሀገሩ የግዛት ክልል ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር ሰራተኞችን ህጋዊ ለማድረግ ወይም ደግሞ ወደየመጡባቸው አገሮች እንዲመለሱ እና ህገወጥ ማባረር፣ እስራትና ስቅይትን ለማስቀረት በማለት ያስተላለፈውን ትዕዛዝ በሚገባ ያውቃሉ፡፡ የአድሃኖም ገዥው አካልም በተመሳሳይ መልኩ በሳውዲ አረቢያ ውስጥ ምንም ዓይነት ህጋዊነት  ሳይኖራቸው የሚሰሩና የሚኖሩ በርካታ ህገወጥ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን/ት እንዳሉ ከማመናቸውም በላይ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሳውዲ ገዥ እ.ኤ.አ በጁላይ 2013 በሀገሩ ውስጥ የሚገኙትን ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸውና ምንም ሰነድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች በማስመልከት ህጋዊ እንዲሆኑ ወይም ሀገር ለቀው እንዲወጡ አጽንኦ በመስጠት እ.ኤ.አ እስከ ኖቬምበር 2013 ድረስ ቀነ ገደብ መስጠቱን አድሃኖምና ገዥው አካላቸው በሚገባ ያውቁታል፡፡ ግና የአድሃኖም ገዥ አካል ከመስማት ባለፈ የአዋጁን እንደምታና ወደፊት በስደተኛ ዜጎቹ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጉኑ ሊያየው ስላልፈለገ የወደፊቱን ማቀድም አልቻለም፣ በቀጣይነት በገፍ ወደ ሳውዲ አረቢያ በሚጓዙ ዜጎች ላይ እንዲሁም በሳውዲ አረቢያ ፖሊስና ወሮበሎች በቀጣይነት ስለሚደረገው ጥቃት የሚሉት ነገር አልነበራቸውም፡፡ በአጭሩ ምንም ነገር ሳያደርጉ እጃቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ ሲመለከቱ በከንቱ ሳይጠቀሙበት ጊዚያቸውን አባክነዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እ.ኤ.አ በኖቬምበር 2013 በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ዜጎች ላይ ማህበራዊ ቀውስ ይደርሳል የሚለውን ሁኔታ እንዴት አድሃኖም በእርግጠኝነት መተንበይ አልቻሉም ይቻላል?
አድሃኖም ፈጣን የፖሊሲ እርምጃ ለመውሰድ ብቃት የሌላቸው ሰው መሆናቸውን የድርጊቶች ኩነት በተጨባጭ ያሳያል፡፡ እንደ “ቁንጮ የዲፕሎማሲ ሰው” ብዙ መማር ይጠበቅባቸዋል፣ እንዲሁም ወደፊት ሊከሰቱ በሚችሉ ነገሮች ላይ ትኩረት በመስጠት የነገሮችን የአመጣጥ ሁኔታና ችግሮችን አስቀድሞ በማየት ተጨባጭ መፍትሄ ለማምጣትና ወደተግባር ለመፈጸም የሚያስችል ብቃትን ሊጎናጸፉ ይገባል፡፡ ፈላስፋው ጎቴ የሚከተለውን ሲል እውነትም ትክክል ነበር፣ “ምንም  ድንቁርናን በተግባር ከማየት የበለጠ አስደንጋጭ ነገር የለም ብሏል።
አድሃኖም ያልተናገሩት ወይም ያላደረጉት፤
በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የኃይል እርምጃ ለማስቆም የኢትዮጵያ ገዥው አካል ስላደረገው ሁኔታ አድሃኖም አንድም ያሉት ነገር የለም፣ ሆኖም ግን አገዛዙ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት የረዥም እና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ለማምጣት ብዙ ርቀት የተጓዘ መሆኑን ከመግለጽ ውጭ ተጨባጭነት ያለው እርምጃ አልታየም፡፡ በተጨባጭ እየሆነ ያለው ግን አድሃኖም እና ገዥው አካላቸው አትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ዜጎቻቸው በሳውዲ አረቢያ መንገዶች እንደ አውሬ እየታደኑ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ከዳር ቆመው ጣቶቻቸውን በመቀሰር፣ ጭንቅላቶቻቸውን በመነቅነቅ ከመታዘብ ውጭ ሌላ መገለጫ የለውም፡፡ አድሃኖም በዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የኃይል እርምጃ ለማስቆም ምንም  ጥረት አለማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን ትንሿን ነገር ለዓም አቀፉ ማህብረሰብ በማሳወቅ በሳወዲ አረቢያ መንግስት ላይ ጫና እንዲደረግ እንኳን ሙከራ አላደረጉም፡፡ አድሃኖም ካልተናገሯቸው ወይም ካልፈጸሟቸው ጉዳዮች ውስጥ ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
