ይሄይስ አእምሮ
ከጥቂት ሣምንታት ወዲህ በተለይ የኢትዮጵያን የወያኔ መንግሥት በሚቃወሙ የሚዲያ ማዕከላት ዘንድ ዋና መነጋገሪያ ሆኖ የሚገኘው በሳዑዲ የኢትዮጵያውያን መንገላታትና መሰቃየት እንዲሁም ከኢሰብኣዊነትም በወረደ ሁኔታ በግፍ መጨፍጨፍ ነው፡፡ ዜጎቻችን በአካፑልኮ ቤይ የመዝናኛ ሥፍራ ሲንሸራሸሩ ከርመው የመጡ ይመስል ይህ ምስል በኢትዮጵያው የወያኔ ሚዲያ በአስደሳች መልክ እየቀረበ ቢሆንም ትክክለኛውን መረጃ ከአማራጭ የዜና ምንጮች እንደወረደ እንደምንከታተለው ከሆነ ግን ከሀገርና ከሕዝብ ኅልውና አኳያ ነገሩ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ከአንድ ጨለማ ውስጥ ብርሃን እንደሚጸነስ ሁሉ ከዚህ አስከፊ ገጠመኝ ውስጥ የፈነጠቀው የሕዝብ አንድነት ግን በሌላ ወገን ተስፋችን እንዲያንሠራራ አድርጓል፡፡ ፈረንጆቹ “blessing in disguise” ወይም “mixed blessing” እንደሚሉት ይህ መጥፎ አጋጣሚ ሊረሳ የተቃረበውን የሕዝብ አንድነት በማደስ በመላው ዓለም የተበተነው ኢትዮጵያዊ በአንድነት ቆሞ ድምፁን እንዲያሰማና ለጋራ ኅለውናው እንዲያለቅስ አስችሎታል፡፡ በተመሳሳይም የሕዝቡ ስሜትና እውነተኛ ፍላጎት በየስብሰባዎቹና ሰላማዊ ሰልፎቹ ሲንጸባረቅ እንደተመለከትነው ወያኔን ከመሰሉ በርካታ ከፋፋይ የዘር ፖለቲከኞችና የሃይማኖት ቡድኖች ሸረኛ ሤራ ባፈነገጠ መልኩ በአንድ ሉዓላዊ መንግሥትና በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ሥር የመኖር የቆዬ ኢትዮጵያዊ አብሮነቱን የታዘብንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በዚህ ስቃይ ለማትረፍ የሚፈልጉ በተለይም ወያኔዎችና መሰል ልበ ደንዳናዎች ለምርጫ ዝግጅት በፕሮፓጋንዳነት ሲጠቀሙበት፣ ለገቢ ማግበስበሻም ከማዋል እንደማይመለሱ እየተነገረ ነው፡፡
ከጓደኞች ጋር ስንወያይ አንዳንዶቻችን ይህ ነገር በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ የተነጣጠረ ሣይሆን በአጠቃላይ በሰው ልጅ ኅልውና ላይ የተቃጣ ታላቅ የክፍለ ዘመኑ ወንጀል መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ስለዚህ ማፈር ያለበት ነጭ ጥቁር ሳይል የሰው ልጅ በአጠቃላይ እንጂ ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም ወደሚለው እሳቤ አዘንብለናል፡፡ አንድ የዓለም ዜጋ በመጥቆር በመንጣቱ ወይም በመክበር በመደኽየቱ፣ በዚህ ወይ በዚያ ዘውግ አባልነቱ፣ በዚያ ወይ በዚህ ቋንቋ ተናጋሪነቱ፣ ወይም በመስለምና ባለመስለሙ፣ በክርስትና እምነትም በመጠመቁ ወይ ባለመጠመቁ ሣይሆን በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ግፍ የሚደርስበት ከሆነ ነግ ከነግ ወዲያ ታሪክ ሲለወጥ ይህ ዓይነቱ ውርጅብኝ በማንም ሌላ ወገን ላይ እንደማይደርስ ማንም ዋስትና ሊሰጥ አይችልም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ዕልቂት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአይሁዶች ላይ ከደረሰው ቢበልጥ እንጂ አይተናነስም፤ አሁን በኢትዮጵያውያን ላይ በሀገራቸው ውስጥም ሆነ ከሀገራቸው ውጭ እየደረሰባቸው የሚገኘው ዕልቂት ሩዋንዳና ዩጎዝላቪያ ወይም ኢራቅና አርመን ውስጥ ከደረሰው ጭፍጨፋ ቢብስ እንጂ አያንስም፡፡ መነሻ ምክንያታቸው የሚለያዩ ግን ይበልጡን ከኢኮኖሚ ጥቅምና ከዓላማ ቁርኝት ጋር የሚያያዙ የሰው ዘር ፍጅቶች በየዘመናቱ በብዙ ሀገራት ተፈጽመዋል፤ አሁንም ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ግንዛቤ ያላገኘው ነገር በአንዱ ላይ የሚፈጸመው ነገር በለሌላው ላይ እንደተፈጸመ ያለመቁጠር ነው፡፡ ይህ ትልቅ ዓለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ በአንድ የየትኛውም ሀገር ዜጋ ላይ የሚደርስ ችግር በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ እንደደረስ ችግር ካልተቆጠረ በሰው ልጆች አጠቃላይ አስተሳሰብ ላይ የተዛባ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ይህ የተቃወሰ አስተሳሰብና አመለካከት መፍትሔ ካላገኘ የሰው ልጅ በውድቀት መንገድ እንደነጎደ ይቀጥላል ምፅዓቱንም ያቃርባል እንጂ ዓለማችን ወደተሻለ ኅሊናዊና ቁሣዊ የዕድገት ጫፍ አትደርስም፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው መከራና ውርደት ወቅቱን ጠብቆ ነገ በሌላ ሕዝብና መንግሥት ላይ ይደርሳል – እንደእስካሁኑ ሁሉ፡፡ ይህ አነጋገር የትንቢት ጉዳይ ሣይሆን ማንም አእምሮ አለኝ የሚል የዓለም ዜጋ ሁሉ ሊረዳው የሚችል ነባራዊ እውነታና የማይሸሹት ወረፋ ነው – ወረፋ እስኪደርስ ያለው የጊዜ እርዝማኔ እያነሆለላቸው ብዙዎች ይሞኛሉ፡፡ ያዋጣ የነበረው አካሄድ ግን በምንም ዓይነት የልዩነት አጥር ራስን ሳያካልሉ በሰው ልጅነት ብቻ አንዱ የአንዱን ችግር ለማስወገድ መጣር ነበር፡፡ በሆነ አጋጣሚ አንድኛችን ከሌላኛችን በተለዬ ሁኔታ ወደአውሬነት በምንለወጥበትና እንደሳዑዲዎች አንድ ምሥኪን ወገን ላይ ቀን የሰጠንን ኃይልና ጉልበት በምናሳይበት ጊዜ በዝምታና በአግራሞት ማለፍ ሣይሆን ሃይ ብንልና ብናስቆም ተጠቃሚዎቹ ሁላችንም የሰው ዘሮች በሆንን ነበር፡፡ ሰዎች ግን ለዚያ አልታደልንምና የዘራነውን እንዳጨድን ዝንታለማችንን በየተራ ስናለቅስ እንኖራለን፡፡ ወደኋላው ላይና ቋቱ ሲሞላ ግን ሁላችንም በኅብረት የምናለቅስበት ዘመን መምጣቱ አይቀርም – ያኔ ታዲያ አልቃሽም አስለቃሽም፣ ፊሽካ ነፊም አስተኳሽም … ሁሉም ተያይዞ የደም ዕንባ እንደጎርፍ ያወርዳል፡፡ የምናስቀምጠው ነገር ሁሉ የኛው ነው – ማንም አይወስድብንም፡፡ በባንክ የምናኖረውን ገንዘብ ሲያስፈልገን አውጥተን እንደምንጠቀምበት ሁሉ በሰዎች ላይ የምንሠራውን የግፍ መዝገብም ሁሉ የምናወራርድበት ጊዜ ሲመጣ በእጃችን የገቡ ሌሎች ምሥኪኖችን ባስለቀስነው መጠንና ከዚያም በላይ እኛም እናለቅሳለን፡፡ አሁን ግን በብረት አጥር ውስጥ የምንኖርና መቼም ቢሆን ምንም ችግር እንደማይደርስብን የምንቆጥር ወገኖች አንዳችን በአንዳችን ችግር እየተዝናናን መኖርን መርጠናል፡፡ የምንመርጠው መንገድ ሁሉ ግን አዋጭ ሊሆን እንደማይችል ከታላቁ መምህር ከታሪክ መማር በተገባን ነበር፡፡ ያለቀሱ ይደሰታሉ፤ ያስለቀሱም ያለቅሳሉ፡፡
ዐረቦች በእኔ ዕድሜ ኢትዮጵያ ውስጥ በርሜል ገፊ ነበሩ፡፡ የሚገፉት በርሜልም የነዳጅ ሣይሆን የውሃ ነው፡፡ ከአምስትና ከአሥር ኪሎ ሜትሮች ከሚገኙ የወንዝና የጉድጓድ ውሃዎች በሽክናና በቅል እየቀዱ ሃዲድ በተገጠመላቸው በርሜሎች በመግፋት ለሀብታም ኢትዮጵያውያን እየሸጡ በሚያገኙት የላብ ፍሬ ይተዳደሩ ነበር – የዛሬውን አያድርገውና፡፡ ዛሬና አሁን ግን ያን መገፋታቸውን ፈጣሪ ተመልክቶ ይሄውና በየሥፍራው እንደምንጭ እየቆፈሩ በሚያወጡት ነዳጅ ጠግበው ይሠሩትን አጥተዋል፡፡ ለዚህም ያበቃቻቸው ባለብዙ ካርድ ሀገር የሆነችው አሜሪካ ናት፡፡ ገንዘብ በፍጥነት የሚገባለት ጭንቅላት ውስጥ ደግሞ የሚያስብ አንጎል አይኖርም፤ ገንዘቡ ወደ ኪስ ሲንዶለዶል አንጎል ከጭንቅላት እየወጣ ወደከርስ ወርዶ ይደበቃል፡፡ ዐረብ ደግሞ ስናየው አብዛኛው ሃይማኖት የለሽ ጥጋበኛ ነው፡፡ እንደዐረብ አስመሳይና መረን የለም፡፡ ዕውቀቱ ሣይኖር ፔትሮዶላሩ ተትረፈረፈላቸውና የሚሆኑትን አጡ፡፡ ዕድሜ ለአሜሪካ ሥልጣኔን በገንዘባቸው ከአሜሪካና አውሮፓ አመጡላቸው – ዐረቦች የዛሬ ስንት ዓመት ከተማቸውን በፍየልና በዓሣሞች ያስጸዱ እንዳልነበር ዛሬ የሀበሻ ጉልበትና የአሜሪካን ቴክኖሎጂ አጠገባቸው፡፡ እነዚህ ለይስሙላ “አላሁኣክበር” እያሉ ሃይማኖት ያላቸው የሚመስሉ ስድ ሰዎች በተለይ ሀብታሞቹና የቤተ መንግሥት ልዑላኑ የሚሠሩትንና በኪታቦቻቸው የሠፈሩትን ቀኖና ሃይማኖት ብናስተያይ ከሞላ ጎደል ሁላቸውም የሰይጣን አምላኪዎች መሆናቸውን መረዳት አይከብደንም፡፡ እነዚህ የለዬለትን ጥቁር ሰይጣን አምላኪ ዐረቦች በግልጽ ባይሆንም ብዙዎቹ በኅቡዕ ሉሲፈርን ከሚያመልኩ የሩቅ አጋዦቻቸውና የሀብት ተጋሪዎቻቸው ነጫጭባዎች ጋር እየተመሣጠሩ ዓለምን ከሃይማኖት፣ ከሞራልና ከባህላዊ ትውፊቶች አንጻር እያላሸቋት ይገኛሉ፡፡ የሁለቱም እምነት አንድ ነው፤ በገራምነት ሉሲፈር የተሻለ ቢሆንም ሲመጣበት ከሰይጣን ባልተናነሰ ቁጡ ነው፤ ለአንድ ክፋት ተመጣጣኝ ደግነት እንዳለው የሚያምኑት ሉሲፈራውያን ለጥቅማቸው ሲሉ ከሰይጣናውን በማይተናነስ ሁኔታ ዓለምን እስከመሸጥና መለወጥ ይደርሳሉ፡፡ የሁለቱም የእምነት መሠረት ገንዘብ ነው፡፡ ገንዘብ ሁሉን ያደርጋልና ሥልጣንንና ገንዘብን የተቆጣጠረ ወገን ሁሉ ያሻውን መሆንና ማድረግም ይችላል፡፡ ዴሞክራሲ፣ ፍትህና ነጻነት ጭምብሎች ናቸው – ለሁሉም እኩል የማይሠሩ የሚጠሉትን የማንበርከኪያ ካርዶችም ጭምር፡፡ ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ የተባለው ለጊዜውና በአሁኑ የዓለማችን ቅርጽ እውነት ነው፡፡
ገንዘብ ካለህ ዴሞክራሲን ከአሜሪካም ሆነ ከእንግሊዝ ትገዛለህ፤ ገዝተህም ለሕዝብህ ታድላለህ፤ አድለህም “ዴሞክራሲን ለሕዝቤ አደልኩ!” ብለህ ብትናገር ትታመናለህ፡፡ ባትታመንም በዴሞክራሲያዊነትህ ተቀባይነትን አታጣም፡፡ ዕድሜ ለገንዘብህ፡፡ ድሃ ከሆንክ ግን በኢዴሞክራሲያዊነት፣ በአሸባሪነት፣ በሰብኣዊ መብት ጣሸነት፣ በምርጫ አጭበርባሪነት፣ … ትወቀሳለህ፤ ወደ ጓንታናሞ ልትላክና ልትበሰብስ ዕድል ከቀናህም ወደዘሄግ የነሱው መሣሪያ ልትቀርብ ትችላለህ፡፡ በአይኤም ኤፍና በዓለም ባንክ ልምጮችም ልትሸነቆጥ ትችላለህ፤ በልዩ ልዩ ማዕቀቦችና ጠና ሲልም በኔቶ ጦርና በተናጠል የኃያላን ብትርም ልትኮረኮም ትችላለህ፡፡ ዓለማችን እንዲህ ዐይናቸውን በጨው ባጠቡና ባፈጠጡ መድሎዎች የተሞላች ናት፡፡ አንበሣ ምን ይበላል ተበድሮ ምን ይከፍላል ማን ጠይቆ ነው ነገሩ – ግን አይምሰልህ – የቀንም ቀን አለው ፤ የጀግናም ጀግና አለው፤ ፍርድ ቢዘገይ አይቀርም፡፡ እናም ወዮ እንላለን – ወዮ ለቀኑ፡፡ ከሳዑዲና ከመሰል ጭራቅና ሰይጣን መንግሥታት አንሶላ ለምትጋፈፈዋ የሉሲፈር ሀገር ወዮላት! የ”ወዮላት!” መንስኤውም ፍርደ ገምድልነቷና ያንን ተከትሎ ቢሊዮኖች መከራና ስቃይ ውስጥ መግባታቸው ነው – ሚዛናዊ ፍርድን የማያውቅ እንዲያውቅ የሚገደድበት አጋጣሚ ይመጣለታል – ወደደም ጠላም፡፡ ይህች ሀገር የምትለውንና የምትሠራውን አጥኑ፡፡ ያለባትንም ወዮታ ልብ በሉ፡፡ የአሁኑንም ብቻ አትመልከቱ፡፡ ለዚህ ለዚህማ ኢትዮጵያም በዓለም ከነበሩ አራት ኃያላን መንግሥታት አንዷና እስከየመንና ከዚያም ባለፈ የምታስገብር ታላቅ ሀገር ነበረች፡፡ ብዙ የአሁን ነገሮች ታሪክ የሚሆኑበት፣ ብዙ የወደፊት ነገሮችም የአሁን የሚሆኑበት ዕፁብ ድንቅ ሁኔታዎች ይከሰታሉና እንዳለ የሚቀር፣ እንደቀረም የሚኖር ነገር አለመኖሩን ማስታወስ ይገባል፡፡ ይህች ቀን በቅርብ ታልፋለች፡፡…
