የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክና በባህል ትስስሩ፤ በረጂም ግዜ አብሮ መኖር ልምዱና እንዲሁም በነፃነትና ዲሞክራሲ ትግል ምዕራፉ ዉስጥ በጋራ ያፈራቸዉና በባለቤትነት የሚጋራቸዉ የተለያዩ እሴቶች አሉት። ቆየት ያሉትንና በኩራት የሚያስፈነድቀንን የአድዋን ድል ወይም በኃዘን ስሜታችንን ሁሌም የሚቆጠቁጡዉን የሰማዕታት ቀን ትተን የአጭር ግዜ ትዉስታችንን ስንፈትሽ ፊታችን ላይ እንደ መስታወት ድቅን እያሉ እራሳችንን ከሚያሳያዩን ቀኖች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ግንቦት 7 1997 ዓም የዋለዉ ታሪካዊ ቀን ነዉ። ይህ ቀን በኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ትግል ሂደት ዉስጥ የፀሐይንና የጨረቃን ያክል ገዝፎና ደምቆ የሚታይ ልዩ ቀን ነዉ። ግንቦት ሰባት 1997 ዓም የኢትዮጵያ ህዝብ ብሩህና የወደፊቱን አመላካች የሆነ ፍሬያማ ጉዞ ጀምሮ ፍሬዉን ከማየቱ በፊት የጀመረዉን ጉዞ እንዲያቋርጥ የተገደደበትና ለዘመናት አንገቱ ላይ አንደ ቀንበር ተጭኖበት የቆየዉን የአምባገነኖች ክፉ ጫና አዉልቆ ለመጣል ሲዘገጅ ዝግጅቱ በአጭር የተቀጨበት ጨለማና ተስፋ፤ ቁጭትና ጽናት አንድ ላይ የታዩበት ትንግርታዊ ቀን ነዉ።
ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. በዛሬዉና ለወደፊት በተከታታይ በሚመጣዉ ኢትዮጰያዊ ትዉልድ ልብ ውስጥ ተስፋን፤ ልበሙሉነትን፤ ጅግንነትንና መስዋዕትነትን እየጠቆመ ለዘለአለም የሚዘከር ቀን ነዉ። ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያ ህዝብ በጠመንጃ ኃይል እላዩ ላይ የተጫነበትን ዘረኛ አምባገነን ስርዐት በምርጫ ካርድ ጥሎ ለእድገት፤ ለሰላምና ለአንድነቴ ይበጁኛል ያላቸዉን መሪዎቹን መርጦ ስልጣን ወንበር ላይ ለማስቀመጥ ታሪካዊ እርምጃ የወሰደበትና አርቆ አሰተዋይነቱን ለአለም ህዝብ ያሳየበት ቀን ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ ግንቦት ሰባት አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ለህዝብ ምርጫና ፍላጎት የማይገዛና የስልጣን ዘመኔን ያሳጥርብኛል ብሎ ያሰበዉን ሁሉ ያለ ርህራሄ የሚገድል ጸረ ህዝብ ኃይል መሆኑን ያረጋገጠበት ቀን ነዉ።
ግንቦት ሰባት ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ ቋንቋ፤ ክልልና ኃይማኖት ሳይከፋፍሉት ከዳር ዳር አንደ አንድ ሰዉ በመቆም ያሳየዉ የኢትዮጵያዊነት፤የአንድነትና፣ የወንድማማችነት ስሜት በጻነትና በዲሞክራሲ ትግላችን ታሪክ ዉስጥ ለዘለአለም ሲታወሱ የሚኖሩ የህዝብ ትዉስታዎች ናቸዉ። ሆኖም ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱንና ለዲሞክራሲ ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጠዉን ያክል ጠላቶቹም እነሱ ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሊኖር የሚችለዉ ዲሞክራሲ ከእነሱ ዉጭ ሌላ ማንንም ወደ ስልጣን የማያመጣ መሆኑን በጠመንጃ ኃይል ያረጋገጡበት ቀን ነዉ።
ግንቦት ሰባት 1997 ዓም የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ልብና አዕምሮ ዉስጥ መንግስትን በምርጫ ካርድ መቀየር እንችላለን የሚል ስሜት እንዳይለመልም በህግ ሽፋን ተከታታይ እርምጃዎችን መዉሰድ የጀመረበት ቀን ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ህዝብም በበኩሉ ነጻ የመገናኛ ተቋሞች፤ ነጻ ፍርድ ቤት፤ገለልተኛ የምርጫ ተቋምና ለህገ መንግስት የሚገዛ ጦር ኃይል በሌለበት ሁኔታ ዉስጥ የሚካሄዱ ምርጫዎች እንደማይጠቅሙት አዉቆ ወያኔን ማስገደድ የሚችል የትግል እስትራቴጂ የቀየሰበት ቀን ነዉ።
ግንቦት 7 ቀን 2000 ዓም የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔ በጠመንጃ ኃይል የነጠቀውን መብት በተቀነባበረ ሁለገብ ህዝባዊ ትግል ለማስመለስና ኢትዮጵያ ዉስጥ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ህዝብ ብቻ መሆኑን ለማረጋገጥ አዲስ የትግል ስልትና ግንቦት ሰባት የፍትህ፤የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን አምጦ የወለደበት ቀን ነዉ። የግንቦት 7 ብቸኛ አላማ ኢትዮጵያ ዉስጥ መንበረ ስልጣን ትክክለኛ ባለቤቱ ወደ ሆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ዉስጥ እንዲገባ ማድረግና የወያኔን አገዛዝ አገራችን ዉስጥ የመጨረሻዉ አምባገነን ስርአት ማድረግ ነዉ። ግንቦት 7 ይህ አላማዉ ግቡን እስኪመታ ድረስ ህዝባዊ ትግሉን እንደሚገፋበት ለኢትዮጵያ ህዝብ የገባዉ ቃል ኪዳን ዛሬም ህያዉ መሆኑን ያረጋግጣል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
No comments:
Post a Comment