በጠንካራ ቃላት የተዘጋጀ የውግዘት መግለጫ፤ አድሃኖም እንዲህ ብለዋል፣ “ገዥው አካል የሳውዲ አረቢያ መንግስት በግዛት ክልሉ ውስጥ ባሉ ስደተኛ ሰራተኛ ዜጎቻችን ላይ ያደረሰውን ጭካኔ የተሞላበት የኃይል እርምጃ እናወግዛለን፣ ይህ በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የለውም፣ የሳውዲ መንግስት ለጉዳዩ አጽንኦ በመስጠት ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ እናደርጋለን፣ ዜጎቻችን ባሉበት በክብርና በመልካም ሁኔታ እንዲያዙ ሆኖ ዜጎቻችንን ወደ ሀገራቸው የምንወስድ መሆኑን እናሳውቃለን“ የሚል ነበር፡፡ “ተቀባይነት የለውም“ የሚለው ቋንቋ በሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል፣ በፖሊስ ኃይሉ እና በወሮበሎች እየተፈጸመ ያለውን ዘገናኝ ጭካኔ፣ ለመናገር የሚዘገንን አረመኔነት፣ አስደንጋጭ ስቅይትና ወንጀለኝነት ለመግለጽ የሚጠቀሙበት የውግዘት ቃል ነው፡፡ እንደ አድሃኖም ግንዛቤ “ምርመራ“ ማለት የሳውዲ ገዥ ክፍል ከዚህ ከተፈጸመው ዘግናኝ ወንጀል አንጻር ጠንካራ እርምጃ ተወስዶ ማየት ነው፡፡
አድሃኖም “ተቀባይነት የለውም“ የሚለውን ቋንቋ በውል የተገነዘቡት አይመስልም፡፡ ይህ አባባል በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ የዲፕሎማሲ ሰዎች ምንም ነገር ሳይሉ አንድ ነገር እንዳሉ በማስመሰል የሚጠቀሙበት ባዶና መሰረት የለሽ ቃል ነው፡፡ ሁሉንም ነገር የሚል ትርጉም የያዘ ቃልም ነው…”ምንም ዓይነት ጠንቅ የለዉም አይኖረዉም ማለትም  ነው”:: እንደዚህ ነው እንግዲህ የዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ  ባህሪያት፡፡ አንድ መስመር ዓረፍተ ነገር ሁለት የማይገናኙ ዓላማዎችን ሊያስተላልፍ የሚችል መልዕክት ሊኖረው ይችላል፡፡ በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ አትዮጵያውያን/ት ላይ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት “ተቀባይነት የለውም” የሚል መልዕክት ለሳውዲ አረቢያ አምባሳደር በማስተላለፍ አድሃኖም በጉዳዩ ላይ የይስሙላ ስራን በመስራት ጉዳዩ አስኪረጋጋ ድረስ መጠቀሚያ ያደርጉታል፣ ከዚያ በኋላ ግን ሁሉቱም ወገኖች ወደነበሩበት ግንኙነት ተመልሰው የመሞዳሞ ስራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ቃሉን በትክክል ለመግለጽ “ተቀባይነት የለውም” የሚለው ቃል ብልህነት የጎዳላቸው ፉከራና ባዶ ኳኳታ በሚያሰሙ ምንም ነገር እና አንድም ነገር የማያደርጉ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡
የጥገኛውን ሀገር አምባሳደር በመክሰስ የብጥብጡን ሁኔታ እንዲረዳና በፖሊስና በህገወጦች የሚፈጸመውን ህገወጥ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ማድረግ፡ አድሃኖም የሳውዲ አረቢያ አምባሳደርን በመክሰስ እንዲህ ብለዋቸዋል፣ “የሳውዲ አረቢያ መንግስት ህገወጥ ስደተኞችን ለማስወጣት የተከተለውን መርህና የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣኖች በህገወጥ ስደተኞች ላይ የወሰዷቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ኢትዮጵያ ታላቅ አክብሮት አላት፡፡ እንዲሁም በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ የተወሰደውን ህገወጥ አያያዝና ግድያ ታወግዛለች“ ይላል፡፡ ግን ሰው  ምን ዓይነት አሽከርነትና ጫማ ላሽነት ውሰጥ ይዘፈቃል?! ለዜጎቹ የሚቆረቆር በምድር ላይ የሚኖር ማንም አገር ቢሆን የራሱን ዜጎች የስቃይ ሰለባ ላደረገ ሌላ አገር በምንም ዓይነት መልኩ ቢሆን “ክብር አለው” የሚል ቃል አይተነፍስም፡፡ አድሃኖም በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም፣ ምክንቱም ጉዳዩ ስለሳውዲ አረቢያ የግዛት ሉዓላዊነት ወይም ስለስደተኞች ፖሊሲ ጉዳይ አይደለም፣ ጉዳዩ የሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኛ ዜጎች ላይ እየፈጸመ ስላለው የሰብአዊ መብት ረገጣ ተገቢውን እርምጃ የመውሰድና ያለመውሰድ ጉዳይ ነው፡፡
ከዚህም በላይ አደሃኖምም ሆነ ወይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የሚኖርን ተቃውሞ በይፋ ለህዝብ አላሳወቁም፡፡ “የተቃውሞ ደብዳቤ” ወይም “የዲፕሎማቲክ ማስታወሻ” የአንድ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሌላው ጥፋት ለፈጸመው መንግስት ይቅርታ የማይደረግለትን የማይናወጥ አቋም በመግለጽ በይፋ ያሳውቃል፡፡ የተቃውሞ ደብዳቤው በምንም ዓይነት መልኩ ቢሆን “ተቀባይነት የለውም” የሚል ቃል አይጠቀምም፡፡ በጥቂቱም ቢሆን ስለ “”አሳሳቢ ጉዳዮች” እና ነገሮች መሻሻል ካላሳዩ ወደፊት “ጉዳት ሊያመጡ” የሚችሉ ጉዳዮችን በመጥቀስ ሊያሳውቅ ይችላል፡፡ አድሃኖም እንዳደረጉት እንቁጠረውና የተቃውሞ ደብዳቤ ለሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጻፉ መሆኑን ለህዝብ ይፋ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ በሚመለከት የአፍሪካ ህብረት የውግዘት መግለጫ እንዲያወጣ ማድረግ፤ እ.ኤ.አ በ2015 አስከሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ድረስ የአድሃኖምን ወንበር እያሟሟቁ የሚገኙት የይስሙላው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያ ደሳለኝ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት የዝውውር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በአፍሪካ መሪዎች ላይ የዘር አደን ይፈጽማል በማለት የዘር አደናውን ለማስቆም የአፍሪካ መሪዎችን በማሰባሰብና በማስተባበር ቆላ ደጋ በማለት ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ እና እንዲያውም የህብረቱ አባል አገራት የሮማ ስምምነተን በመጣስ ከአይሲሲ አባልነት እንዲወጡ በመሃንዲስነት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸወ የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ የአገራቸው ዜጎች በሳውዲ አረቢያ መንገዶች በፖሊሶች፣ በወሮበሎችና በህገወጦች “የዘር አደና” ጥቃት ሲፈጸምባቸው ትንፍሽ አላሉም፣ የጎመንዘር ቅንጣት የምታክል ድርጊት አልፈጸሙም፡፡ (በነገራችን ላይ ይህ ሁሉ ስቃይ በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ ሲፈጸም የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአገር ውስጥ ነበሩን? ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ “የዘር አደን” እየተፈጸመባቸው መሆኑን አስመልክቶ ቃል ትንፍሽ ሲሉ የሰማ ይኖራልን?)
