የሕዳሴው ግድብና ዐባይ፣ የሚሊኒየሙ ዐባይ ተጋቦት
አዘጋጅ ለኢትዮጵያ ፍቅር ከቃሊቲየዐባይ ሥረ_መሠረትና የሕዳሴው ግድብ ማነጣጠሪያ እነሆ!
- ጥናቱ የተፈጸመው ሚያዚያ 2003 (2011 እ ኤ አ) ነው።
- አቅርቦት የፀሐፊው ትክክለኛ ቅጂ (በአቀራረባዊ ጥንቅር)
- የጊዜው የኢትዮጵያ ጉዳይ ሆኖ የቀጠለውና ሕዝቡም የጠየቁትን እያደረገ ያለበት የሚሌኒየሙ ታላቅ የዐባይ ግድብ እንደተነገረው፤ የሚገደበው ከሱዳን ድንበር 17 (አሥራ ሰባት) ኪሎሜትር ባለ ቀረቤታ በዐባይ ወንዝ ላይ ነው።
- ግድቡ ወደ 62 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም አለው።
- የውኃው መጠን የጣና ሐይቅ ከሚይዘው ውኃ እጥፍ ይሆናል።
- በሚቋረው ውኃ 5250 (አምስት ሺ ሁለት መቶ ሃምሳ) ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል ሊመረት ታቅዷል። የሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንና ለግብፅም ሊሸጥ ታስቧል። ይህ ግንባት 80 ቢሊዮን ብር ይፈልጋል።
- ገንዘቡ በግብፅ ተፅዕኖ ሳቢያ የውጭ ብድር ወይም ዕርዳታ እንዳያገኝ ሰለሚጠናወት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ የመዋጮና ቦንድ ሺያጭ ሊሸፈን ነው ተብሏል።
- ለሕዝቡም ታሪካዊ ተዐምር ሊሠራ እንደሆነና የልማት ሁሉ አንጋፋ እንደሆነ ተነግሮት የቻለውንና ያልቻለውንም ከማድረጉ በላይ ለሃገር የሚበጅ ልማታዊ ድንቅ እንደተፈጠረ ተበስሮለታል።
- ባለፈው ሚያዚያ (April) 2013 እ ኤ አ ወር ማብቃያ አካባቢ በወጣው ዜና ደግሞ (ይህ ጥንቅር ከቀረበ ከሁለት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው። ቻይና ለሚሌኒየሙ ግድብ ግንባታ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ልታበድር ነው ተብሏል።
እኮ ቢጠቅማቸውማ ነው ዝምታቸው፤ የዐባይ ልጅ ይህ እንዴት ያየዋል?
ዝርዝሩን ምድር ላይ ያለውን እንየው፤
አባይ (ናይል)እየተባለ የሚጠራው በዓለም ረዥሙ ወንዝ፣6671 ኪሎ ሜትር እርዝማት ሲኖረው፣ከዘጠኝ አገሮች ይመነጫል።ግብፅ ምንም የምታመነጨው የውኃ አስተዋፆ የላትም። ሆኖም በናይል ውኃ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ አገር ናት። ግብፅ 100% የሰሐራ በረሃ አካል በመሆኗ በሜዲቴሪንያን አካባቢ ጥቂት ዝናብ ጠብ ከማለቱ ሌላ ከዓመት ዓመት ዝናብ አይጥልም።
በሌላ በኩል ደግሞ ከሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች ይበልጥ የ80% በመቶ ከአባይና ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንዞች የሚገኘው ውኃ አባይን ይገልጸዋል። በጠቅላላው የናይል ወንዝ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በዓመት ሲሰጥ ከዚህ ውስጥ ከኢትዮጵያ የሚገኘው የውኃ ድርሻ መጠን 54 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ነው። የዚህ ሁሉ ውኃ ምንጭ ኢትዮጵያ ስትሆን፤እንደ ሱዳንና ግብፅ እምነት ጥቂት ውኃ እንኳን ለመጠቀም መብት የላትም።ሌሎቹንም የናይል ውኃ አመንጪና ባለቤት የራስጌ አገሮችን በማግለል መብታቸውን ገፍፈው ሱዳንና ግብፅ ተከፋፍለውታል።
