Friday, October 18, 2013

አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ኢትዮጵያ የሰቆቃ ደሴት ናት አለ

    
26351fb59e29fb0a1375427042
October 18/2013
“ሂዩማን ራይት ዋች” በሚል የአንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል የሚጠራዉ አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አዲስ አበባ ዉስጥ የሚገኘዉ ማዕከላዊ እስር ቤት ሰላማዊ ዜጎች (ጋዜጠኞች፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤ ወጣቶችና ባጠቃላይ ስርአቱን የሚቃወሙ ዜጎች) ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የማይችል ሰቆቃ የሚፈጸምበት ቦታ ነዉ በማለት የወያኔ አገዛዝ በሰዉ ልጆች መብት ላይ የሚፈጽመዉን በደል ለአለም ህዝብ እንደገና ይፋ አደረገ። “እነሱ የሚፈልጉት ያሰሩት ሰዉ ሲናዘዝ ማየት ብቻ ነዉ” የአዲስ አበባዉ ማዕከላዊ እስር ቤት የሰቆቃና ሰላማዊ ዜጎችን የማሰቃያ ቦታ ነዉ በሚል መሪ ቃል በ70 ገጾች ታትሞ በወጣዉ የድርጅቱ ሪፖርት ላይ ከ35 በላይ ማዕከላዊ እስር ቤት ታስረዉ የወያኔን ግፍና መከራ በአይናቸዉ ያዩና ሰቆቃ የተፈፀማባቸዉ የቀድሞ እስረኞች የምስክርነት ቃል ተካትቶበታል።
የሂዩማን ራይት ዋች የአፍሪካ ዘርፍ ተጠባባቂ ዳይረክተር የሆኑት ወይዘሮ ሌዝሊ ሌፍኮ የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ሰላማዊ ዜጎችን አስረዉ ለማናዘዝ የሚያደርጉት ድብደባና የሚፈጽሙት ሰቆቃ እንኳን በጋዜጠኞችና በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ላይ በጦር ወንጀለኞች ላይም ሊፈጸም የማይገባ ወንጀል ነዉና አለም ይሀንን አይነት በደል ህገ መንግስታዊ መብታቸዉን ተጠቅመዉ ሀሳባቸዉን በገለጹ ዜጎች ላይ ሲደርስ ዝም ብሎ መመልከት የለበትም ብለዋል። ማዕከላዊ እስር ቤት ዉስጥ የሚደረገዉ ምርመራ እስረኞችን የሚደበድብ፤ እስረኞች ዉስጥ እግራቸዉን ከተገረፉ በኋላ ለብዙ ሰዐታት በእግራቸዉ እንዲቆሙ የሚያደርግና አጥንት የሚሰነጥቅና የዘረኝነት ይዘት ያላቸዉ የቃላት ዉርጅብኝም እንደሚያጠቃልል ወይዘሮዋ የተናገሩ ሲሆን አንድ ከኦሮሚያ ክልል ተወስዶ የታሰረ ተማሪ እንደተናገረዉ ምግቡን ሲበላ ጭምር እግሩን እንደሚታሰርና እጅና እገሩን ታስሮ ለቀናት በጨለማ ቤት ዉስጥ እንደተጣለ ተናግሯል።

No comments:

Post a Comment