Tuesday, June 17, 2014

ለምን የሳሙኤል ዘሚካኤል ጉዳይ ያን ያህል ያስደንቀናል?


ከበትረ ያዕቆብ
ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ ገፆች አካባቢ የህዝብን ቀልብ መሳብ የቻለና አሁንም ዋና መወያያ አጀንዳ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ተከስቷል፡ የሳሙኤልዘሚካኤልየሀሰትዶክተር እናኢንጂነርነት፡፡ ጉዳዩ ብዙዎችን አጃኢብ አስብሏል ፤ አሁን በርካቶች ብስጭታቸዉን እና ቁጣቸዉን በተለያየ መንገድ እየገለፁ ይገኛል፡፡ ብዙ ሰዎች በአንድ ወቅት የስኬት ምልክታቸዉ እስከ መሆን የደረሰና አድናቆታቸዉን ያጎረፉለት ሰዉ ድንገት የሀሰት ሆኖ ሲያገኙት መደናገጣቸዉ አልቀረም፡፡
Samuel Zemicael
የሳሙኤል ዘሚካኤል
እርግጥ ነዉ ነገሩ ትንሽ የሚያስገርም ነዉ፡፡ ወጣቱ የሄደበት እርቀት ግራ የሚያጋባና ድፍረቱ የሚያስገርም ነዉ፡፡ ሌላዉን ትተን በሀገር ዉስጥ የሚገኙትን ዩንቨርሲቲዎች ስም ደጋግሞ እያነሳ ይህንን ሸለሙኝ ፣ ይህንን ሰጡኝ ፣ የረዳት ፐሮፌሰርነት ማዕረግ ተበረከተልኝ ወዘተ ማለቱ በእርግጥም ከማሰገረም አልፎ ብዙ ያስብላል፡፡ ያም ሆኖ ግን እኔን ይበልጥ ያስገረመኝ ጉዳዩ የዚያን ያልህ  እንደ ተዓምር የመታየቱ ነገር ነዉ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ እየተደረገ ያለዉን ዉይይት ስመለከት እንዴ ነዉ ነገሩ ብየ መደነቄ አልቀረም፡፡
በዚህ ወጣት የተፈፀመዉ አሳፋሪ ተግባር ዛሬ የተከሰተ አዲስ ክስተት አይደለም ፤ የነበረና አሁንም  እየተፈፀመ ያለ ነገር ነዉ፡፡  እዉነቱን መነጋገር ካለብን መሰል ማጭበርበር ቤተ-መንግስት አካባቢ በጣም የተለመደ እና  ብዙዎች የተጨማለቁበት ተግባር ነዉ፡፡ ይታያችሁ ፣ ቤተ-መንግስት ነዉ ያልኩት፡፡ ይህንን ስናይ ወጣቱ የፈፀመዉ ተግባር የሚደንቅ አይመስለኝም፡፡ እንዴትስ ያስደንቃል፡፡
ዛሬ ሳሙኤልዘሚካኤልእድል ጥሎት ሁሉም ተረባረበበት እንጅ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የትምህርት ማስረጃ ቢመረመር ስንት ከሱ የባሰ ጉድ ይገኝ ነበር፡፡ እንግዲህ ሀገርን ያህል ትልቅ ነገር እንመራለን የሚሉ  ግለሰቦች መሰል ተግባር በሚፈፅሙበት አገር የዚያ ወጣት ተግባር ጉድ የሚያስብልበት ምክንያት አይታየኝም፤፤ እንዴትስ ሊያስብል ይችላል፡፡ ከዚህ ይልቅ ቤተ-መንግስት ተቀምጠዉ አገርን የሚዘዉሩ ግለሰቦች ፣ በያንዳንዳችን እጣ ፈናታ ላይ የመወሰን ስልጣን በጉልበት የጨበጡ ባለስላጣናት የሀሰት ማስረጃ ሊያስደንቀን ፣ ሊያበሳጨን ፣ ሊያስደነግጠን ይገባ ነበር፡፡
