Saturday, January 4, 2014

ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ ከማንኛውም የፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸውን አገለሉ – “አርጅቻለሁ፤ በቃኝ”


 
negaso gidada (ዘ-ሐበሻ) በቅርቡ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ባደረገው ምርጫ ስልጣናቸውን ለኢንጂነር ግዛቸው ያስረከቡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፓርቲያቸው አንድነት የመስራች ጉባኤውን በአዲስ ቪው ሆቴል እያደረገ ባለበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ቀጣይ የፖለቲካ ህይወታቸውን አስመልክቶ የደረሱበትን ውሳኔ አሳወቁ።
የፓርቲውን የመመስረቻ ጉባዬ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የአንድነት ሊቀመንበር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ‹‹ከአሁን በኋላ ከየትኛውም የፓርቲ ፖለቲካ ራሴን አግልያለሁ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ዕድሜዬ 70 መድረሱ ነው፡፡ትግሉን ወጣቶች መምራት እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ስለዚህ በቀሪው ህይወቴ ገለልተኛ በመሆን አገሪን ለማገልገል እሰራለሁ፡፡በአንድነት አዲሱ ብሄራዊ ምክር ቤት ከ65ቱ ውስጥ 47 ወጣቶች መሆናቸው አስደሳች ነገር ነው፡፡አዲሱ ፕሬዘዳንት ስራ አስፈጻሚ ውስጥ ከ65% በላይ ወጣቶች እንደሚሆኑ መናገራቸውም ያስደስተኛል፡፡›› ማለታቸውን የአንድነት ፓርቲ ሚድያዎች ዘግበዋል።
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ኢሕአዴግን ሲለቁ አቶ መለስ ዜናዊን “አሁንስ መንግስቱ ኃይለማርያም መሰልከኝ” በሚል በቃኝ ያሉ ሲሆን አሁን ደግሞ ከማንኛውም የፓርቲ ፖለቲካ በቃኝ ያሉት በእድሜ መግፋት ነው።
ዛሬ በአዲስ ቪው ሆቴል ኢንጂነር ግዛቸው በአብዛኛው በወጣት የተያዘውን ካቢኔያቸውን ይፋ አድርገዋል። ዝርዝራቸውም የሚከተሉት ናቸው፦
1) አቶ ተክሌ በቀለ ——- ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት 2) አቶ በላይ ፈቃዱ ——– ምክትል ፕሬዘዳንት 3) አቶ ስዩም መንገሻ ——– ዋና ጸሀፊ 4) አቶ ዳንኤል ተፈራ ——– የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ 5)አቶ ሃብታሙ አያሌው ——- የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ 6)አቶ ዘለቀ ረዲ ——— የውጪ ጉዳይ ሀላፊ 7) አቶ አስቻለው ከተማ ——- የፋይናንስ ጉዳይ ሃላፊ 8)አቶ ሰለሞን ስዮም ——– የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ 9) አቶ ዳዊት አስራደ ——– የኢኮኖሚ ጉዳይ ሃላፊ 10)አቶ አለነ ማህጸንቱ ——- የማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ 11) ወ/ሮ የትናየት ቱጂ ——- የህግና ሰብአዊ መብት ጉዳይ ሃላፊ 12) አቶ ትእግስቱ አወሉ ——- (የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሃላፊ በመሆናቸው በቀጥታ የካቢኔ አባል ሆነዋል)

ኢህአዴግ በመንግስት ወጪ ለመጪው ዓመት ምርጫ ሕዝብ የማደራጀትና የመቀስቀስ ስራ ጀመረ

                    

ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ ከ2007 አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተለይ በአዲስአበባ ከተማ ሕዝብ ቅሬታ የሚያቀርብባቸውን የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና የልማት ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው።

የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የ2006-2007 ዕቅድ አካል እንዲሆን በተደረገው ይህ ከመጪው ዓመት ምርጫ ጋር በቀጥታ የተያያዘው ዘመቻን በብቃት እንዲያስፈጽሙ ለክፍለከተማና ወረዳ አመራሮች ግልጽ መመሪያ ከመተላለፉም ባሻገር በአቅም ግንባታ ስልጠና መወጠራቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ መሰረት በከተማ አስተዳደር ውስጥ መልካም አስተዳደርን ሊያሰፍንና ልማትን ሊያፋጥን የሚችል የልማት ሠራዊት በመገንባት ፣የወረዳዎችን ሁለንተናዊ አቅም ማሳደግ፣ቀልጣፋ፣ውጤታማ ፍትሐዊ አስተዳደር በማስፈን የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ ዓቢይ ዕቅድ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ይህንንም ለማሳካት በአዲስአበባ በየደረጃው የሚገኙ የ3 ሺ 500 አመራሮች አቅምና ክህሎት በማሻሻል
ዕቅዱን የማስፈጸም ብቃትና ቁርጠኝነትን ለማሳደግ ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው።
በአስተዳደሩ በተለያዩ ቢሮዎች የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞችንም አመለካከትና የክህሎት ችግሮችን በመቅረፍና ልማታዊ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ ማድረግም የዕቅዱ አካል ሲሆን በመንግስት መዋቅሩ ካሉት ሰራተኞች 75 በመቶ የሚሆኑትን የለውጥ ኃይል ለማድረግ፣ከዚህ ውስጥ 60 በመቶው በያዝነው በ2006 በጀት ዓመት ለመፈጸም ታቅዶ እየተሰራበት መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢህአዴግ ከዚህ ቀደም የፈጠራቸው የተለያየ አደረጃጀቶች ማለትም የወረዳና የክፍለከተማ እንዲሁም የከተማ የሕዝብ አማካሪ ምክርቤቶች ፣የሴቶች፣የወጣቶች የመሳሰሉ አደረጃጀቶችን በመጠቀም በመጪው ምርጫ ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ “ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማፋጠን” በሚል ሽፋን የአስተዳደሩ የበጀትና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ መሠረት 38ሺህ የከተማ፣የክፍለከተማና የወረዳ ምክርቤት አባላትን፣ 50ሺህ የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶችንና ልዩ ልዩ ተለጣፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የሲቪክ ማህበራት አቅም በዚህ ዓመት እንዲያድግ እንደሚደረግ ታቅዶአል፡፡
ገዥው ፓርቲ ከምንም በላይ አነስተኛ ጥቃቅን ተቋማትን በብዛት በማደራጀትና ያሉትንም በብድር በማጠናከር ለምርጫ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከወዲሁ እየሠራ ነው፡፡ በዕቅዱ መሰረት ዘንድሮ እና በቀጣይ ኣመት በድምሩ ለ475 ሺህ ስራአጥ ወጣቶች ስራ እፈጥራለሁ ብሎአል፡፡ አዲስ ስራ ፈላጊ ዜጎች ፍላጎታቸው እየታየ በ16 ሺህ 500 ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ እንደሚደረግ፣ ከዚህ ውስጥ 8 ሺህ 750 በዚህ ኣመት እንደሚደራጁ ተመልክቶአል፡፡በተጨማሪም ለአዲስ ስራ ፈላጊዎችና ለነባር ኢንትርፕራይዞች ብር 1 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን እንዲቆጥቡና 2 ቢሊዮን 7 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲመቻችላቸው ተወስኖ እየተሰራበት መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል፡፡
ኢህአዴግ ለቀጣዩ ዓመት አገር አቀፍ ምርጫ ከወዲሁ በልማትና በመልካም አስተዳደር ሽፋን ሕዝብ የማራጀትና የመቀስቀስ ስራዎችን ማከናወኛ የሚውለውን በጀት በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የሚሸፈን መሆኑም የአስተዳደሩ ምንጭ ጠቁሟል፡፡