Wednesday, March 27, 2013

“አሁን በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ባመዛኙ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የባንዳ ልጆች ነበሩ”


ፍኖተ ነጻነት መጋቢት 15 ቀን 2005 ዓ.ም.
የዛሬው እንግዳችን አቶ ታዲዎስ ታንቱ ይባላሉ፡፡ አቶ ታዲዎስ የታሪክ ምሁርና በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ነፃ ፕሬስ ውስጥ ትልቅ ሚና ያላቸው ሲሆን በአሁን ወቅት “ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ኮሚቴ” ዋና ሰብሳቢ ናቸው ፡፡ በተለይ ለፋሺስቱ ግራዚያኒ ከተሰራው ሐውልት ጋር በተያያዘ አጭር ቆይታ አድርገናል ተከታተሉን፡፡
በጣሊያን የሩዶልፍ ግራዚያኒንን የሐውልት ለመቃወም የሐሳቡ ጠንሳሽ ማን ነው?
አቶ ታዲዎስ፡- የፋሽቱ ጣሊያን የኢትዮጵያውያን ዋና ጨፍጫፊ የነበረውን ሩዶልፍ ግራዚያኒ ሐውልት መሰራት ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃውሞው የተጀመረው በውጭ ሀገር ባሉ
Interview with Ato Tadiwos Tantu
አቶ ታዲዎስ ታንቱ
ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት
ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ
ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ግን የሐሳቡ ጠንሳሽ “ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ኮሚቴ” ነው፡፡ ከዛ በኋላ የባለዕራዕይ ወጣቶች ማኀበር ሰልፉን ለማስተባበር ፈቃደኛ መሆኑን ገለፀልን፤ በዚህም ላይ ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚተባበረን ከገለፀ በኋላ መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰልፉን ለማካሄድmወሰንን፡፡
ተቃወቅሞውን ለማቅረብ ያነሳሳችሁ ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር?
አቶ ታዲዎስ፡- ብዙውን ጊዜ እኔ በጋዜጦች ስለ አርበኞች ታሪክ ያነበብኩትንና ያወቅሁትን እፅፋለሁ፣ እመረምራለሁ፡፡ የጣሊያኑ ፋሽስት ግራዚያኒ ሀገራችንን በመውረር በአባቶቻችንና እናቶቻችን አርበኞች ላይ የፈፀሙት የግፍ ግድያ አሰቃቂ እንደነበር ስለተረዳሁ፤ ያ ሲቆጨኝ ደግሞ አሁን በጣሊያን ሀገር ለእሱ ሙዚየምና ሐውልት የመሰራቱን ወሬ ከኢንተርኔት ምንጮች ስላየሁ በጣም ተናድጄ እንደውም ተቃውሞ ማሰማት አለብን ብዬ ተነሳሁ፡፡ በኋላ ደግሞ እኛም የአንተ ዓይነት ሐሳብ ነበረን ብለው የባለ ዕራዕይ ወጣቶች ማኀበር አነጋገሩን፡፡ ከዛ በመቀጠል ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ እንስራ የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ በዚህ ምክንያት ሶስቱ አካላት በጋራ ሰልፉን ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ ጀመርን፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ጠላት አይደለም ጣሊያን ሀገር ጨረቃም ላይ ቢሆን ሀውልት እንዲሰራ አንፈቅደም፡፡
በጊዜው ሩዶልፍ ግራዚያኒ ወንጀለኛ በመሆኑ የነበረው ፊልድ ማርሻል ማዕረግ ተገፎ ከወታደርነቱ ተባሮ በጦር ወንጀል ተከሶ 19 ዓመት ተፈርዶበት ቅጣቱን ሳይጨርስ ከእስር ቢለቀቅም እ.አ.አ. በ1955 ዓ.ም. ሞቷል፡፡ ታዲያ ይህ በጊዜው ወንጀለኛ ለተባለው ሰው ሐውልትም ሆነ የመታሰቢያ ሙዚየም ማሰራት ኢትዮጵየውያንን መናቅና የአባቶቻችንን ክብር የሚነካ በመሆኑ ሊሰራለት አይገባም፤ እንደውም ለፈፀመው እልቂት ጣሊያን በቂ ካሳ ስላልከፈለች ካሳ መክፈልና በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይገባታል የሚል አቋም ይዘን ነው የወጣነው፡፡ ስለዚህ ግራዚያኒ ከነ አዳፋ ታሪኩ ሌላው እንዳይደግም ሲወሳ መኖር አለበት እንጂ እንደ ጀግና ሐውልት ሊሰራለት፣ሊወደስና ሊመሰገን አይገባም እንላለን፡፡
በወቅቱ የደረስው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ይቻላል?