ዛሬ በርካታ የኢህአዴግ/ህወሀት ጉምቱ ባለስልጣናት እንከዋን ትምህርት ቤት ገብተዉ ሊማሩ በበሩ እንኳን ሳይልፉ ባለሁለተኛ እና ሶስተኛ ድግሪ የመሆናቸዉ ጉዳይ ለብዙዎቻችን ሚስጥር አይመስለኝም፡፡ ዛሬ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲት ድግሪና ማስትሬት በቀጭን ትእዛዝ እንዳሻቸዉ የሚሰበስቡት ተራ ነገር ነዉ፡፡ ሲያሻቸዉም ከዉጭ በገንዘብ ይሸምቱታል፡፡ ሲልም እድሜ በሙያዉ ለተካኑ የቻይና እና የህንድ ዜጎች እንደፈለጉት አሳምረዉ አዘጋጅተዉ ኮንግራ ይሏቸዋል፡፡ከዛም ከለታት አንድ ቀን ብቅ ብለዉ ይህ አለን ይላሉ፡፡ ይህ ነዉ ለኔ አሳፋሪዉ ፣ አስደንጋጩ፡፡
በእንዲህ አይነት መልኩ በርካታ ትልልቅ ባለስልጣናት የሀሰት የክብር ካባ ለመደረብ ሞክረዋል፡፡ አሁንም ብዙዎች ይህንን መንገድ ቀጥለዉበታል፡፡ ከብዙ ወራት በፊት አንድ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዉስጥ የሚሰራ ወዳጄ ሲያጫዉተኝ “ዩንቨርስቲዉ በካድሬ መመራት ከጀመረበት እለት አንስቶ በርካታ የኢህአዴግ መኳንንቶችን በማዕረግ” አመርቋል” ነበር ያለኝ፡፡ ይታያችሁ እርሱ ያለዉ “በማዕረግ” ነዉ፡፡ ይህ ማለት ሳይማሩ ፣ ሳያጠኑ ፣ ሳይፈተኑ ኤ በ ኤ ይሆናሉ ማለት፡፡ ለኔ ይሄ ነዉ አስደንጋጩ ጉዳችን፡፡ ይህ ወዳጄ እንደነገረኝ አልፎ አልፎም በዉጭ ዩኒቨርስቲ መማር የሚፈልጉ ከተገኙም የሚፈልጉትን የትምህርት መስክ መርጠዉ የመዓረግ ተመራቂ ተብሎና ሁሉም ነገር ተሟልቶለት ይሰጣቸዋል፡፡ እኒህ ሰዎች ናቸዉ ዛሬ ሀገሪቱን የሚመሩት ፤ ከእኛ በላይ አዋቂ የለም የሚሉን ፣ የጭቆና ቀምበር ጭነዉ ፍዳችንን የሚያሳዩን፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁለት ግለሰቦች ማንሳት እዉዳለሁ፡፡ ይህ ለምሳሌ ያህል ብቻ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ በአንድ ወቅት እንደ ምሁር ለመፈላሰፍ ሲቃጣዉ የነበረዉ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ነዉ፡፡ ሰዉየዉ ትምህርቱን ከዩንቨርሲቲ አቋርጦ በረሀ እንደ ወረደ እና ከ17 አመት የትጥቅ ትግል በኋላ በለስ ቀንቶት ቤተ-መንግስት እንደገባ ነዉ ነበር የምናዉቀዉ፡፡ ሆኖም ከእለታት በአንዱ ቀን አቶ ምን ይሳነዋል ባለሁተኛ ድግሪ ምሁር ነዉ ሲባል ሰማን ፣ ያም አልበቃ ብሎ ሌላም እንዳከሉበት የቀብሩ እለት ተነገረን፡፡ የአቶ ሳሞራ የኑስም ታሪክ ተመሳሳይ ነዉ፡፡ 11ኛ ክፍል አቅርጠዉ በረሀ ገብተዉ እንደታገሉ እንጅ ሌላ የምናዉቀዉ ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም  እርሳቸዉ ከ11 ክፍል በአቋራጭ ከፈለጉት ቦታ ላይ ጉብ አሉ፡፡ በሀዉልታቸዉ ላይም ባለ ሁለተኛ ድግር ምሁራ ናቸዉ ተብሎ ተፃፈ፡፡ እንዴት ብሎ የጠየቀም አልነበረም፡፡ እስከማዉቀዉ ድረስ በጉዳዮ ላይ ጥያቄ ያነሳ ብቸኛ ሰዉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ብቻ ነዉ፡፡ ዛሬ “ለእዉነት ቆሜያለሁ” የሚለዉ ሬድዮ ፋናም ያኔ አዳች ነገር ትንፍስ አላለም ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በቅርቡ ብዙ አፍሪካዊ ጋዜጠኞች  የተሳለቁበት በሀሰት የትምህርት ማሰረጃ በመንግስት ሴራ የአፍሪካ ህብረት አካል በሆነ ድርጅት ዉስጥ ትልቅ ስልጣን እስከመጨበጥ የበቃዉ የኢህአዴግ ካድሬም በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
እንግዲህ ይታያችሁ እነዚህ ሰዎች ሀገር መሪ ነን ይላሉ፡፡ እነዚህ ናቸዉ የሀገሪቱን ፖሊሲና እስትራቴጅ ቀራፂያን ፣ እነዚህ ናቸዉ ሀገሪቱ እና እኛን ወክለዉ ከሌሎች ጋር የሚደራደሩት ፣ እነዚህ ናቸዉ ዛሬ በእያንዳንዳችን ህልዉን ላይ ወሳኝ ሆነዉን የሚገኙት፡፡ ይህ ነዉ እኔን ይበልጥ የሚያሳፍረኝ ፣ የሚያሰገርመኝ፡፡ ይህ ነዉ ለኔ ትልቁ ጉድ፡፡ እንዴት ነዉ እንዲህ አይነት የሀገር መሪዎች ባሉበት ሀገር አንድ ከደሀ ቤተሰብ የወጣ ልጅ የፈፀመዉ የማጭበርበር ተግባር የሚደንቀዉ፡፡ ነዉ ወይስ አላዉቅም ልንል ነዉ፡፡
ከባለስላጣናቶቻችን እና ከእኛ ዜጎች አልፎ ተርፎ እንኳ በየዩንቨርስቲዉ በዶክተር እና ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ስም የሚያጭበረብሩት የዉጭ ዜጎች በርካታ አይደሉም? የመጀመሪያ ድግሪ ይዘዉ በዶክተር ስም የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑ ወጣት ልጆች ላይ ሲቀልዱ አላየንም ፣ አልሰማንም ? ለምሳሌ እንኳን በቅርቡ ወደ አንድ የዉጭ ዩንቨርስቲ  ሁለተኛ ድግሪዉን ለመማር ያቀና ወጣት ዶክተር ነኝ ብሎ ካስተማረዉ የዩንቨርሲቲ መምህሩ ጋር በአንድ ክፍል ዉስጥ ለትምህርት እንደተገናኙ ሲተረክ ሰምተናል፡፡
በጥቅሉ እንነጋገር ከተባለ በርካታ ጉድ በዙሪያችን አለ፡፡ ዘርዝረን አንጨርሰዉም፡፡ በመሀከላችን በርካታ የቀበሮ ባህታዊያን እንዳሉ ልብ ልንል ያገባል፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት አገር የሳሙኤልተግባር ለኔ ብዙ የሚያስደንቅ ነዉ ብየ አላስብም፡፡ እንዴዉም በአንድ ግለሰብ የማጭበርብር ተግባር ላይ ብቻ ማፍጠጡ ችግሩ እንደሌለ ያስመስለዋል ፤ ወደ መፍትሄም አይወስድም፡፡ ስለዚህም ችግሩን ሰፋ አድርጎ ማየትና አፍረጥርጦ መነጋገር ተገቢ ነዉ እላለሁ፡፡ ሬድዮ ፋናም ቢሆን “ለእዉነት ቆሜያለሁ” የሚል ከሆነ በአንድ ግለሰብ ተግባር ላይ ብቻ ከማንባረቅ በዘለለ የሌሎችንም በተለይም ሀገር እንመራለን በሚሉ የኢህአዴግ/ህወሀት አምባገነን ባለስልጣናት እየተፈፀሙ ያሉ ማጭበርበሮችን ሊያጋልጥ ይገባል፡፡ እርግጥ ኢህአዴግ አምጦ ከወለደዉ ተቋም ይህን መጠበቅ ሞኝነት ነዉ፡፡ ለሁሉም ቸር እንሰንብት !

ተባበር ወይንስ ተሰባበር!?


ከዋስይሁን ተስፋዬ
ሰኔ 10 ቀን 2006 እ.ኢ.አ.