አስቸኳይ ምርመር እንዲካሄድ ለተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ኮሚሽነር ማሳወቅ፣ ዩኤንኤችሲአር/UNHCR በተባበሩት መንግስታት በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት “ዓለም አቀፍ የስደተኞችን ጥበቃ ማድረግና በስደተኞች ችግር ላይ ውሳኔ የመስጠት እንዲሁም ስደተኞችን የመምራትና የማስተባበር ስራ” ያከናውናል፡፡ ስደተኞች አግባብ ባልሆነ መልክ ሲያዙና የሰብአዊ መብት ጥሰት ካለ የመመርመር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ አድሃኖም UNHCR ጉዳዩን እንዲመረምረው መጠየቃቸውን የገለጹበት ሁኔታ የለም፡፡ ምናልባትም ጥያቄ አቅርበው ከሆነ መጠየቃቸውን የሚገልጽ መረጃ አልቀረበም፡፡
እንዲህም ሆኖ UNHCR ስደተኛ ሰራተኞችን ግጭት ከተከሰተበት ቦታ ወደ ሌላ ለማዘዋወር የሎጅሰቲክስ እርዳታ ብቃት አለው፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.ኤ.አ በ2011 በሊቢያ ጸረ መንግስት አመጽ በተቀሰቀሰ ጊዜ UNHCR በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ ሰራተኞችን ከሊቢያ ወደ ጎረቤት አገሮች በማመላለስ የተቀላጠፈ ስራ ሰርቷል፡፡
ጉዳዩ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር/UNHCR እና በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጽ/ቤት/OHCHR ቀርቦ እንዲጣራ ቅሬታን ማስመዝገብ፤ ከOHCHR ዋና ዋና ተግባራት መካከል “የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ማጣራት” እና “የሰብአዊ መብት ጥበቃ ስራዎችን ማከናወን” ናቸው፡፡ የማጣራት ስራውን እንዲሰራ የሳውዲ ገዥ አካልን ከመጠየቅ ይልቅ አድሃኖም እንዲያጣሩትና ጣልቃ እንዲገቡ UNHCR እና OHCHRን መጠየቅ ነበረባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ከሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ መፍቀድ፤ ኢትዮጵያውያን/ት በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላይ በተፈጸሙባቸው እና እየተፈጸሙባቸው ባሉት የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ምክንያት ተዋርደዋል፣ ሀፍረትም ደርሶባቸዋል፡፡ አድሃኖም በኢትዮጵያ ጥገኝነት እንዲጠይቁ ነብዩ መሀመድ ተከታዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ጥገኘነት የሚጠየቅባት ምቾትና እርዳታ የሚደረግባት ቅዱስ ቦታ ነበረች፡፡ ኒልሰን ማንዴላና ሌሎች የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ አመራሮች እ.ኤ.አ በ1962 ስልጠና ለመውሰድ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ በአጼ ኃይለ ስላሴ ልዩ ትዕዛዝ መሰረት ኒልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው ተደርጎ ያለምንም ችግር ዓለምን ሲዞሩ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያውያን/ት በዓለም ላይ የሚከበሩና የሚሞገሱ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደካሞችና በባርነት የሚገዙ ሆነዋል፡፡ ያሰቡትን በመናገራቸው