በጋምቤላ የደረቁን ወቅት ወይም በጋውን በወንዞች ዳር ውሃ ተንተርሶ መኖር የተለመደ ነው። ከቋሚ የመኖሪያ ቀዬ ወደ ወንዝ ዳርቻ በመሄድ አድኖ መመገብና አሳ አስግሮ ዕለትን ማሳለፍ የባህል ያህል ነው። በአገሬው ልምድ መሰረት ከቋሚ መኖሪያቸው ወደ ውሃ ዳር የሚሄዱት ወንዶች ሲሆኑ ጉዞውም የሚደረገው በቡድን ነው።
በዚሁ መሰረት በጋምቤላ ክልል የጎክዲፓች ነዋሪዎች የደረቁን ወቅት ለማሳለፍ በጊሎ ወንዝ ዳርቻ ወደምትገኘው አብሌን ያመራሉ። በቡድን ወደ አብሌን ያመሩት ሰዎች ከወንዝ አሳ በማስገርና ያገኙትን በማደን ቀን እየገፉ ሳለ የካቲት 21፤2005ዓም (28/2/13) በድንገት የመከላከያ ሰራዊት ከበባቸው። ተኩስ ተከፈተ። ለጊዜው ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንና የቆሰሉ እንዳሉ ለተጎጂዎቹ ቅርበት ያላቸው ያስረዳሉ።
ሰዎቹ ከጋምቤላ ከተማ 120 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አብሌን ተቀምጠው ኑሯቸውን እየገፉ ሳለ በድንገት የተከበቡት በጥቆማ እንደሆነ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል። “አቶ ኡሞት ኡዶል እና ሌሎች መሳሪያ የታጠቁ አብሌን ታይተዋል” የሚል ጥቆማ የደረሰው ኢህአዴግ፤ ሰራዊቱን ሰዎቹ በቋሚነት ወደሚኖሩበት ጎክዲፓች በመላክ ቤተሰቦቻቸውን በመያዝ፣ በማሰርና፣ በመግረፍ ሰዎቹ ያሉበትን ቦታ እንዲያሳዩ አስገደዱ።
አቶ ኡሞት በዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የነበሩ ሲሆን የአሜሪካ ዜግነትም አላቸው። ኢህአዴግ ከመሬት ነጠቃ ጋር በተያያዘ በክልሉ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ አጥብቀው በግልጽ የሚቃወሙ ሰው መሆናቸውን የሚያውቋቸው ይናገራሉ። አቶ ኡሞት ከመሬት ነጠቃ ጋር በተያያዘ ህዝብን የሚያስተባብሩና ለዓመጽ የሚያነሳሱ ናቸው በሚል ኢህአዴግ ቢወነጅላቸውም ውንጀላውን በማስረጃ ማቅረብ እንደማይችል እነዚሁ ክፍሎች ይገልጻሉ። ስለተፈጸመው ግፍ የተሞላበት ግድያና ከግድያው በኋላ ስለተከናወነው “አረመኔያዊ የእንስሳ ተግባር” ሲያስረዱ በቁጣ ነው።
በተጠቀሰው ቀን ቤተሰቦቻቸውን ቀበሌያቸው ድረስ በመሄድ በመግረፍና በማስፈራራት ወደ አብሌን ለከበባ በጠቋሚ የመጡት የመከላከያ አባላት ሰዎቹን እንደተመለከቱ ተኩስ ከፈቱ። በድንገት የተከበቡትና ዛፍ ሥር ተቀምጠው የነበሩት አንዳችም ጥያቄ ሳይቀርብላቸው በጥይት የተደበደቡት ሰዎች የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትግል ቢያደርጉም አልሆነም። ተደራጅቶ በሶስት የወታደር ካሚዮን ከባድ መሳሪያ ታጥቆ የመጣው ሰራዊት ጨፈጨፋቸው። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደተናገሩት ወዲያው ህይወታቸው ካለፈው ስድስት ንጹሃን መካከል አቶ ኡሞት መሞታቸው ሲታወቅ የሰራዊቱ አባላት አውካኩ፤ በደስታ ጨፈሩ። አስከሬኑንን ጭነው ፉኙዶ ወደሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ በመሄድ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ደስታቸውን አበሰሩ።