እ ኤ አ 1959 ዓ ም በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ፤ሱዳን ደግሞ 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ይወስዳሉ።በተለይ ግብፅ የውኃው ዋና ባለቤት እራሷን አድርጋ በመቁጠር አመንጪዎቹን የራስጌ አገሮች ለአነስተኛ የውኃ ጠቀሜታ እንኳን ፈቃጅ መሆን አለብኝ ባይ ናት። ለዚህም ኢትዮጵያን ማዳከም ወይንም ማጥፋት ተልኮዋ ሆኗል።
የአባይ ጠቀሜታ
- ግብፅና ሱዳን ፍፁም ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፤ በተቃራኒው የውኃ መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አልሆነችም።
- ግብፅ 3.0 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ታለማለች።
- ሱዳን 1.8 ሚሊዮን ሄክታር እንደዚሁ በናይል ወሰኗ ታለማለች።
የግብፅ በረሃ በናይል ውኃ በሺ ዓመታት የሚቆጠር የመስኖ እርሻ ልምድ ለምቶ እራሳቸውን ከመመገብ አልፈው የዳበረ ኢኮኖሚ ገንብተውበታል። አባይን ወደ ምዕራብ የግብፅ በረሃ ቀይሰው በመውሰድ ተጨማሪ 1.2 ሚሊዮን ሄክታር በረሃ ለማልማት መንቀሳቀስ ከጀመሩ ቆይተዋል።በዚህ ምዕራባዊ ከተማ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርበት ዘመናዊ ከተማ እየተገነባ ነው። የሲናይንም በረሃ ለማልማት በዓመት 4.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የአባይ ውኃ የሚያስተላልፍ ቧንቧ ዘርግተዋል። የመስኖ ሥራቸውን ለማካሄድ ያስቻላቸውም ታላቁ የአሳዋን ግድብ ነው።ግድቡ 162 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የማከማቸት አቅም አለው። በክረምት ወራት ከኢትዮጵያ የሚፈሰውን ውኃ አጠራቅመው በመያዝ በሰከንድ 1500 ቶን ውኃ እየለቀቀ በረሃውን ያለማል። ይህም ሆኖ በግብፆች ዕቅድ ተጨማሪ በረሃ ለማልማት 15ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ተጨማሪ ያስፈልገዋል። ለዚህም የተለያዩ ፕሮጀክቶች አስጠንተዋል። ጥናቱ ተጠናቆ ግንባታውም ተጀምሮ የነበረው አንዱ ፕሮጀክት በደቡብ ሱዳን ክልል ያለው የጀንገሌ ካናል ፕሮጀክት ነበር። የናይል ወንዝ በደቡብ ሱዳን ሱድ እየተባለ የሚጠራውን ረባዳና ረግረግ ሰፊ መሬት አቋርጦ ያልፍል።ወንዙ በክረምት ከአፍ እስከ ገደብ ሲሞላ ግደቡን ጥሶ ለጥ ወዳለው ሜዳ መፍሰስ ይጀምራል።ግድቡን አልፎ የተንጣለለው ውኃ ተመልሶ ወደ ወንዙ ሊገባ ስለማይችል፤እንደተንጣለለ ይደርቃል።ይህም በፀሐይ ሙቀት እየተነነ ይጠፋል። ታዲያ ግብፃውያን የጀንግሌ ካናልን ፕሮጀክት ያጠኑትና ሥራውንም የጀመሩት በትነት የሚባክነውን ውኃ በማግኘት የናይልን ውኃ መጠን 10% ከፍ ለማድረግ ነበር።
