Sunday, July 21, 2013

መና ሁሉ ዝናብ እንደማይሆነው ከዳሁ ያለ ሁሉም ወዳጅ አይባልም


ዳኛቸው ቢያድግልኝ
ለአየር ትንበያ የንፋስ አቅጣጫ፣ የአየሩ ሙቀትና እርጥበት፣ የደመናው አይነትና ፍጥነት ሁሉ እገዛ ያደርጋሉ። ለፖለቲካም እንዲሁ ለትንበያ የሚመቹ በፖለቲካው ትኩሳት፣ በውስጥ ሽኩቻ ብዛትና በተቃዋሚው ጥንካሬና ብቃት መነሻነት ወደ ሌላኛው ጎራ ሲቀላቀሉ የሚታዩ መጪውን ለመተንበይ የሚያስችሉ አመላካች ሰዎች አሉ። የአየር ትንበያ ሰራተኞች እንደ መሳርያዎቻቸው ዘመናዊነት፣ እንደመረጃ ማሰባሰቢያ ነጥቦችና በእውቀት የተካኑ ባለሙያዎች ብዛት ወደ እውነት የተጠጋ ትንበያን ማቀበል ይችላሉ። ፖለቲካም እንዲሁ ነው። የውስጥ አዋቂ መረጃ፣ የውጪው ዓለም የሀይል አሰላለፍ፣ የህዝብ መነሳሳትና፣ የገዢዎችን የፖለቲካ ትኩሳት በማገናዘብ መጪውን የፖለቲካ አቅጣጫ ማመላከት ይቻላል።Birhanu Damte Aba mela
ለፖለቲካው ትንበያ የሚያግዙ አጥር ሰብረው የሚመጡ የነበሩበት ትክክል እንዳልነበር እየተናገሩ ሌላኛውን ጎራ ልንቀላቀል መጥተናል ተቀበሉን እያሉ የምሬትና የእሮሮ እንጉርጉሮ ይዘው መድረኮች ላይ ብቅ ብቅ የሚሉ ሲኖሩም ለፖለቲካ አቅጣጫ ትንበያ እገዛ ያደርጋሉ። ያደረሱትን በደል በማሰብ ከመጨነቅ ሊያጠፉ ከሚችሉት በመቆጠባቸውና የጠላትን ጎራ የማዳከማቸው ዋጋ የበለጠ ነውና እንዳመጣጣቸው መቀበል ሌላኛውን ጎራ ለማዳከም ይረዳል። አመጣጣቸው በቀናም ይሁን በተለየ ተልዕኮ መጡልን ብሎ ከራስ በላይ ማድረግ ግን ከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ያመጣል። የሚበላ ሲጎድል፣ በራሳቸው ኩርፊያና ሽኩቻ ወይም ሌላ መሰረታዊ ባልሆነ ልዩነት የሚመጡትን ከፍ ከፍ ማድረጉ ደግሞ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። እንዲህ አይነቶቹ ይሉኝታቢሶች ለመታመን ሲባል የማያደርጉት የለምና ሀቀኞችንና ለዓላማ የቆሙትን ለስልጣን ጥመኞች የጥቃት ሰለባ ያደርጋሉ።
ይህንን ምልልስ በዘመናችን ተመልክተናል። ከድተን መጣን ብለው የተበላ መረጃ ሰጥተው የተሻለ መረጃ ይዘው ያፈተለኩና መልሰው የወጉ ብዙ ነበሩና ከተሞክሮ እንጂ እንደ አዲስ የምንማረው አይደለም። የሀገራችን የመከላከያ ሰራዊት ከገንጣይ ሀይሎች ጋር ግብ ግብ ገጥሞ በነበረበት ሰዐት መጡልን ተብለው የታቀፉ የተገንጣይ ወንበዴዎቹ ሰላዮችና አብዮቱን ተቀላቀልን ብለው የካድሬ ህጋዊነት ተሰጥቷቸው ጓደኞቻቸውን ያረዱ፣ ለዚህች ሀገር በሀቀኛነት ያገለገሉትን በየጉድባው እየገደሉና እያስገደሉ አሁን ወደምንገኝበት እንደርስ ዘንድ አስተዋጽኦ ያደረጉ በርካቶች መኖራቸውን ብዙዎች የምናውቀው እውነት ነው። ደርግ ሲዳከም ደግሞ ወዲህኛው ጎራ ተቀላቅለው ተገርፈን፣ ተሰደን፣ መከራ በልተን ተገደን እያሉ ሌላኛ ዙር ጥፋታቸውን ሲያከናውኑ የኖሩቱ አሁን ደግሞ ማርሽ ቀይረው ሌላ መዝሙር ሲዘምሩ እየተመለከትን ነው። እንዲህ አይነቶቹ ሰዎች በዚህ ከፍተኛ ልምዱ አላቸውና አኪያሄዳቸውን ሲቀይሩ ያኛው ቤት የተበላ እቁብ እንደሆነባቸው በመገመት የወያኔ ነገር ላይጠገን እየተሰበረ መምጣቱን መገንዘብ ይቻላል። ተቃዋሚ መስለው ክብርና ስም ይዘው የስለላ ስራቸውን የሚያጧጡፉ ወይም በተቃዋሚው ጎራ ያለውን እርስበርሱ እያናከሱ ጉርሻቸውን የሚቀበሉ እንዳሉም እናውቃለን። ወሬ የፈታው እንዲሉ እርስበርስ በማላተም፣ ጥርጣሬ እንዲፈጠርና መተማመን እንዲጠፋ በማድረግ ስራ የተጠመዱም በርካቶች መሆናቸው ይታወቃል።
ለዚህም ነው እነዚህ ዐይንአውጣዎች ጀንበር ሳለች እሩጥ አይነት ዘዴ የበሉበትን ወጪት ሰብረው ወደሚበላበት ለመጠጋት ቁና ወሬ ይዘው ሲመጡ ዊንድቬን ለንፋስ እንዳልነው ለፖለቲካ አቅጣጫ ትንበያም እነርሱ ያገለግላሉ ማለት የምሻው። እንደዚህ ያሉ ባለ ዘርፈብዙ አንደበቶችን የፖለቲካ ‘ዊንድቬን’ ብንላቸው የሚመጥን ስም ነው። ዊንድቬን ነፋስ በነፈሰበት አቅጣጫ የመሽከርከሩን ያህል እንዲህ አይነት ሞቅ ያለበት አለን የሚሉ ሰዎችን እንደ አሽከርካሪው ንፋስ የመቁጠር አዝማሚያ ሊወገዝ የሚገባው ነው። አቅማቸው ንፋስ የመግፋትና ሞገድ መፍጠር ሳይሆን በነፈሰበት የሚሽከረከሩ ክንፋሱ በላይ ጫጫታ የሚፈጥሩ ናቸውና በዚህ ጫጫታቸው የፖለቲካውን አየር እንዲበክሉ መፍቀድ የሞኝ መንገድ ነው።
ልክ የአየር ትንበያው ላይ እንደተጠቀሰው እነዚህ አመላካች ሰዎች በሚያደርጉት መገለባበጥ የወዲያኛው ቤት ላይጠገን መፍረሱን መገንዘቡ ግን ሊያበረታታ ይገባል። ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት ሰዎችን እንደነቢይ መቁጠርና የማይገባቸውን ሽቅብ መቆለል ሁዋላ በአስቸጋሪውና ከፍተኛ መስዋዕትነት በሚከፈልበት ጊዜ ሰው ሆነው በተገኙት ላይ ተረማምደው እንዲሄዱ ማመቻቸት መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ዓላማቸውና ግባቸው ሆዳቸው ብቻ ነውና ሲቃወሙም ሚዛን የሚደፋ ምክንያት የላቸውም፤ ሲደግፉም የእውቀት ገለባነታቸው ከፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ በላይ አይሆንምና ነው።
ሀገራችን ከታገለው አርበኛ ይልቅ የከዳው ነውጠኛ የሚከበርበት፣ ከታገለው ጀግና ይልቅ የሰለለው ባንዳ የሚሾምባት
ሀገር ነበረች አሁንም እንደዚያው ነች። እና ዛሬም ይህንኑ መንገድ ተከትለው የሚያምታቱና አንቱ በሉኝ የሚሉ አሉ። ለነዚህ ደግሞ ከበሮ የምንመታና እልል የምንል ራሳችንን የታክቲክና ስትራቴጂ መሀንዲሶች አድርገን የምንመለከት የእውቀትና የልምድ ረሀብተኞች አለን። ይህንን በማስተዋልና ዘወር ብሎ የትናንቱን በማየት ብልህነት ሊታረም የሚገባው ነው እላለሁ።
በእውቀታቸው አነስ ያሉ በልምዳቸው ያልጠነከሩ ግን ሰው በሚፈለግበት ጊዜ ሰው ሆነው የተገኙ፣ ሌሎች የራሳቸውን ህይወት ለማመቻቸት ስራና ትምህርታቸውን ሲማሩ እነርሱ ግን እንኳን ሥራና ትምህርት ሕይወትም ለመስጠት ዝግጁ ነን ብለው በቃላቸው የተገኙት እየተገፉና እየተወነጀሉ፤ በምትካቸው የጀርባ አጥንት የሌላቸው ልፍሰፈሶች ሲንደላቀቁ መመልከት አዲስ አይደለም። ሌላው ቢቀር ይህ ደካማውና አንገት አስደፊው አሰራራችንን አጥብቀን ልነኮንነው ይገባል። ለዚህም ፖለቲካ ስድብ፣ እርግማንና አሽሙር የሚመስላቸው ሰዎችን አይዞአችሁ ማለቱን ማቆሙ እገዛ ያደርጋል።
በኢትዮጵያ በቻ ሳይሆን በበርካቶች ለነጻነት በተደረጉ ትግሎቸ ላይ የዓላማ ጽናት ያላቸው ለሕዝቡ ነጻነት፣ ሰላምና የሕግ የበላይነት የታገሉ አርበኞች መመታትና መባረር የሚጀምሩት ከነፃነት ማግስት ነው። ከነፃነት በሁዋላ የሚያስፈልጉት የዓላማ ጽናት ያላቸው፣ ቆራጦቹና ጀግኖቹ ሳይሆኑ ለስልጣን አስጊ ያልሆኑት ሰግዶ አደሮችና ወኔ አልባዎቹ ናቸው። እነዚህ አዳኝ ግዳይ እስኪጥል ወይም ተፈጥሮአዊ ሞት ቀለብ አስኪሰፍርላቸው አሰፍስፈው እንደሚጠብቁቱ ጆፌ አሞራዎች ይመሰላሉ። ለገዢው ሰግደው ለእውነት የቆሙትንና መስዋዕትነት የከፈሉትን አንገት የማስደፋት ተግባር ላይ ብርቱዎች በመሆናቸው ለአምባገነኖች መጠናከር ምክንያቶችም ናቸው። ለዚህ ነው ደመናዎች ሁሉ ዝናብ ያዘሉ ያለመሆናቸውን ያህል የትግሉን ጎራ ልንቀላቀል መጣን ያሉ ሁሉ የትግሉ አጋር ናቸው ማለት አስቸጋሪ የሚሆነው።
ይህ ጽሁፍ የነበሩበትን ጎራ ስህተት በሚገባ ተረድተው መንገዱ መንገዴ አይደለም ብለው ስለ እውነት፣ ስለሕዝብና ሀገር ተቆርቋሪ ለመሆን በንጹህ ልብ የሚመጡትን ሳይሆን የፖለቲካ ‘ዊንድቬን’ የሆኑ ጥቅም እስካገኙ ድረስ ከማንም ወግነው ማንንም ለማጥቃት የማይመለሱትን ወዳጅ አድርጎ ማቀፉ ያለውን አደጋ ለማመላከት ነው።
የነጻነት ቀን የመቅረቡን ያህል ጀግኖቻችንና ድላችን ላለማስነጠቅ ተግተን እንሥራ!
biyadegelgne@hotmail.com

No comments:

Post a Comment