‹‹ሁለት እግሮች አሉኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ መውጣት አይቻልም›› ተብሏል፡፡ ትናንት ‹‹ወገኖቼ እንኳን ደህና መጣችሁልኝ›› ብሎ የተንከባከባቸውን ሕዝብን ዓይንህን ላፈር ያሉት፣ ፀባችን ከመንግሥትና ከሥርዓት ጋር ነው ሲሉ ቆይተው ጊዜ ሲያመቻቸው ሕዝቡን እንደበደላቸው ጠላት የረገሙት ሰዎች፣ ዛሬ ደግሞ አይ ለጥቅማችን ሲሆንማ እንፈልግሃለን ያለህን ደግ ነገር አጋራን ያውም በእኩል ባለመብትነት ሲሉት ምን ይሰማቸዋል? ኢትዮጵያውያንስ እንዴት እንዲመለከቷቸው ይመኛሉ? ኤርትራ ለኢትዮጵያውያን ዝግ ናት ኢትዮጵያ ግን ለኤርትራውያን ጥቅም መናኸሪያ ትሁን ነው ጉዳዩ?
ብቻ እኮ ቀደም ሲልም እነ ዶክተር አማረ ተክሌ፣ ‹‹ኤርትራውያን ወደ አዲስ አበባ የምናየው ለኑሮ ምቾታችንና ለመበልፀግ ለሚሰጠን ዕድል ብቻ ሲሆን፣ ለማንነታችንና ለመንፈሳዊ ዕርካታ ግን የምንዞረው ወደ አስመራ ነው፤›› በማለት አስገንዝበውን ነበር፡፡ አሁንም ብዙዎቻቸው የሚወተውቱን ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ነገም ያሻቸውን ያድርጉ፡፡ ምንም ነገር አይነካባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ኤርትራ ውስጥ ቦታም መብትም የላቸውም ነው፡፡ ይቺ ናት ጨዋታ! ፈረንጆች በበደል ላይ በደል ሲጨመር፣ ‹‹ማቁሰል አንሶ ማዋረድ›› የሚሉት ነገር መጣ! የለም ሰዎች ኢትዮጵያ ከእንግዲህ መንከባከብ ያለባት በኢትዮጵያውያነታቸው የሚያምኑ፣ የሚኮሩና ይህንኑ ለማስከበርና ለማደራጀት የሚቆሙትን ወገኖቿን ነው፡፡ ‹‹የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› እየተባለች መሞኘትና መታለሏ ማብቃት አለበት፡፡
የአገሮችና የሕዝቦች ግንኙነት ሕግጋትም ሆኑ ወጎች እንዲህ ዓይነቱን የተዛባ አሠራር አይደግፉም፡፡ አሁን የኤርትራውያን ሕልውና ውሳኔ በእጃቸው ስለሆነ የፈለጉትን መርጠዋልና ይመቻቸው፡፡ የሚበጀን ከኢትዮጵያ መለየት ነው ብለው ሁሉንም የኅብረት መማፀን ረግጠው ሄደዋልና ራሳቸውን መቻል አለባቸው፡፡ አዲስ አበባ ያሉትን ተባባሪዎቻቸውን ተገንና መሣሪያ በማድረግ እስካሁን በአገሪቱ ሀብትና ንብረት የተጠቀሙት አንሶ፣ ለወደፊትም ይህንኑ ዓይን ያወጣ አድሎአዊ ግንኙነት በሕጋዊ ሽፋን ለመቀጠል የተያዘው የማመቻቸት ዘዴ መገታት ይኖርበታል፡፡ በወዳጅነትና በመልካም ጉርብትና ለመኖርም እኮ ጥቅምና ግዴታን በተመጣጣኝ መንገድ መጋራትን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን መላ አገራችንን የወል አድርገን ‹‹የእኛን ለእናንተ የእናንተንም አብረን›› ሲባሉ አሻፈረን ያሉ ኤርትራውያን ይባስ ብለው፣ ‹‹የእኛን ለእኛ የ‹‹እናንተንም ለእኛ›› ማለት ይሉኝታ ቢስንት ነው፡፡ የራስን ድርሻ በጉያ አፍኖ የሌላውን ለማፈስ መፈለግ ስህተትም ሆዳምነትም ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ስለቀሩ ኤርትራውያንም ሆነ በተለያዩ መንገዶችና ምክንያቶች ስለሚገቡት ኤርትራውያን መንግሥት የሚከተለው ለአንድ ወገን የሚያደላ ፖሊሲ ከዚህ አንፃር መታየት አለበት፡፡ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖራቸው መብትና ጥቅም ደረጃና ስፋት፣ በአፀፋው ኢትዮጵያውያን በኤርትራ ውስጥ ከሚኖራቸውና ከሚገባቸው ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲሁም ኢትዮጵያ የራስዋን ሕዝቦች ለመንከባከብና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ከሚያስፈልጋት አማራጭ አንፃር መመዘን ይኖርበታል፡፡ ካለበለዚያ በሁለቱ ወገኖች መካከል መቃቃርንና እያደርም ግጭትን እንደሚያስከትል የብዙ ማኅበረሰቦች ልምድ ያስተምረናልና ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡
በመሠረቱ ዝምድናም ሆነ ወዳጅነት የጋራ ካልሆነ ጠቀሜታው ዘላቂነትም የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ካለ ኤርትራ መኖር እንደሚያዳግታት ወይም ኤርትራ ካለ ኢትዮጵያ ራሷን እንደማትችል ተደርጎ የሚቀርበው ክርክርም አንፃራዊ በሆነ አመለካከት ካልሆነ በስተቀር ብዙም በእውነታ የተደገፈ አይደለም፡፡ ሁለቱ ወገኖች ቢሆንላቸውና ተደጋግፈው ቢኖሩ የአገር ስፋት፣ የሀብትና ንብረትና የሰው ኃይል ብዛት፣ ወዘተ ተቀናጅተው ለሁለቱም ይበልጥ ይጠቅማል፡፡ ካልሆነ ግን ሁለቱም በየበኩላቸው ሊያድጉና ለጋራ ጥቅማቸው በሚስማሙበት መንገድ በእኩልነት ሊደራደሩና ሊተባበሩ ይችላሉ፡፡ በዜግነት መብት፣ በንብረት ባለቤትነትና በመሳሰሉትም ረገድ እንዲሁ ከዚህ ውጪ የሚደረግ ጥረት ሁሉ ለጊዜው እንጂ አያዛልቅም፡፡
ለረዥም ዘመን ባይሆንም ኢትዮጵያ ያለ ኤርትራ ኖራለች፡፡ ኤርትራም በሌላ እጅ ቆይታለች፡፡ ያኔ ማን ተጠቅሞ ማን እንደተጎዳ በኋላስ እንደገና መዋሀዱ ለማን እንደበጀ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ያም ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች አብረው መኖር ባለመቻላቸው በጦርነት ጭምር ተፋልመው ተለያይተዋል፡፡ በሰላም ባይለያዩም አሁን የሚሻለው በሰላማዊ ጉርብትና አብሮ ለመኖር መሥራት ነው፡፡ ብዙ ስለሚነገርለት የወደብ ጉዳይም ቢሆን የትኛውም አገር የራሱ የባህር በር ቢኖረው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ስትራቴጂያዊ ጥቅሙ ግልጽ ነው፡፡ በተለይም አሰብን በሚመለከት በዓለም አቀፍ ሕግጋት ማዕቀፍና ሰላማዊ ድርድር የጋራ መፍትሔ ብናገኝለት እሰየው፡፡ ካልሆነ ግን ካለወደብ መኖር ብቻ ሳይሆን መበልፀግም ይቻላል፡፡ ኤርትራ በወደቦችዋ ትናኝባቸው፣ ኢትዮጵያም ባላት ልማትዋን ታቀላጥፍ፡፡ እስቲ አንዱ ከሌላው ተለይቶ ምን እንደሚሆን ይታይ፡፡ በየበኩሉ የቱን ያህል እንደሚራመድ ይገማመት፡፡ ዕድሜ ልክ ኢትዮጵያ የኤርትራን ዕድል ጎታችና የዕድገቷ ማነቆ እንደሆነች ተደርጎ ‹‹ዓመድ አፋሽ›› መሆኗ አብቅቷልና በሌላ ስውር የጥገኝነት ሥልት አንፈተን፡፡ በኤርትራ ምክንያት ለጦርነት መዳረግ በኢኮኖሚ መድቀቅና ለፖለቲካዊና ለአስተዳደራዊ ችግሮች ማመካኛ መሆኑም ያክትም፡፡
ለነገሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሮች ቢኖሩበትና በያለበት የሚሰደድ ቢሆንም፣ የመሻሻል ዕድል ፍለጋ ኤርትራ መሄድ አይሻም እንጂ ቢሆንም ኖሮ ግንኙነቱ መስተናገድ ያለበት በ‹‹ሰጥቶ መቀበል›› መርህ ማዕቀፍ እንጂ፣ በአንድ አቅጣጫ ጥቅም ላይ ተመሥርቶ አይደለም፡፡ ይህን ሚዛን ማጣትና የፍትሐዊነት መጓደል ደግሞ በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ ብቻ በማላከክ ማለፍ አይቻልም፡፡ በሕዝቡና እንወክለዋለን በሚሉት ወገኖችስ ምን የተለየ ነገር ይታያል? እንዲያው ለመሆኑ ከመንግሥታቸው ጋር ተጣልተናል የሚሉትስ እውነት እንኳን ቢሆን ግጭቱ ለኢትዮጵያ ተብሎ ነው? እውን አሁን የፖለቲካው ሆያ ሆዬ ጋብ ብሎ ማጣፊያው ሲያጥር ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፉት ኤርትራውያን የሠሩት ቆጭቷቸው፣ አቋሞቻቸውን አቃንተው ሌላው ቢቀር በሕዝብ ለሕዝብ ወንድማማችነት በማመን ለመኖርና ለመሥራት ፈልገው ነው? ወይስ ካሉባቸው ችግሮችና ለማምለጥና ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርቶብናል የሚሉትን ቅሪት ሀብትና ንብረት ለመቃረም፣ ካመቻቸውም ከአዳዲሱ የአገራችን ትሩፋት ለመሻማት?
ግዴለም ቤተሰብ እንኳን ይቀያየማል ይጣላል፡፡ ሁኔታዎች ሲለዋወጡ ደግሞ አመዛዝኖ ይቅር ይባባላል፡፡ በሒደትም በዳይ ክሶ የተጎዳም አቻችሎ መታረቅ ያለ ነው፡፡ የዚሁ ሁሉ መሠረቱ ግን የደረሱ ሁኔታዎችን በሀቅ ማጤንና የድርሻን ኃላፊነት መቀበል ነው፡፡ ያለፈውን በትክክል መገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለመጪውም ጠቃሚ ትምህርት መቅሰም የሚቻለውም ይህ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ‹‹አድበስብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› እንዲሉ የሁለቱን ሕዝቦች ታሪክ እንደተመረዘ ማቆየትና ለማያስፈልግ መጥፎ ቀውስ ማመቻቸት ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ሁኔታዎች ሲለዋወጡ የሚቀረው እውነታ ብቻ ነው፡፡ የአንዴ ጥፋትን በስህተትነት ማለፍ ይቻላል፡፡ ሲደጋገም ቸል ማለት ግን የዋህነት ሳይሆን ጅልነት ይሆናል፡፡ ብልጥ ነኝ ባዩም ቢበዛ ጥቂት ሰዎችን ሁልጊዜ አሊያም ብዙ ሰዎችን ለተወሰነ ጊዜ ቢያታልል እንጂ፣ ሁሉንም ሰው ሁልጊዜ ለማታለል መሞከር ግብዝነት ይሆናል፡፡
በአንዳንድ ኢትዮጵያውያንም በኩል አሁንም በቅንነትም ይሁን ወይ ከአመለካከት ጥራት ማነስ የሚሰነዘሩ ስሜታዊና እውነታዊ የማይደግፋቸው ሐሳቦች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ በሪፖርተር ግንቦት 18 ቀን 2005 አሮን ሰይፉ በተባሉ ጸሐፊ የቀረበው ጽሑፍ ስለመዋሀድና አንድነት የሚሞግት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እንግዲህ ችግሩ ይህ ነው፡፡ ያለፈው ያነሰ ይመስል አሁንም ነገሮችን ባናምታታና ቅደም ተከተሎችን