1ኛ የጀንግሌ ካናሉ ግንባታ የተጀመረው የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ድርጅት የነፃነት እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ስለነበር ፕሮጀክቱ ሳይገፋ አገራችን ይደርቃል፣ ኢኮሎጂውም ይለወጣል፣ በማለት ኤስ .ፒ .ኤል. ኤም ፕሮጀክቱ ላይ ጥቃት በመሰንዘር አጨናገፈው።
2ኛ ተጨማሪ ውኃ ለማግኘት ያስችላል ተብሎ የተጠናው ሌላው ፕሮጀክት ደግሞ በኢትዮጵያ ትልልቅ ግድቦች መገንባትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ነው። ግብፅ በረሃማ አገር በመሆኗ የፀሐይ ሙቀት ያጠቃታል፤በዚያ የተነሣ በአገራቸው ከተገነባው ቃላቁ የአስዋን ግድብ በፀሐይ ሙቀት ብቻ በትነት ከተከማቸው ውኃ 12% ይባክናል።ይህ በጣም የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው። ብዙ ውኃ ሊይዝ የሚችል ሌላ ትልቅ ግድብ ለመገንባት የሚቻለበት ቦታ ስለሌላቸው ተጨማሪ ውኃ በሃገራቸው ውስጥ ለማከማቸት ያላቸው ዕድል በጣም የመነመነ መሆኑን ተረዱት። በዚህ የተነሣ ጥረታቸውን በኢትዮጵያ ላይ አድርገዋል።በደጋው ኢትዮጵያ ትላልቅ ግድቦች ለገነቡባቸው የሚችሉበት ቦታዎች በርካታ ናቸው። በሚገደቡት ግድቦች የሚከማቸው ውኃ በትነት የመባከን አደጋ አያጋጥመውም።ውኃው ሳይባክን ለብዙ ጊዜ ተጠብቆ የመቆየት ዕድል አለው።ኤሌክትሪክ ለማምረት እየተባለ ከሚገነቡት ግድቦች ከሚለቀቀው ውኃ ምን ያህል ተጨማሪ ውኃ ሊገኝ እንደሚችል ግብፃውያን አስጠንተው አውቀውታል።በጥናቱ መሠረት በኢትዮጵያ 23 ትላልቅ ግድቦችን በአባይ መጋቢ ወንዞች ላይ መገንባት የሚቻልባቸው ቦታዎች ተለይተው ታውቀዋል፤መነሻ ጥናት ተካሄዶባቸዋል፤እንደጥናቱ በእነዚህ ቦቻዎች በሚገነቡ ግድቦች ብዙ ቢሊዮን ሜትር ኩብ መጠን ያለው ውኃ ይከማቻል።ከዚያም በያንዳንዱ ግድብ የሚተከሉት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ተርባይን ለማሽከርከር ውኃ ይለቀቃል።የአባይ ወንዝ በሚሞላበት ወቅት የአገራችንን ድንበር አልፎ ሱዳን ሲገባ የሚያፈሰው የውኃ መጠን 400 ሜትር ኩብ ውኃ በሰኮንድ ሲሆን አባይ ደረቀ በሚባልበት በበጋው ወቅት ደግሞ 4 ሜትር ኩብ ውኃ በሰኮንድ ይፈሳል። ልዩነቱን አጢኑት በበጋው የሚፈሰው በአንድ መቶ ጊዜ ይቀንሳል።ከዚህ ሁኔታ መገንዘብ የሚቻለው በሱዳንም ሆነ በግብፅ በክረምት ወራት ከኢትዮጵያ የሚፈስላቸውን ውኃ ገድበው በመያዝ በበጋ ወራት እየለቀቁ መጠነኛ የእርሻ ሥራ ከማካሄድ ውጭ የመስኖ እርሻ እንቅስቃሴ አያካሄዱም ማለት ነው። በኢትዮጵያ ግድቦች ተገንብተው ውኃ እየለቀቁ ተርባይኖችን ማሽከርከር ሰንጀምር ግን ይህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ይለወጣል። ከተጠኑት 23 የግድብ ሥፍራዎች ውስጥ አነስተኛ ውኃ የማከማቸት አቅም ያላቸው አራት ግድቦች ቢገነቡና በየአንዳንዱ ግድብ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት፤ አራት አራት ተርባይኖች ቢተከሉና እነዚህን ተርባይኖች ለማሽከርከር 20 ሜትር ኩብ ውኃ በሰኮንድ ቢለቀቅ ሱዳንና ግብፅን አባይ ሲደርቅ 80 ሜትር ኩብ ውኃ በሰኮንድ ያገኛሉ ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ብቻ ለማምረት ፈልጋ ግድብ ከገደበችና ተርባይኖችን ለማሽከርከር አንድ ጊዜ ውኃ መልቀቅ ከጀመረች በኋላ ውኃውን በከፊል ወይም በሙሉ ለመስኖ እርሻ ልማት መጠቀም ብትሞክር የሱዳንና የግብፅን ሕዝቦች በረሃብ ፈጀች፤ የአባይን አቅጣጫ ቀየረች፤ በሚል ሰበብ ለጦርነት መነሳታቸው አይቀርም። በዓለም አቀፍ ደረጃም እንድተወገዝ ፓለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ጫና እንዲወድቅባት ያደርጋሉ።
በዚህ ምክንያት በአባይ ወይም በአባይ ገባር ወንዞች ላይ ግድብ ገንብተን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከመጀመራችን በፊት ውሎ አድሮ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ሁኔታ አለመፍጠሩን ከብዙ አቅጣጫዎች መመርመር አለብን። እንደሚታወቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማንኛውም አገር ዕድገትና ሥልጣኔ ወሳኝ ኃይል ነው። ኃይል እንደመሆኑ ሁሉ ኢትዮጵያም የኢሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ያስፈልጋታል። በቀላል መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ደግሞ ያላትን የውኃ ኃይል መጠቀም ይኖርባታል። በውኃው ኃይል ኤሌክትሪክ ስናመርት ግን ተርባይኖቹን የሚያሽከረክረው ውኃ ተለቆ የሚሄድ ሳይሆን ለመስኖ ልማት ላይ መዋል ይኖርበታል።ግድብ ፣ገድበን ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ስናስብ፣ የሚለቀቀው ውኃ እታች ወርዶ ማሳውን እንዲያጠጣ ተደርጎ መታቀድ ይኖርበታል።በዚህ አኳኋን ካልታቀደ በከፍተኛ ወጪ ያጠራቀምነውን ውኃ ያለምንም ክፍያ ለሱዳንና ለግብፅ አሳለፈን ሰጠን ማለት ነው። ከዚህ ግንዛቤ በመነሣት በደርግ ጊዜ የመልካ ዋከና የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያ ሲገነባ በተጓዳኝ በኡጋዴን ጎዴ አካባቢ ተርባይኑን ለማሽከርከር የሚለቀቀው ውኃ ተጠልፎ እስከ 50ሺ ሄክታር የመስኖ እርሻ እንዲያጠጣ ታቅዶ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ሥራ እንደጀመረ የ20ሺ ሄክታር ማሳ እንዲያለማ ተደርጎ ነበር።በሌላ በኩል ከልማት ጋር ሣይያያዝ የተገነባው የፊንጫ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያ የሚለቀቀው ውኃ ያለጥቅም መፍሰሱን በመመልክት ለስኳር ፋብሪካ ጥሬ ዕቃ የሚሆን ሸንኮራ አገዳ በ10ሺ ሄክታር ማሳ እንዲያለማ ታቅዶ ሥራው ተጀምሮ ነበር።የጣናን ሃይቅ በማሳደግ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ሲወሰን በተመሳሳይ መንገድ የሚለቀቀውን ውኃ በመጠቀም በበለስ ሸለቆ እስከ 100ሺ ሄክተር የመስኖ እርሻ ለማት ለማካሄድ እንቅስቃሴው ተጀምሮ ነበር።በሌሎች አካባቢዎችም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በሚታሰብበት ጊዜ የሚለቀቀው ውኃ ጥቅም ላይ ውሎ የአገራችንን ኤኮኖሚ ለማሳደግና በምግብም ራሳችንን እንድንችል እንዲረዳ ጎን ለጎን መታቀድ ነበረበት።