በኢትዮጵያ ሃገራችን በፍቅር፣ በመተሳሰብና፣ በመቻቻል ለዘመናት የኖረ ህዝብ እርስ በርሱ በጥርጣሬና በጥላቻ ሲጎሻሸም፤ ቤተሰብ ከቤተሰብ መተማመን ጠፍቶ ግለኝነት ሲነግስ፤ የአብሮነታችን ማሰሪያ የሆነው ፍቅራችን ጠፍቶ አንዱ ብሄር በሌላው ብሄር ላይ ጥላቻን ሲዶልት፤ መከባበራችን ረክሶ አንዱ ሃይማኖት ሌላውን ሲጠራጠር፤ ባጠቃላይ በሃገሪቱ ፍቅር ጠፍቶ ጥላቻ ሲነግስ በማየቴ አዘንኩ። ገዢው የኢህአዴግ ከፋፋይ ሥርዓት የዘረጋው አፋኝ መዋቅር ህዝብ ከጥላቻ ውጪ ሌላ ምንም አይነት መረጃ እንዳያገኝ አፍኖ፤ በሃገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን፤ ብሎም ኢትዮጵያዊነት ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና እየጠፋ እንደሆነ ሳስተውል ደግሞ ፈራሁ። በአንፃሩ ደግሞ ይህ አደገኛ ሁኔታ ለመናገር በሚዘገንን መልኩ አስከፊ በሆነበት በዚህ የጨለማ ዘመን፤ በተቃዋሚ ስም ራሳቸውን ሰይመው ‘እኔ ካልኩት በላይ ምንም ሊሆን አይችልም’ በሚል አምባገነናዊ አስተሳሰብ፤ በህዝብ ስም ለህዝብ ነፃነት ሳይሆን የራሳቸውን የግል ፍላጎት ለማሳካት የህዝብን በደል በማባባስ ላይ የተሰማሩ ስብስቦች እንደ አሸን በዝተው ስመለከት ተረበሽኩ። በመሆኑም በሃገራችን በጎ ነገር እንዲሰፍን በመመኘት፤ ያላስተዋለ ተገንዝቦ፣ አይቶ ዝም ያለም የሃገርና የህዝብ ውድቀት ነውና ማፈግፈጉን ትቶ ወደ እውነተኛው የህዝብ ነፃነት መንገድ ይራመድ ዘንድ፤ በዚህች አጭር ፅሁፍ ጥቆማዬን ለአንባቢያን ማቅረብን ፈቀድኩ።
ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነትና የሃገሪቱ ህልውና በኢህአዴግ መንግስት በጎ ፍቃድ ብቻ የሚወሰን መሆኑ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልፅ ነው። በመሆኑም መንግስት እንዳሻው ሃላፊነት በጎደለው አካሄድ ህዝብን ለዘመናት ሲያፈናቅል፤ ንጹሃን ዜጎችን መጥፎ ስም በመስጠት ባልሰሩት ሃጥያትና በተፈበረከ የሃሰት ውንጀላ በየእስር ቤቱ እንዲማቅቁ ሲያደረገ፤ የሃገሪቱን መሬት በፈቀደው መልኩ ለባእዳን ሃገራት ሲያድልና ሲሸጥና ብዙ ሌሎች በደሎችን በህዝብና በሃገር ላይ በተደጋጋሚ ሲፈፅም ማየት የተለመደ ሆኗል። በኔ አስተሳሰብ ኢህአዴግ ይህንን ማድረግ የቻለበት ዋንኛው ምክንያት የሚዲያ ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር በመቻሉ ነው። በሃገራችን የሚገኙት መንግስታዊ የሚዲያ ተቋማት የኢህአዴግን የዘረኝነት ፖሊሲ ብቻ በመስበክ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ስለ ሃገሩ አንድነት፣ ስለ ህዝቧ ፍቅርና፣ በሃገሪቱ ስላሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እንዳይሰማና እንዳያውቅ በማድረግ አስተሳሰቡ ከአካባቢው የማያልፍ ጠባብ አድርጎታል። ለዚህም በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲተውኑት ያየነው ትእይንት አይነተኛ ምስክር ነው። ለአንድ ሃገርና ህዝብ የወደፊት አቅጣጫና ህልውናን በመወሰኑ ረገድ ሚዲያ እጅግ ወሳኝ ድርሻ አለው።ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው የሚዲያ ተቋማት የሚያሰራጨውን የዘረኝነትና የእርስ በርስ የጥላጫ መርዝ በመቋቋም የነፃነት ትግሉን ወደፊት መግፋትና ለውጤት ማብቃት የሚቻለው፤ ኢህአዴግ እየፈፀማቸው የሚገኙትን በደሎች ከማጋለጡ ባሻገር፤ ህዝቡ በተቃራኒው ስለአንድነትና ፍቅር እንዲሁም ስለተቃዋሚዎች በቂ እውቀት እንዲኖረውና፣ ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በጋራ እንዲሰሩ የሚገባውን ጫና እንዲያደርግ፣ አልያም የመረጠውን መቀላቀል ይችል ዘንድ ሁለገብ መረጃዎችን በስፋት ለህዝብ ለማድረስ የሚሰራ የሚዲያ ተቋም መገንባት ሲቻል ብቻ እንደሆነ ይሰማኛል። በተለይ እንደ ኢህአዴግ የሚዲያ ጠላት በሆነና ህዝብን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ ከፋፍሎ የእርስ በርስ ጥላቻና ቂም ለማስፋፋት ታትሮ በሚሰራ አረመኔአዊ አገዛዝ ስር ለወደቀ ህዝብ ነፃ የመረጃ ስርጭት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ሁላችንም እንደምናየው የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ወቅት የተቃዋሚ ቡድኖች ከመጠን በላይ በመብዛታቸው ምክንያትና መረጃ በብቃት ስለማይደርሰው፤ የድርጅቶቹን አላማ፣ ግብ፣ ራእይ፣ በጎ ጎኖችና ግድፈቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ልዩነቶቻቸውን በቅጡ መለየት ተስኖት፤ ምኑን ከምኑ፣ የትኛውን ከሌላኛው መለየት ባለመቻሉ ግራ በመጋባቱ ‘የነፃነት ትግል የውሸት፤ ፖለቲካ አይንህ ላፈር’ በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ተወስኖ፤ የሚደርስበትን ችግር ለማስቆም በጋራ ከመታገል ይልቅ በዝምታ መቀመጥን መርጦ ይገኛል። በመሆኑም የተቃዋሚ ድርጅቶች ያለ ህዝብ ተሳትፎ ብቻቸውን ሲያጨበጭቡ ይታያሉ።
ከላይ ለመግለጽ የሞከርኳቸውንና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ዋንኛ መሳሪያው ብቃት ያለው የሚዲያ ተቋም መኖር በመሆኑ የተለያዩ የተቃዋሚ ቡድኖች ተቋማትን መስርተው ሲንቀሳቀሱ እናያለን። ነገር ግን እዚህጋ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ተቋማቱን መመስረት ብቻ ሳይሆን የሚያስተላልፉት የመረጃ ይዘቶችና አይነቶች እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን ነው። በኔ እይታ የሚዲያዎች አትኩሮት በተለየ ሁኔታና በስፋት፤ በተቃዋሚዎች መካከል ያሉትን ልዩነቶች፣ የተቃዋሚዎችን በጎ ጎኖችና ግድፈቶች፣ ከገዢው መደብ ጋር ያላቸውን ልዩነቶች በመረጃ ማቅረብ፣ ለሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ያለ አድልዖ እኩል መድረክ የሚሰጡና በሃገሪቷ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተቃራኒ አመለካከቶች ያሏቸውን ምሁራንንና የፖለቲካ ሰዎችን በማወያየት ህዝብ በስነልቦና በእውቀት እንዲጎለብት በስፋት የሚሰሩ ሊሆኑ ይገባል። ከዚህ መነሾነት ሲስተዋሉ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ መረጃን ለማስተላለፍ በሚል አላማ ከሚሰሩት የሚዲያ ተቋማት አብዛኛዎቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢህአዴግን መሰረታዊ አላማዎች ከማስተጋባት ያለፈ የሚጨበጥ ስራ ሲያከናውኑ አይታዩም። በእርግጥ አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ ስመለከታቸው እንደ Addis Dimts Radio፣ SBS Australia፣ የVOA እሰጥ-አገባና እንወያይ የራዲዮ ዝግጅቶች ሊመሰገኑ የሚገባ መሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ።
ከአድማጮችና ከደጋፊዎች ብዛት አንፃር የኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ስለሚመስለኝ ሃሳቤን ለመሰብሰብ ይሆን ዘንድ፤ ታዋቂ ሰዎችና የፖለቲካ መሪዎች ከአድማጮች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች በኢሳት ራዲዮ ምላሽ የሚሰጡበት፤ የ “ጥያቄ አለኝ” ዝግጅት ላይ፤ የኢሳት ቴሌቢዥንና ራዲዮ በማኔጅመንት ዳሬክተሩ በአቶ ነአምን ዘለቀና በጋዜጠኛ ብሩክ ይባስ ትብብር መላሽ የነበረበትን ለሁለት ሳምንታት የተላለፈ ዝግጅት ላይ ከአንድ አድማጭ የቀረበ ጥያቄንና ከኢሳት የተሰጡ መልሶችን እንደምሳሌ ማንሳት አስፈላጊ ነውና ከዝግጅቱ ከታዘብኩት ጥቂት ልበል። እኝህ ኢትዮጵያዊ የኢሳት አድማጭ ለኢሳት ያቀረቡት ጥያቄ ከላይ ካነሳሁት መሰረታዊ ሃሳብ ጋር በፅኑ ስለሚገናኝና አድማጩ ኢሳትን ሊያስገነዝቡ የሞከሯቸው ጭብጦች በአምባገነን ስርዓቶች ለአመታት ሲሰቃይ ለኖረው ህዝብ ነፃነት መጎናፀፍ ጉልህ ሚና ስለሚኖራቸው፤ ጥያቄያቸውም የበርካታ ኢትዮጵያውያንም ጥያቄ እንደሆነ ስለምገምት ለአንባቢያን ጥያቄውን አቀርባለሁ።
ምስጋና ይህን ወሳኝ ጥያቄ ላቀረቡት ለእኝህ ቀና ኢትዮጵያዊ የኢሳት አድማጭ ይድረስና፤ ባይሳካም የጉዳዩን ወሳኝነት ለማሳሰብ አቀራረቡን የበለጠ ግልፅ አድርገው በሁለተኛው ሳምንትም በድጋሚ ጠይቀዉት ነበር። ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና፤ እንደኔ አረዳድ የጥያቄያቸው መንፈስ ይህን ይመስላል፤ “እስካሁን ድረስ የተለያዩ መረጃዎችን ስትሰጡን ኖራችኋል። ነገር ግን የምትሰጡን መረጃዎች የኢትዮጵያ ህዝብን ወደ ድል ሊያበቁ አልቻሉም። ሁላችንም እንደምናየው ወያኔ የሚፈልገዉን ነገር ከማድረግ የሚያግደው ምንም ሃይል ሊፈጠር አልቻለም። የዚህ ዋና ምክንያት ደግሞ የምትሰጡት መረጃ ወያኔ በደሉን ከህዝብ ለመደበቅ የጭቆና ስልቱን በመቀየር ስህተቱን እንዲያርም ከማድረግና ከማገልገል በስተቀር ለህዝብ የረባ ፋይዳ አላስገኘም። ለወያኔ ደካማ ጎኑን እንደምትነግሩት ሁሉ፤ ለተቃዋሚዎችም ስህተታቸውን እንዲያርሙ እንድታሳስቧቸው ዘንድ፤ ብሎም ተቃዋሚዎች እየሰሩት በሚገኙት በደል ምክንያት ለነፃነቱ ላለመቆም ሳይወድ እንዲሸሽ ለተገደደው የኢትዮጵያ ህዝብ ብርታት እንደሚሆነው በማስገንዘብ ከብዙ አድማጮች አስተያየት ቢሰጣችሁም፤ ተግባራዊ ልታደርጉ አልቻላችሁም። የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ሃይሎች ኢህአዴግ ከሚያጠፋው በላይ በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ጥፋት እያደረሱ ይገኛሉ፤ ምክንያቱም እኔ ካልኩት ሃሳብ በላይ ማንም ሊሆን አይችልም ብለው ስለሚያምኑ፤ ልስራ ብሎ የሚመጣውን አንዱ ሲያዳክም፤ አንደኛው ሌላኛውን ሲያጠፋ እያየን እንገኛለን። ፊትለፊት አምጥታችሁ አገናኝታችሁ በጋራ እንዲሰሩ ልዩነቶቻቸውን ህዝብ አውቆ እንዲፈርድና የመረጠውን እንዲቀላቀል የማትረዱት ለምንድነው?”።
ለጥያቄው በትብብር የሰጡትን መልስ መሰረት በማድረግ ለአቶ ነአምን ዘለቀና ለጋዜጠኛ ብሩክ ይባስ ማሳሰብ የምፈልጋቸው ነጥቦች፤ የእኚህ አድማጭ ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያከ መሆኑን፣ የተጠየቀው ጥያቄ እርስዎ(አቶ ነአምን) አስረግጠው እንዳስገነዘቡን የኢሳትን ነፃ ሚዲያነት የሚጋፋ ሳይሆን በተቃራኒው ኢሳት እንደ አንድ ለኢትዮጵያ ህዝብ መረጃ ለማቀበል የሚሰራ ነፃ የሚዲያ ተቋም በስፋትና በከፍተኛ ትኩረት ሊሰራበት የሚገባዉን ወሳኝ ጭብጥ የያዘ መሆኑን፣ ለህዝብ ነፃነት የሚበጀው አንድ የተቃዋሚ ድርጅት ትእይንት ባዘጋጀ ቁጥር ብቻ ወይንም ገዢው መንግስት በህዝቡ ላይ በደል በፈጠመ ጊዜ ብቻ የተቃዋሚ መሪዎችኒና ታዋቂ ግለሰቦችን ማነጋገር ሳይሆን፣ የህዝቡን የመረጃ ክፍተት መሰረት ያደረገና ዘላቂነት ያላቸው የተጠኑ ውይይቶችን ለህዝብ ጆሮ ማቅረብ እንዳለበት ለማስገንዘብ የቀረበ መሆኑን አውቃችሁ ግዴታችሁን ለመወጣት ብታተኩሩ መልካም ነው፣ የሚሉ ናቸው።
በዚህ አጋጣሚ የኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያደርሳቸውን በደሎች በማስተጋባት ብሶቱን ለማሰማት እለት ተለት የሚያደርገውን ጥረት ለማድነቅ እወዳለሁ። ሆኖም በኔ እይታ ይህ የኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን ጥረት ብቻውን፤ ለህዝብ ብሶቱን ከማሰማት ያለፈ አስተዋዕፅዎ ይኖረዋል ብዬ አላምንም። በመሆኑም ኢሳት እንደ ነፃ የሚዲያ ተቋም ህዝቡ በቂ መረጃን አግኝቶ እየደረሱበት የሚገኙትን ከመጠን ያለፉ ችግሮች ለማስቆምና፤ ብሎም ለነፃነቱ በጋራ ትግሉን ይቀላቀል ዘንድ ለማስቻል፤ የህዝብ ብሶትን ከማሰማት ባለፈ እጅግ በጣም ብዙ መስራት የሚጠበቅበት መሆኑን በማስገንዘብ፤ የህዝብ ነፃነትን እውን ለማድረግ በሚደረገው ትግል ላይ እንደ ሚዲያ ሃላፊነቱን ለመወጣት መጠነ ሰፊ የሆነ የዝግጅትና የአቀራረብ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርበት ጥቆማዬን አቀርባለሁ።
ይህን ሃሳብ ሳካፍል ፅሁፌን ያየ ያነበበ የኢትዮጵያ ልጅ ሁሉ፤ እኔ የተረዳሁትን ተረድቶ መፍትሄውን እንዲፈልግ፤ አልያም ሃሳቤን ለማካፈል የሞከርኩት ‘ነፃ ሚዲያ ያጎናፀፈኝን እድል’ ተጠቅሜ ነውና፤ ከተሳሳትኩ የመታረም መብቴ የተጠበቀ መሆኑን እንዲረዳልኝ እጠይቃለሁ። ስለሆነም የኔ ማጠቃለያ የነፃ ሚዲያዎች ትኩረትና የአንባቢያን ጠቃሚ አስተያየት እንደሚሆን በእጅጉ ተስፋ አደርጋለሁ።
ቸር እንሰንብት
ከዋስይሁን ተስፋዬ
ttwasyhun@gmail.com