በልጅነቴ ቤተሰብ ወደሱቅ ሄጄ ዕቃ እንደገዛ ይልኩኝ የነበረው “ዐረብ ቤት ሄደህ ይህን ዕቃ ገዝተህ ና!” እንጂ ወደሱቅ ሂደህ ይህን ወይ ያን ግዛ አይሉኝም ነበር፡፡ በ”ሰይቼንቶ ሄድኩ” ይባል የነበረውና አሁንም ድረስ በአንጋፋ ዜጎች የሚባለው የመጀመሪያዋን የጣሊያን ታክሲ መኪና እንደሚያስታውሰን ሁሉ ዐረብ ቤትም የሚያስታውሰን የሱቅ ሸቀጦች ይበልጡን በዐረቦች መጀመራቸውን ወይም በነሱ ይካሄዱ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእኛም በላይ የነሱ ቤት ነበረች፡፡ “ፈረስት ሂጅራ”ን ትተነው ትናንትናና ከትናንት ወዲያ በነገሥታቱ ዘመን የአሁኗ ኢትዮጵያ በልጽገውና ከብረው ከእኛው ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ እየተዘባነኑ የሚኖሩባት የእኩል ሀገር ነበረች – ለነገሩ ኢትዮጵያ ለውጪዎች እንጂ ለራሷ ልጆች ሆና አታውቅም – ሀገራችን ብዙውን ጊዜ የሚጠቅማትን ከማይጠቅማት ያለመለየት ችግር አለባት፡፡ ዛሬ ወያኔ የሚባል ሀገር አጥፊ አንበጣና ተምች መላዋ ሀገራችንን ቀስፎ ስለያዛት የተለዬ ውርደት ገጠመንና ለዚህ ውርደት ተዳረግን እንጂ ዐረቦች ልብ ኖሯቸው እንዲህ ሊጫወቱብን የሚቃጡ አልነበሩም፡፡ ጊዜ ነው፡፡ ጊዜ ሁሉም ነገር ነው፡፡ ‹ጊዜ ባለውሉ› ሁሉንም ያሳያል፡፡ … ዕድሜ ከሰጠን ደግሞ ወደፊት ይህን ሂሳባቸውን ሲያወራርዱ እናይ ይሆናል፡፡ አንድዬን ለበቀልና ለአጸፋዊ ምላሽ ማን ብሎት? አሁን አሁንስ ፈጣሪ ለዚህ ተግባር ብቻ ያለ ይመስለኛል – ለቅጣትና የኃጢኣት ዋጋን ለመስጠት፡፡
የሆኖ ሆኖ ግን ኢትዮጵያዊ መንግሥት ስለሌለን እየደረሰብን ያለው ይህ ግፍና ቅጣት በኛ ላይ ብቻ የወረድ የውርደትና ቅሌት መዓት ሣይሆን በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለ መቅሰፍት መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ በሳዑዲ አንድ ዜጋ አለኃጢኣትና አለወንጀል ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ በጠራራ ፀሐይ ታረደ ማለት የታረደው ሰው በሃይማኖትና በፆታ ወይም በመልክዓ ምድር ሳይወሰን ነጭም ነው፤ ጥቁርም ነው፤ ቢጫም ነው፡፡ አለፍርድና አለአበሳው የታረደው ሰው ሁሉንም የሰው ዘር የሚወክል እንጂ አንድን ሀገር ብቻ ለይቶ፣ የአንዲትን ሀር ዜጎች ብቻ አጣቅሶ በውርደት የሚያስጠራ ክልላዊ ወይም ብሔራዊ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይህን ማድረግ ድፍረት እንጂ ሌላ ባለማስፈለጉ በማንም ላይ እንዲህ ማድረግ ቀላል ነው፡፡ በአሳቻ ቦታ አንድን ነጭ አሜሪካዊ ማረድ ወይም ጠቃሚ የሰውነት ብልቶቹን እያወጡ ለሀብታም መሸጥ ቀላል ነው፡፡ በአሳቻ ቦታ አንድን ነጭ እንግሊዛዊ ወይ ሞስኮባዊ ማረድ ቀላል ነው፡፡ በተመቸ ሥፍራ አንድን ነጭ እስራኤላዊ አንቆ በከንቱዎች ዘንድ መዘባበቻ ማድረግ ቀላል ነው – በአልቃኢዳዎች ሲደረግ የነበረም ነው፡፡ አደጉ ከተባሉ ሀገራት የተመለመሉና አንቱ በተባለ ዘመናዊ የጦር ሥልት ሠልጥነው ለግዳጅ የተሠማሩ “የሰለጠነው ሀገር” ወታደሮች ኢራቅ ውስጥ ሬሣ ላይ ሲሸኑ አይተናል፤ ያኔም በዓለም የሥልጣኔ ደረጃ “ምጥቀት” ተደንቀናል – ከዚህች ሰዎች ሰዎችን ከምድረ ገጽ ሊያጠፉ አሰፍስፈው ከሚታዩባት፣ የሞተ ሰውን ሳይቀር በ”ማሰቃየት” ሰይጣናዊ እርካታ ለማግኘት ከሚማስኑባት ከዚህች ድውይ ዓለም፣ ሳዑዲዎች እየፈጸሙት ከሚገኘውና ከመሳሰለው አረመኔነት ሌላ ምን ይጠበቃል? ዕውር ዕውርን እየመራው ገደል እንጂ ገነት አይጠበቅም፡፡
