Saturday, April 27, 2013
ኦባማ አርፍደው ወደ ኢትዮጵያ? “በአፍሪካ ብዙ ስራ አለን” ጆን ኬሪ
በአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ከሚገኙት የተለያዩ እንግዶችና ባለስልጣናት በተጨማሪ አራት ታላላቅ መሪዎች እንደሚገኙ እየተነገረ ነው። በዋናነት የሚጠቀሱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኦባማ ሲሆኑ፣ የቻይና አቻቸውም ዋናውና ታላቁ እንግዳ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ባለፈው ረቡዕ ለአሜሪካ ኮንግረንስ ኮሚቴ የተናገሩትን በመጥቀስ ዜናውን የላኩልን ክፍሎች እንዳሉት ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ሊያመሩ ይችላሉ።
ውጪ ጉዳይ ሚ/ሩ ኦባማ ኢትዮጵያ ስለመሄዳቸው ፍንጭ ቢሰጡም ስለጉዞው ዝርዝር አለመናገራቸው ታውቋል። የቻይና በአፍሪካ ሚና መጉላት ውሎ አድሮ የጠዘጠዛት አሜሪካ፣ በመጪው ወር በሚካሔደው የአህጉሩ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በፕሬዚዳንቷ ለመወከል መወሰኗ “ጉባኤ አድማቂ” አሰኝቷታል።
“በአፍሪካ ብዙ የምንሰራው ስራ አለን” ሲሉ የተናገሩት ኬሪ “በድግሱ” ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል። እየተጣጣመ የመጣው የአፍሪካና የቻይና ፍቅር እንዲሁም ቻይና በአፍሪካ ያላት ሰፋ ያለ ኢንቨስትመንት ለአሜሪካ አሳሳቢ ከመሆኑ ባሻገር ቻይና የምትከተለው የንግድ ስልት በአጠቃላዩ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ውጪ ጉዳይ ሚ/ር ኬሪ አልሸሸጉም፡፡ ዝርዝር ከመስጠት ቢቆጠቡም ጉቦ፣ ሙስና፣ አምባገነኖችን መርዳት በማለት የተወሰኑትን በግልጽ ከመጥቀስ አላለፉም፡፡
ኦባማም ወደ ኢትዮጵያ የሚያቀኑበት ጉዳይ አሜሪካ በአፍሪካ ለምትከተለው አዲስ እቅድ ማጠናከሪያ ካስማ ለመቸንከር እንደሆነ አብዛኞች ይስማሙበታል። “ቻይናን በቅርብ ሆኖ መቆጣጠር” በሚለው መርህ የአፍሪካን አምባገነኖች ወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት ልቡናቸውን የመስለብ እቅድ ይዛ እየሰራች ያለችው አሜሪካ፣ የቻይናና የአፍሪካ ግንኙነት “የፓለቲካ እባጭ” የሆነባት ቻይና ድፍን የአፍሪካ መሪዎችን ቤጂንግ ጋብዛ ወዳጅነቷን አደባባይ በማውጣት ጸሐይ ካስመታቸው በኋላ ነበር። በርካታ መረጃዎችም በዚሁ ዙሪያ ቀርበዋል።
በቤጂንጉ ጉባኤ ቻይና ዶላር ለሚናፍቁት የአፍሪካ መሪዎች ብድር ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ፣ የመንገድ ግንባታ፣ የተለያዩ ርዳታዎች ለማድረግ፣ ከዚህም በላይ አምባገነኖች የስለላ መዋቅራቸውን እንዲያደራጁ የሚያስችላቸው በገሃድ እንዳይሰራጩ የተከለከሉ የአፈና መሳሪያዎችን ጭምር ለመስጠት ቃል ገብታ አፍሪካን የገበያዋ ሳሎን ስታደርግ አሜሪካና አውሮፓውያኖቹ ደነገጡ፤ ታመሙ።
