ህዝባዊ ምርጫዎች በመጡ ቁጥር ስልጣኑን እነማን ይርከባሉ? ምርጫው ምን አዲስ ነገር ይፈጥርልን ይሆን? ምርጫው ሰላም ወይም አለመረጋጋት ... ወዘተ ይቀሰቀስ ይሆን? የሚሉ መሰል ጥያቄዎች በበርካታ መራጮች አይምሮ ውስጥ መመላለሱ የተለመደ ነው።
ከአምስት አመት (2007/2008 እ.ኤ.አ.) በፊት ተካሄዶ በነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሳቢያ ከ1300 በላይ ዜጎቿን ያጣች፣ ከ600 ሺህ በላይ ዜጎቿ የተፈናቀሉባት እና በቤሊዮኖች የአሜሪካ ዶላሮች የሚገመቱ ንብረቶች የወደሙባት ጎረቤት አገር ኬኒያ በያዝነው የፈረንጆቹ መጋቢት 4 2013 እ.ኤ.አ. ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አድርጋለች። ከአንድ ሳምንት በፊት በጋዜጠኞች አዘጋጅነት ስምንት እጩ ፕሬዝዳንታዊ ተመራጮች ባደረጉት 3 ሰአት የፈጀ የመጀመሪያው ዙር ክርክር በ34 ራዲዮኖች እና ስምንት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በቀጥታ ተተላልፋል። ይህ ከትምህርት ፖሊሲ አንስቶ እስከ የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ድረስ ያካተተው ክርክር ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚገመተው የኬኒያ ህዝብን ቀልብ ከመሳብ አልፎ አለማቀፋዊ ትኩርትን መሳቡ አልቀረም።
በዚህ የጦፈ ክርክር ላይ እጩ ፕሬዝዳንታዊ ተመራጮቹ ከተሰጣቸው ጊዜ ሲያልፉ ወይም ለጥያቄው ተገቢ ምላሽ ሲያጡ ተናጋሪዎቹን በማቋረጥ ተከታታይ ጥያቄዎችን ያለ ፍርሃት በመደርደር (እንደ አስፈላጊነቱ ) በማድረጋቸው አወያዮቹ (ሞደሬተሮቹ) ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። የወዳጆች መገናኛ ብዙሃናት የሆኑት አነ ፌስ ቡክ እና ቲዊተርም ቢሆኑ በአስተያየት ሰጬዎች ተጨናንቀው ነበር የሰነበቱት። የበርካታ ኬኒያዊያን አንገት ያስደፋው እና ቁስሉ እስከ ዛሬ ድረስ ያልደረቀው የድህረ 2007/2008 እ.ኤ.አ. ምርጫ መዘዝ በሰሞኑ የምረጡኝ ዘመቻ ክርክር ላይ መነሳቱ አልቀረም። በአይነ ቁራኛ የሚተያዩት እና በሰሞኑ ምርጫ ላይ የአሸናፊነቱ እድል እንዳላቸው ሰፊ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ጠ/ሚ/ር ሪያላ ኦዲንጋ እና የኬኒያ መሰራች እና የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆሞ ኬኔያታ ወንድ ልጅ የሆኑት ኡሁሩ ኬኔያታ ያለፈው ቅራኔያቸውን እና ልዩነታቸውን ወደጎን በማድረግ፣ ከጥላቻ እና ከከፋፋይነት አመለካከት ይልቅ በአገር ጉዳይ አብሮ መስራት ጠቀሜታ እንዳለው በተለያዩ መድረኮች ላይ የተናገሩ ሲሆን ያለፈውን ቁርቋሶ በተመለከተ እጃቸው አለበት ተብልው እስከ አሁን ድረስ ከተከሰሱት 14 ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት እጩ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኔያታ "ፕሬዝዳንት ሆነው ቢመረጡ በሆላንዷ ዘ-ሔግ ከተማ በተሰየመው የአለማቀፉ የወንጀለኞች ችሎት (ICC) የቀረበቦትን የዘር ማጥፋት ውንጀላን እንዴት ያደረጋሉ?" ለሚለው የሞደሬተሩ (አወያዩ) ጥያቄ ሲመልሱ "የኬኒያ ህዝብ እንዳገለግለው ከመረጠኝ በዘ-ሔግ ላይ የቀረበብኝ ውንጀላን በተመለከተ ተሟግቼ እራሴን ነጻ አደርጋለሁ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በምረጡኝ ክርክሩ ላይ የተሳተፉት ጠ/ሚ/ር ኦዲንጋ ለጥቅ አድርገው "ዘ-ሔግ ላይ ሆኖ አገርን በስካይፕ (ኢንተርኔት አማካኝነት) መምራት ከባድ ይመስለኛል። ተቃዋሚ ነን የሚሉ ወገኖች ካግበሰበሱት ሰፋፊ መሬት ጥቂቱን እንኳን ለደሃው ህዝብ ቢያካፍሉ? በማለት ታዋቂው ፎርቢስ መጽሄት በቅርቡ የኬኔያው ቁጥር አንድ ቱጃር ሲል የሰየማቸው ኡሁሩ ኬኔያታን በነገር ወረፍ አድርገዋቸዋል። በነገራችን ላይ ኡሁሩ ኬኔያታ እና የጥምረት አጋራቸው የሆኑት ዊሌየም ሩቶ በዘ-ሔግ ላይ የተረመሰረተባቸው ክስ አነርሱን ከፖለቲካው መድረክ ለማባረረ በስልጣን ላይ ባለው ገዤ መንግስት እና በምእራባዊያን የተወጠነባቸው ሴራ አንደሆነ ይናገራሉ።
ሰሞኑን የተሰበሰቡ ቅድመ የህዝብ የምርጫ አስተያየቶች እንዳመለከቱት ምርጫው ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ቢካሄድ ኖሮ ኡሁሩ ኬኔያታ ጠ/ሚ/ር ኦዲንጋን በ740 ሺህ ድምጽ አንደሚያሸንፋቸው የምርጫ ተንታኞች ተንበየው ነበር። ያለፈውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ተከትሎ ኬኔያ በደረሰባት የፖለቲካዊ፣ የኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ሳቢያ አለማቀፉ ማህበረሰብ በተለይ ደግሞ የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሃፊ የሆኑት ጋናዊው ኮፌ አናን አማካኝነት የተካሄደው የሸምጋይነት ጥረት የተነሳ በጡረታ ተሰናባቹ በፕሬዝዳንት ማዋዬ ኬባኬ እና በተቀናቃኛቸው የአሁኑ ጠ/ሚ/ር ኦዲንጋ መካከል ጥምር መንግስት ለማቋቋም የተገደደችው ጎረቤት አገር ኬኔያ ህገመን ግስቷን በአዲስ መልክ በማሻሻል፡የፍትህ ስርአቷ ገለልተኛ እንዲሆን ጥርት በማድረግ በኩል እና ዜጎቿን ለብቀላ የሚጋብዙ ቃላትን እና ብሄርን በብሄር ላይ ለአመጻ የሚያነሳሱ አስተያየቶችን ከመጠቀም የሚያግድ የቁጥጥር ኮሚሽን በማቋቋም የሰሞኑ ምርጫ 2013 እ.ኤ.አ. የተሻለ ምርጫ ለማድረግ ውስጣዊ ጥረቶችን ብታደርግም ምርጫ ይሳካ ዘንድ ያለፈውን ደህረ ምርጫ ይመሰለ ዘግናኝ፡ የብቀላ እና ኤ-ዲሞክራሲያዊ እርምጃ እንዳይደገም እና የናይሮቤ መንግስት ዜጎቹን እንዲታደግ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ከማሰጠንቀቀ አልቦዘንም። በወላጅ አባታቸው በኩል ኬኔያዊ ዝርያ ያላቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሰሞኑን ለኬኔያ ህዝብ በላኩት የቬዲዮ መልእክት ኬኔያዊያን ነጻ ፡ዴሞክራሲያዊ እና የሰከነ ምርጫ እንዲያካሄዱ ተማጽነዋል። የኬኔያ ቀኝ ገዢ የነበረችው እንግሊዝም በበኩሏ በምረጫ ስም ስርአተ አልበኝነት እንዲከሰት እንደማትሻ ገልጻለች።
