Thursday, October 17, 2013

አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ !!!

  


ኃይለማሪያም ደሳለኝ በአንድ ወቅት ዉሸትን የማያዉቅ ጠንካራ ክርሰቲያን ነዉ ተብሎ ሲነገርለት ሰምተን ነበር፤ ታድያ ይህ ሰዉ መለስን ሲተካ ብዙዎች በጥርስ የለሽ አንበሳነቱ ቢስማሙም ዉሸት እንደ ንጉስ በነገሰባት ኢትዮጵያ ዉስጥ ዉሸት የማያዉቅ መሪ መጣ መባሉ ብዙዎቻችንን ነጻነት የተገኘ ያክል አስደስቶን ነበር። ሆኖም ከወያኔ ጋር የዋለ ሰዉ እራሱን ሆኖ መክረም አይችልምና ኃይለማሪያምም ባስቀመጡት ቦታ የማይገኝ የሌላ መንደር ሰዉ ሆኖ ተገኘ። በዚህም የዜጎችን ተሰፋ አመከነ፤ ደስታቸውንም ወደ ኃዘንና ትካዜ ለወጠው።
ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ላይ በመገናኛ ብዙኋን ፊት ያየዉን አላየሁም፤ የሰማዉን አልሰማሁም፤ ያልሆነዉን ሆነ የሆነዉን ደግሞ አልሆነም እያለ ሽምጥጥ አደርጎ የካደዉ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፤ በእርግጥም ጎበዝ የመለስ ዜናዊ ተማሪ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል። ኃይለማሪያም ባለፈዉ ዓርብ አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። ይህ ግለሰብ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫዉ ኢትዮጵያን ያክል ትልቅ አገር ከሚመራ ሰዉ ቀርቶ ከአንድ ተራ የቢሮ ተላላኪ እንኳን የማይጠበቅ መልስ ሲመልስ ተስተዉሏል።
ኃይለማሪያም በጋዜጣዊ መግለጫዉ ወቅት ከቀረቡለት ብዙ ዲሪቶ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ አገር ቤት ውስጥ እየተደረገ ያለው ሠላማዊ ሰልፍ ጉዳይ ነበር። ኃይለማሪያም አገር ቤት የሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች “በራሳቸው የሚደረጉ ሳይሆኑ ከኋላ ባሉ ሌሎች ኃይሎች መሪነት የሚደረጉ” ናቸው ሲል ተናግሯል። ኃይለማሪያም ጌቶቹ ፊቱን በጨርቅ አስረዉት የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር፤ መከራና ስደት አልታይ ብሎት ነዉ አንጂ ወያኔን የመሰለ ነብሰ ገዳይ ባለበት አገር ዉስጥ የህዝብን ብሶት የሚያስጋቡ ጥያቄዎች በየቀኑ ይመነጫሉ አንጂ ከዉጭ አገርማ አይመጡም። በሌላ በኩል ደግሞ ይሄዉ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያፈራቸዉ ዋሾ ሰዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚያደርጉት ሠላማዊ እንቅስቃሴ የአሸባሪዎች እጅ ያለበትና፤አማኞቹ ሃይማኖታቸውን የወደዱ መስሏቸው ሳያውቁ የገቡበት ስለሆነ እንዲታረሙ እንመክራቸዋለንም” ብሏል። እዚህ ላይ በግልጽ እንደምናየዉ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እመራዋለሁ የሚለዉን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ፈጽሞ ሊረዳ አልቸለም፤ ስለዚህ ምክር የሚያስፈልገዉ መብትና ነጻነት ምን እንደሆኑ ገብቶት የሚታገለዉ የአትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ኃይለማሪያም እራሱ ነዉ።