ባናበላሽ ጥሩ ነው፡፡ ባለንበት ጊዜና ሁኔታ አንገብጋቢው ጥያቄ እንደገና መዋሀድ ወይም አንድነት የሚል ምኞታዊና ወቅቱ የማይደግፈው መፈክር አይደለም፡፡ በተጨባጩ እውነታ ላይ ተመርኩዘን የምናስብ ከሆነ ቅድሚያ የሚሰጠው ግንኙነታችንን ጤናማ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ለማድረግ መጣር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በተረጋጋ መንፈስ ወደ ቀረበ ወዳጅነትና ትብብር እናመራለን፡፡ ከትብብር ወደ ቅንጅትና ውህደት መሸጋገሩ ደግሞ እንዲህ ቀላል ሒደት አይደለም፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ በሀቅ መፈላለግንና በኢኮኖሚ መተሳሰርን እንዲሁም በርካታ የፖለቲካና ሌሎችም ሥራዎችን ይጠይቃል፡፡ ይህን ማሰብና እንደ አጀንዳ ማቅረብ በተጨባጭ ቁሳዊና መንፈሳዊ መሠረት ላይ ካልሆነ የዋህነት ይሆናል፡፡ ከአንጀት ለመቀራረብ የምንፈላለግ ከሆነ እስቲ የተንጠለጠሉትን የድንበርና መሰል ጉዳዮች መልክ እናስይዝ፡፡ ስለዚህ አሁን የሚያስፈልገው አጣዳፊ ተግባር በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶችና የቅርብም ሁኔታዎች በመራራ ጦርነቶች ጭምር የተቋሰለውን ግንኙነት በደበዘዙ ሥልቶች ማደናገርና ፍትሐዊ ባልሆኑ ድርጊቶች ማባባስ ሳይሆን፣ ጥንቃቄ በተሞላበት አሠራር እንደ ሁለት አጎራባች አገሮች ግንኙነቶችን መምራት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ መብትና ጥቅም ሳይጋፉ እውነተኛ የሕዝብ ለሕዝብ መቀራረብና መልካም ጉርብትና እንዲዳብር መትጋት ነው፡፡
እርግጥ ከኤርትራውያን ጋር ከሌሎች አጎራባች ሕዝቦች የተለዩ ታሪካዊ መተሳሰር ያለን ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ አገር ዜጎችም ለዘመናት ኖረናል፡፡ ግን እኮ ይሁን ሁሉ እንዳልነበረ ያደረጉት እነሱው ናቸው፡፡ በእኛ በኩል በኢትዮጵያውያነታቸው ኮርተው ለአንድነታችን ተጋድሎ ያደረጉ በአጠቃላይም ለጋራ ታሪካችንና ለአብሮ መኖር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ኤርትራውያንን ሁሉ ምንጊዜም በአክብሮትና በባለውለታነት እንዘክራቸዋለን፡፡ አሁንም ልዩ ሁኔታዎችን በውል በማጤን አንዳንድ ለየት ባለ ሁኔታ የምናያቸው ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ በተለይም በጓደኝነት፣ በወዳጅነት፣ በጋብቻና በመሳሰሉት የተሳሰርን ሁሉ እስካሁን ካደረግነውም በበለጠ የቀረበ መልካም ግንኙነታችንን በተቻለ አጠናክረን መቀጠሉ ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም በእውነት የስደተኝነት መጠጊያና ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚሹ አቅማችን በሚፈቅደው ሁሉ አለኝታ ልንሆንላቸው ይገባል፡፡ ያም ሲሆን እነዚህ ሁኔታዎች ሁለቱ አገሮች አሁን ያሉበትን ሉዓላዊነት ያገናዘቡ፣ የኢትዮጵያውያንን መብት ጥቅምና ክብርም የማይጋፉ መሆናቸውን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡
የመብትና የጥቅም ነገር ሲነሳ የራስን ድርሻ ከፍ ለማድረግ መሞከር በብዙ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች፣ አልፎም በማኅበረሰቦች ላይ የሚታይ ባህርይ ነው፡፡ ግን ለዚህ ሲባል ሌላውን መድፈርና መብቱንም መንጠቅ ፍትሕና ሚዛናዊነት የጎደለው ይሆናል፡፡
በአንዳንድ ኤርትራውያን በኩል የሚታየው የዚህ ዓይነት አዝማሚያ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ የሚገባቸውን አይጠይቁ፣ ጥቅምና መብታቸውን አያስከብሩ ለማለት አይደለም፡፡ ግን ችግሩ ይህንን ሲያደርጉ የሌላውን ወገን መጋፋት፣ የአቻን መብትና ጥቅም መርገጥ ድንበርን ማለፍ ይሆናል፡፡ ይህን ዓይነቱ ባህርይ ደግሞ የተገፋውና የተጠቃው ወገን ትዕግስት ሲያልቅ የሚያስከትለው ጠንቅ አደኛ ነው፡፡ ‹‹ማር እንኳ ሲበዛ ይለመራል›› ተብሎ የለ?
የታሪክ ማዛባቱን፣ የሕጋዊ ትክከለኛነቱንና ሌላውን የተገቢነት ክርክር ትተን ዛሬ ያለንበት እውነታ ተገንጣዮች ጊዜና ሁኔታ አሟልቶላቸው ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመነጠል የራሳችን የሚሉት አገርና መንግሥት የመሠረቱበት ዘመን ነው፡፡ ገና ከዋዜማው አንስቶ አቀንቃኞቻቸው በየመድረኩ በጠላት ላይ ድል መጎናፀፋቸውን ብቻ ሳይሆን፣ መገንጠል ብቸኛው የችግሮቻቸው ሁሉ መፍትሔ እንደሆነ ከዚያም አልፎ ከኢትዮጵያ ከመለየት ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌለ አስተጋብተዋል፡፡ ብዙዎቹ ‹‹እንደገና ከኢትዮጵያ ጋር መዛመድ መቼም ፍፁም እርም ነው፤›› እያሉ ሲምሉና ሲገዘቱ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ኤርትራውያንን ወገኖቼ ናቸው አይራቁኝ በተለይም በጠላት እጅ አይውደቁብኝ በሚል ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ለዘመናት የባዕዳንን መዳፍ ለመከላከል ታግሏል፡፡ ከአቅሙ በላይ ሆኖ ለተወሰነ ጊዜ በቅኝ አገዛዝ ሥር በወደቁበት ወቅት በሚቻለው ሁሉ እየረዳና በጋራ እየታገለ ነፃ እንዲወጡ ተባብሯል፡፡ ኤርትራውያን የእኛ፣ እኛም የኤርትራውያን ነን በሚልም ብዙ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ዘመቻ አካሂዷል፡፡ በዚህም ከፍተኛ መስዋዕትነት በጠየቀ ትግል ወገን ከወገኑ ሊቀላቀል በቅቶ ነበር፡፡ ከአንድነት መመለስ ወዲህ ለኤርትራውያን በክልላቸው ከተደረገላቸው ልዩ እንክብካቤ ባሻገር ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ምን ያህል ስንቅ? ምን ያህል ንብረትና ጥሪት ይዘው እንደተሰማሩና የቱን ያህል ከብረውና በልፅገው እንደተመለሱ፣ የተቀሩትም በምን ዓይነት አንፃራዊ ምቾትና ድሎት ላይ እንደኖሩ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ መማሪያቸው፣ መሾሚያቸው፣ መነገጃቸውና በአጠቃላይም ማደጊያቸው ከኤርትራ ይልቅ ሌላው አካባቢ መሆኑን እንኳን ሰው ግዙፍና ግዑዝ ንብረቶቻቸው ይመሰክራሉ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው በፍቅር ተቀብለው በርህራሔ አስተናግደው፣ አግዘውና አቋቁመው በመተባበር ከመኖር በስተቀር የመቀናቀንና የጥላቻ ስሜት ከቶ አሳይተው አያውቁም፡፡ የከረረ የፖለቲካ ውጥረትና የከፋ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት እንኳ ከፍልሚያ ሜዳዎች ውጪ በአንድም ክልል ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ›› በኤርትራውያን ላይ የደረሰ በደል አልነበረም፡፡
ዛሬ ባለጊዜ የሆኑት የሻዕቢያ ጉልበተኞች ገና አስመራ በገቡ ማግሥት በዓለም የተወገዘውን ‹‹የብሔረሰብ ፅዳት›› በማካሄድ በኤርትራ ይኖሩና ይሠሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ንብረታቸውን እየገፈፉ ሲያባርሩ፣ እናቶችና ሕፃናት ሳይቀሩ ለስቃይ ተዳርገዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኤርትራውያን ካልሆኑ ጋር የተጋቡት ወገኖቻቸው ጭምር ተዋርደውና ተሰቃይተው በበረሃ እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ የዚህን ዓይነት ደባ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስቦት አያውቅም፡፡ ከ1990 ጦርነት በኋላ የመረጡ ኤርትራውያን በአመዛኙ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረገውም ራሳቸው በቆሰቆሱት ግጭትና በቀደዱት ፈር አጋራቸው በሆነው መንግሥት የተፈጸመ ነው፡፡ ቀድሞም ጦርነቱ በብሔራዊ ግዴታ መልክ ተጭኖበት እንጂ የሕዝቡ ፍላጎት ሰላምና የጋራ ጥቅም ነበር፡፡ አሁን ሁላችንም ባካሄድነው ትግል የችግራችን መሠረት የሆነው ሥርዓት ተወግዷል፡፡ ከእንግዲህ ተባብረን እንኑር፡፡ የሚያዋጣን የአንድነት ጥንካሬያችን እንጂ መከፋፈል ድክመት ነው ቢባሉ ተገንጣዮቹ በትምክህት ወግዱ ብለዋል፡፡
የሚያሳዝነው የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን የጨበጠው ኃይል የዚህን አገር የሚያስቆርስ ውጥን አሳላጭ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ኤርትራ ውስጥና በሌሎችም ክፍላተ ሀገር ሆነው ከመገንጠል ውጪ ገንቢ አማራጮችን የሚያቀርቡ ኤርትራውያን ፍላጎት የሚገለጽበት ዕድል፣ ይህንኑ በዴሞክራሲያዊ መንገድ አዛምተው ድጋፍ የሚሹበት ሁኔታ እንዲያገኙ አልተደረገላቸውም፡፡ እንዲያወም ተቆርቋሪ ወገኖች እንደ ጥፋተኞች በመቆጠር ይነቀፉ፣ ይገለሉም ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ያውም በሃያኛው ክፍለ ዘመን ‹‹ነፃነት ወይ ባርነት›› የሚል የፌዝ አማራጭ ቀረበላቸው፡፡ በዚህ መልክ አማራጮች ተገድበውና የሐሳብ ልዩነት ያላቸው ወገኖች ታፍነው በተካሄደ ሪፈረንደም የሚገኘው ‹‹ሕዝባዊ ውሳኔ›› ምን እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ ለዚህም ነው ከምርጫው አስቀድሞ ውጤቱን ከመቶ ይህን ያህል በሚል በልበ ሙሉነት ለመተንበይ የተደፈረው፡፡