(ለውጥ ፈላጊ ኬንያዊያን መራጮች ደምጽ ለመሰጠት ተራቸውን ሲጠባበቁ) |
ባለፈው ሳምንት (ሰኞ እለት) ለሁለተኛ እና የመጨረሻ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ክርክር ወደ መገናኛ ብዙሃናት ብቅ ያሉት እጩ ፕሬዝዳንቶች ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ (እሁድ እለት) በተካሄደ አንድ ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በመገኘት ከህዝቡ ጋር የህብረት ጸሎት ያደረጉ ሲሆን ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ ኬኔያን ወደ ተሻለ እና ዲሞክራሳዊ ስርአት የሚለውጧት ኬኔያዊያን ብቻ እንደሆኑ በጾሎት ስርአቱ ላይ ለተገኘው በአስር ሺዎች ለሚቆጠር መራጭ እና ጸሎተኛ ህዝብ በጋራ ተናግረዋል። እንዚህ ባለፈው በምርጫ ሳቤያ ጥርስ የተናከሱት እጩ ፕሬዝዳንታዊ ተመራጮች ምርጫው ቢጭበረበር እንኳን ተሸናፊው ወገን ቅሬታ ካለው አግባብነት ወዳለው የፍትህ አካል ከመሄድ ውጪ አንዳለፈው ድህረ ምርጫ ውዝግብ ዜጎች ቢላዋ፣ ሜንጫ፣ ጦር፣ እና ጠመንጃ እንዲያነሱ እንደማይገፋፉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቃል ገብተዋል።
በ2010 እ.ኤ.አ. በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ አማካኝነት በተገኘው ከፍተኛ የህዝብ ድምጽ የጸደቀው አዲሱ የኬኔያ ህገ መንግስት ተመራጩ ፕ/ት ከ50% በላይ የህዝብ ድምጽ ማግኘት እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን ሰሞኑን IPSOSበተባለ የህዝብ እሰተያየት ማሰባሰቢያ ተቋም አማካኝነት የተገኘ ቅድመ ምርጫ ግምት ለኡሁሩ ኬኔያታ 44.8% ብልጫ የሰጠ ሲሆን ጠ/ሚ/ር ራያላ ኦዲንጋ በ44.4% እንደሚከተሉ ግምት ሰጥቶ ነበር። የቁጥሮቹ ተቀራራቢነት የመርጫውን ምን ያህል አጓጌነት እና በብርቱ ፉክክሮች ይታጀበ መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን ማክሰኞ እለት የተቆጠሩ የድምጽ ካርዶች ውጤት አንደሚገልጹት ከሆነ 14.3 ሚሊዮን ህዝብ ለምርጫ ተመዝግቦ 70 ከመቶው ድምጹን ለማሰማት በአገሪቱ በሚገኙ 30 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች የሚፈልገውን መሪ ለመምረጥ በወጣበት የኬኒያው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኡሁሩ ኬኒያታ ተቀናቃኛቸው ጠ/ሚ/ር ራያላ ኦዲንጋን 56% ለ40% በሆነ የድምጽ ብልጫ እየመሯቸው እንደሆኑ ዘገባዎች ይገልጻሉ። ይህ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ነጻ እና ሰላማዊ ነው ባይባልም ምርጫውን ተከተሎ የቱሪስት መነሃሪያዋ የወደብ እና ሁለተኛ ከተማ ሞምባሳ "ኬኔያዊ አይደለንም በሚሉ ወይም እንገነጠላለን የሚል አቋም ባላቸው" ወገኖች እና በጸጥታ ሃይሎች መካከል በተከሰተ ግጭት 5 ፖሊሶች እና በረካታ ሴቬሎች መገደላቸው ታውቋል። ይሁንና የተፈጠረው ድንገተኛ ግጭት መራጮች ድምጻቸውን ከመስጠት አላገዳቸውም ተብሏል። ጋሬሳ በተባለ ሰሜናዊ አካባቢም መጠነኛ ችግሮች እንደነበሩ ከመዲናይቱ ናይሮቢ ተላንትና (ማክሰኞ እለት) የወጡ ዝገባዎች ይናገራሉ።
ምንም እንኳን የኬኒያው የፕሬዝዳንታዊ ምረጡኝ ዘመቻ በአመዛኙ እንደተቀረው የአፍሪካ አህጉር የምረጡኝ ዘመቻዎች በጎሳ ፖለቲካ ፡በመሬት የባለቤትነት ጥያቄ እና ፖለቲካዊ አመለካከቶች ዙሪያ ያተኮረ ቢሆንም ኬኔያዊያን ተቀዋሚዎች ሆኑ ገዢው መንግስት እንደ እኛ አገሩ ምርጫ 97 "ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረስ "አይነት አካሄድ ሳይከተሉ ወይም ተቃዋሚዎች ከምርጫው በሁዋላ የፖለቲካው ምህዳር ጠቧል ጫናውም በዝቶብናል ... ወዘተ ብለው እራሳቸውን ከእነ አካቴው ከውድድር እንዳራቁበት እና አገዛዙም በተቃዋሚዎች ላይ የተለያዩ የማግለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ፈላጭ ቆራጭነቱን አንዳረጋገጠበት አካሄድ ሳይሆን ኬንያዊያን ከምርጫው ጋር በተያያዘ ለተፈጸመው የሰላማዊ ዜጎች ህይወት መጥፋት እና የንብረት ውድምት በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ በህግ የሚጠየቁ ወገኖች ተጠይቀው ገሚሱም ለተፍጸመው ስህተት በአደባባይ ይቅርታ ጠይቀው በረካታ ተበዳዮችም እንደ አንዳንድ አገር መራጮች በደረሰባችው ጠባሳ ምክንያት ተሸማቀው "እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው" ባለማለት ወይም ከምርጫ ባለመሸሽ በተቃራኒው ቁጥራቸውን አብዝተው ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መሰባሰባቸው ለተቀረው የአፍሪካ አህጉር አምባገነኖች ሆኑ ተቃዋሚዎች ነን የሚሉ ጥሩ ትምህርት የሚሰጡ የመስላሉ። ይህ ማለት ግን ደሀር ምርጫውን ተከትሎ በደረሰው ችግር ሳቢያ የሁሉም ኬኔያዊ እምባው ታብሶለታል ማለት አይደለም።
ዛሬ ድረስ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኬኒያዊያን ከተሰደዱበት አካባቢ ወደ ትውልድ ሰፈራቸው ለመመለስ ብዙ ፈተናዎች ከፊታቸው ተደቅነውባቸው ይገኛሉ። አያሌ የድህረ 2007/2008 እ.ኤ.አ. ምርጫ ሰልባዎች ተመሳሳይ የብቀላ እርምጃ እንዳይወሰድባቸው ቀደም ብለው ሽሽትን የመረጡ ቢሆኑም በምርጫው ሳቢያ ዛሬም ድርስ የስጋቱ ደመና በተወሰነ ደረጃ ቢኖርም ምርጫው ከተሳካ ኬናዊያን ምርጫቸውን የተሳካ ምርጫ ለማድርግ የተጓዙበት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከጎርቤቶቻቸው አልፎ ለምእራባዊያን ጭምር ትምህርት ሰጪ ነቱ ቀላል አይሆንም።
No comments:
Post a Comment