እኛ ግንቦት ሰባቶች ወያኔን የመሰለ ጨካኝ እና ምንም አይነት አገራዊ ኃላፊነት የማይሰማውን ዘራፊና ዘረኛ ቡድን በሠላማዊ መንገድ የሚጋፈጡ ወገኖቻችንን እናደንቃለን። እነዚህ ወገኖቻችን ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንደሚለው የማንንም አጀንዳ የተሸከሙ ሳይሆኑ የራሳቸው የሆነ አጀንዳ ያላቸውና ኃይለማሪያም በዉክልና ለሚያስረግጣቸዉ ወገኖቻችዉ መብትና ነጻነት የሚታገሉ ጅግኖች ናቸዉ። አጀንዳቸውም የተደበቀ ወይም ከጀርባውም ሌላ ነገር ያለው አጀንዳ አይደለም።አጀንዳቸው ግልጽ እና የታወቀ የነፃነት፤ የእኩልነት፤የፍትህና የሠላም አጀንዳ ነው። ኃይለማሪያም ደሳለኝ የዜጎችን ጥያቄ አድምጦ መልስ መስጠት ሲገባው እነዚህን የኢትዮጵያን ህዝብ አጀንዳ ተሸክመው የሚታገሉ ወገኖች ደካሞች አድርጎ ለመሳል የሚያደርገዉ ሙከራ አንድም በተቃዋሚዎቹ ዙሪያ የተሰባሰበውን የሰው ኃይል ካለማወቅ፤ አለዚያም ደግሞ “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሏታል ጅግራ” እንደሚባለው ነገር ነው።
ሌላው ኃይለማሪያም የሚናገረዉ ቃል ጠፍቶት በተደጋጋሚ ሲንተባተብ የታየዉ በሽብርተኝነት አካባቢ የተጠየቀዉን ጥያቄ ሲመለስ ነዉ። በእኛ እይታ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዋነኛው አገር በቀል አሸባሪ ህወሃት እና ህውሃት ብቻ ነው። ህወሃት ስልጣን ላይ ያቆየኛል ብሎ ከገመተ የማይመሰርተው የክስ ዓይነት፤ የማያፈሰው የንጹህ ሰው ደም ፤የማያፈነዳው የቦንብ እና የፈንጂ ዓይነት እንደሌለ ከሃውዜን እስከ አዲስ አበባ ያሉ መንገዶች ቋሚ ምስክሮች ናቸው። ይህንን እኩይ ተግባሩን ዓለም ሁሉ እንደሚያውቀው በዊክ-ሊክ ላይ የወጣው መረጃም አሳይቷል።
የህውሃት ታማኝ ሎሌ የሆነዉ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሠላማዊ ትግሉን ለማፈን ከፈለገ በትግሉ ዙሪያ የተሰባሰቡትን ዜጎች ከሌላ ከማንም ጋር ማነካካት አያስፈልገውም። ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ሁሉ አንደ ኃይለማሪያም ሞቶ የተቀበረን ሰዉ ራዕይ የተሸከሙ የአመለካከት ደሃዎች ሳይሆኑ የራሳቸው አስተሳሰብና ህያዉ ራዕይ ያላቸው ዜጎች ናቸው። አነዚህን ሠላማዊ ታጋዮች ከማይገናኝ ሌላ ኃይል ጋር አቆራኝቶ ለመምታት መሞከር ለኃይለማሪያምም ሆነ ለጌቶቹ አይበጃቸዉም። ዛሬ በወያኔ ነብሰ ገዳይ ወታደሮች ተከብቦ እዩኝ እዩኝ የሚለዉ ኃይለማሪያም ደሳለኝም የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣ የነደደ ቀን ደብቁኝ ማለት ይመጣልና ያ ቀን ከመምጣቱ በፊት የበደለዉን ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ የነጻነት ኃይሎችን እንዲቀላቀል ወገናዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