ይደበደባሉ፣ ይታሰራሉ፡፡ አዲስ አበባ በሚገኘው የሳውዲ አረቢያ አምባሳደር ፊት ለፊት በመገኘት ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማሰማት ሲሞክሩ የሳውዲ አረቢያ ፖሊስ በሀገሩ ኢትዮጵያውያንን/ትን ባስተናገደበት መጥፎ አያያዝ ሞዴልነት በተመሳሳይ መልኩም በአዲስ አበባ እንዲደረግ ሆኗል፡፡ ተዋርደዋል፣ ርህራሄ በጎደለው መልኩ ተደብድበዋል፣ በቁጥጥር ስርም ውለዋል፡፡ የገዥው አካል አፈቀላጤ የሆነው ሽመልስ ከማል ገዥው አካል በሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ብሏል፣ ምክንያቱም ይላል፣ “አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች በኢትዮጵያና በሳውዲ አረቢያ መካከል ጸንቶ የቆየውን ጠንካራ ግንኙነት የሚያበላሽና ጸረ አረብ የሆኑ መልዕክቶችን የያዙ በመሀናቸው ነው::
“ማንም ቢሆን ከሚቀርበው ጓደኛው ጋር የመስታወት ላይ ጠብ ያደርጋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ አድሃኖምና ገዥው አካል እንዲያስታውሱት የምፈልገው ነገር…”ለመበሳጨት ዘገምተኛ የሆነውን እሱን ተጠንቀቁ፣ ለመምጣት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ፣ ከመጣ ደግሞ ኃይለኛው እርሱ እንደሆነ እና ለብዙ ጊዜ የሚቆይ ነው፡፡ የተዋረደ ትዕግስተኝነት ወደ ቁጣ ይቀየራል::”
የአጣዳፊ ሁኔታውን ለመስራት ልዩ ግብረ ኃይል አያስፈልግምን? ኢትዮጵያ በሳውዲ አረቢያው እንደደረሰባት ዓይነት ኪሳራ በሚደርስባት ጊዜ ለዜጎቹ የሚያስብ ገዥ አካል ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትና ለማስተባበር የአስቸኳይ ጊዜ ማስፈጸሚያ ግብረ ኃይል ያቋቁማል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች ተመላሽ ስደተኛ ወገናቸውን ለማገዝ  እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እገዛ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ፡፡ አነዚህ አልተደረጉም:: በሳውዲ አረቢያ ያለው የኢትዮጵያውያን/ት ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልፋል፣ ስለዚህም ብዙ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለሳውዲ አረቢያ ኢንቨስተሮች በመስጠት የተለመደው ቢዝነስ በተለመደው ሁኔታ ይቀጥላል የሚል ስሌት በአድሃኖምና በገዥው አካል አቅዋም የተያዘ መሆኑም ይገልጣል፡፡
አድሃኖም ወደፊት አንደሚሉ ፤
አድሃኖምና ገዥው አካል ከሳውዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱትና ለሚቋቋሙበት የተመደበውን 50 ሚሊዮን ብር ተመድቧል ብለዋል:: ይህ ከባልዲ ውኃ አንዷ ጠብታ ናት፡፡ ይህም ገንዘብ ወደ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል፡፡ በዚህች በጣም ትንሽ በሆነች 2 ሚሊዮን ዶላር 200 ሺ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ከስደት ተመላሾችን ለማስፈር፣ ለማዘዋወርና ለማጓጓዝ የሚያስችል አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ገዥው አካል ይህን ያህል ገንዘብ ለእነዚህ ተግባራት ተብሎ የተያዘ ለመሆኑ ማረጋገጫ የለም፡፡ እ.ኤ.አ ጁላይ 2013 የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ተልዕኮ መግለጫ መሰረት ኢትዮጵያ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለምታስገባቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች ለሶስት ወራት ብቻ ሊያቆይ የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዳላት ይፋ አድርጓል፡፡
አድሃኖምና ገዥው አካል ብዙም ሳይቆዩ ተመላሽ ዜጎቸን ለማጓጓዝና ለማቋቋም የልመና ኮሮጃቸዉን አንጠልጥለው ወደ ዓለም አቀፉ የመንገድ ልመና መውጣቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ የሚገኘውን እርዳታ ለመቀራመት የሚችሉ የራሳቸውን አትራፊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስቀድመው ያቋቁማሉ፡፡ አድሃኖም ይለምናሉ፣ እንዲህ በማለት፣ “ከሳውዲ አረቢያ ለሚመለሱ ስደተኛ ዜጎች ገንዘብ በጣም ብዙ ገንዘብ እንፈልጋለን፡፡“ ጋሻጃግሪዎቻቸው በህዳሴው ግድብ ወይም በሌላ መልክ እንደሚጠሩት እንዳደረጉት ሁሉ በዓለም ዙሪያ በመሰማራት ኑስ ሳንቲም ሳይቀር ልመናቸውን ያጧጡፋሉ፡፡ ለገዥው አካል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች ይህ ሁኔታ ንፋስ አመጣሽ ዘረፋ ነው፡፡ በልመናው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚገኝ በመገመት እነዚህ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እጃቸውን በማሻሸት እና ለሀጫቸዉን በማንጠባጠብ ሰፍ ብለው ይጠባበቃሉ፡፡ ግን በልመና ብዙ ዕርዳታ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ነው በሳውዲ አረቢያ መንገዶች ላይ እጃቸውን በመዘርጋት ምጽዋት፣ ቢለምኑ አልደነቅም ያልኩት፡፡
ለኢትዮያችን አለቅሳለሁ፣ ለውዲቷ አገሬ! ግን “ከዋሻው መጨረሻ ብርሃን አለ“
አድሃኖም እንዲህ አሉ፣ “ከዋሻው መጨረሻ ብርሃን አለ፣ እና ይህን እውን እንደምናደርገው እናውቃለን፣ እና ድህነትን ተረት እንደምናደርገው ጥርጥር የለንም”፡፡ እኔ ደግሞ እላለሁ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ከዘውዳዊነትና ከአምባገነንነት ዋሻ መጨረሻ ብርሃን አለ፡፡ ከአድማስ ባሻገር አዲስ ቀን አለ፡፡ መደጋገፍ አለብን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁለት አስርት ዓመታት እና ከዚያ በላይ ከዘለቀው የጭቆና እና የመሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች እጦት ዋሻ ውስጥ ተጉዘን በድል አድራጊነት መውጣት አለብን፡፡
በሳውዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን/ት ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ አስመልክቶ የተዘጋጁትን የእኔን ትንታኔዎች ያነበበ ሁሉ እኔ በጣም ህግ አጥባቂና ሲበዛ ትንታኔ ሰጭ እንደሆንኩ ሊናገር ይችላል፡፡ እንዲያውም ታላቁን የሰው ልጅ ሰቆቃ “ለመፈላሰፊያ ትምህርታዊ ክህሎት” አውሎታል ብለው ሊከሱኝ ይችላሉ፡፡ ይህን ሊሉ ይችላሉ ምክንያቱም ለዚህች ተወዳጅ አገሬ ምን ያህል እንዳለቀስኩና ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጥኩ ስለማያውቁ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1948 በዚሁ ዓመት አፓርታይድ በአፍሪካ ህግ ሆነ፣ አላን ፓቶን እንዲህ ሲል ጻፈ…”ውዷ ሀገሬ አልቅሽ“… እና በደቡብ አፍሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ ያለውን የታሟጠጠ ተስፋ ገለጸ፡፡ የእኔም በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ላይ ያለኝ ተስፋ ፓቶን ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ፓቶን ሲጽፍ፣