በመሠረቱና በእውነትም ብዙ ክፉ ነገሮችን ማድረግ በጣም ቀላል ነው፡፡ ዋናው ነገር ልክ እንደጥጋበኞቹ ዐረቦችና ተባባሪዎቻቸው ወያኔዎች ኅሊናን የመሳትና ወደአውሬነት የመለወጥ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ተዋራጁ ጨካኙ አውሬና ሰብኣዊነት በአጠቃላይ እንጂ የሚታረደውማ ዋናውን የዕልቂት በርኖስ ተከናንቦት እያለ የምን ውርደትን መደረብ ነው? እውነትን መነጋገር ከተፈለገ እንግዲያውስ የታረደ ከበረ፡፡ የታረደ በፈጣሪ ዘንድ የሰማዕትነትን ካባ ተጎናጸፈ፡፡ በከንቱ ጭዳ የሆነ የዘላለም ክብርን አገኘ፡፡ ተጠየቁ እንደዚህ ነው፡፡ የተዋረደው እዳር ቆሞ “አይዞህ ወንድሜ እረዳቸው፤ ቀብጠዋልና ጉልበትህን አሳያቸው፤ እኛን ጠልተው ከሀገር ስለወጡ ቀኝ እጃችንን አውሰንሃልና እንደፈለግህ አድርጋቸው” እያለ በስቃይ የሚደስት ወገን ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ወዮ ለዚህ ዓይነቱ ፍጡር! እናም ውድ ኢትዮጵያውያን ለቅስቀሳ ፍጆታው ያህል ልክ ነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተዋርደናል፤ ተንቀናል፤ ከዚያም በላይ፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ግን የተዋረደው ዓለም ነው፤ የተናቀው የሰው ልጅ ዘር በአጠቃላይ ነው፤ የታረደው በትዕቢትና በዕብሪት አንገታችንን እየቆለመመ በሠይፍና በጎራዴ እየቀነጠሰን ያለው በሌላኛ ጠርዝ የሚገኘው የሰይጣን አሽከርና ሎሌ የሆነው የሰው ልጅ ነው፡፡ እንጂ ኢትዮጵያማ በአሁኑ ሰዓት በጽርሓ አርያም ከሁሉም በበለጠ ክብርና ሞገስ እየተሸሞነሞነች ናት፡፡ የዚህን አያዎኣዊ(paradoxical) አነጋገር አንድምታዊ ፍቺ ወደፊት ምናልባትም በቅርብ የምናየው ይሆናል፡፡ … የተዋረድን የመሰልነው ደግሞ በውጭ ብቻ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ወያኔ እስካለ ክብር የለንም፤ ከነአካቴውም እንደሰው አንቆጠርም፡፡ የሁሉም መጫወቻ ነን፡፡
እንደብዙዎች ዜጎች ኢቲቪን አልመለከትም፡፡ ስመለከት በሽታየን የሚቀሰቅስ አንዳች ነገር ስለማገኝ አላይም – ስህተት ነው – ግን ምን ላድርግ፤ ከጤና የሚበልጥ ነገር ደግሞ የለም፡፡ ዛሬ ለምሳሌ ትልቅ በሽታ ነው የተቀሰቀሰብኝ፡፡ ወደሌላ ጣቢያ ላልፍ ስል ድንገት ኢቲቪን ስከፍት ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚባለው ዳግማዊው መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርስ በወቅቱ የወገኖቻችን አሰቃቂ ጉዳይ በ”ጋዜጠኛ” እየተጠየቀ አየሁ፤ ኃይለማርያም ደንቆሮና በልጆች ቋንቋ ጀዝባ መሆኑን ዛሬ ከእስከዛሬው በበለጠ ልብ አልኩ፡፡ ራሴን እንደምንም አሳምኜ ትንሽ ልከታተል ወሰንኩና ማየቴን ቀጠልኩ፡፡ ግን የጋዜጠኛ ተብዬውና የሰውዬው የአቀማመጥ ሁኔታ ራሱ ትልቅ የፕሮቶኮል ችግር ስላለበት መከታተል አትበሉት – እየቀፈፈኝ እንደምንም ለጥቂት ደቂቃዎች ታገስኩና ተከታተልኩ፡፡
ጋዜጠኛው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬው ደግሞ ጋዜጠኛ መስለዋል፡፡ ጋዜጠኛው እግሮቹን አጣምሮ ተንቀባርሮና እጅግ ተዝናንቶ ‹ሲጠይቅ›፣ ኃ/ማርያም እግሮቹን በሥርዓቱ ዘርግቶ ሽቁጥቁጥ እያለ ሲመልስ አንጀትን ይበላል – በ”ሥርዓቱ” ባልኩበት መንገድ መቀመጡ ጥሩ ሆኖ የ“ጋዜጠኛው” “ጠቅላይ ሚኒስትራችን”ን በማንጓጠጥ መልክ እግሮቹን አጣምሮ መጠየቁ ነው የቆጨኝ – በጠቅላይ አሽከሩ አማካይነት የናቁን ግብጾችና ሳዑዲዎች ብቻ ሣይሆኑ ጋዜጠኞቻችንም ናቸው ማለት ችያለሁ፤ ወያ በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማዋረድ የማይፈነቅለው ድንጋይ አለመኖሩን ስረዳ የወያኔን ሥነ ልቦናዊ ደዌ የክብደት ደረጃና የኛን የምሕረት ዘመን መንቀራፈፍ አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ነገር መለስን እንዳንረሳ ሲባል በወያኔዎች ሆን ተብሎ የተቀናበረም ይመስላል፡፡ የሚናገረውን ብቻም ሣይሆን እንዴት መቀመጥ እንዳለበትም መመሪያ ቢጤ ሳይሰጡት አልቀረም፡፡ ቤተሰቤ በሙሉ ነው በዚህ ነገር የተሸማቀቀው፡፡ በርግጥም አቶ መለስን አስታወስነው – ተሳክቶላቸዋል፡፡ አቶ መለስ ‹ጋዜጠኞቹን› እንዴት እንደሚገላምጣቸውና አጥንተው ከመጡት ይጠይቁትን ያሳጣቸው እንደነበር ትዝ አለኝ፡፡ ከመሞቱ አጎደለን ማት ነው? በርግጥም እኮ መለስ ቢኖር ኖሮ ሳዑዲዎችም ይህን ያህል አይማግጡም ነበር ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ በርግጥም እኮ መለስ ቢኖር ኖሮ ግብፆች በኃ/ማርያም ላይ እንዳፌዙበት በርሱ ላይ አያፌዙበትም ነበር፡፡ ስለዚህ ወያኔ የቀረው ጊዜ አንድ ወርም ይሁን አንድ ዓመት ለምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዱ ወያኔ አይሆንልንም? እውነቴን ነው – እንደለመድነው አንዱ ትግሬ ቁጭ ይበልበትና ይህን ኮንዶም ሰውዬ ወደማስተማር ሙያው ይመልሱት፡፡ “ውርደታችን” እኮ ለከት አጣ፡፡ በንነው እስኪጠፉ ድረስ በዚህች እንኳን አንዋረድ፡፡ በአሁኑ ሰዓት እኮ ኢትዮጵያውያንን እንደውዳቂ ዕቃ የማይቆጥርና እንደጠፍ አህያ ልቡ እስኪጠፋ የማይጭን የለም፡፡ እስኪያልፍ ያለፋልና አይዞን!!!
በቅድሚያ ይህ ሰውዬ ብዙዎች እንደሚሉትና በብዙዎች እንደሚታመነው ከአንድ ሀብታም ሰው የቤት ጠባቂ ያነሰ የስብዕና ደረጃና የሥራ አፈጻጸም ሥልጣን ያለው መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ነገር ነው፡፡ የዚህ ሰውዬ ጭንቅላት ሥሪት ምን እንደሆነ ግራ የሚያጋባ በመሆኑ እንጂ እኔ እሱን ብሆን እንደዚህ መሣቂያና መሣለቂያ ሆኜ መኖርን አልመርጥም ነበር – የሰው ተፈጥሮ ግን በውነቱ አስገራሚ ነው፡፡ ከኃይለማርያም ደሳለኝ ይልቁንስ የፍቅር እስከመቃብሩ ፈረጃ ይሻላል፤ “ፈረጃ በሚለው የባሪያ ስሜ የሚያውቀኝ ሰው ምን ይለኛል?” በሚል መዘባበቻ ያደርገኛል ብሎ የፈራውን ዕዝራ የሚለውን አዲሱን ስሙን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም – ባህሉንና ማኅበረሰብኣዊ አወቃቀሩን ተረድቶታልና የሰው የሃሜት ግርፋት አስቀድሞ የታዬው ይመስላል፡፡ (ይህን ስል ነገሮችን ለንጽጽር አስቀመጥኩ እንጂ ፍርድ ውስጥ እንዳልገባሁ ማስታወስ እፈልጋለሁ)፡፡ በዚህ መልክ እየተሸቆጠቆጠ አንድም የራሱ ቃል ሳይኖረው (with out any say in ‘his’ government) የሰጡትን የሚያስተላልፍ አሸንዳ ሆኖ መኖሩ ምን ዓይነት እርካታና ደስታ እንደሚያገኝበት አይገባኝም፡፡ አለኝ ከሚለው ሃይማኖትም ሆነ ከራሱ ኅሊና ጋር እንደተጣላ እስከመቼ በሌሎች ሰዎች ጭንቅላት እየተመራ – ለቃሉ አጠራር ይቅርታ ይደረግልኝና – ኮንዶም ሆኖ እንደሚኖር አላውቅም፡፡ ራሱ ነጻ ቢወጣ ይሻለዋል፡፡ ኃይለማርያም ራሱን ቢሆንና በነጻይቱ ኢትዮጵያ ባሰኘው የሥልጣን እርከን ተወዳድሮ በራሱ አእምሮ የሚንቀሳቀስበትን መድረክ ቢጠብቅ፣ ለዚሁ መድረክ እውንነትም የበኩሉን ትግል ቢያደርግ እንደሚሻለው በዚህ አጋጣሚ ብጠቁም ብዙ የዘገየሁ አይመስለኝም፡፡ ካሰበበት ይችላል፡፡ አሁን ካለበት የጥፋት መንገድ ግን በአፋጣኝ ይውጣ፡፡ ክፉኛ መሽቷል፡፡ ወያኔ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚዳክር፣ በራሱ ኃይልና ጥበብ ሳይሆን በአጋጣሚዎች መወሳሰብ ብቻ እስትንፋሱ ብን ብን እያለች የሚኖር ድርጅት ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ወያኔ እንዳይወድቅ እያገዘው ያለው የጥቂቶች ብፁዓን አባቶች ጸሎት ነው፤ መውደቁን የምንመኘው ዜጎች ራሳችንን ሳናስተካክል እንዲሁ በባዶ ሜዳ ርስ በርስ እየተናቆርን በምንገንበት ሁኔታ ወያኔ አሁን ቢወድቅ ጦሱ ብዙ፣ መዘዙም በቀላሉ የማይወገድ ነው፡፡ በመቶዎች የተከፋፈለ ፖለቲከኛ፣ ለሥልጣን የቋመጠ ጎጠኛ፣ በዘር የተቧደነ ጦረኛ፣ ለበቀል ያሰፈሰፈ ሸፍጠኛ፣ ለሀብት የተስገበገበ ሆዳም፣ … በየጉራንጉሩ አንዳች ዕድል በሚጠባበቅበት ሁኔታ ይህ በቁሙ ሞቱን ጨርሶ ጣር ላይ ያለ የማፊያ ቡድን ለይቶለት እንዳይወድቅ እኔም ብጸልይ የሚኮንነኝ እንዳይኖር እማጠናለሁ፡፡ መውደቅ ያለበትን ጊዜ በበኩሌ አውቃለሁ፡፡ ያም ቀን አሁንና ዛሬም ሊሆን በቻለ፡፡ ግን ፈጣሪ የታከለበትና ሌላ አደጋ የማያስከትል እንዲሆን የምንመኝ ብቻ ሣይሆን በርትተን የምንጸልይ ወገኖች አንጠፋምና ጌታ ይሰማናል፡፡ ችግሩ የመንግሥት ለውጥ አይደለም፡፡ መንግሥት መቼም ሊለወጥ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ‹አሮጌው ወይን በአዲሱ አቅማዳ እንዳይገባ› የመጠንቀቅ ጉዳይ ነው – ለኢትዮጵያ ደግሞ ከሰው በላይ የሚጠነቀቅላትና የሚጨነቅላት አምላክ አላት፤ እንደሰው ቢሆንማ እስካሁን ድረስም ቢያንስ በሕይወት መቆት ባልተቻለን ነበር – ወርቁ ጠፍቶ ሚዛኑ ያለው በአንድዬ ተራዳኢነት ብቻ ነው – ይህን አንተ ላታምን ብትችል አልፈርድብህም – ምክንያቱም የሰቆቃው ዘመን በእጅጉ በመራዘሙ ሳቢያ ከአምላካችን ጋር የተጣላን ዜጎች ቁጥር ብዙ መሆኑን መገንዘብ አያስቸግርምና፡፡ እንጂ በመሪና በመንግሥት መለወጥማ መንግሥቱስ በመለስ ተተክቶ አልነበረምን? እናም በዚህ አምናለሁ – ወያኔን መጣል የሴከንዶች ጉዳይ ነው፡፡ እንዲያውም ሴከንዶችንም ላይፈጅ ይችላል፡፡ ዱሮውን የወደቀ ነውና – የታመመ ሰው ሲሞት እኮ ሳይተጣጠብ፣ ሳይከፈንና ሳይበጃጅ መሞቱ ለቤተሰብ ተነግሮ እንዲለቀስ አይደረግም፤ የወያኔም ነገር እንደዚሁ ነው – ከሞተ ቢቆይም ገናዥ እስኪገኝ – ገናዦች እስኪስማሙና ወደሬሣ ክፍል ደፍረው እስኪገቡ ድረስ ኅልፈቱ አይነገርም፤ “እባብ ልቡን ዐይቶ እግሩን ነሣው” – ወያኔም እንደ እባብ አናቱን ተቀጥቅጦ እንደድመት በዘጠኝ ነፍስ፣ ከዘጠኙም በመጨረሻዋ ይኖራል – “የተበዮች አለመስማማት ለበዮች ይመቻል”፡፡ አሁን የሚታየው ትልቁ ነገር ወያኔን ሥልጣን የሚረከበው አጥቶ ራሱንም በሚገርመው አኳኋን ሀገሪቱ ሰው አልባ ሆና መቅረቷ ነው – ይህ ካልሆነ በስተቀር ወያኔ አልሞተም ተብሎ ሊዋሽ የሚችልበት አንድም ሀገራዊ ሁኔታ የለም፡፡ ይህም ሥራ የተሠራው በደርግ፣ በወያኔ በራሱና የኢትዮጵያን ኅልውና በማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ነው – ኢትዮጵያ ከአናት ተመታች – ለጊዜው እስትንፋሷ ፀጥ አለና የሞተች መሰለች፤ “hibernate” ባደረገው ሕይወት ያለው በድኗም ላይ ወያኔ እንደልቡ ተንጎማለለባት – የማይቀር ፍርድ ነበረና እንደምንም ተወጣነውና ይህም ክፉ ቀን ሊያልፍ የምሥራቹ ደረሰ፡፡ ፈጣሪ እሾህ አሜከላውን ሲገፍላት፣ ይህን የ80 ሚሊዮኖች የአስተዳደር ወንበር ሊረከቡ የሚችሉ የበቁ ዜጎች ፈጣሪ ፈልጎ ሲያገኝና ከያሉበት ሲያሰባስብ ኢትዮጵያ ምን በመሰለ ክብርና ሞገስ እንደምትነሣ ለማየት ያብቃን፡፡ እንዲህ በል አለኝ እንዲህ አልኩ፡፡ በትንሣኤዋ የሚፈራ ይፍራና ይውጣለት፡፡ የማይቀርን መናገር ነውር አይደለም፡፡ ሞቶ መነሳት በግለሰብ እንጂ በሀገር ደረጃ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሞቶ ያልተነሳ ሀገር የለም፡፡
