Friday, August 16, 2013

አምና የወያኔ ባለስልጣን ሲዋኙ ባየሁ ግዜ ደስ አለኝ…

    
 ተፃፈ ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን
እነሆ ክረምት መጣ… ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሞቱ አመት ሞላ፡፡ ኢቲቪ በግድ አስታውሱ በግድ ዳግሞ አልቅሱ ብሎ ሙት አመት ምናምን እያለ ሆዳችንን ሊያባባ ይሞክራል እንጂ እኛማ ከሳቸው ሞት በኋላ ስንት የሚያስለቅስ ገጥሞናል፡፡ ሆድ ይፍጀው ብለን እንጂ፡፡
አሁንም ክረምት መጣ ኧረ እንደውም ወደ መጋመሱ ነው…እኛም ያኖርንበት የጠፋንን ወፋፍራም ልብስ በራሳችንና በአጋዥ ግብረሀይል ተረድተን ፈልገን አጠብን ተኳኮስን፡፡ ከአምና የተረፈ ቡትስ ጫማ ያለን እሱን ጠራረግን…የሌለንም ለሸመታ ወጣን…ምን ዋጋ አለው? …ዋጋው ጨምሯል…ንሯል!
ለአንድ ደንበኛ ቡትስ የሚጠየቀው ብር ከሆኑ ዓመታት በፊት ጋሻ መሬት ይገዛበት ነበር አሉ፡፡
በጣም እርር…አንጀታችን ቁስል…ወሽመጣችን ቁርጥ ብሎ…እንደው የት ሀገር ልሂድ? ብለን አልተማረርንም፡፡ እኛ እኮ ኩሩ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ቲማቲም እንኳ በኪሎ 25 ብር እየገዛን አይደለም እንዴ?
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በዝርክርክ አሰራር 3 ነጥብ አስቀነሰብን ሲባል እንዳላንባረቅንበት…ግብርና ሚንስቴር የቲማቲም በሽታ ሊገባ መሆኑን እያወቀ ምንም ሳያደርግ አንቀላፍቶ ይህው የ10 ሳንቲም ፌስታል(መጠሪዋ እንጂ ለካ ዋጋዋ 25 ሳንቲም ገብቷል) የማትሞላ ቲማቲም በ100 ብር ስንገዛ የፈረደበትን ፈጣሪን አማረርን እንጂ ተቋሙን ምንም አላልንም፡፡
ይበለን!
ግብርና ሚኒስቴር ልጅ…ፌዴሬሽኑ የእንጀራ ልጅ ነው እንዴ? ነው ወይስ መንግስት በፌዴሬሽኑ ጉዳይ እንደርጎ ዝንብ ጥልቅ አይልም ስለተባለ ማን አባቱ ያስጥለዋል ብለን ነው?
መተውን የመሰለ ነገር እያለ ምን አበሳጨኝ…ቲማቲም ሆይ እደጊ ተመንደጊ በኪሎ መቶ ብር ግቢ፡፡ እኔ እንደው እርሜን አውጥቻለሁ ያለቲማቲም አይኖርም እንዴ? ብያለው፡፡
ስለክረምት ነበር አይደል የማወራው?
የዘንድሮው ክረምት ለየት ያለ ነው፡፡ የናንተን ባላውቅም በተለይ እኛ ሰፈር በረዶውም አይጣል ነው፡፡ ይቀውራል፡፡ ምቱ ሃሳብን…አልፎ አልፎ ደግሞ የበሉትን ሁሉ እየበተነ የአምቦ ውሃን ስራንም ደርቦ ይሰራል፡፡
አቤት አስፓልቱ ደግሞ…ጉድ አይደል?
እመት ቻይና እጅሽ ይባረክ ብያለሁ፡፡ እውነት አሁን እሷን የመሰለ ወዳጅ ከወዴት ይገኛል? በአንድ ክፍያ መልቲ ፐርፐዝ የሆነ አስፓልት ሰርታልን መሄዷን ልብ ብላችኋል?
በጋ በጋ እንደ አስፓልት ክረምቱን ደግሞ የዋና ገንዳ ይሆናል፡፡
ያኔ አቶ መለስ ዜናዊ አስረስ የሞቱ ግዜ….ስናለቅስ ደረታችን ስንደቃ  ሳምንት ከምናምን አለፈና…አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንዲሉ የእሳቸውም (የአቶ መለስ) አስክሬን ከቤተመንግስት ወጥቶ  ወደ መስቀል አደባባይ ሲሄድ ከዛም ወደ ቀብር ቦታ ሲሸኝ ሰውም ባቻ ሳይሆን ሰማዩም አለቀሰ፡፡እንደጉድ ዘነበ፡፡ አስፓልቱም 2ኛ ስራውን ደርቦ መስራቱን ተያያዘ፡፡
ማን ባለስልጣን ቀረ? ከሟቹ በቀር፡፡ አባይ የተቀየሰው ወደ አዲስ አበባ በሚመስለው አስፓልት ላይ መሪዎቼ ሲምቦጫረቁ ሳይ ልቤ አላዘነም፤ እስቲ ይቅመሷት አለ እንጂ፡፡ ብዙዎቹ ማለት ይቻላል ያን ህይወት ረስተውታል፡፡
ወዳጅነታችን ውሃ ለመሻገር እስከመተዛዘል መድረሱን በዚህም የፈጠርነው የስራ እድል መንግስት በኮብልስቶን ለተደራጁት ከሰጠው እንደማይተናነስ የምናውቀው እኛ ነን፡፡
መሪዎቻችን ያንን ቀን…እንዳያልፉት የለ እያሉ…አለፉት ግን ረሱት መሰለኝ፡፡ ይኸው እኛ ተረኛዎቹ ዛሬም እንዋኛለን፡፡
ለነገሩ ይበለን!
መቸም ጣት መቀሰር ይቀናናል እንጂ ሰው አየ አላየ ብለን የጣልነው ቆሻሻ እና የደፈነው ቱቦ ገና ብዙ ያሳየናል፡፡
የራሳችን ጥፋት በሙሉ አፋችን የመንግስታችንን ስህተት እንኳ እንዳንናገር ሸብቦናል፡፡
ይበለን!
ስንዋኝ እንገናኝ ይሆናል፡፡

ሁሉም የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ ኣይደለም (አብርሃ ደስታ – ከትግራይ)


የትግራይ ህዝብና ህወሓት! (በአብርሃ ደስታ – ከትግራይ)
abraha desta
እውነት ነው። የህወሓት መሪዎች የትጥቅ ትግሉ ጀመሩት። ደርግ ዓማፅያኑ ለማጥፋትና ትግራይን ለመቆጣጠር የሃይል እርምጃ መውሰድ ጀመረ። ትግራይ የጦርነት ኣውድማ ሆነች። የትግራይ ገበሬዎች በሰላም የእርሻ ስራቸው ማከናወን ኣቃታቸው። የደርግ ወታደሮች ገበሬዎቹን ማስፈራራት፣ ሴቶችን መድፈር፣ ወጣቶችን በግደል (በጥርጣሬ) ተያያዙት።

በደርግ ኣሰራር የተማረረው የትግራይ ገበሬ ጫካ ገባ። እዛው ጫካ ከህወሓቶች ጋር ተቀላቀለ። ኣብዛኛው ታጋይ (ገበሬ ወይ ኣርሶ ኣደር) ደርግን ለመታገል ጠመንጃ ያነሳው በደርግ ስርዓት በነበረ ጥሩ ያልሆነ የሰለማዊ ሰዎች ኣያያዝ እንጂ እንደሚነገረን እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ። በዚ ምክንያት በትግራይ ከኣንድ ቤተሰብ ቢያንስ ኣንድ ታጋይ (የተሰዋም በህይወት ያለም) ነበር (ኣለ)።

ነገር ግን ሁሉም የትግራይ ተወላጅ የህወሓት ደጋፊ ኣይደለም። ምሳሌዎችን ልጥቀስ።

ምሳሌ ኣንድ

የትግራይ ኣርሶ ኣደር የታገለበት ዓላማና የመሪዎቹ ለየቅል ነበር። በ1983 ዓም የህወሓት መሪዎች ኣራት ኪሎ ቤተ መንግስት ከገቡ በኋላ የመሪዎቹ ዓላማ ለታጋይ ገበሬዎቹ ግልፅ ሆነ። በታጋዮቹና መሪዎች የዓላማ ልዩነት ግልፅ ሆነ። ታጋይ ገበሬዎቹ ጥያቄ ኣስነሱ። ጥያቂያቸው ምን ነበር??? ስድስት ጥያቄዎች:

(1) የኤርትራ ረፈረንደም (ነፃነት ወይ ባርነት የሚል ኣማራጭ) ስሕተት ነው፤ ለሀገር ኣንድነት መስራት ሲጠበቅብን ምንሊክ የሰራው ስሕተት እየደገምን ነው (ኃይለስላሴ እንኳ ለማስተካከል ሞክሮ ነበር)።

(2) የባህር በር (ወደብ) ያስፈልገናል። ሁሉም ነገር ለሻዕቢያ መስጠትና ኣገልጋይ መሆን በታሪክ ተጠያቂዎች ያደርገናል።

(3) የተታገልንበት ዓላማ መንገዱ እየሳተ ነው። ዓላማችን ስልጣን መያዝ ብቻ ኣልነበረም፤ ዲሞክራሲ ማስፈን ነው።

(4) ሙስና እየተስፋፋ ነው፣ ትግላችንና መስዋእትነቻን በኣሉታዊ መልኩ ይጎደዋል።

(5) የደርግ መሪዎች እንጂ ሁሉም የደርግ ወታደሮች ጠላቶቻችን ኣይደሉም፤ በመከላከያ ሰራዊታችን ይጠቃለሉ፣ ብዙ የሰለጠኑና የሀገር ሃብት ፈሰስ የተደረገባቸው ናቸው።

(6) ሻዕቢያ ሊወረን እየተዘጋጀ ነው፤ ወታደራዊ ዓቅሙ እየገነባ ነው። እኛ ደግሞ ሀገራዊ መከላከያ ሰራዊት ይኑረን።
የሚሉ ጥያቄዎች ተነሱ። ነገር ግን ጥያቄዎቹ ወድያው ሻዕቢያ ጀሮ ደረሱ። የሻዕቢያ መሪ ኢሳያስ ኣፈዎርቂ ከመለስ ዜናዊ ጋር ተነጋገሩበት። እንደዉጤቱም በ1985 ዓም ከ32, 000 በላይ የሚሆኑ የህወሓት ታጋዮች (ጥያቄ ያነሱ) እንዲባረሩ ተደረገ።

እንኳን የትግራይ ህዝብ በሙሉ፣ ህወሓት የታጋዮቹ ድጋፍ የለውም። መረጃ ስለሌለን ግን ሁሉም የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ ኣድርገን እናስባለን።

ምሳሌ ሁለት
ሑመራ ኣከባቢ ነው፣ ልዩ ስሙ ማይካድራ። ኣንድ የድሮ ታጋይ ሴት ሦስት ልጆች ብቻዋ ታሳድጋለች። የማይካድራ ህዝብ (እንደሌላው ሁሉ) በመለስ ሞት ምክንያት የሓዘን ሰልፍ እንዲያደርግ በካድሬዎች ታዘዋል። ሴትየዋ በሓዘን ሰልፉ ኣልተገኘችም። በፖሊስ ተይዛ እንድትታሰር ተደረገ (የታሰሩ ብዙ ናቸው ግን ይቺ ሴት መረጥኩኝ)። በፖሊስ ለምን እንዳልተገኘች ተጠየቀች።

ሴትየው: ስራ ስለበዛብኝ ነው ያልመጣሁት

ፖሊስ: ስራ ቢበዛብሽስ??? ስራ ከመለስ ይበልጣል?

ሴትየው: እኔ ኮ ብቻየን ሦስት ልጆች ኣሳድጋለሁ።
ፖሊስ: እና?
ሴትየው: እናማ ስራ ይበልጥብኛል። ደሞኮ ሞት ብርቅ ኣይደለም። መስዋእትነት ኮ እናውቀዋለን። ባሌን ታውቀዋለህ። ታጋይ ነበር። ድሮ ተሰውተዋል። ልጆቹ ማሳደግ ኣይችልም። የኔና የተሰዋው ባለቤቴ ሓላፊነት ተሸክሜ ልጆቻችን ለማሳደግ ሌት ተቀን መስራት ኣለብኝ። መለስ ከሞተ እናንተ ቅበሩት።

ፖሊስ: ኣንቺ ራስሽ ታጋይ ነበርሽ። ባልሽም ተሰውተዋል። መለስ ደግሞ የሰማእታት ኣርኣያ ነው። ስለዚ ልታዝኚለት ይገባል።

ሴትየው: መለስ ከምወደው ባሌ ኣይበልጥብኝም። ኣሳዛኝ መስዋእት ኮ ጫካ ዉስጥ ተሰውተው ያለቀባሪ ተጥለው የቀሩ፣ ሬሳቸው የጅብና ኣሞራ ሲሳይ የሆነ፣ (ኣብ ፈቀዶ ጎቦታትን ሽንጥሮታትን ዝተረፉ) እንጂ ……. መለስ ኮ ብዙ ነገር ኣይተዋል። ኣሁን ደግሞ በክብር፣ በስርዓት እያረፈ ነው። ባሌኮ የቀብር ስነስርዓት ኣልተደረገለትም። ምን ታካብዳላቹ?! በመለስ ሞት ግን ባሌና የትግል ጓደኞቼ (ስውኣት ብፆተይ) ኣስታውሼ ኣዝኛለሁ።

ሴትዮዋ ተፈታች። እኛ ግን የትግራይ ህዝብ በስርዓቱ ደስተኛ ይመስለናል። ዉስጡ እየነደደ ነው።

ምሳሌ ሦስት

በትግራይ ሓውዜን ኣከባቢ ነው። ኣንድ ኣብሮ ኣደጌ (ጓደኛየ) ኣስታወስኩ። ኣብረን እንማር ነበር (እስከ ስድስተኛ ክፍል)። ከስድስተኛ ክፍል በላይ ትምህርቱ መቀጠል ኣልቻለም። የልጁ ኣባት የህወሓት ታጋይ ነበር፤ ተሰውተዋል። ከኣያቶቹ ጋር ይኖራል። ኣያቶቹ ሦስት ልጆች ነበሯቸው። ሁሉም ተሰውተዋል። የቀራቸው የልጅ ልጃቸው (እሱ ብቻ) ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት ልጁ ከመንግስት የወሰደውን ብድር መመለስ ስላልቻለ ወደ ሑመራ ኣከባቢ ይጠፋል። ኣያቶቹ ይታሰራሉ።

መታሰራቸው ሰምቶ መጣ። ብዙ ነገር ደረሰበት። የጣብያ (ቀበሌ) ካድሬዎቹ ተቃወማቸው። ካድሬዎቹ ኣስተዳዳሪዎችም ኣባቱ የተሰዋበት ዓላማ ተቃወመ ብለው የኣከባቢው ሰዎች ከነሱ ቤተሰብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳያደርጉ ተነገራቸው። (ያ ሦስት ልጆች የተሰውበት ቤተሰብ እንዲገለል ተደረገ)። በኣሁኑ ሰዓት ግን ይሄን የማግለል ስትራተጂ እየተውት ይገኛሉ።

ምሳሌ ኣራት

በትግራይ ኣስተማሪዎች በገዢው ፓርቲ የሚደርሳቸው ኣስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ በደል በመቃወም የተለያዩ እርምጃዎች የሚወስዱበት ኣጋጣሚ ኣለ። ተደጋጋሚ የስራ ማቆም ኣድማ ይደረጋል። ኣንዳንዴም የመምህርነት ስራው ጠቅልሎ የመተው ነገር ኣለ። ለምሳሌ ትግራይ ምስራቃዊ ዞን የመማር ማስተማር ሂደቱ ተስተጓጉሏል። ነጋሽ ኣከባቢ በሚገኝ ኣንድ ትምህርትቤት ሁሉንም ኣስተማሪዎች (ዳይሬክተሩ ጨምሮ) ትምህርትቤቱ ዘግተው ጠፍተዋል። ግን የሚዘግበው ሰው የለም።

ምሳሌ ኣምስት

በኣንዳንድ ኢትዮዽያውያን የትግራይ ተወላጆች የኢህኣዴግ መንግስት በመደገፍ ኢትዮዽያውያንን ይበድላሉ ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ብዙዎች ይህንን እንደሚቃወሙ እንዴት ልንገራቹ?

ዓረና ትግራይ ፓርቲ በሺዎች የሚቆጠሩ ኣባላት እንዳሉት ሰምቻለሁ። እነዚህ ታድያ ህወሓት የሚቃወሙ ኣይደሉምን? ዴምህት የተባለ ኣማፂ ቡድን 60 ሺ ወታደሮች እንዳሉት ይነገራል። 60 ሺው ትክክል ላይሆን ይችላል። ግን ከ 20-25 ሺ ወታደር እንደሚኖረው ግን ይገመታል። እንዚህ ሁሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው።

በ1997/98 ዓም ከሻዕቢያ ሬድዮ በሰማሁት መረጃ መሰረት (ቃለ መጠይቅ ሲደረግባቸው) ብዙዎቹ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ኣባላት ነበሩ። ወደ ኤርትራ የገቡበት ምክንያት ሲያስረዱ በ1997 ና98 በነበረ የህዝብ ዓመፅ የተወሰደ እርምጃ በመቃወም ነበር። ስለዚ ሁሉም የትግራይ ህዝብ ገዢው ስርዓት ይደግፋል ብሎ ማሰብ ስሕተት ነው።

በሌላ በኩል ስናየው ደግሞ ስራ ነው። ኣንድ ሰው ስራ ፈልጎ ወደ ፖሊስነት ወይ ውትድርና ሊገባ ይችላል። የእንጀራ ጉዳይ ነው። ከገባ ታድያ (ደመወዙን ለማግኘት) የታዘዘውን መስራት ኣለበት። ካልሰራ ይባረራል፤ ከተባረረ መኖር ኣይችልም (ሌላ ስራ እስካላገኘ ድረስ)። ስለዚ ጠንክሮ ቢሰራ ኣይደንቀኝም።

ባጠቃላይ የትግራይ ህዝብ በሙሉ የህወሓት ደጋፊ ነው ማለት ኣይቻልም። ብዙ የሚቃወም ኣለ። ብዙ የሚጨቆን ኣለ። በትግራይ የሌለው ጭቆናን የሚያጋልጥ ነው። በሌሎች ኣከባቢዎች (ከትግራይ ውጭ) ሰው ሲታሰር ወይ ሲገደል የሚናገርለት ወይ የሚጮህለት ወገን ኣለው። በትግራይ ግን የለም። ኣንዱ ሲታፈን ሌላው ኣብሮ ዝም ይላል። ይሄ ነው ልዩነቱ እንጂ በትግራይ ጭቆና ስለሌለ ኣይደለም።

በመጨረሻም

እንደው ሁሉንም ትተን፣ የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ቢደግፍ (ከህወሓት ጎን ቢቆም) ችግሩ ምንድነው? ኣንድ ህዝብ የፈለገውን የመደገፍ ወይ የመቃወም መብቱ የተጠበቀ ነው። የትግራይ ህዝብ ህወሓትን (በፍላጎቱ ኣይደግፍም እንጂ) ቢደገፍ ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱ ‘ለምን ህወሓትን ትደግፋለህ?’ ሊባል ኣይገባም። ሌሎች ህዝቦች ህወሓትን የመቃወም መብት ያላቸው ያህል የትግራይ ህዝብም የመደገፍ መብት ኣለው።

ስለዚ (1) ሁሉንም የትግራይ ህዝብ (ብዙዎች እንደሚያስቡት) የህወሓት ደጋፊ ኣለመሆኑ እንዲታወቅ። (2) የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ይደግፋል ብሎ መውቀስም ተገቢ ኣይደለም