Tuesday, March 26, 2013

የትግራይ ህዝብ ‘ብኡ የሕልፎ’ በሚል የህወሓትን ጭቆና የተቀበለው ለምንድነው? (ኣብርሃ ደስታ ከመቐለ)

“… የትግራይ ህዝብ በሙሉ የህወሓት ደጋፊ ነው ማለት ኣይቻልም። ብዙ የሚቃወም ኣለ። ብዙ የሚጨቆን ኣለ። በትግራይ የሌለው ጭቆናን የሚያጋልጥ ሰው ነው። በሌሎች ኣከባቢዎች (ከትግራይ ውጭ) ሰው ሲታሰር ወይ ሲገደል የሚናገርለት ወይ የሚጮህለት ወገን ኣለው። በትግራይ ግን የለም። ኣንዱ ሲታፈን ሌላው ኣብሮ ዝም ይላል። ይሄ ነው ልዩነቱ እንጂ በትግራይ ጭቆና ስለሌለ ኣይደለም።”
ከዚህ በመነሳት Prof. Mesfin Wolde-Mariam እንዲህ ጠየቁ:
“አብርሃ ደስታ፤ ያልከውን አምናለሁ፤ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህና አንተ በተመቸህ መንገድ መልስልኝ፤ በትግራይ ሰዎች ሲበደሉና ሲጠቁ ሌላው ሰው ዝም የሚለው በምን ምክንያት ነው?”
መልስ
ኣብዛኛው የትግራይ ሰው የህወሓት መንግስት በዜጎች በደል ሲያደርስ ከመቃወም ይልቅ “ብኡ የሕልፎ” የሚል ብሂል (ወይ ኣባባል) ተግባራዊ ያደርጋል። “ብኡ የሕልፎ” የትግርኛ ኣባባል ሲሆን Literally ‘በዛ ይለፍልን’ (ወይ ‘የባሰ ኣታምጣ’) ዓይነት ትርጉም ኣለው።
ለምንድነው የትግራይ ህዝብ ‘ብኡ የሕልፎ’ (የባሰ ኣታምጣ) በሚል የህወሓትን ጭቆና ‘ኣሜን’ ብሎ ለመቀበል የሚገደደው?
(1) ደርግ በትግራይ ህዝብ ብዙ ግፍ ያደረሰ ቢሆንም ህወሓት ከደርግ የባሰ ኣደገኛ ገዳይ መሆኑ የትግራይ ህዝብ በደምብ ያውቃል። የህወሓት የኣገዳደል ወይ ጭቆና ስልት በጣም የረቀቀ ነው። በዚህ የረቀቀ መንገድ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ተገድለዋል ወይ እንዲጠፉ ተደርገዋል። ስለዚ የትግራይ ህዝብ ‘ህወሓት ከደርግ የባሰ ኣደገኛ ነው’ ብሎ ያስባል፤ ይፈራልም። ለምሳሌ እኔ ህወሓትን ፊት ለፊት ስቃወም ብዙ ጓደኞቼ ህወሓት ሊገድለኝ እንደሚችል ስጋታቸው ያካፍሉኛል። (የህወሓት ተግባር በደምብ ስለሚረዱ)። ይህም ሁኖ ግን በኣሁኑ ሰዓት ብዙ የሚቃወም ኣለ። (ፓርቲውም እየተዳከመ ነው)።
(2) የትግራይ ህዝብ: ህወሓት ደርግን ማሸነፍ በመቻሉ (ደርግ ኣስፈሪ ነበር) ‘ሃይለኛ ነው’ የሚል የሃሰት ግምት ተሰጥቶታል። በዚ መሰረት ህወሓት በሰለማዊ ተቃውሞ ስልጣን ሊለቅ ይችላል የሚል እምነት የለውም። የህወሓት ካድሬዎች (ፖሊት ቢሮ ኣባላትን ጨምሮ) ለህዝቡ የሚናገሩት ይሄንን ነው። “ጫካ ገብተን፣ ብዙ መስዋእት ከፍለን ያመጣነው ስልጣን በምላሳቸው ለሚቃወሙን የደርግ ርዝራዦች ስልጣን ኣሳልፈን ልንሰጥ ኣንችልም ይላሉ።
የትግራይ ህዝብ ታድያ እንዴት በሰለማዊ ተቃውሞ ስልጣን ሊለቅ የማይችልን ስርዓት ይቃወም? ህዝቡ ህወሓቶች ከስልጣን እንደማይወርዱ ኣምኖ ከተቀበለ ፣ መቃወም ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መረዳቱ ኣይቀርም። መቃወማቸው ዉጤት ካላመጣ የሚቃወሙ ሰዎች ይገለላሉ፣ የባሰ በደል ይደርሳቸዋል። (የEDU ደጋፊዎች ነበሩ ተብለው የተፈረጁ ሰዎች እስከኣሁን ድረስ በመጥፎ ዓይን ይታያሉ)።
ከተቃወሙ ስራ ኣያገኙም ወይ ከስራቸው ይባረራሉ። የመንግስት ኣገልግሎት (መብታቸው ቢሆንም) ይነፈጋሉ። ለምሳሌ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የደገፉ ሰዎች፣ ከመንግስት ምንም ዓይነት ድጋፍ (የፖሊስ፣ ዳኝነት፣ የደህንነት ከለላ ባጠቃላይ) ‘ኣንፈልግም’ ብለው እንዲፈርሙ (መቃወምን ከመረጡ ማለት ነው) የሚያስገድድ ማስፈራርያ ይደርሳቸዋል (በተለይ በገጠር ኣከባቢ)።
ስለዚ በትግራይ መቃወም ማለት የመንግስት (ፓርቲ) ለውጥ ለማምጣት መታገል (ከተሳካም ገዢው ፓርቲ መቀየር) ማለት ሳይሆን የመንግስትን ኣገልግሎት ላለማግኘት መወሰን (በራስ ላይ ችግር መፍጠር) ማለት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር በትግራይ መቃወም ክፉኛ እንደሚጎዳ ነው። ለዚህ ነው ኣንዱ ሲታፈን ሌላው ኣብሮ ዝም የሚለው።
(3) የህወሓት የጥላቻ ፖለቲካ ወይ ፕሮፓጋንዳ ሌላው ምክንያት ነው። ህወሓት ደርግን የፈፀመው ግፍ እንደ ጥሩ ኣጋጣሚ በመጠቀም “እኔ ከሌለሁ ጅብ ይበላችኋል” ይለናል። በደርግ ዘመን ደርግና ህወሓት ትግራይን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጦርነት የትግራይ ህዝብ ብዙ ስቃይ ኣሳልፈዋል። በጦርነቱ ምክንያት ብዙ ግድያ ነበረ፣ ትምህርት ኣልነበረም፣ ሰላም (መረጋጋት ማለቴ ነው) ኣልነበረም፣ ገበሬው፣ ነጋዴው … በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ኣልቻለም ነበር። ባጠቃላይ ያ ዘመን ለትግራይ ህዝብ (ለመላው የኢትዮዽያ ህዝብም ጭምር) መጥፎ ነበር። ህወሓት ታድያ (ደርግን በማባረሩና ጦርነቱ ጋብ ስላለ) ‘ከዚህ ሁሉ ችግር ያዳንኳቹ እኔ ነኝ። እኔ ባልኖር ኖሮ የደርግ ወታደር ይበላቹ ነበር። ህወሓቶች ከሌለን ደርግ መጥቶ ይገድላችኋል” ይለናል።
ይባስ ብሎ ደግሞ ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የደርግን ኣስከፊነት ያስታውሳል፤ የተከፈለ መስዋእትነት 24 ሰዓት ይተርካል። ይህ የትግራይን ህዝብ ቁስል በመንካት ድጋፉን እንዲሰጥ የማስቻል ስትራተጂ ነው። ለዚህ ዓይነት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ኣንድ ሬድዮ (ድምፂ ወያነ) ና ሦስት ኤፋኤም FM ሬድዮ ጣብያዎች ኣሉ።
ከዚህ በተያያዘ ህወሓት ህዝብን ሲሰብክ ደርግ ኣማራ ኣድርጎ ያቀርበዋል (የደርግን ዓይነት ጨቋኝ ስርዓት የመምጣት ዕድል እንዳለ ለማመልከት ተፈልጎ ነው)። ደርግ ላይመለስ ሞተዋል። ስጋት ሊሆን ኣይችልም፣ ተመልሶ ሊመጣ ኣይችልም። ህወሓት ግን ህዝቡን ለማጭበርበር እስከኣሁን ኣደጋው እንዳለ ለመጠቆምና የትግራይን ህዝብ ድጋፍ እንዳይለየው ለማድረግ ‘ፀረ ደርግ’ የነበረ ትግል ‘ፀረ ኣማራ’ እንደሆነ ኣድርጎ ኣቀረበልን። (በኣንደኛ ደረጃ ትምህርታችን ሳይቀር ተምረነዋል።)
በኣሁኑ ሰዓት ታድያ ሰው (ከትግራይ) ሲቃወም: “ከነዚህ የጠላት ቡድኖች (በብሄር ደረጃ ኣማራ ወይ ሸዋ) ወይ የደርግ ርዝራዦች (Remnants of the Derg Regime) ወግኖ ደርግን ወደ ስልጣን ለማስመለስ ህወሓትን ይቃወማል” በሚል ሰበብ ስሙ ይጠፋል። (እኔ ህወሓት ስለ ተቃወምኩ የሚሰጠኝን ስም መመልከት ይቻላል)። ይሄ ነገር ታድያ እየታፈንክ ዝም ኣያሰኝም???
(4) ደርግ የትግራይን ህዝብ ጠላት ተደርጎ ነው የሚወሰደው (በፈፀመው ግፍ)። የትግራይ ህዝብ ያን የደርግ ኣገዛዝ ኣይፈልግም። ‘ደርግ ይመለሳል’ ከተባለ ታድያ (ማመዛዘን ቢያስፈልግም) ህዝቡ ከደርግ ህወሓትን መምረጡ እንዴት ይቀራል?
የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ሲቃወም ከተቃዋሚዎች ጎራ እንደተሰለፈ ይቆጠራል። ተቃዋሚዎች ደግሞ ‘ደርጎች’ መሆናቸው ነው ለህዝቡ ሲነገር የቆየው። ስለዚ ኣንድ ሰው (ወይ ብዙ ሰዎች) ህወሓትን ከተቃወመ ከደርግ ጋር እንደተባበረ ነው የሚቆጠረው። በትግሉ ወቅት ከደርግ ጋር የተሰለፈ ሰው ምን ዓይነት ቅጣት ይሰጠው እንደ ነበር ህዝቡ በደምብ ያውቃል። ስለዚ የትግራይ ህዝብ ‘የመቃወም ቅጣት’ ይፈራል። ፈርቶም … ሲጨቆን ዝም ይላል (የባሰ ኣታምጣ ወይ ብኡ የሕልፎ ብሎ)።
(5) ኣብዛኛው የትግራይ ህዝብ ድሃ ነው። ድህነት በራስ የመተማመን ዓቅማችን ያሽመደምደዋል። ለመቃወም የኢኮኖሚ ነፃነት ወይ ዓቅም መገንባት ያስፈልጋል (ከገዢው መደብ ለሚደርሱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሽብሮች ለመቋቋም)። ድሃ ጭቆናውን ቢቃወም እንደውጤቱ የባሰውን ይጨቆናል። ለኣምባገነኖች; ጭቆና ተቃውሞን ለመቀነስ ይጠቀሙታል። ስለዚ የባሰውን ጭቆና ለማስቀረት ያለውን ጭቆና ‘ኣሜን’ ብሎ መቀበል (የትግራይ ህዝብ) እንደኣማራጭ የወሰደው ይመስለኛል።
ሌላው ችግር ደግሞ የትግራይ ህዝብ የመረጃ ዓፈና (ከሌሎች ክልሎች በባሰ ሁኔታ ሊባል በሚችል ሁኔታ) ይፈፀምበታል። የመረጃ ችግር ኣለ። ወደ ትግራይ የሚገባ መረጃና ከትግራይ የሚወጣ መረጃ በተቻለ መጠን ሳንሱር ይደረጋል። የትግራይ ህዝብ መረጃ እንዳያገኝ ይደረጋል። በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ስለ የኢትዮዽያ ፖለቲካ በቂ መረጃ ኣለው ብዬ ኣላምንም።
በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ የሚፈፀሙ ችግሮች፣ በደሎች፣ ጭቆናዎች የሚዘግብና የሚያጋልጥ ሚድያ የለም። በፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚድያ ሚና የማይናቅ ነው። በትግራይ ያሉ ችግሮች በኣግባቡ ስለማይዘገቡ ሰሚ ኣያገኙም። ሰሚ ካላገኙ (1) ሰዎቹ ተቃውመው ምንም ለውጥ ሊያመጡ እንደማይችሉ ስለሚረዱ እየተጨቆኑም ዝም ብለው ዝም ይላሉ፤ (2) ካልተዘገቡ በሌሎች ህዝቦች በትግራይ ችግር እንደሌለ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ስለዚህ ገዢው ፓርቲ ዓፈናን ለመሸፈን ዓፈናን (ራሱ) እንደመሳርያ ይጠቀመዋል። እንደውጤቱም በትግራይ ተቃውሞ እንኳ ቢኖር ስለማይዘገብ ግን ህዝቡ ህወሓትን እንደሚደግፍ ወይ እንደማይቃወም ተደርጎ ይወሰዳል። ትልቁ ችግር ይሄ ነው።
(6) የትግራይ ህዝብ የገዢው ፓርቲ ዓፈናን ተቋቁሞ ዝምታን የሚመርጥበት ዋናው ምክንያት ስለተቃዋሚዎች ትክክለኛና በቂ መረጃ ስለሌለውና ተቃዋሚዎችም ለህዝቡ ቀርበው በማነጋገር ዓላማቸውና ማንነታቸው በግልፅ ማስረዳት ባለመቻላቸው ነው።
ተቃዋሚዎች የትግራይን ህዝብ በሙሉ ህወሓትን እንደሚደግፍና ‘ጠላት’ እንደሆነ ኣስመስለው እንደሚያቀርቡ በብዙ የትግራይ ተወላጆች (በህወሓት ፕሮፓጋንዳ ምክንያት) ይታመናል። ይህንን እምነታቸው ህወሓትን የሚጠቀመው “ተቃዋሚዎች ደርጋውያን ናቸው፣ ደርግ ሙሉ በሙሉ ሞቶ ስላልተቀበረ ህወሓት እስከኣሁን ድረስ ከደርግ ጋር እየተዋጋ ነው ወዘተ” የሚል የማጭበርበር ፕርፓጋንዳ ለመቀበል ይገደዳሉ።
በዚ መሰረት ህወሓትን እየተቃወመም ቢሆን የተቃዋሚ ድርጅቶች ግን ከህወሓት ሊብሱ ይችላሉ ብሎ እንዲያስብ ስለሚገደድ ግራ ተጋብቶ ‘የባሰ ኣታምጣ’ ብሎ ኣብሮ ዝም ይላል።
ስለዚ ተቃዋሚዎች ከትግራይ ህዝብ ጋር መወያየትና መግባባት ያስፈልጋቸዋል። ምክንያቱም ሳያውቁት (በሚጠቀሙት የፖለቲካ ስትራተጂ) የትግራይን ህዝብ (target የሚያደርጉ ስለሚመስሉ) በህወሓት ቢጨቆን እንኳ ህወሓትን ላለመቃወም እንዲወስን (የባሰ እንዳይመጣ) ያደርጉታል። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ዝምታ ምክንያት ኣለው (ህወሓት ስለሚደግፍ ግን ኣይደለም)።
“የትግራይ ህዝብ” የሚወክለው ኣብዛኛውን ህዝብ እንጂ ጥቂት የስርዓቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጠቃሚዎችን ኣያጠቃልልም። ጥቂት የስርዓቱ ተጠቃሚዎች በሚሰሩት ተግባር ሁሉም የትግራይ ህዝብ ህወሓት እንደሚደግፍ ኣስመስለው ለማቅረብ ስለሚሞክሩ ሌሎች ሰዎች እውነት ሊመስላቸው ይችላል።
… ግን ዝምታ መፍትሔ ሊሆን ኣይችልም።

No comments:

Post a Comment