ለተገነጣጠለው ጎሳ፣ ለወደቀው ባህልና ህግ አልቅስ! አዎ! ለሞተው ሰውዬ ድምጽህን ከፍ በማድረግ አልቅስ፣ ፍቅሩን ላጣችው ሴትና ለልጆቹ አልቅስ፡፡ ለውድ ሀገርህ አልቅስ፣ እነዚህ ነገሮች በእራሳቸው የመጨረሻ አይደሉም፡፡ ፀሐይ በመሬት ላይ ብርሀኗን ትፈነጥቃለች፣ በተወዳጁ መሬት ሰው ባልተደሰተበት ላይ፡፡ የልቡን ፍርሃት ብቻ ያውቃል፡፡
አኔም በኢትዮጵያ “ለተበጣጠሰው ጎሳ” አለቅሳለሁ፡፡ ከሰውነት በታች ሆነው በሳውዲ አረቢያ ለሚሰቃዩት ወንድሞቸና እህቶቸ በዝምታ አለቅሳለሁ፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚደፈሩት፣ ለሚደበደቡት እና በመስኮት ለሚወረወሩት፣ ከጣራ እና ከዛፍ ላይ ተሰቅለው ለሚሞቱትና በፈላ ውኃ ሰውነታቸውን ለሚጠበሱት እህቶቸ አለቅሳለሁ፡፡ በሳውዲ ሌባ ጭንቅላቱን ለሚበረቅሰው ወጣት አለቅሳለሁ፡፡ ነጻነት በማጣታቸው እና በሀገራቸው መብት እንደሌላቸው በመቆጠራቸው ምክንያት ሀገር ጥለው ለመሰደድ ለሚገደዱት ወጣት ወንዶች እና ሴቶች አለቅሳለሁ፡፡ ህይወታቸውን ለማሻሻል በማሰብ የየመንንና የሳውዲ አረቢያን በረሀዎች ሲያቋርጡ በሞት ለተለዩ ኢትዮጵያውያን አለቅሳለሁ፡፡ በየዕለቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲኦሉ ሳውዲ አረቢያ ለሚበሩ ወጣት ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅት አለቅሳለሁ፡፡
የ2005 ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ በኢትዮጵያ በየጎዳናው በግፍ ለተገደሉት ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ እንዲሁም አባቶች እና እናቶች አለቅሳለሁ፡፡ ለእህቴ ለርዕዮት ዓለሙ እና ለወንድሞች ለእስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ፣ አቡበከር አህመድ፣ እና በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች አለቅሳለሁ፡፡ መሪ በመምሰል በባዶ ልብስ ለተጀቦኑትና በሙሰኛ ሌቦች መዳፍ ስር ለወደቁት ኢትዮጵያውያን/ት አለቅሳለሁ፡፡
አዎ አለቅሳለሁ እናም አለቅሳለሁ፣ “ልቅሶዎቸ ያልተሳኩ ቢሆንም“ ለውዲቷ አገራችን አለቅሳለሁ፣ ግን እኮ ጩኸታችን ይሰማል፣ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ የአምባገነንነት ዋሻ ወጥቷል፣ ኒልሰን ማንዴላም ቃል ገብተዋል…”በፍጹም በፍጹም እና በፍጹም ይህች የተዋበች መሬት ተመልሳ የአንዱ በአንዱ ላይ መጨቆኛ አትሆንም፣ ክብር የታጣባት የተዋረደች ዓለም አትሆንም“::
ኢትዮጵያውያን/ት እንደገና ክብራቸውን ይቀዳጃሉ፣ እና በአገር ውሰጥም ሆነ በውጭ የተከበሩ ይሆናሉ፡፡ “የዓለም ተዋራጂ” ሆነው አይቀጥሉም፡፡ እና በጥልቅ ከልብ አምናለሁ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች፣ እንደገና አናለቅስም፣ ሀሴትንም እናደርጋለን፡፡

No comments:

Post a Comment