አቶ ታዲዎስ፡- በወቅቱ ግራዚያኒ በፊርማው በግፍ ኢትዮጵያውያንን ያስጨፈጨፋቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ከነደብዳቤው አለ፤ የዚህ ቅጂ እኔም ጋር አለ ይታወቃል፡፡ በተለይ የካቲት 12-14 ቀን 1929 ዓ.ም. ከ30 ሺህ በላይ ዜጎቻችንን በግፍ አዲስ አበባ ላይ እራሱ ግራዚያኒ አስጨፍጨፏል፡፡ ከ250 በላይ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ መነኮሳትን አስጨፍጭፏል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በ1938 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው አለም አቀፍ ጉባኤ ያቀረበው ሰነድ እንደሚያስረዳው 760,300 ሺህ ዜጎች ወዲያው ሲገደሉ 525,000 ደግሞ ከነቤት ንብረታቸው እንዲቃጠሉ ተደርጎ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከሁለት ሺህ በላይ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው መነኮሳት ተገድለዋል፣ በርካታ ቅርሶች ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡ በርግጥ ከተዘረፉ ቅርሶቻችን መካከል እስካሁን የተመለሰው የአክሱም ሐውልት ብቻ ነው፤ ሌሎቹ ግን አሁንም እዛው ናቸው፤ ሊመለሱልንም ይገባል፡፡ ከዛ ውጭ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶች በወቅቱ ተዘርፈው ተወስደዋል፤ 7 ሺህ ግመሎችም ተገድለውብናል፡፡ ይህም በሰነድ በተደገፈ ማስረጃ ለዓለም አቀፉ የሰላም ጉባዔ የቀረበ ነው፡፡ በወቅቱ ሰነድ ያልቀረበባቸውና ሰፊ ጥናቶች ሊደረግባቸው የሚገቡ በርካታ ጥፋቶች ተፈፅመዋል፡፡
ይህንን ተቃውሞ በዋነኝነት ማቅረብ የነበረበት መንግስት ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ፤ እርስዎስ ምን ይላሉ?
አቶ ታዲዎስ፡- እኔም እስማማለሁ፤ ነገር ግን መንግስት ማዘጋጀት ካልቻለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ማዘጋጀት ይችላል፡፡ እኔ እንደሚገባኝ መንግስት ተቃውሞ ያላቀረበው ከጣሊያን የሚያገኘው ዕርዳታ ይቀርብኛል በሚል ይመስለኛል፡፡ እኔ እስከማውቀው ይሄ መንግስት ዕለታዊና የፖለቲካ ገበያ ጥቅምን መሰረት ያደረገ እንጂ ወደፊት ትውልድ የሚኮራበትን ስራ የመስራት ዓላማ የለውም፡፡ ከዚህ በፊት የቀደሙ አባቶቻችን የሰሩትን በጎ ታሪኮች ሲያንቋሽሽ የኖረ መንግስት ስለሆነ እንዲህ ዓይነት የአባቶቻችንና እናቶቻችን አርበኞች ታሪክና ክብር የሚያስጠብቅ ስራ ይሰራል ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ስሜት ያለው፣ ብሔራዊ ስሜትን የጠበቀ ህዝባዊ መንግስት ቢሆን ኖሮ ህዝቡን አስተባብሮ ይሄንን ስራ በቀዳሚነት መስራት የነበረበት እሱ ነበር፡፡ ስለዚህ መንግስት ባያደርግም ዜጎች ይህንን ሰልፍ የማድረግ መብት ስላላቸው እኛም ሰልፉን አድርገናል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሀውልት ግንባታውን አለመቃወሙ ምን ያስረዳናል?
