Thursday, March 7, 2013

ጋምቤላ አሁንም በወያኔ ወራሪ ሠራዊት እየታመሰች መሆኗ ተሰማ

 

በ1996 ዓም ከ400 በላይ አኝዋኮችን በግፍ የጨፈጨፈዉ የወያኔ ወራሪ ሠራዊትና ልዩ ኃይል ከሰሞኑ በብዛት ወደ ጋምቤላ በመዝመት ሠላማዊ ዜጎችን በተለይ የአካባቢዉን አርሶ አደሮች እየያዘ ማሰርና መግደል መጀመሩን ከአካባቢዉን እየሸሹ ጫካ የገቡ ዜጎች ለኢሳት ሬድዮና ቴሌቪዥን ስልክ እየደወሉ በሚልኩት ዜና ገለጹ። በተለይ ካለፈዉ አርብ ጀምሮ ፌዴራል ፖሊስ፤ መከላከያ ሠራዊትና የደህንነት ልዩ ሀይሎች ተቀናጅተዉ በጋራ በወሰዱት የማጥቃት እርምጃ ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ ተቃዋሚዎችን ይረዳሉ ወይም ታጣቂዎችን ሊቀላቀሉ ይችላሉ ብለዉ የጠረጠሯቸዉን ሠላማዊ ዜጎች ማሰራቸዉንና እራሳቸዉን ለማዳን የሞከሩ ሰዎችን ተኩሰዉ መግደላቸዉን ከአካባባዉ የደረሰን ዜና ጨምሮ ያስረዳል። በአሁኑ ወቅት የወያኔ ወራሪ ሠራዊት በብዛት ወደ ጋምቤላና አካባቢዉ እየዘመተ ሲሆን የአካባቢዉ ህዝብም እራሱን ለማዳን ጫካ እየገባ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የወያኔ ወራሪ ሠራዊት ካለፈዉ ዐርብ ጀምሮ በወሰደዉ የማጥቃት አርምጃ ከአስራ ሁለት በላይ ሠላማዊ ዜጎችን የገደለ ሲሆን ከሟቾቹ ዉስጥ አንድ የአካባቢዉ ተወላጅ የሆነ የአሜሪካ ዜጋ ይገኝበታል። የግንቦት ሰባት ድምጽ ዝግጅት ክፍል የወያኔ ጦር በአካባቢዉ ያደረገዉ ጭፍጨፋ እንደተሰማ በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ባለስልጣናትን ሰልክ ደዉሎ ሁኔታዉን ለማጣራት ሞክሮ ነበር ፤ ሆኖም የዝግጅት ክፍላችን ያናገረዉ ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣን በአካባቢዉ ምንም አይነት ግጭት የለም በማለት በአለም ዙሪያ የተሰራጨዉን እዉነት ለመካድ ሞክሯል። በሌላ በኩል አዲስ አበባ ዉስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች የጸጥታ ሀይሎች ጋምቤላ አካባቢ የአማጽያንን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በሚል በወሰዱት እርምጃ አንድ የአሜሪካ ዜግነት ያለዉ ሰዉ መገደሉን ለአሜሪካ ኤምባሲ ተናግረዋል።
የአዲስቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መሪ የሆኑት አቶ አባንግ ሜቶ ከኢሳት ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በጋምቤላና በአካባቢዉ ያለዉን ወታደራዊ ዉጥረት ድርጅታቸዉ በቅርብ እንደሚከታተለዉ ተናግረዉ ከሰሞኑ በወያኔ ወታደሮች ተገደለ ስለተባለዉ የአሜሪካ ዜጋ አስፈለገዉን የክትትል መረጃዎች ለአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መስጠጣቸዉን ተናግዋል። ዜጎችዋ በዉጭ አገር በሚደረጉ ወታደራዊ ግጭቶችና አመጾች ሲገደሉ ወይም ደብዛቸዉ ሲጠፋ ክፍተኛ ክትትል የምታደርገዉ ዩ ኤስ አሜሪካ አሁንም ጋምቤላ ዉስጥ በወያኔ ወታደሮች ተገደለ የተባለዉን ዜጋዋን ጉዳይ መከታተል መጀመሯን ለማወቅ ተችሏል። በቅርቡ የኦባማ አስተዳደር ከአሸባሪዎች ጎን ተሰልፈዉ በሚዋጉ የአሜሪካ ዜጎች ላይ የሚወስደዉን አርምጃ በተመለከት ሾልኮ የወጣዉ መረጃ ኮንግሬሱን ጨምሮ አያሌ አሜሪካኖችን እንዳስቆጣ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህ ከሰሞኑ ጋምቤላ ዉስጥ የተገደለዉ አሜሪካዊ ጉዳይ ይበልጥ በተሰማና በታወቀ ቁጥር ወያኔ ላይ መዘዝ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ብዙዎች በመናገር ላይ ናቸዉ።
 


No comments:

Post a Comment