ዶ/ር ነጋሶ የመጀመሪያው ፈራሚ ሆነዋል
“የአገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ እንጂ በውጭ ተቋማት መተማመንይቅር” – ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም
አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ከትላንት በስቲያ በይፋ የጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ የፀረ-ሽብር አዋጁን ማሰረዝ ዋነኛ አላማው እንደሆነ ገለፀ፡፡ ለዚህ ዓላማውም የአንድ ሚሊዮን ሰዎችን የድጋፍ ፊርማ (ፒቲሽን) በዕለቱ ማስፈረም የጀመረ ሲሆን የመጀመሪያው ፈራሚ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሆነዋል፡፡ ፓርቲው የፀረ-ሽብር ህጉን ለማሰረዝ ከሚንቀሳቀስባቸው ምክንያቶች አንዱ ህገ-መንግስቱን በእጅጉ የሚጥስና የኢትዮጵያን ዜጐች በማጥቃት የሚጀምር በመሆኑ ነው ብሏል – የህዝባዊ ንቅናቄው ኮሚቴ በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
ፓርቲው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል የጀመረው የሶስት ወር ንቅናቄ የአንድ ሚሊዮን ህዝቦችን ድምፅ በማሰባሠብ የአገሪቱን ዜጐችና ተቋማትን በማጥቃት፣ በሀይማኖት ጣልቃ በመግባት፣ ከአባትና እናት የተወረሠን ንብረትና ሀብት በሽብርተኝነት ስም የሚገፈውን አዋጅ ለማሰረዝ ጥረት እናደርጋለን፤ ወደ ክስም እንሄዳለን” ብሏል፡፡ “ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ካላት ተፈጥሯዊ ሀብትና መሠል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የፀረ-ሽብር ህግ አያስፈልጋትም ማለት እንዳልሆነ የገለፁት የንቅናቄው ኮሚቴ አባል አቶ ትዕግስቱ አወል፤ አሁን ስራ ላይ ያለው የፀረ ሽብር አዋጅ ግን ሰዎችን እና ተቋማትን የሚያጠቃ ነው ብለዋል፡፡
ከተጠቁት ተቋማት ውስጥ አንድነትና መድረክ ዋነኞቹ እንደሆኑ፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ሰዎችም የዚሁ አዋጅ ሠለባ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ከህገ መንግስቱ ጋርም በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚቃረን ትኩረት አድርገንበታል ሲሉም አክለዋል፡፡ “ምንም እንኳን በፍትህ ተቋማቱ ላይ ያለን እምነት የተሸረሸረ ቢሆንም አሁንም መብታችንን ከመጠየቅ የሚያግደን የለም” ያሉት የንቅናቄው ኮሚቴ አባል አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ መንግስት የ1 ሚሊዮን ሠው ድምፅና ጥያቄ አልቀበልም ካለ የፓርቲውን ሳይሆን የህዝቡን ጥያቄ አልመልስም እንደማለት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ፓርቲው በሶስት ወሩ ህዝባዊ ንቅናቄ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካተት ገልፆ፤ በዋናነት ህገ-መንግስቱን የሚፃረረውን የፀረ ሽብር አዋጅ ማሰረዝ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን በገጠርና በከተማ የዜጐች መፈናቀልና የመሬት ቅርምት ማስቆም፣ የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት እንዲቀረፍ ማድረግ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃ እንዲወሠድና የንግዱ ማህበረሠብ ከወንጀለኝነት ስምና ስግብግብ ከመባል ወጥቶ ጤናማ ውድድር እንዲኖር፣ እንዲሁም ማጥላላትና ማዋከብ እንዲቆም ማድረግ የሚሉት በዋናነት ተቀምጠዋል፡፡ የንቅናቄው ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተክሌ በቀለ፤ ንቅናቄው አሁን የተጀመረበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ “እስከዛሬ ንቅናቄውን ያልጀመርነው ፓርቲው በአየር ላይ የተንጠለጠለ እንዳይሆን በእግሩ እንዲቆም በማድረግ ስራ ላይ እና በውስጥ አደረጃጀት ተጠምደን ስለነበር ነው” ብለዋል፡፡
“እስከዛሬ እግር ሲያወጡ እንቆርጣቸዋለን እየተባለን፣ እግር ስናወጣና ስንቆረጥ ቆይተናል” በማለት ያከሉት አቶ ተክሌ፤ አሁን ግን በኢህአዴግ የሚደርስብንን ብቻ ሳይሆን የውስጥ ህመማችንንም ስናክም ቆይተን ከጨረስን በኋላ በእውቀት ላይ የተመሠረተ የህዝብ ንቅናቄ ለመጀመር ጊዜው አሁን እንደሆነ ውሳኔ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡ “በፍ/ቤቶች ላይ እምነታችን ቢሸረሸርም ፍትህ መጠየቃችንን አናቆምም” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ የአንድ የሚሊዮኖችን ድምፅ የምናሠባስበውም ለዚሁ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሀይሉ አርአያ በሠጡት አስተያየት አንድ አካል አጥፍቶ ያለመጠየቅን ነገር ፈረንጆቹ (Impunity) ይሉታል” ካሉ በኋላ “እዚህ አገርም አጥፍቶ የሚጠየቅ የለም፤ ስለዚህ በአገራችን ፍ/ቤት ካልተሳካ ወደ አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚኬድበት አማራጭም መዘንጋት የለበትም” ብለዋል፡፡ ነጋዴዎችን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ “የዚህን አገር ነጋዴዎች ለማወቅ የግድ የመጫኛ ነካሽ ልጅ መሆን አያስፈልግም” በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት የንቅናቄው ኮሚቴ አባል አቶ አቶ ዳዊት ሰለሞን፤ በአሁኑ ሰዓት ነጋዴው ሌባ፣ ዘራፊ፣ ሙሰኛ እየተባለና እየተብጠለጠለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “ገዢውን ፓርቲ የተጠጉ አካላት በአንድ ጀምበር የሀብት ማማ ላይ ሲወጡ፣ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች በስቃይ ላይ ናቸው ያሉት አቶ ዳዊት፤ የጥሬ እቃ እጥረትና መሠል ችግር ሲፈጠር መንግስት ጣቱን በነጋዴ ላይ እንደሚቀስር ጠቁመው፣ ነጋዴው በአገሩ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር የሚደረግበት አካሄድ እንዲቆም እንጠይቃለን ብለዋል፡
No comments:
Post a Comment