ከውሳኔው በኋላ ኤርትራውያን ምርጫችን ነው ካሉ በግድ አብረን እንሁን በሚል መነታረክና ለሌላ እልቂት መፈላለግ ተገቢ አለመሆኑን ኢትዮጵያውያን ተገንዝበው የከረረውን የአንድነት ፍላጎት አርግበዋል፡፡ የጋራ መፈላለግና የእርስ በርስ ጥቅም ካላስተሳሰረ በስተቀር በጉልበት ወይ በማባበል ብዙም እንደማይዘለቅም ካለፈው አሠራር ተገንዝበዋል፡፡ ታሪክ ሲዛባ፣ ጊዜ ያጋጠመው ደባ ሲፈጸም ማየቱ ቢያስቆጭም ለዚህ አፀፋ የሁለቱም ወገን ሕዝቦች እንደገና ለግጭትና ችግር እንዲጋለጡ ማድረግ ስህተትን መድገም ይሆናል በሚል እውነታውን ለመቀበል ተገድደዋል፡፡
በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድን ጠላቴ ነህና አልፈልግህም ብሎ ያመፀንና ረግጦት ለመውጣት የወሰነን ወገን ፍላጎት ለማሟላት በበጀትና በቁሳቁስ መደገፍ አንሶት፣ ንብረቱን እየተገፈፈ እንዲሰቃይ መደረጉ የበደል በደል መሆኑ አልበቃ ብሎ፣ ‹‹እርም ከኢትዮጵያ ጋር…›› ያሉት ኤርትራውያን ራሳቸው ዞር ብለው የኢትዮጵያም ዜግነት እንዲኖራቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባለሙሉ መብትና ባለንብረት ለመሆን መሯሯጥ ያዙ፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ደጋፊ የሥልጣን መዋቅር በመታገዝ ሥልታቸውን ቀጠሉ፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ካለፈው ጦርነት በኋላ ጋብ ቢልም አሁን ደግሞ በተለያዩ መንገዶች እያገረሸበት እንዲያውም እየተባባሰም ይታያል፡፡
በተረፈ ኢትዮጵያ አሁን የተደቀነባት ትልቁ ተግዳሮት ኤርትራ መገንጠሏ ሳይሆን፣ የቀረውን አስማምቶ ዘላቂ ሰላም ማስፈንና ከመፈክር ባሻገር በእኩልነትና ፍትሐዊ መዋቅር አስተባብሮ የሕዝቦቿን ሕይወት የሚለውጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አያሌ ከፍተኛ ትልሞች አሉንና እነሱን ከግብ ለማድረስ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥል፡፡ እስቲ ምርታችን ይትረፍረፍና የንግዱ እንቅስቃሴ ይስፋፋና ማስተላለፊያ ወደብ ይቸግረን፡፡ ከለማንና በፍትሐዊ ሥርዓት ከደረጀን እንኳን የቅርብ ወገን የሩቅ ባዕድም ይፈልገናል፡፡ ከአጎራባቾች ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ተደራድረንና ተወዳድረን የምንሻውን እንገበያያለን፡፡ በውጤታችን ስንከበር ደግሞ እንደ ትናንቱ ሁሉም ይጠጉናል፡፡ ለወዳጅነትና ለአጋርነት ይማፀኑናል፡፡ እንዴ ይህ እኮ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በተለያዩ የታሪክ ወቅቶችና ሁኔታዎች ተስተውሏል፡፡ ከዚህ ውጪ ከብዙ ውጣ ውረድ የተረፈው የሕዝብ ለሕዝብ በጎ ስሜት እንዳይሟጠጥና የወደፊቱ ጉዞ እንዳይታወክ እኛም ከአውነታው ውጪ አጀንዳ አንፍጠር፡፡ ኤርትራውያን ደግሞ እያደቡ ሥልት በማፈራረቅ ‹‹የእኛንም የእናንተንም ለእኛ›› አይበሉን፡፡
No comments:
Post a Comment