ኃ/ማርያም ከተናገረው ፍሬፈርስኪ አንዱ አስገርሞኛል፡፡ በዚህ በወቅቱ የዜጎቻችን በ‹ቅጡ አለመያዝ› ምክንያት ስለሳዑዲና ኢትዮጵያ ወዳጅነት መጠልሸት መቻል አለመቻል ሲጠየቅ “በዚች ክስተት፣ በዚህች ትንሽ ነገር” በማለት ይህን በሙሉጌታ ሉሌ አነጋገር – ቃል በቃልም ባይሆን ጭብጡን ልጥቀሰው – “ይህ ሳዑዲ ዐረቢያ ውስጥ በሀገራችን ዜጎች ላይ የተከሰተው ዕልቂትና ስቃይ መንግሥት ቢኖረን ኖሮ ጦርነት የሚያሳውጅ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ ነው፤ ብዙ የዓለም ጦርነቶች የተቀሰቀሱት ከዚህ በሚያንሱ ትናንሽ አጋጣሚዎች ነው፡፡ ይህ የኛው ጉዳይማ ወዲያውኑ ክተት የሚያስብል ነው፡፡…” ተብሎ የተመሰከረለትን ሀገራዊ ታላቅ ጉዳይ እንደተራ የጎረቤት ጠብ ቆጥሮት ዐረፈው፡፡ ያኔ የዚህን ሰውዬ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን አእምሮኣዊ ጤንነቱንም ተጠራጠርኩ፡፡ አቶ መለስ እንደዚህ ያሉ ጀዝባ ሆዳሞችን፣ እንደደመቀ ያሉ ደናቁርት ጌኛዎችን መርጦ አጠገቡ ማስቀመጡ ለወያኔው ሥርዓት ዕድሜ መራዘም በርግጥም ጠቅሞታል፡፡ እናላችሁ ይህን ላንቃችን እስኪበጠስ እያስጮኸን የሚገኘውን ታላቅ ጉዳይ፣ ደም እስክናነባ እያስለቀሰን የሚገኘውን የሚሌንየም ሰቆቃ እንደቀላል ነገር ቆጥሮ “በዚች ክስተት ወዳጅነታችን አይሻክርም…” ብሎን ዕርፍ፡፡ ይህ – በነሱው ቃል – ወደር የማይገኝለት ተንበርካኪነት ወያኔዎች ከሕዝብ ስለተጣሉ ከዐረቦቹም ጋር ላለመቀያየምና በል ልዩ ሰበብ አስባቦች ከነዳጁ ዶላር ለመመጽወት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የሚመነጭ እንጂ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ቢኖረን ኖሮ ሰው አይደለም አንዲት ጥንቸልም ብትገደልብን ብሔራዊ ጦርነት ያሳውጃል፡፡ አንደኛውን ይሁን ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት የቀሰቀሰችው እኮ አንዲት ዓሣማ ናት አሉ፡፡ እንዲያው ለነገሩ ግን በወገን ደም ለመቀለድ ይህን ያህል ድንቁርናና የገረረ ቆዳ ከየት አመጡት? በዘርና በቋንቋ ተመሥርተው በስቃይ ላይ ከሚገኙ ወገኖች የራሴ ናቸው የሚሏቸውን ዜጎች እየመረጡ ወደ ሀገር መመለስንስ እንዴትና ከየትስ ተማሩት? የበረሃው ወያኔ ከ23 ዓመታት በኋላ እንዴት ይህን ዓይነቱን የጫካ የመድሎ አሠራር አይረሳም? ቂም በቀልንና የነገር ቁርሾን ለአፍታም እንዳይዘነጉ ምን ዓይነት ሶፍትዌር ይሆን በየጭንቅላታቸው ያስገጠሙት? ለነሱም ሆነ ለኛ ምን ዓይነት መረገም ይሆን? የሚመለሱትን ብዙዎቹን ስትመለከቱ እኮ የሕወሓት የጦር ባታሊዮን ይመስል ቋንቋቸው … ምንም ይሁን … ያው ግን ወገኖቻችን ናቸውና ምን ይደረጋል፤ ሀዘናችንና ልቅሶኣችን ቅጥ አጣ – ሟቹም ገዳዩም እቤቷ መሽገውባት አትስቀው አታለቅሰው ነገር ሆነባትና ግራ ገብቷት እንደተቸገረችው ያቺ ምሥኪን ወይዘሮ ሆነናል፡፡ ብቻ ግን ከዚህ ሁሉ የመንግሥትነት ዘመን በኋላ እንደዚህ ያለ አድልዖ ሲታይ ክፉኛ ያምማል፡፡ በዚህ የግሎባላይዜሽን ዘመን የሰው ዘር ስለሰው ዘር መጨነቅ ሲገባው ሊያውም የሁላችን የምንለው መንግሥት የኤምባሲዎቻችንን ሥራና ባጀት ለራሱ ሰዎች ብቻ ማዋሉ ከማሳዘን ያለፈ የሀገር ሸክምና ዕዳ ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ በዐረቦች እንዲጨፈጨፍ ተትቶ የራስ የሚሉትንና መዋጮና ድጋፍ ያደርግ የነበረን እየመረጡ ከእሥር ማስፈታት፣ ቅድሚያም ሰጥቶ ወደሀገር ማስገባት … ነገ የሚያመጣውን የዞረ ድምር ካለማየት የሚመጣ ድንቁርና ነው፡፡ አቤት የዚህ ዘመን ትንግርት! እግዚአብሔር ሆይ ቶሎ ናልን!!
yiheyisaemro@gmail.com
No comments:
Post a Comment