በተመሳሳይ ቻይና ዘይትና የተለያዩ ማዕድኖችን ከአፍሪካ በመዛቅ የገበያ ድሯን ዘርግታ አፍሪካን ተጣባቻት። ዜጎቿንና የንግድ ተቋሞቿን አፍሪካ ምድር በትና ከላይም ከታችም ተቆጣጠረቻት። ከዚህ በኋላ ነበር መቀደሟ ያሳሰባት አሜሪካ ቻይናን በቅርብ መከታተል በሚል አዲስ ስልት የነደፈችው።
ባለሙያዎችና የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት አሜሪካ በኢኮኖሚና በገንዘብ ድጋፍ የአፍሪካን ሆዳም መሪዎች በማባበል ቻይናን ለመፎካከር በዛሬው ጊዜ አይቻላትም፤ በገሃድ እከተለዋለሁ የምትለውን ግብዝ ፖለቲካ ያበላሽባታል። እንደውም አታስበውም። ለዚህ ይመስላል የአፍሪካ አገሮችን ወታደራዊ ሃይል በማሰልጠን፣ በማደራጀት፣ በማስታጠቅ፣ የየአገራቱን ወታደራዊ እዝ ከበላይ ሆኖ በመምራት የቻይናን እንቅስቃሴ ለመበርበር የተንቀሳቀሰቸው። (ከዚህ በፊት “የኦባማ አስተዳደር መጪው የአፍሪካ ዕቅድ” በሚል የጻፍነውን እዚህ ላይ ይመልከቱ)
አምባገነኖች የመከላከያ ኃይላቸውን እንደ ብረት ለማጥበቅ ካላቸው የጸና ፍላጎት አንጻር አሜሪካ የነደፈችው ስልት የተዋጣለት እንደሆነ የሚናገሩ ክፍሎች “አሁን አሜሪካ ወታደራዊ ሃይልን ለማጠናከር በሚል ወደ አፍሪካ የገባችበት ስልት፤ ከአፍሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች እውቅና ውጪ የሚፈጸም ተግባር ስለሌለ መረጃ የማግኘት አቅሟ የቻይናን መስኮት በርግዳ ሳሎኗን የማየት ያህል ነው” ይላሉ፡፡
አሜሪካ አሁን ባለችበት ደረጃ አፍሪካ 50ኛ ዓመት በዓል ስታከብር በይፋ ባይረጋገጥም ኦባማ የመገኘታቸው ሚስጥር ከፖሊሲያቸውና ቻይናን በቅርብ ሆኖ ከመቆጣጠር አዲሱ ስልታቸው በመነሳት እንደሆነ የማያሻማ ነው። በጉባኤው ላይ አራት ከፍተኛ የአገር መሪዎች እንደሚገኙ የኢህአዴግ አንደበት ፋና ጠቁሟል ግን ዝርዝር አላቀረበም። ጆን ኬሪ “ከአፍሪካ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት ከአህጉሪቷ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል እንሰራለን” ማለታቸውን ፋና ምንጭ ሳይጠቅስ አስፍሯል።
ፋናም ሆነ ሌሎች የመንግስት ሚዲያዎች ይፋ ባያደርጉትም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ባለስልጣናትና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የስብሰባው ታላቅ እንግዳ እንደሚሆኑ ፖለቲከኞች ቅድመ ግምታቸውን አኑረዋል። በኢህአዴግ ጉባኤዎች ላይ የክልል አንድ ልዩ ዞን ተወካይ እስኪመስል ልዑክ በመላክና የቻይንኛ ቀረርቶ በማሰማት ተሳትፎ ያላት ቻይና ለአፍሪካ ህብረት ታላቅ ስጦታ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።
የአፍሪካ ኅብረትን ዘመናዊ ህንጻ በራስዋ ወጪ ያስገነባቸው ቻይና በቤቷ፤ ኦባማም ከተገኙ በእንግድነት የኅብረቱን የምስረታ ዘመን አስመልክቶ ቻይና በነጻ ገንብታ ባስረከበችው ህንጻ ውስጥ ሆነው ህንጻውን እያደነቁ ይደሰኩራሉ።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment