በምስራቅና በምዕራብ ሃረርጌ ድርቅ በመግባቱ አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ዶይች ቬለ ሬዲዮ የአሜሪካን የርዳታ ድርጅት USAIDን ጠቅሶ ዘገበ። የድርጅቱ የምግብ አቅርቦት ተንታኝ ብሬክ ስታበረር እንዳሉት በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ በሶማሊና በኦሮሞ አርብቶ አደሮች መካከል ግጭት አስከትሏል።
በተፈጠረው የውሃ ችግር ምክንያት ከብቶቻቸውን ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ይዘው በሚሄዱ አርብቶ አደሮች መካከል የይገባኝልና ውሃና የግጦሹ ሳር ያልቃል በሚል ግጭት ተነስቷል። ተንታኙን የጠቀሰው ሬዲዮ በግጭቱ ስለደረሰው ቀውስ ያለው ነገር ባይኖርም ከተለያዩ ወገኖች የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሶማሊና ኦሮሞ አርብቶ አደሮች መካከል በተከሰተው ግጭት ከሰባ የማያንሱ ሰዎች ተገድለዋል።
የበልግ ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ ችግሩ መከሰቱን ተመልክቷል። በዚሁ ሳቢያ ምርቱ ከጠጠበቀው በታች ሃያ ከመቶ ሊሆን ችሏል። የዝናብ እጥረቱ በዚሁ ከቀጠለ ችግሩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው አስጠንቅቀዋል። ከብቶቻቸውን በመያዝ ምግብና ውሃ ፍለጋ የሚንከራተቱት አርብቶ አደሮች ከቤታቸው ርቀው ስለሚጓዙ ቤተሰቦች ወተት ማግኘት አልቻሉም። በአካባቢው ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኘው የጫት ምርትም በውሃ እጥረቱ ጉዳት ደርሶበት አርሶ አደሮቹን ገቢ እያሳጣቸው ነው። መንግስት ተከሰተ ስለተባለው ድርቅ ያለው ነገር የለም። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በዘንድሮው ዓመት የሚጠበቀው ምርት ከፍተኛ ስለሚሆን ግሽበቱን ያውረደዋል በማለት ለፓርላማ መናገራቸው ይታወሳል። መንግሥት የምግብ እጥረት እንጂ ድርቅ የለም በማለት እንደሚከራከር የሚዘነጋ አይደለም።
No comments:
Post a Comment