G7 March 5, 2013
ባለፈዉ አመት መጨረሻ አካባቢ የወያኔ አገዛዝ አላሰራ ብሎት ኢትዮጵያን ለቅቆ የወጣዉ ሄንሪክ ቦል ፋዉንዴሺን የተበላዉ የጀርመን ምግባረ ሰናይ ድርጀት ዋና ዳይረክተር ኢትዮጵያ ዉስጥ ምንም አይነት የህዝብን ኑሮ የሚለዉጥ ስራ መስራት አይቻልም ሲሉ የወያኔን አገዛዝ ደንቃራነት አወገዙ። ሚስትር ፓትሪክ በርግ የተባሉ የምግባረ ሰናዩ ድርጅት ዋና ዳይረክተር ይህንን የተናገሩት ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ የለቀቀበትን ምክንያት ብሉምበርግ ለተባለዉ የዜና ማሰራጫ ተቋም ባስረዱበት ወቅት ነዉ። እንደ ዳይረክተሩ አባባል ኢትዮጵያ ዉስጥ ሌላ ቀርቶ የጥበብ ስራ እንኳን በአሁኑ ጊዜ በጥርጣሬ የሚታይ ነው፣ እኛ የምንሰራዉ ስራ ደግሞ ከሰብዓዊ መብቶች መከበር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለሆነ አገዛዙ በፍጹም አልወደደዉም ካሉ በሁዋላ ይህንን ከመብት ጋር የተያያዘውን ስራችን አቁሙ በመባላችን ኢትዮጵያን ለቅቀን ወጥተናል” ብለዋል።የኢትዮጵያ መንግስት ከጾታ እኩልነትና ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጋር የምንሰራዉን ስራ ለመግታት እራሱ ከጻፈዉ ህገመንግስት ጋር የሚጻረር ህግ አዉጥቷል ያሉት ሚስተር ፓትሪክ በርግ አገዛዙ ነገሮችን የሚያየዉ ህዝብን ይጠቃማል ወይስ ይጎዳል ብሎ ሳይሆን ከራሱ የስልጣን ዘመን ጋር እያስተያየ ስለሆነ ከዚህ አይነት አገዛዝ ጋር ምንም አይነት ህዝብንና አገርን የሚጠቅም ስራ መስራት አይቻልም ብለዋል።
ድርጀቱን ወክሎ ከሚስትር ፓትሪክ በርግ ጋር የተወያየዉ የብሉምበርጉ ሚስትር ዊልያም ዳቪሰን ደግሞ የሲቪክ ሶሳይቲና ቻርቲ ህግ የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ውርስ መሆኑን ተናግሮ ህጉ የወጣዉ ከመንግስት የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ተቃዋሚዎችና ምግባረ ሰናይ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር ነዉ በማለት አምነስቲ ኢንተርናሽናልን በመጥቀስ ተናግሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል በቀለ ፣ መንግስት ያወጣው የሲቪክ ሶሳይቲና ቻሪቲ ህግ ዋና ግቡ በአገር ውስጥ ካለው ፖለቲካና ሲቪክ ሶሳይቲ ስራ ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ የሆነዉ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ህጉ በሙስና የተዘፈቁ የሲቪክ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር ተብሎ የተረቀቀ መሆኑን በመግለጽ፣ የወያኔን አቋም አንጸባርቋል።
No comments:
Post a Comment