አቶ ታዲዎስ፡- ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በእጅ አዙር ለሀውልት ግንባታው እውቅና እንደሰጠ ይቆጠራል፤ ይህንን እኔም አምናለሁ፡፡ ከዚህም በላይ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ባመዛኙ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የባንዳ ልጆች የነበሩ ናቸው፡፡ እንደውም ነፃነታችንን ባወጅንበት ሁለት ዓመት ሳይሞላ በአርበኞች ላይ ጦርነት የከፈቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለግራዚያኒ የጀግና ሐውልት መሰራቱን ባይቃወሙ አይገርመኝም፤ ምክንያቱም እነሱ የማን ልጆች ናቸው? እስኪ በስልጣን ላይ ካሉት (ከኢህአዴግ) መካከል ለሀገሩ እና ለወገኑ ብሔራዊ ስሜት፣ ነፃነትና ክብር የተዋጋ የአርበኛ ልጅ አንድ ሰው ካለ ንገረኝ? አንድም ሰው የለም፡፡ ስለዚህ የባንዳ ልጅ ለጨፍጫፊው ግራዚያኒ በእጅ አዙርም ሆነ በቀጥታ እውቅና በመስጠት ድጋፍ ቢያደርጉ አያስደንቀኝም፡፡
እናንተ ሰላማዊ ሰልፉን ከማድረጋችሁ አንድ ቀን በፊት መጋቢት 7 ቀን 2005 ዓ.ም ስምንት ሰዎች መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ክስተት በሰልፉ ወቅት እስር እንደሚኖር አልጠቆማችሁም?
አቶ ታዲዎስ፡- እሱን አውቀንም ነው ሰልፍ የወጣነው፡፡ አንድ ቀን አስቀድሞ ሌሎች ቢታሰሩም መውጣት አለብን ብለን ነው የወጣነው፤ እኛም ብንታሰር ሌሎችም እንደሚወጡ እናውቃለን፡፡ ችግር ይፈጠራል ብለን አልተውንም ፤መተውም የለብንም፡፡ ምክንያቱም ይሄ የሀገርና የወገን ጉዳይ ነውና፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሰልፉ ላይ የተገኙትን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
የታሰራችሁት ምን ወንጀል ሰርታችኋል ተብላችሁ ነው?
አቶ ታዲዎስ፡- ፍቃድ አልጠየቃችሁም ፣ አላስፈቀዳችሁም በሚል ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በነበሩ የአጼ ኃይለስላሴ፣ በደርግ ዘመንም ሆነ አሁንም በወያኔ አገዛዝ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ፈቃድ ይጠየቃል የሚል የተፃፈ ህገመንግስትም ሆነ አዋጅ አልነበረም፤የለምም፡፡ ዋናው ከእኛ የሚጠበቀው ሰላማዊ ሰልፍ እንደምናደርግ ማሳወቅና አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ ማድረግ እንጂ ፈቃድ መጠየቅ አይደለም፡፡ ይህንንም ለእኛ ጥቅም እንጂ እነሱን ለማስደሰት አይደልም፡፡ እኛ ደግሞ የሀገሪቱን የተፃፈ ህግ ተከትለን ሰልፉን ከማድረጋችን 10 ቀናት አስቀድመን አሳውቀናል፡፡
ኢትዮጵያውያንን በግፍ ለጨፈጨፈው ግራዚያኒ የተሰራለትን ሐውልት በመቃወማችሁ በኢትዮጵያ መንግስት መታሰራችሁ ምን ስሜት ፈጠረባችሁ? ለእኛ የበለጠ የተነሳሽነት ስሜት ሰጥቶናል፡፡ ጉዳዩንም አጠናክረን እንድንሄድ ትልቅ የሞራል ድጋፍ ሆኖናል፡፡
ከእስር ሲለቋችሁ ምን ብለው ነው?
አቶ ታዲዎስ፡- ምንም ሳይሉን ለሁለት ሰው አንዳንድ ዋስ በማስጠራት ለቀውናል፡፡ ምክንያቱን ግን አልነገሩንም፤አላወቅንም፡፡ ከዛ ስትፈለጉ ትመጣላችሁ ብለው በዋስ ለቀውናል፡፡
በታሰራችሁበት ወቅትስ የገጠማችሁ ችግር አለ?
አቶ ታዲዎስ፡- በርግጥ እኔ ላይ ድብደባ አልፈፀሙም እንጂ ተመትተው ፊታቸው በተለይም አፋቸው አካባቢ የደማ ወጣት አይቻለሁ፡፡ ፊታቸው ያባበጠ ወጣቶችንም አይቻለሁ፡፡ ሌሎችንም ወጣቶች እንደደበደቧቸውም ሰምቻለሁ፡፡ በተለይ ደህንነቶች ማታ መጥተው በግል እያስጠሩ በቢሮ ያናግሩ ነበር፡፡ ስራው ግን የፖሊሶች እንጂ የደህንነቶች አልነበረም፡፡ በታሰርንበት ዕለት ያለምግብና ውሃ ቀን ሙሉ እንድንውል ተደርገናል፡፡ በተለይ እስር ቤቱን ስቃይ አራዳ ፖሊስ መምሪያና ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ ያለውን ስታይ ዕቃ ለማስቀመጥ ሆነ ለሌሎች እንሰሳቶች ለአንዲት ደቂቃ እንኳን እንዲቆዩበት አይመችም፡፡ እስር ቤቱን ስታይ በጣም ያሳዝናል፤ እዛ የገቡ እኮ ጤነኛ ሆነው የመውጣታቸው ዕድል እራሱ አነስተኛ ነው፤ለበሽታ የሚያጋልጡ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ብቻ በጣም ያሳዝናል፡፡ ይሄ ደግሞ የወንበዴ ስራ ነው፤ ይሄንን መንግስት ማረም አለበት፡፡ ሌላው መርማሪ ፖሊሶችና ደህንነቶች ያልተገቡና ከእስሩ ጋር የማይገናኙ የግል ህይወትን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ፣ የኢ-ሜይል የይለፍ ቃል ይጠይቃሉ፣… ብቻ ብዙ ነው፡፡ በግል እኔን ደግሞ ፊታቸውን በኮፊያ የሸፈኑና ጥቁር መነፅር ያደረጉ ደህንነቶች ዋስ ጠርቼ ከወጣሁ በኋላ አንተ የአርበኞችን ታሪክ እያነሳሳህ ወጣቶችን እያነሳሳህ ስለሆነ ብታርፍ ይሻልሃል፤ በግል ልናናግርህ እንፈልጋለን እያሉ ለማስፈራራት ሞክረዋል፡፡ እኔ ግን በህጋዊ ደብዳቤ ያውም ያመንኩበት ካልሆነ ብትጠሩኝ አልመጣም፤ አላናግርም ብያለሁ፡፡
ከዚህ በኋለስ ይህን ተቃውሞ ለመቀጠልስ እቅዱ አላችሁ?
አቶ ታዲዎስ፡- አዎ አለን፡፡ ይህ ተቃውሞ ምላሽ አግኝቶ ያሰብነው እስኪሳካ እንቀጥላለን፡፡ ነገር ግን ዝርዝር ሁኔታውን በተመለከተ እያጠናን ስለሆነ ወደፊት ሀገር ውስጥ ያለነው ውጭ ካሉ ወገኖቻችን ጋር በመመካከር ምን መልክ መያዝ እንዳለበት ስንወስን ይፋ እናደርጋለን፡፡
 

No comments:

Post a Comment