በመጨረሻም ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ስለ ግንቦት ሰባት ተጠይቆ ሲመልስ ግንቦት ሰባት “በህልም ውስጥ ያለ ድርጅት” ነው ብሏል። ታድያ ምነዉ ተኝቶ ህልም የሚያልም ድርጅት ኃ/ማሪያምንና ጌቶቹን እንዲህ ያቃዣቸዋል? ለምንስ ይሆን ወያኔና ታማኝ ሎሌዉ ኃ/ማሪያም ያገኙትን ሁሉ ግንቦት ሰባት እያሉ የሚያስሩት፤ የሚደበድቡትና የሚገድሉት? ያገኛችሁትን ሁሉ የግንቦት ሰባት አባል እያላችሁ ትከሳላችሁ? ለምንስ በግንቦት ሰባት ስም ታስራላችሁ? ትገርፋላችሁ? ትገድላላችሁ? ተኝቶ ለሚያንቀላፋ ድርጅት ለምን ትሸበራላችሁ፤ ለምንስ እንቅልፍ አጥታችሁ ትባዝናላችሁ? ግንቦት ሰባት እናንተ አልገባችሁም አንጂ መነሻውንና መድረሻውን አጥርቶ የሚያውቅ፤ ከደመናው ባሻገር ፍንትው ያለ የነፃነት ዉጋገን የሚታየው ባለ ታላቅ ራዕይ ድርጅት ነው። አስኪ ምናልባት ቢገባችሁ ተረት ቢጤ እንንገራችሁ፤
“አንዲት ሚዳቋ ነበርች አሉ። ሚዳቆ ከመሬት ገንዘብ ተበድራ ሲትኖር ከእለታት አንድ ቀን መሬት አፍ አውጥታ ብድሬን መልሽ አንጂ ብላ ትጠይቃታለች። ሚዳቆዋም ደንግጣ ከነበረችበት ቦታ ፈትለክ ብላ ወደ ተራራ ጫፍ ላይ ወጥታ እፎይ ያንን ድምጽ ከአሁን በኋላ አልሰማም አለች። መሬትም በይ ብሬን ክፈይኝ ስትል ዳግም ጠየቀቻት። እንዴ ይህች መሬት የሌለችበት ዬት አገር ሊሂድ ብላ ሚዳቆ ወደ ማይታወቅ ቦታ ተፈተለከች። ከዚያም እያለከለከች በቃ አሁንስ አታገኚኝም ስትል አሁንም መሬት ብቅ ብላ እየጠበኩሽ ነውኮ ብድሬን ክፈይ እንጂ ስትል ጠንከር አድርጋ ጠየቀቻት። ሚዳቆዋም መሬት የሌለችበት ልትደረስ ስትበር ስትበር ሳንባዋ ፈንድቶ ሞተች”ይባላል።
የፍትህ፤ የእኩልነት፤ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች እንደ መሬት ናቸው። የትም ሂዱ፤ የትም ግቡ ይከተሏችኋል። መስጊድ ዉስጥ አሉ፤ ቤተክርስትያናት ውስጥ አሉ። ቤተመንግሰት ዉስጥም አሉ። የሌሉበት ቦታ የለም። መፍትሄው እንደ ሚዳቆዋ መሸሽ አይደለም። መፍትሄው ዜጎች የሚያነሷቸውን የፍትህ፤ የእኩልነ፤ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን አድምጦ ትክክለኛ መልስ መስጠትና ከዕዳ ነጻ መሆን ብቻ ነዉ ። ከዚህ ዉጭ ጥያቄን ላለመስማት ወይም ሰምቶ ለመደፍጠጥ የሚደረገው ከንቱ ሩጫ መጨረሻው እንደ ሚዳቆዋ መፈንዳት እንጂ ህይወት አይሆንላችሁም።
እኛ ግንቦት ሰባቶች ዘረኛዉንና አሸባሪውንና የወያኔ ስርዐት ለመደምሰስና ህዝብ በነፃነት ያለፍርሃት የሚኖርበትን አገር ለመፍጠር ቆርጠን ተነስተናል። ከእንግዲህ የሚያቆመን ምንም ነገር የለም። የምንታገለዉ ለህዝብ ጥያቄያችንም ህዝባዊ ጥያቄ ነዉና እኛም አንደጥያቄዉ በየመስጊዱ፤ በየቤተክርሲቲያኑና በየሰፈሩ ዉስጥ አለን።እኛ የሌለንበት ስፍራ የለም። በዚህ አጋጣሚ የዘመናት ትግላችን ፍሬዉ የሚታይበት ቀን እጅግ በጣም ቅርብ ነዉና የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም አገር ተረካቢ የሆነዉ ወጣቱ ትዉልድ እራሱን፤ ወገኖቹንና እናት አገሩን ለማዳን የሚደረገዉን የነጻነት ትግል እየመጣ እንዲቀላቀል ወገናዊ ጥሪያችንን አቅርበናል። ኑ እና ተቀላቀሉን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment