ኢትዮጵያውያን ደማቸው የዐረብን አስፋልት አቀለመው፡፡ ባንዲራውን በራሱ ላይ ሸብ ያደረገው
የእማማዬ ልጅ የእኔ ጀግና ማንነቱን እየተናገረ በአናቱ ላይ የወረደውን የድንጋዩን ናዳ በሀገሩ ፍቅር ተቋቁሞ
በክብር አሸለበ፡፡ ለእርሱ ከዚህ በላይ ሌላ ድል አልነበረምና፡፡ ድንጋዩስ እርሱን አሳርፎታል፡፡ ነፍሱን ይማርልን
እንጂ! ባንዲራችን ግን እንደተመታች እንደታመመች ናት፡፡ እውን ይኽ የሆነው በእኛ ላይ ነው?
ዳግማዊ ሆሎኮስት በኢትዮጵያውያን ላይ? እንዴት እንዴት? ደግሞ በ ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን፡፡ የሰውን ሕይወት
የሚያስገብር ምን ጥፋት ተገኝቶ ነው ወይስ የሟርት መስዋእታቸው እኛ ነን፡፡ “ከሕግ አስከባሪው ፖሊስ” እስከ
ዱርየው የእኅቶቻችን ክቡር ሰውነት እንደ ውሻ ሲጎተት ከማየት የሚዘገንን አረመኔነት ምን አለ? ይህ እኮ ንቀት
ነው፡፡ ይህ እኮ ድፍረት ነው፡፡ ይህ እኮ የሀገርን ሉዐላዊነት መድፈር ነው፡፡
ምንም ዓይነት ወንጀል የሠራ ሰው የሚዳኝበት ሥርዓት አለው፡፡ ስንቶች አእምሯቸውን ስተው ተመለሱ…ዝም
አልን፡፡ ስንቶች እንደ ከብት ከግመሎቻቸው እጅግ በተዋረደ ሁኔታ እንደ ሸቀጥ ተጠፍረው ተላኩልን…ያኔም ዝም
አልን፡፡ ስንቶች ከፎቅ ራሳቸውን እየወረወሩ ተፈጠፈጡ… አሁንም ዝም አልን፡፡ ዛሬ ደግሞ በዚህ መጡ…ዝም እንዳልን
እንቀጥል ይሆን? ስጋቴ ይህ ነው፡፡ አስኪ በማነህ ማነህ የተረፉትን እንድረስላቸው፡፡
ለመጽሓፋቸው (ኢትዮጵያን አትንኩ ለሚለው) ያልተገዙ በቀላሉ ይተውናል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ
እኮ ወንዝ እና ተራራዋን ማለት አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ሕዝቧ እንጂ…ቀጥሎ ወንዝ እና ተራራዋ ሜዳ እና
ሸለቆዋ…ወዘተ ይከተላሉ፡፡ ስለሆነም የሚከተሉትን ለማድረግ ብንተጋ፤
፩. በየቤቱ የተዘጋባቸውን እና በእንግልት ብዛት የሚቃስቱትን ፈልጎ ማግኘት እና አሰቸኳይ እርዳታ ማድረግ፣ መመለሻቸውን ማበጃጀት፣
፪. በየፖሊስ ጣቢያው ወይንም ወኅኒው የታሰሩትን ፈልጎ ማግኘት እና ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው ጋር መነጋገር፣
፫. የተቃውሞ ድምጻችንን በሕጋዊ መንገድ በያለንበት ማሰማት፣
፬. ችግር የደረሰባቸው፣ ሰብአዊ መብቶቻቸው የተጣሱባቸው ወገኖቻችን ከሳኡዲ ሁሉ ካሣ የሚያገኙበትን ማፈላለግ፣
፭. ከተመለሱም በኋላ የሚያገግሙበትን እና መደበኛ ኑሮ የሚገፉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት፡፡
፮. እነዚህን እና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚፈጽም ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋም፡፡
ለዚህ አልተፈጠርንምና፡፡
source: danielkibret.com
No comments:
Post a Comment