አስከሬን በመኪና በመጫን ከተማ እየዞሩ ደስታቸውን ገለጹ። በማግስቱ በጋምቤላ ከተማ ስታዲየም አስከሬኑን ህዝብ እንዲመለከተው ታዘዘ። ህዝብ ስታዲየም ተገኝቶ የአቶ ኡሞትን አስከሬን እንዲሳለም፣ ኢንቨስተሮችም ያለስጋት የመሬት ነጠቃቸውንና “ልማታቸውን እንዲቀጥሉ”፣ መሞታቸውን አይቶ ሕዝቡ እንዲያምንና ሞራሉ እንዲጎዳ የተላለፈው ውሳኔ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተስተጓጎለ። ለጎልጉል መረጃውን ያስተላለፉ እንዳሉት አቶ ኡሞት አሜሪካዊ መሆናቸው ሲታወቅ ማዕከላዊ መንግስት ከአዲስ አበባ አስቸኳይ ትዕዛዝ አስተላለፈ። አስከሬኑን ባስቸኳይ እንዲቀብሩ መመሪያ ሰጡ። ሁሉም ነገር በመመሪያው መሰረት ተጠናቀቀ። የአቶ ኡሞት አስከሬን ባልታወቀ ቦታ ተቀበረ። አስከሬኑንን ለማየት በግዳጅ ተሰባሰበው ህዝብም ምንም ነገር ሳይመለከት ወደ ቤቱ ተመለሰ። ሁኔታውን ተከትሎ በተፈጠረ አለመረጋጋት የኢህአዴግ ሠራዊት በጎክ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የጋምቤላ ተወላጆች በተለይም ወንዶችን እያሠሩና እያሰቃዩ እንደሆነ ከሥፍራው የደረሰን ዜና ያረጋግጣል፡፡
የአኙዋክ የፍትሕ ምክርቤት ጉዳዩን ለአሜሪካ መንግስት እንዳሳወቀና የአሜሪካ መንግስት ጉዳዩን ከስር መሰረቱ ጀምሮ እንደሚመረምረውና እስከ መጨረሻው የመንግሥት አካል እንደሚደርሱ ማረጋገጡ ታውቋል። ኢህአዴግ አቶ ኡሞትን የገደለበትን ምክንያት በማስረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም አስታውቀዋል። አቶ ኡሞት የሚጠረጠሩበት ድርጊት እንኳን ቢኖር በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ መጠየቅ እየተቻለ እንዲገደሉ መደረጋቸው ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ የሚከራከሩላቸውና ጉዳያቸውን ይፋ ያደረጉት ክፍሎች ይናገራሉ።
በወቅቱ ህይወታቸው ያለፈው ንጹሃንና የደረሱበት ያልታወቀው ሰዎች ስም ዝርዝር ከስፍራው የደረሰን ሲሆን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
- ጎጎ ኦቻላ
- ቻም ኦቻላ
- ዑከች አቻው
- አኳይ ኦሞት
- ኦሞት ኦባንግ
- አጂባ አኳይ
- ኦሞት ኡጁሉ ኦጎታ
- አንበሳው ኡጁሉ
- ቱወል ኦሎክ
- ኦችዋል ኦባንግ
- ኦዋር ቻም
- ኒሙሉ አጎሌ
- አብራች ኒሙሉ
- አኩኔ ኦሞት
- አግዋ ቻም
- ኦዋር ኒግዎ አጋክ
- ኦሞት ኡዶል (አሜሪካዊው)
No comments:
Post a Comment