ከመስኖ ልማት ጋር ሳይያያዝ ግድብ መገንባትና ኤሌክትሪክ ማመንጨት የግብፅን ፍላጎት በፍቃደኝነት ማሟላት ማለት ነው።ግብፅ ሙሉ ወጪውን በመሸፈን በኢትዮጵያ ትላልቅ ግድቦችን ለመገንባት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የሚለቀቀውን ውኃ ሳይቀናነስ እንድትወስድ ማረጋገጫ ቢሰጣት ያለ ማቅማማት እንደምትስማማ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል።ግብፅ ውኃውን ከምንም ነገር አስበልጣ ስለምትፈልገው በኢትዮጵያ ግድቦች ቢገነቡና ኤሌክትሪክ በቻ እንዲመረት ቢደረግ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አታሰማም።ለማስረጃ ያህል በጣና ሃይቅ የአባይ ወንዝ መውጪያ ላይ የተወሰነ ግድብ ተገንበቶ የጣና ውኃ መጠን እንዲጨምር ከተደረገ በኋላ በምዕራብ አቅጣጫ ጣና ተሸነቁሮ ውኃውን ቁልቁል በመልቀቅ ተርባይን እንዲያሽከረከር ተደርጎ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከተጀመረ ቆየት ብሏል፤ የተከዜ ወንዝ ተገድቦ የተጠራቀመው ውኃ እየተለቀቀ ኤሌክትሪክ ማምረት ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።ታዲያንስ ግብፅች የተጠራቀመ ውኃ በጣም በሚያስፈልጋቸው በድርቅ ጊዜ ሳይቋረጥ የሚያገኙት መሆናቸውን ሰለሚያውቁ ለምን በጣና ሃይቅ ኤሌክትሪክ ይመረታል፣በተከዜ ወንዝ ላይ ግድብ ተገንብቶ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ለምን ተጀመረ ጥቅማችንን ይጎዳል ብለው አልተናተሩም ፤ ተቃውምም አላሰሙም፤ ምክንያቱ ተጠቃሚዎቹ እነሱ ናቸውና።
አባይን አስመልክቶ ይህን ያህል ከተነጋገርን ስለ’’ ታላቁ የሚሊኒዮም ግድብ’’ አንዳንድ ነገር ብናነሳ መልካም ይመስለኛል።እንደተነገረን ግድቡ የሚገነባው በቤኔኛንጉል ክልል ከሱዳን ድንበር 17 ኪሎሜትር ርቀት በሚገኝ ቦታ ላይ ነው። ግድቡ 62 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ይይዛል።የግንባታው ወጪ 80 ቢሊዮን ብር ሲሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ ይሸፈናል ተብሏል።በግድቡ ውኃ 5250 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ይመነጫል።እንግዲህ ከግድቡ ኢትዮጵያ የምታገኘው ጥቅም የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ መሆኑ ነው።ግብፅና ሱዳን ግን ተጨማሪ ውኃ ያገኛሉ።ኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት ምን ያህል ተርባይኖች እንደሚተከሉ አይታወቅም። 5250ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ለማምረት አንዱ ተርባይን 50 ሜጋ ዋት እሚያመነጭ ቢሆን እንኳን ከ 100 ተርባይኖች በላይ መትከል ይኖርባቸዋል።አንዱን ተርባይን ለማሽከርከር 5 ሜትር ኩብ ውኃ በሰኮንድ መልቀቅ ያስፈልጋል ቢባል እንኳን 100 ተርባይኖችን ለማሽከርከር 500 ሜትር ኩብ ውኃ በሰኮንድ መልቀቅ ያስፈልጋል ማለት ነው። አባይ ሲሞላ በክረምት ወራት ከተጠራቀመው ውኃ ተርባይኖችን ለማሽከርከር መልቀቅ አስፈላጊ አይሆንም። ወንዙ በግድቡ ላይ ሰለሚያልፍ እግር መንገዱን ተርባይኖቹን እያሽከረከረ ያልፋል።በግድቡ የተከማቸውን ውኃ መልቀቅ የሚያስፈልገው በበጋ ወራት አባይ ሲደርቅ ነው።ተርባይኖች ከዓመት ዓመት መሽከርከር ሰለአለባቸው ከግድብ እየተለቀቀ የሚወርደው ውኃ በቋሚነት ያስፈልጋል። በዚህ አሠራር በክረምት ወራት አባይ ሲሞላ ከመገኘው የውኃ መጠን የበለጠ ግብፅና ሱዳን በበጋ ወራት ያገኛሉ ማለት ነው።ይህ መጠን በተፈጥሮ ከሚያገኙት በእጅጉ ይበልጣል።በተፈጥሮ የሚያገኙት ውኃ እየቆጨን እያለ እያንዳንዱ እትዮጵያዊ እየተመጠጠ በተሰበሰበው ገንዘብ ትልቅ ግድብ ገድበን ውኃ አጠራቅመን በተጨማሪ መስጠታችን እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተረዳው ወይም የተገነዘበው አይመስልም።ሕዝቡ የሚመስለው ወንዙ ተገድቦ ለልማት ውሎ ከረሃብ እንደሚወጣ ነው። በጥቅሉ አባይ ሊገደብ ነው እየተባለ ይነገረዋል።በሚገደበው ግድብ ከሚከማቸው ውኃ አንድ ሄክታር መሬት እንኳን በመስኖ እንደማይለማ አይነገረውም። ከታላቁ ግድብ ጋር ምንም የመስኖ ልማት ፕሮግራም አልተያዘም። ወደፊት ውኃውን ለልማት እናውለዋለን እንዳይባል ከግድቡ በታች ለእርሻ የሚሆን መሬት የለም። በርባራ አካባቢ ነው፤ ከዚያም ቢሆን ውኃው ተለቆ ተርባይን ከአሽከረከረ በኋላ በቀጥታ ሱዳን ውስጥ ይገባል።ምክንያቱም በሱዳን ጠረፍና በግድቡ መሐል 17 ኪሎ ሜትር ብቻ እርቀት ነው ያለው።የውኃ ጉዳይ ለግብፅ የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ ነው። ከኢትዮጵያ የምትወጣዋን ውኃ ትቆጣጠራለች። ይህ አዲሱ ግድብ ሥራው ተጠናቆ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ውኃ መልቀቅ ከጀመረ በኋላ ውኃውን ማቆም አይቻልም።ምክንያቱም ከዓመት ዓመት የሚፈሰው ውኃ እየተለካ ይመዘገባል።ኤልክትሪክ ማምረት አቁማአለሁ ብላ ኢትዮጵያ ብታቆም ጦርነት እንደማወጅ ተቆጥሮ በግብፅና ከሱዳን ጋር ውጊያ መግጠምን ያስከትላል።በመሆኑም ዛሬ የሐገር ፍቅር ስሜታችንን ቀስቅሰው በሚገባ ገልፅ ሳይሆንልን የግድቡን ሥራ መደገፋችን ገንዘብ ማውጣታችን ወደፊት መዘዝ ያስከትልብናል። ‘አባይ ሊያለማን ወይስ ሊያጠፋን’ ብን መጠየቅም ይኖርብናል። ግድቡ የመስኖ ልማት ጋር ቢያያዝ ከረሃብ ከድህነት ልንወጣ ስለምንችል ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ሕዝብ ቢከፍል ተገቢ በመሀነ ነበር፤ ከሕዝብ ጎን ጋር ያልተዛመደ ግዙፍ ሥራ መወጠኑ በኋላ አሁን ለሚደረገው የሚያስጠይቅ ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልተካፈለበትና በድበቅ በተያዘ የዚህን ግዙፍ ሥራ በሕዝብ ሰም ማንነታቸው ባልታወቁ ነገ በሃላፊነት በማይጠየቁ ግለሰቦች መንግሥት ነን ባሉ መመራቱ ለወደፊቱ የትወልድ ጦሰ መሆኑን ቆም ብለን፤ የሚመጣው መዘዝ በጥልቅት አስተውለን፤ የዜግነትን ኃላፊነታችንን መወጣት ግድ ይለናል።የሚገርመው ደግሞ ከዚህ ድንቅ ከተባለው ግድብ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳንና ለግብፅ ይሸጣል መባሉ ነው።የሚሸጠውም በጣም በአነስተኛ ዋጋ ነው።በአሁኑ ጊዜ ለሱዳን አንድ ኪሎዋት የሚሸጠው በስድስት ሳንቲም የአሜሪካን ሲሆን፣ሱዳን በሃገሯ እስከአሁን የምትሸጠው ሃያ ስድስት ሳንቲም የአሜሪካ ነው።በዚህ ዓይነት የ ሃያ ሳንቲም ትርፍ ታገኛለች ማለት ነው።ሱዳንና ግብፅ በውኃችን የተነሣ ጠላት አድርገውን በዙ ጎድተውናል።ወደፊትም ይጎዱናል። ሃገራችንን ለመከፋፈልና ለመገነጠል ለተሰለፉት ዛሬ ኤርትራ ገንጥለው ለሚያስዳድሩትና የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር በጎሣ ከፋፍለው የሚመሩትን ቡዱኖች አጋር ሆነው ቆይተዋል።’አንዳንዴ የአባይ ግድባ ለነዚህ ሃገሮች ዎሮታ ይሆን’ ብለው የሚጠይቁ ሃገር ወዳዶች አሉ። ታዲያ በዚህ የጠላትነት መንፈስ እየተመለከቱን እያሉ ኤሌክትሪክን ያህል የልማት ኃይል አቅራቢ ሆነን እንዲያድጉና እንዲበለጽጉ በወታደራዊ ቴክኔክና ቴክኖሎጂ እንዲዳብሩ መርዳቻችን እንደሆነ መገንዘብ አልቻልንም።ኤሌክትሪክ ለጎሮቤት አገሮች የመሸጥ ሐሣብ በደርገ ዘመን ተነስቶ ነበር።የጦር መሣሪያ ከማስታጠቅ አይተናነስም ተብሎ ሐሣቡ ውድቅ ተደርጎ ነበር።ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌሎች ወንዞች ማመንጨት ይቻላል ተብሎ፤በግልገል ግቤ በርካታ ግድቦች ተገድበው በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመረትበት ቦታ የሌለ ይመስል ታላቁ ግድብ ኤሌክትሪክ በኤሌክትሪክ ያደርገናል ችግራችን በሙሉ ይወገዳል፤እየተባለ የሚካሄደው አዳናጋሪ ፕሮፓጋንዳ ወደፊት ሃቁ መታወቁ አይቀርም።እኔ እንደምገምተው ከግብፅ ጋር ስምምነት አድረገው በጋራ የነደፉት ፕሮጀክት ይመስለኛል።በጥናቱም ላይ የግብፅ እጅ ይኖርበታል የሚል ግምት አለኝ።የዚህ ግድብ ሥራ ግብፅን የሚጎዳ ቢሆን ኖሮ በዓለም ከፍተኛ ጩህትና የፖለቲካ ትረምስ ይሰማ ነበር። ግብፅ ያለችው ነገር ቢኖር ቴክኒካል ወረቀቶቹን ስጡኝ ነው፤ይህም ለማለት ያህል እንጂ ቴክኒካል ጥናቱ ቀድሞ በእጇ ይገኛል። አሁን ለግብፅና ለሱዳን የሚጠቅም ሥራ ኢትዮጵያ በማቀሳቀሷ ከዚህ በፊት በአባይ ጉዳይ ላይ አልነጋገርም፤ ስምምነትም በአዲስ መልክ አላደርግም ሲሉ የነበሩ ሁለቱ አገሮች በጉዳዩ ላይ እንደራደራለን የሚል አቋም ይዘዋል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ማውጣቱን እንዲቀጥል ብቻ አልፍ አለፍ እያሉ በለሆሳስ የግድቡ ሥራ አሳስቦናል ይላሉ።
ዘለዓለማዊ የሃገር መታደግና ዕድገት ሳይሆን ሰለዓለማዊ ጠንቅ እንዳይተከልባት ለምን? ለማን? እንዴት? የሚለው የሃገር ጥቅም መለኪያ፣ሊተኮርበት ይገባል።ከራስ እያወለቁ ጠላትን እያስታጠቁ ግንባታ ስንኩል ስለሆነ አባይ መዘዝ ሳይሆን ሕዝብ አገዝ እንዲሆን ሁሉም ዕድሉ አሁን መሆኑን መገንዘብ ይገባዋል።
የኢትዮጵያ ፍቅር ከቃሊቲ
No comments:
Post a Comment